ጎንደር – የቅዱሳት መካናት ማኅደር

ሚያዚያ 14 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ጸበል ጸዲቅ /ክፍል ሦስት/


ጎንደር ገብተናል፡፡ ዞር ዞር እያልኩ ለመቃኘት ጊዜ አልወሰድኩም፡፡ የምችለውን ያህል እግሬ እሰከመራኝ ተጓዝኩ፡፡ ጎንደር ውስጥ አንድ ቤተ ክርስቲያን ለማግኘት አንድ ኪሎ ሜትር መጓዝ አይጠበቅብዎትም፡፡ ቀና ብለው አካባቢውን በዓይንዎ መቃኘት ብቻ ይበቃዎታል፡፡  ከሰሜን ወደ ደቡብ፤ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ቢመለከቱ በእርግጠኝነት የቤተ ክርስቲያን የጉልላት መስቀል እንዳሻዎት ያገኛሉ፡፡ በቃ ወደ ተመለከቱበት አቅጣጫ ማምራት፡፡ 44ቱ ተቦት የሚለው አባባል ቀድሞ በጎንደር 44 ታቦታት ስለነበሩ አይደል?

ወቅቱ የዐብይ ጾም በመሆኑ ከሌሊት ጀምሮ ስብሐተ እግዚአብሔር እንደ ጅረት ውኃ ያለማቋረጥ ከሊቃውንቱ አንደበት ይፈስሳል፡፡ ተኝተውም ይሁን ሥራ ላይ ሆነው አብረው ለማዜም ይገደዳሉ፡፡ ይህንን ዓለም አስረስተው ሰማያዊውን መንግሥት በተመስጦ ያስባሉ፡፡ ነፍስዎ በሚደርሰው ስብሐተ እግዚአብሔር ይለመልማል፡፡

ከጠዋት እስከ ስድስት ሰዓት፤ ከዚያም እስከ 9፡00 ሰዓት ምግብ ቤቶች፤ ሆቴሎችና ሻይ ቤቶች ሳይቀር ወንበሮቻቸውን ታቅፈው የሰው ያለህ ማለታቸው ጎንደር ውስጥ በጾም ወራት የተለመደ ነው፡፡ አንገቱ ላይ ክር ያላሰረ ለማየት ይቸግራል፡፡ ጎንደር ፈካ ደመቅ ማለት የምትጀምረው ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ሥርዓተ ቅዳሴ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው፡፡ ጎንደር! የታላላቅ ቅዱሳት መካናት፤  የሊቃውንት ማኅደር፤ የነገሥታት አሻራ ያገዘፋት ከተማ!!

የጋዜጠኞቹ ቡድን ጎንደርን ተከፋፈልናት፡፡ በውስጧ ሸሽጋ ያኖረቻቸውን የአብያተ ክርስቲያናት ታሪክ፤ የሊቃውንቱ የሕይወት ተሞክሮ ለሌሎች ለማቃመስ ቸኩለናል፡፡ ለዛሬ ጎንደር ካቀፈቻቸው ቅዱሳት መካናት መከካል አንዱን ከብዙ በጥቂቱ እንካችሁ ጸበል ጸዲቅ ቅመሱ፡፡

የደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም ገዳም
kuskuam 01የደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም ገዳም ከጎንደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በስተ ሰሜን አቅጣጫ ተራራው አናት ላይ በጥንታዊ ስልጣኔ አሻራ ባረፈበት ግንብ አጥር ታቅፎ ለሚያየው ውስጡን ይመረምሩ ዘንድ ይጋብዛል፡፡ ዓይኔም ልቦናዬም አርፎበታልና ስለዚህ ቤተ ክርስቲያንና ቤተ መንግሥት ለማወቅ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ አቀበቱን እንደወጣሁ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአብነት ትምህርት ተማሪዎች ጎጆዎችን አገኘሁ፡፡ ከተማሪዎቹ መካካል አንዱን እንኳን ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ወደ ገዳሙ የሚያስገባው መንገድ እየተሠራ በመሆኑ አንዱን ሠራተኛ ጠየቅሁት፡፡ ወደ ጫካ ለቅኔ ቆጠራ ሄደዋል አለኝ፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መግቢያ ተጠጋሁ፡፡ ከሦስት ሜትር በላይ እርዝመት ያለውና በኢትዮጵያውያን  ጠቢባን በድንጋይ የተገነባ ግንብ ጥንታዊነቱን በሚመሰክር ሁኔታ እርጅና ቢጫጫነውም ጥንካሬው ጎልቶ ይታያል፡፡ አጥሩ በዐፄ ፋሲል ግንብ ዲዛይን የተሠራ ነው፡፡   

ተሳልሜ ደጀ ሰላሙን እንዳለፍኩ አባቶችን ሳፈላልግ የገዳሙ የሙዝየም አስጎብኚና የቅኔ መምህሩ የኔታ ዳንኤል ኃይሉን አገኘሁ፡፡ የመጣሁበትን አስረድቼ፤ የተጻፈልኝን የፈቃድ ደብዳቤ በማሳየት ለምጠይቃቸው ጥያቄ ይመልሱ ዘንድ ፈቃደኛ በመሆናቸው አንድ ጥግ ያዝን፡፡ የነገሩኝን እንዲህ አዘጋጀሁት?!

አመሠራረቱ፡-
የደብረ ጸሐይ ቁስቋም ማርያም ገዳም በ1930ዎቹ ዓ.ም በአፄ በካፋ ባለቤት በእቴጌ ምንትዋብ አማካይነት የተሠራ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ አመሠራረቱም ዐፄ በካፋ ከሞቱ በኋላ እቴጌ ምንትዋብ ልጃቸውን ኢያሱን አንግሠው ከዐፄ ፋሲል ቤተ መንግሥት ግቢ በመውጣት ይህ ዓለም ይቅርብኝ፡ እመቤቴ ቅድስት ድንግል ማርያም በስደት በግብፅ በደብረ ቁስቋም ተራራ ላይ እንደተገኘች ሁሉ እኔም ለብቻዬ ልቀመጥ በማለት ቤተ መንግሥታቸውን ጥለው ቤተ ክርስቲያኑን በማሠራት ተቀመጡ፡፡  ከዚሁ ጋር በማያያዝም ቤተ መንግሥታቸውን አሠሩ፡፡ ቤተ ክርስቲያኑንና ቤተ መንግሥቱን ለማሠራት አንድ ሺሕ ግንበኞችና ባለሙያዎች የተሳተፉበት ሲሆን ለሁለት በመክፈል አምስት መቶው ሠራተኞች አንድ ቀን ሲሠሩ ሌሎቹ ደግሞ እያረፉ በየተራ ሠርተውታል፡፡ቤተ ክርስቲያኑንም ስደታቸውን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስደት ጋር በማያያዝ በደብረ ቁስቋም ሰየሙት፡፡ ከሁለት ሃምሳ በላይ ቀሳውስትና ካህናት አገልጋዮች ነበሩት፡፡

እቴጌ ምንትዋብ ሲያርፉም በቤተ ክርስቲያኑ ምድር ቤት ውስጥ ባሠሩት መቃብር ቤታቸው አስከሬናቸው እንዲያርፍ የተደረገ ሲሆን ልጃቸው ኢያሱና የኢያሱ ልጅ ኢዮአስkuskuam 03 ሲያርፉም አብረው በእቴጌ ምንትዋብ መቃብር ቤት ተቀብረዋል፡፡

