የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት

ዘወረደ

በዲያቆን ደረሰ ተሾመ

የካቲት፤፳፻፲፮ ዓ.ም

በዚህ ሳምንት የቃል ርደት፣ የወልድ ልደት፣ የአዳም ድኅነት ቢነገርም እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከሰማይ የወረደ ሰማያዊ፣ በክብር ያረገ በኩረ ትንሣኤ መሆኑ አይዘነጋም፡። ለዚህም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ነገር ግን ምስክርነታችንንም አትቀበሉትም። በምድር ያለውን ስንነግራችሁ ካላመናችሁኝ፥ በሰማይ ያለውን ብነግራችሁ እንዴት ታምኑኛላችሁ? ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው። ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለው የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀል ዘንድ አለው፡፡ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዳይጠፋ፣ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶታልና” እንዳለ እርሱ ምድራዊ ያይደለ ሰማያዊ ነው። (ዮሐ.፫፥፲፩-፲፮) “ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ” ስለ ፍቅሩ በፈጠረው የተጠመቀ ሰማያዊ ነው።

ጾመ ድጓው የሚጀምረውም እንዲህ በማለት ነው፤ “ዘወረደ እምላዕሉ፣ አይሁድ ሰቀሉ…. እግዚአ ኩሉ ዘየሐዩ በቃሉ፤ ….በቃሉ የሚያድነውን ከላይ የወረደውን የሁሉን ጌታ አይሁድ ሰቀሉት…”

ዘወረደ የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት ነው። ስያሜውም የቅዱስ ያሬድ ነው። ትርጉሙም “ከሰማያት የወረደ” ማለት ነው። ቅድመ ዓለም ከአባቱ ከአብ የተወለደ ፣ድኅረ ዓለም ከድንግል ማርያም የተወለደ ነው። ስም አጠራሩ ያለና የነበረ፣ እግዚአብሔር፣ በፈቃዱ ዓለምን ለማዳን የመምጣቱን ምሥጢር የምንረዳበት ሳምንት ነው። ይህ የመጀመሪያው ሳምንት ‹ጾመ ሕርቃል› እየተባለም ይጠራል፡፡ ሕርቃል (ኤራቅሊዮስ) በ፮፻፲፬ ዓ.ም የነበረ የቤዛንታይን ንጉሥ ነው፡፡ለክርስቲያኖች ባደረገው ርዳታ ምክንያት አንድ ሳምንት ጾመውለት ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ጾመ ሕርቃል እየተባለ ይጠራል፡፡ ሙሉ ታሪኩ በፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ አንቀጽ ፲፭ ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ ሳምንት ቤተ ክርስቲያን ስለ ጾም ጥቅምና እንዴት መጾም እንዳለብን ታስተምረናለች፡፡ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው “አከለክሙ መዋዕል ዘኃለፈ ዘተቀነይክሙ ለግዕዘ ሥጋክሙ፤ ለሥጋቸሁ ፈቃድ የተገዛችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃችኋል፤ ከአሁን በኋላ ግን ጹሙ፣ ጸልዩ ለእግዚአብሔር ተገዙ” እያለ የጾም አዋጅ ያውጃል። ጾም ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ፣ ፈቃደ ነፍስን ለፈቃደ እግዚአብሔር የምናስገዛበት መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡፡

ጾሙ በሚጀመርበት ሰንበት በሚሰበከው ምስባክ እንዲህ ብሎ ያሳስበናል፤ “ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፣ በረዓድም ደስ ይበላችሁ” ጾም ከምግብና ከመጠጥ እንዲሁም ከሌሎች ምቾቶችና ደስታዎች ከመከልከል ያለፈ ጥልቅ ትርጉም ያለው ተግባር ነው። (መዝ.፪፥፲፩-፲፪) “ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ ከመ ያብርህ ብርሃነ ስብሐቲሁ በላዕሌነ፤ (የእግዚአብሔር) የክብሩ ብርሃን በላያችን ላይ ያበራ ዘንድ ጾምን እንጹም፤ወንድማችንንም እንውደድ” እንዲል። (ጾመ ድጓ)

በዘወረደ እሑድ የሚነበቡት ምንባባትም ይህንን የጾምን ጸጋ የያዙ ናቸው።“ነገር ግን ፈጣሪያችን የምትበልጠውን ጸጋ ይሰጣል፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔርን እሺ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል፡፡ እግዚአብሔርን ቅረቡት፤ ይቀርባችሁማል፤ እናንተ ኃጥኣን እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ፡፡ እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ÷ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል፡፡” (ያዕ.፬፥፮-፲)

“በውኑ እንግዲህ በስሙ እናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን? ነገር ግን ለድሆች መራራትን፥ ከእነርሱም ጋር መተባበርን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና፡፡” (ዕብ.፲፫፥፲፭-፲፮)

በጾም የተጠቀሙ ቅዱሳንን እያሰብን ለጾም እንድንተጋም ወደ እነርሱ እንድንመለከት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡“ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያ አልተጠቀሙምና።” (ዕብ.፲፫፥፱) ሳምንቱ በሚጀምርበት ሳምንት የሚነበበው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት እንዲህ ይላል፡፡ ጾመ ድጓው አባቶቻችን ያገኙትን በረከት እንደምናገኝበት ሲገልጽ “የእግዚአብሔር የክብሩ ብርሃን በላያችን ላይ ያበራ ዘንድ ጾምን እንጹም፤ ወንድሞቻችንም እንውደድ፤ ኤልያስ በጾም ወደ ሰማይ አርጓልና፤ዳንኤልም ከአናብስት አፍ ድኗልና፡፡”

