ጨረቃ

በመዝሙርና ኪነ ጥበባት ክፍል

መስከረም ፲፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

እስኪ እንጀምር ከልደቷ

በፍጥረቱ በውልደቷ

ከቀን በዐራተኛ መገኘቷ

በረቡዕ በዐራተኛ

ከተራራ ከፍ ያለች ከፀሐይ መለስተኛ

ረቡዕ ብሎ ራብዕ

ራብዕ ብሎ ረቡዕ

ይሄ ዐራተኛ ቀን ይሄ ዐራት ቁጥር

’ሚሰናሰል፣ ሚጨባበጥ፣ የሚያያዝ አለው ነገር

እውነተኛው ፀሐይ በአናታቸው ካላበራ

ድንቄም ዕውቀት…እምነት ድንቄም ቅናት ሥራ

አለበለዚያማ ፀሐይ ካልወገገ ጨረሩ ካልነካው

እንደ ጳውሎስ መሆን ነው እንደ ቅድመ ደማስቆው

በዚያ እንደፈዘዘ

እኚህ ዐራቱን ይዞ ፀሐይን ያልያዘ

በረቡዕ በዐራተኛ

ፀሐይ ተጨምራ አምስተኛ

ከተራራ ከፍ ያለች ከፀሐይ መለስተኛ

ረቡዕ ብሎ ራብዕ

ራብዕ ብሎ ረቡዕ

ይሄ ዐራተኛ ቀን ይሄ ዐራት ቁጥር

’ሚሰናሰል፣ ሚጨባበጥ፣ የሚያያዝ አለው ነገር

እውነተኛ አገልጋይ በዚህ ይገለጣል

የነፍሱ ወጋገን በሥጋው አናት ላይ ቦግ ብሎ ይወግጋል፡፡

ጨረቃ እንዲህ ናት

የአገልጋይ መስታወት

የአገልጋይ ግልባጭ የአገልጋይ ተምሳሌት

አገልጋይ ብርሃን ነው ብርሃን የሚያበራ

ከሌላው ለኩሶ ለሌላ የሚያጋራ

ታዲያ ከሌላ ለኩሶ ከሌላ ተውሶ ለሌላ ሊያጋራ

በመላመድ ድፍረት በሚመጣ ኃጢአት በሚያስከትል ቁጣ

በእሳቱ ዋዕይ በእሳቱ ቁጣ

እርሱ ነ’ዶ ጨሶ

የጨመረው ብርሃን ያነደደው እሳት ’ላይጠቅመው መልሶ

እንደሻማ እና ጧፍ ቀልጦ ‘ሚቀር ብቻ አይደለም ጨርሶ

እንደ ጧፍ ሰም ነፍሱ ነድዳ ነድዳ

እንደ ክሩ ሥጋው በስብሳ እሳት አመድ ወልዳ

እንደ ሻማው ክር ነፍሲቱ እየነደደች ሰሙ ሥጋው ተንዳ ተንዳ

ከመቃብር ወርዳ

እሳት መልሚያው ሆኖ እርሱን ካላለማው

ለሰዎች አብርቶ እርሱን ካላበራው

የእርሱ አገልግሎት ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው?

ይሄ ነገር ይጤን ይሄ ነገር ይታይ

የበራ ጨረቃ ነው ትክክለኛ አገልጋይ

እንዲህ ናት ጨረቃ የአገልጋዩ አቻ

ወይም በአቧራ አልያም በደመና

በአንዱ ተሸፍና

ትጠፋለች ብቻ

የጠፋች ቢመስልም

ተጋርዳ ነው ‘ንጂ ግን እኮ አልጠፋችም

አገልጋይም እንዲሁ ሲታይም

የኛ ዓይን ተጋርዶ የርሱን ጽድቅ ለማየት

ለኛ በሚታይ ጽድቅ እርሱ ከሌለበት

‹‹የድሮው መስሏችሁ እርሱ እኮ ትቶታል››

ብሎ ለማውራቱ ማን ሊቀድመን ኖሯል?

እናም የጠፉ ቢመስሉም

ጨረቃ እና አገልጋይ በፍጹም አይጠፉም

እንዲህ ናት ጨረቃ!

ባንዱ ስትወደድ ባንዱ ስትጠላ

ባንዱ ስትሞገስ ባንዱ ስትጥላላ

አንዴ ስትጎድል አንዴ ስትገመስ  አንዴ ስትሞላ

አንዴ ነጥብ ስታህል አንዴ ስትጎላ

አንድ ጊዜ ስትደምቅ ደግሞ ሌላ ጊዜ በጨለማ ጥላ

እንደ ስንጥር ቀጥና እንደ መርፌ ሾላ

እንደ ምንም ጠፍታ እንደ ፀሐይ አብርታ

እንደ አደይ ፈክታ

ደግሞ ብላ…ብላ

ጎዶሎዋ ነጥፎ ሙላቷ ሲሞላ

በቀን ትወጣለች የፀሐይን ሥፍራ ካልሸፈንኩ ብላ

አገልጋይም  እንዲሁ አይደል!

መጉደሉ ሲመጣ መሙላቱን ያስባል ተስፋ ይሰንቃል

መሙላቱ ሲመጣ መጉደሉን ያስባል

የቆመ ሲመስለው ጨርሶ እንዳይጠፋ ይጨነቃል

ደግሞም ጨረቃን ይመስላል

የሙላቱ ሐይቅ ሞልቶ የፈሰሰ ለታ

ቀላል ይመስለዋል የአባቶቹ ቦታ

በቀንም በማታ

እዚህም እዚያም ቦታ

እኔ ካላበራሁም

እኔ ካልሆንኩ ይላል በአባቶቹ ቦታ

ግና ብዙ አይርቅም

ጉድለቱ ይነገረዋል የ’ሱን ጨረቃነት

ተመልሶ ይመጣል ወደነበረበት

ታዲያ እንዲህ ሲሆን በኋላ አትሙት

ጸሎት አድርጉለት በቃ እዘኑለት

ምክንያቱም

እንዲህ ነው አገልጋይ ሲበቃ

እንዲህ ናት ጨረቃ!