በ1881 ዓ.ም. ደርቡሽ ጎንደርን ሲወርር ጎንደር የሚገኙትን ብዙዎቹን ቤተ ክርስቲያናት ስያቀጥልና ሲያወድም ካህናቱ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታቦት ወደ በለሳ በማሸሽ አስቀመጡት፡፡ ደብረ ቁስቋም ቤተ ክርስቲያንም ሙሉ ለሙሉ ወደመ፡፡ ቤተ መንግሥቱንም ደርቡሽ አፈራረሰው፡፡ አብዛኞቹ ቅርሶችም ተቃጠሉ፡፡ የተረፉትም ቢሆን ተዘርፈው ተወሰዱ፡፡ ካህናቱም ወደተለያዩ ቦታዎች ተበተኑ፡፡

ቅርሶች፡- ከጦርነቱ በኋላ ታቦቱን ወደነበረበት በመመለስ ቀድሞ እቃ ቤት የነበረውን  ቤት ቤተ መቅደስ በማድረግ በጥቂት ካህናት ብቻ ለሰማኒያ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ ከቆየ በኋላ በ1960ዎቹ ዓ.ም. ዐፄ ኃይለ ሥላሴ አሁን ያለውን ቤተ ክርስቲያን አሠሩት፡፡ የእቴጌ ምንትዋብና የልጃቸው ኢያሱ፤ እንደሁም የኢያሱ ልጅ ኢዮአስን ዓፅም በአንድ ላይ በመሰብሰብ በሳጥን ውስጥ እዲቀመጥ ተደረገ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በሙዝየሙ ውስጥ ከሚጎበኙ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው፡፡

በሙዝየሙ ውስጥ የእቴጌ ምንትዋብና የልጆቻቸው በእንጨትና በጠፍር/ቆዳ/ የተሠራ አልጋ፤ በቀርከሃና በቆዳ የተሠሩ የከበሩ ዕቃዎች ማስቀመጫ ሻንጣዎች፤ ሚዛን፤ የደርቡሽ ጦር ካወደማቸው ሃይማኖታዊ የብራና መጻሕፍት የተረፉት ወንጌል ቅዱስ፤ ተአምረ ኢየሱስ፤ ግንዘት፤ ስንክሳር፤ ነገረ ማርያም፤ ሃማኖተ አበው፤ አሥራ አራቱ ቅዳሴያት፤ ግብረ ሕማማት፤ ገድለ ሠማዕታት፤. . . ከበሮ፤ የተለያዩ መጠን ያላቸው መስቀሎች፤ ነጋሪት፤ ከሙዝየሙ ውጪ በሩ አጠገብ የእቴጌ ምንትዋብ የድንጋይ ወፍጮ፤ . . .  ይገኛሉ፡፡

kuskuamቅዱሳት ሥዕላት፡- በሙዝየሙ ውስጥ በቅርስነት ከተያዙት ውስጥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስለ ፍቁር ወልዳና የቅዱስ መርቆርዮስ ቅዱሳት ሥዕላት ይገኙበታል፡፡

ቤተ መንግሥት፡- ቤተ መንግሥቱ ሰባት በሮች አሉት፡፡ የእቴጌ ምንትዋብ መኝታ ቤት፤ የገላ መታጠቢያ ቤት፤ ሣሎን፤ በዘመኑ የነበረው ታሪክ ጸሐፊው ጀምስ ብሩስ ይኖርበት የነበረው ክፍል፤ ካህናቱና ቀሳውስቱ የሚመገቡበት የግብር ቤት፤ ቤተ ክርስቲያኑንና ቤተ ክርስቲያኑን ያነጹት ባለሙያዎች ማረፊያ ክፍሎችና ዕቃ ማስቀመጫ ክፍሎች፤ . . . ፈራርሰው ይታያሉ፡፡

