ጥምቀት

ጥር ፱ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የሰው ልጅ ሕገ እግዚአብሔርን በመተላለፉና ለኃጢአት ተገዢ በመሆኑ ንጽሕት ነፍሱ አደፈች፤ ረከሰችም፤ በኃጢአቱም ምክንያት ከአምላኩ ተጣላ፤ ወደ ምድርም ተጣለ፤ ምድርም በእርሱ የተነሣ ተረገመች፤ እሾህና አሜከላንም አበቀለች፡፡ እርሱም ለብዙ ዘመን አዝኖና በሥቃይ ኖረ፡፡

ቸርነቱ የማይልቅ መሐሪና ይቅር ባይ አምላካችን እግዚአብሔር በኅዘኑ አዝኖና ሥቃዩን ተመልክቶ ለእርሱ፤ ስለ እርሱ መከራና ሥቃይ ይቀበልለት ዘንድ ከንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ሊያድነው በገባለት ቃል መሠረት ተፈጸመ፡፡ ከዚያም በኋላ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዮርዳኖስን ብርህት ማኅፀን እንድትሆን፣ ምእመናንም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ፣ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ዳግም ተወልደው መንግሥተ ሰማያት እንዲገቡ  እንደዚሁም ሥርዓተ ጥምቀትን ለማስተማርና አብነት ለመሆን በጥር ዐሥራ አንድ ቀን ተጠምቋልና ይህችን የተከበረች ቀን ሕዝበ ክርስቲያን ያከብር ዘንድ ይገባል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስም ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ፤ እናንተም ከርኵሰታችሁ ሁሉ ትጠራላችሁ›› ተብሎ አስቀድሞ በተነገረው መሠረት ጌታችን በውኃ ተጠመቀ፡፡ የዚህም ምክንያት ሊቀውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስረዱት ውኃ ለሁሉ አስፈላጊ በመሆኑና ያለ ውኃ መኖር የሚችል ባለመሆኑ ያለ ጥምቅት ደግሞ ያለ ጥምቀት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይቻልምና ጥምቀትም ለሁሉም የሚገባ ሥርዓት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ውኃ መልክ ያሳያል፤ መልክ ያለመልማል (ያጠራል)፡፡ ጥምቀትም መልክዐ ነፍስን ያሳያል፤ መልክዐ ነፍስን ያለመልማልና (ያጠራልና)፡፡ (ሕዝ.፴፮፥፳፭)

ዘመነ ሥጋዌ ‹‹ጌታችን  መድኃኒታችን  ኢየሱስ  ክርስቶስ  በዮሐንስ  እጅ  ይጠመቅ  ዘንድ  ከገሊላ  ወደ ዮርዳኖስ መጣ›› (ማቴ.፫፥፲፫፣ማር.፩፥፱፣ሉቃ.፫፥፳፩፣ዮሐ.፩፥፴፪)፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ግን አገልጋይ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጂ ጌታ በአገልጋዩ አይጠመቅም፤ ‹‹እኔ በእንተ ልጠመቅ እሻለሁ፤ አንተ ወደ እኔ ትመጣለህን?›› ብሎ አይሆንም አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ‹‹አሁንስ ተው፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናልና›› አለው፡፡ ከዚህም በኋላ ተወው፡ ጌታችን ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆ ሰማይም ተከፈተለት፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ አየ፤ እነሆም ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው››የሚል ድምጽ ተሰማ፡፡(ማቴ.፫፥፲፫-፲፯)

መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መውረዱም ምሥጢር አለው፡፡ ርግብ ኃዳጊተ በቀል ናት፤ መንፈስ ቅዱስም ኃዳጌ በቀል ነውና፡፡ ርግብ በኖኅ ጊዜ ‹‹ሐጸ ማየ አይኅ ነትገ ማየ አይኅ፤ የጥፋት ውኀ ጎደለ›› ስትል ቆጽለ ዕፀ ዘይት ይዛ ተገኝታለች፡፡ መንፈስ ቅዱስም ተስፋ መስቀልን ያበሥራልና፡፡

እኛም የሐዲስ ኪዳን ሕዝቦች ይህን ምሥጢር በመረዳት፣ መከራ መስቀሉን በመሸከምና እምነት በመጽናት እንድኖንር አስፈላጊ በመሆኑ ነገረ ድኅነቱን በመረዳት በልደቱ እንደዘከርነው ሁሉ በጥምቀቱም እንዲሁ እናደረግ ዘንድ ይገባል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀውም በሠላሳ ዓመቱ ነው (ሉቃ. ፫፥፳፫)፡፡ በሠላሳ ዓመቱ የተጠመቀበት ምሥጢርም አዳም የሠላሳ ዓመት፤ ሔዋን የዐሥራ አምስት ዓመት ሰው ሆነው ተፈጥረው አዳም በዐርባ ቀን፣ ሔዋን በሰማንያ ቀን ከሥላሴ የተቀበሉትን ልጅነት በምክረ ከይሲ ዕፀ በለስን በልተው አስወስደው ነበረና በሠላሳ ዓመቱ ተጠምቆ መልሶላቸዋል፡፡ በሠላሳ ዓመት የመጠመቁ ምሥጢር ይህ ሲሆን እኛ ዛሬ ወንዶች በዐርባ ቀን፣ ሴቶች በሰማንያ ቀን በዕለተ ዓርብ ከቀኝ ጎኑ በፈሰሰው ማየ ገቦ ተጠምቀን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ሁለተኛ የምንወለድበት ምክንያትም አዳም በዐርባ ቀኑ፣ ሔዋን በሰማንያ ቀኗ ከሥላሴ ያገኙትን ልጅነት መሠረት በማድረግ ነው /ኩፋ. ፬፥፱/፡፡ የምንጠመቀውም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡  ወእንዘ ታጠምቅመው በሉ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤ ስታጠምቋቸውም በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው፤››ንዲል(ማቴ. ፳፰፥፲፱)፡፡

በአሁኑ ጊዜም ታቦታቱን ወደ ጥምቀተ ባሕር በማውረድ በዓለ ጥምቀቱን ለሚያከብሩ ክርስቲያኖች በሙሉ ከታቦታቱ ሁለት ሺህ ክንድ ርቀው መከተል እንዲገባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ተብሎ ተገልጿል፤ ‹‹ሕዝቡን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ ከሠፈራችሁ ተነሥታችሁ ተከተሉት፡፡ በእናንተና በታቦቱ መካከል ያለው ርቀት በስፍር ሁለት ሺህ ክንድ ይሁን፡፡ በዚህ መንገድ በፊት አልሄዳችሁበትና፤ የምትሄዱበትን መንገድ እንድታውቁ ወደ ታቦቱ አቅርቡ፡፡›› (ኢያ.፫፥፩-፲፯)

ታቦታቱ ወደ ጥምቀተ ባሕር ወርደው ለማደራቸው መነሻ ይህ ትምህርት ነው፡፡ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀትም ከተጠመቀበት ከ፴ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በየዓመቱ ጥር ፲፩ ቀን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ሲከበር ይኖራል፡፡

ከበዓለ ጥምቀቱ ረድኤት፣ በረከት ይክፈለን፡፡