ጥናትና ምርምር የጥናት ጉባኤው ሊያካሂድ ነው
የካቲት 17 ቀን 2006 ዓ.ም.
በታመነ ተ/ዮሐንስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሚና በፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል” በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሑፍ ሊያዘጋጅ ነው፡፡
እንደማእከሉ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰይፉ አበበ ገለጻ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቷን ሕልውና ከማስጠበቅ አልፋ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ይወጡ ዘንድ ባደረጉት ትግል የነበራትን ሚና ለማመላከት እንዲሁም ግንዛቤ ለማስጨበጥ ይረዳ ዘንድ ማእከሉ ይህንን የጥናት ጉባኤ አዘጋጅቷል፡፡ አያይዘውም የጥናት ጉባኤው በየዓመቱ የሚከበረውን የዓድዋ ድል ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለድሉ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ለማዘከር እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኒቱ የሀገራችንን ሉላዊነት ለማስጠበቅ የተጫወተችውን ሚና በዚህም ዘመን ትውልዱ ማንነቱን በመጠበቅ ዙሪያ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ሊኖረው እንደሚገባ ጥናቱ ያመላክታል ብለዋል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል ይህን መሰል ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተያያዥነት ባላቸው ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ባሕላዊ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን የሚያከናውን ሲሆን በሚገኘውም የሥራ ውጤት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ያደርጋል፡፡
የጥናት ጉባኤው የካቲት 22 ቀን 2006 ዓ.ም በማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጽ/ቤት ሕንጻ ላይ የሚከናወን ሲሆን፤ በዕለቱ ብፁዓን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሑራን እና ጥሪ የተደረገላቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