ጉባኤ ቤት፡- ጥንት የድጓ፤ የቅኔ፤ የአቋቋም፤ የቅዳሴ ጉባኤ ቤቶች እንደነበሩና ደርቡሽ ቤተ ክርስቲያኑን ካፈረሰ በኋላ ግን ጉባኤ ቤቶቹkuskuam 08 ተፈትተው ለረጅም ዘመናት ሳይተከሉ ኖረዋል፡፡ ጉባኤ ቤቱ በተደራጀ መልኩ ከተተከለ ሃያ ዓመታት ብቻ አስቆጥሯል፡፡ የቅኔ፤ የአቋቋም፤ የድጓና የቅዳሴ ጉባኤ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ከ500 በላይ ተማሪዎች ሲኖሩ 280 የሚደርሱት የቅኔ ተማሪዎች ናቸው፡፡

መረጃዎቻችንን እንዳሰባሰብን ያመራነው ወደ ጉባኤ ቤት ነው፡፡ ከየኔታ ዳንኤል ኃይሉ ጋር ተያይዘን ስንሄድ የቅኔ ተማሪዎቻቸው ከያሉበት ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ ሌሊት ዕለቱን በማስመልከት የኔታ ካስረዷቸው በኋላ ለቅኔ ቆጠራ ይሠማራሉ፡፡ የኔታ በተማሪዎቻቸው ተከበቡ፡፡ የነገራ ሰዓት በመሆኑ ለጥቂት ደቂቃዎች እንድታገስ ጠየቁኝ፡፡ አላመነታሁም፡፡ ተማሪዎቹ ወንበር አውጥተው እንዲቀመጡ ካመቻቹላቸው በኋላ በአእምሯቸው ሲያመላልሱት የቆዩበትን ቅኔ ቆጠራ መዝረፍ ጀመሩ፡፡ ሲሳሳቱ እያረሙ፤ ያልተሳካለትን እየገሰጹ ቆዩ፡፡

 
የተማሪዎቹን የውድድር ስሜትና ለትምህርቱ ያላቸው ፍላጎት እያስገረመኝ ከተማሪዎቹ መካከል አይኖቼ ድንገት በለጋነት እድሜ ክልል የሚገኙ መነኩሲት ላይ አረፉ፡፡ ላነጋግራቸውም ወሰንኩ፡፡

የኔታ ከዚህ በላይ ሊያስቆዩኝ አልፈለጉም፡፡  ጉባኤውን አቋረጡት፡፡ እኔም እማሆይን ለመጠየቅ በመፍጠን ማንነታቸውን፤ ለምን መማር እንደፈጉ ጠየቅኋቸው፡፡

kuskuam 07“እማሆ ወለተ መድኅን እባላለሁ፡፡ ከአክሱም ነው የመጣሁት፡፡ በልጅነት ከመነኮስኩ አይቀር ጉባኤ ቤት መግባት አለብኝ ብዬ ስለወሰንኩ እዚህ እየተማርኩ እገኛለሁ፡፡ ትምህርቱንከጀመርኩ አንድ ዓመት ሆኖኛል፡፡ ጉባኤ ቃና፤ ዘአምላክየ፤ ሚበዝኁ፤ ዋዜማ፤ ሥላሴ፤ ዘይእዜ፤ ክብር ይእቲ፤ እጣነ ሞገርን አልፌ መወድስ ላይ ደርሻለሁ፡፡ እግዘአብሔር ቢፈቅድ ትምህርቴን አጽንቼ በመያዝ እግዚአብሔር ቢፈቅድ እንደ እማሆይ ገላነሽ ለመሆን ነው ምኞቴ” አሉኝ፡፡ ምኞታቸው እንዲሳካ ተመኘሁ፡፡

ከቀደሙት ነገሥታት የሃይማኖት ጽናትንና ቅርስን ለትውልድ ማቆየትን ተማርኩ፡፡ ከጉባኤ ቤቶቹ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን የማይነጥፍ የሊቃውንት ምንጭ እንዳላት ተገነዘብኩ፡፡   
የኔታንና ተማሪዎቹን ተሰናብቼ ሌላ መረጃ ልቆፍር ተጓዝኩ፡፡

ይቆየን