ጾም ፈቃደ ነፍስን በፈቃደ ሥጋ ለማሠልጠን የአጋንንት ኃይል ለመቋቋም የሚያስችል የክርስቲያኖች ጋሻ በመሆኑ በሃይማኖት ለሚመሩ ምእመናን እጅግ አስፈላጊና ከምንም በላይ የሕይወታቸው መርሕ መሆን እንደሚገባ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ እንዲህ በማለት ያስተምራል፡፡ ” አሁንም ወንድሞቻችን በዚህ በሥጋችን ሳለን ፈቃደ ሥጋችንን ልንሠራ አይገባም፤ ፈቃደ ሥጋቸውን የሚሠሩ ሰዎች በወዲያኛው ዓለም ምውታን ናቸውና፡፡ የሥጋችሁን ፈቃድ በነፍሳችሁ ፈቃድ ድል ከነሣችሁት ለዘለዓለም ሕያዋን ትሆናላችሁ፡፡ የነፍሳቸውን ፈቃድ የሚሠሩ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና፡፡” (ሮሜ ፰፥፲፪-፲፬)

ጾም አበው ቅዱሳን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ቀምረው፣ በበታ ወስነው፣ በሁኔታ ገድበው… ባስቀመጡልን ወቅት ከእህልና ከውኃ በመከልከልና ሰውነትን በማድከም ብቻ ሳይሆን ለስሕተት ከሚዳርጉ ነገሮችና ቦታዎች ተቆጥቦ በጸሎት መትጋትም እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም ይህንን እውነታ በተመለከተ እንዲህ ይላል፡፡ “እኔ ግን እዘንልን፤ ለምንልን ባሉኝ ጊዜ ማቅ ምንጣፍ ለብሼ አዘንኩላቸው፤ ሰውነቴን በጾም አደከምኩዋት፤ ልመናዬም እኔም ወደመጥቀም ተመለሰችልኝ፡፡” (መዝ. ፴፬/፴፭፥፲፫)

ጾም ከሥነ ምግባራት ሕግ አንዱ በመሆኑ እንኳንስ ያልተፈቀደውን የተፈቀደውም ቢሆን የማይጠቅም ከሆነ ፈጽሞ በመተው ለእግዚአብሔር ያለንን ፍጹም ፍቅር የምናስመሰክርበት ምሥጢር ነው፡፡

ጾም ከመብልና ከመጠጥ ጋር የተያያዘም በመሆኑ መብል ጊዜያዊ ስለሆነ ማለትም በዚህ ዓለም እስካለን ብቻ የምንገለገልበት እንጂ ዘለዓለማዊ ስላይደለ ለጊዜያዊ መብልና መጠጥ ምክንያት ከሃይማኖት ሥነ ምግባር እንዳንወጣ ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት ሲመክሩ “መብል በእግዚአብሔር ዘንድ ግዳጅ አይፈጽምልንም ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ብንበላም አይረባንም፤ አይጠቅመንም፤ ብንተወውም አይጎዳንም” በማለት ሲመክሩን ቅዱስ ጳውሎስም የመብልና የሆድ ጊዜያዊነት አስመልክቶ እንዲህ በማለት አስተምሯል፡፡ (፩ኛቆሮ.፰፥፰) “ሁሉ ነገር ተፈቅዶልኛል፤ ሁሉ ግን አይጠቅመኝም፡፡ ሁሉ ተፈቅዶልኛል በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳን አይሠለጥንብኝም፡፡ መብል ለሆድ ነው ሆድም ለመብል ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ሁለቱንም ያሳልፋቸዋል”፤ (፩ኛቆሮ.፮፥፲፪-፲፫) “ለሚጠፋ ምግብ አትሥሩ፤ ይልቅስ የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት ስለሚሆን ምግብ ሥሩ” እንደ ተባለ (ዮሐ. ፮፥፳፯) ካለን ጊዜ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ጊዜ በመስጠት ቢበሉት የማያስርበውን፣ ቢጠጡት የማያስጠማውን፣ የዘለዓለም ሕይወት የምናገኝበትን ሥጋ እና ደሙን ተቀብለን መንግሥቱን እንድንወርስ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን።

የዕለቱ ምንባባት:-
• በሠራኢ ዲያቆን (ዕብ.፲፫፥፯-፲፯)
• በንፍቅ ዲያቆን (ያዕ.፬፥፮-ፍጻሜ)
• በንፍቅ ካህን (የሐዋ. ፳፭፥፲፫-ፍጻሜ)

ምስባክ፡ “ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐዕ እግዚአብሔር” (መዝ.፪፥፲፩)
ወንጌል፡ ዮሐ.፫፥፲-፳፬
ቅዳሴ፡ ዘእግዚእነ

“ዘበእንቲኣነ ለሰብእ ወበእንተ መድኃኒትነ፡ ወረደ እምሰማያት። ተሰብአ፡ ወተሠገወ እመንፈስ ቅዱስ ወእማርያም እምቅድስት ድንግል፤ ስለ እኛ ስለ ሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ ወረደ፤ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ሆነ፡፡”

ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ናምልኮ፤ እንድናመልከው እኛን ለፈጠረ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን!