ግሸን ማርያም
መስከረም ፳ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ወሎ፣ አምባሰል አውራጃ ውስጥ በደብር በሐይቅና በመቅደላ፣ በደላንታ፣ በየጁ መካከልና በበሸሎ ወንዝ አዋሳኝ የምትገኝ አንድ መግቢያ በር ብቻ ያላት ዙሪያውን በገደል የተከከበች አምባ ትገኛለች፡፡ በበርዋ ራስ ላይም የመስቀል ምልክት ሲኖር አጥርዋን አልፈን ከገባን በኋላ ግቢዋ ከላይ ሜዳና መስቀለኛ ቦታ ነው፡፡
ደብርዋም በመጀመሪያ ደብረ እግዚአብሔር በሚለው ስያሜ ትታወቅ ነበር፡፡ በንጉሥ ቅዱስ ላሊበላ እጅ ከቋጥኝ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራ ቤተ መቅደስ በእግዚአብሔር አብ ስም ስለነበረ ደብረ እግዚአብሔር ተብሎ ተጠራ፡፡ ከዚያም የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ሲመሠረት ሐይቅ ደብረ ነጎድጓድ ተብሎ ሲሰየም ግሸን የሐይቅ ግዛት ስለሆነች ከደብረ እግዚአብሔር ደብረ ነጎድጓድ ተብላለች፡፡ ከዚያም በ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በዓፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት የክርስቶስ ግማደ መስቀሉ ግሸን ገብቶ ሲቀመጥ ከደብረ ነጎድጓድ ደብረ ከርቤ ተብላለች፡፡ የደብሩ አስተዳዳሪም መምህረ እሥራኤል ዘደብረ ከርቤ ትባል ነበር፤ ከደብረ ከርቤም ግሸን ማርያም ተብላለች፡፡
የግሸን ማርያም ደብር መመሥረት ከግማደ መስቀል ጋር የተያያዘ ዋነኛ ምክንያት አለው፡፡ በዳግማዊ ዓፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት የእስክንድሪያ ሙስሊሞች ክርስቲያኖች ላይ ባደረሱባቸው ግፍና በደል ሳቢያ በሥቃይ ሆነው ለኢትዮጵያው ንጉሥ ድብዳቤ ጻፉ፤ ‹‹ንጉሥ ሆይ! በዚህ በግብጽ ያሉ እስላሞች መከራ አጽንተውብናልና ኃይልህን አንሥተህ አስታግሥልን›› ብለውም ጠየቁት፡፡ ዳግማዊ ዓፄ ዳዊትም ፳ ሺህ ሠራዊት አስከትለው በግብፅ ላይ ዘመቱ፡፡
ስለዚህም ግብጾች ፈሩ፤ ተሸበሩም፤ በዚያን ጊዜም ንጉሥ ዓፄ ዳዊትም ‹‹በተፈጥሮ ወንድሞቻችሁ ከሆኑት ክርስቲያኖች ጋር ካልታረቃችሁ ሀገራችሁን መጥቼ አጠፋለሁ›› የሚል ማስጠንቀቂያ ላኩ፡፡ ሙስሊሞቹም የንጉሡ መልእክት እንደደረሳቸው ፈሩ፤ ከክርስቲያንቹም ጋር ታርቀው እንደቀድሞ መኖር ጀመሩ፡፡ ንጉሡም ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው፡፡ አምላካቸው እግዚአብሔርንም አመሰገኑ፡፡
ከዚህም በኋላ ግብፃውያኑም በአንድነት ተማክረው ለኢትዮጵያው ንጉሥ ዓፄ ዳዊት ከ፲፪ ሺህ ወቄት ወርቅ ጋር ደስታቸውን ለኢትዮጵያው ንጉሥ ለዓፄ ዳዊት በደብዳቤ አድርገው ላኩላቸው፤ ንጉሡም ደብዳቤውን በደስታ ቢቀበሉም ወርቁን ግን መልሰው በመላክ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ፃፉ፤ ‹‹በግብፅ የምትኖሩ የክርስቶስ ተከታዮች ሆይ፥ እንኳን ደስ አላችሁ! የላካችሁልኝን ፲፪ ሺህ ወቄት ወርቅ መልሼ ልኬላችኋለሁ፤ የእኔ ዓላማ ወርቅ ፍለጋ አይደለም፤ የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶኝ በተቻለኝ ችግራችሁን ሁሉ አስወገድኩላችሁ፤ አሁንም የምለምናችሁ በሀገሬ በኢትዮጵያ ረሀብና ቸነፈር ድርቅ ስለወረደብኝ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎበት የነበረውን መስቀልና የቅዱሳንን አፅም ከሌሎች ክቡራን ዕቃዎች ጋር እንድትልኩልኝ ነው፡፡››
የእስክንድርያ ክርስቲያናትም መልዕክቱ ሲደርሳቸው ከሊቃነ ጳጳሳቱና ከኤጲስ ቆጶሳቱ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ‹‹ይህ ንጉሥ ታላቅ ክርስቲያን ነው፡፡ ስለዚህ ልቡን ደስ እንዲለው የፈለገውን የጌታችንን ግማደ መስቀል ከቅዱሳን አጽምና ንዋየ ቅድሳት ጋር አሁን በመለሰው ፲፪ ወቄት ወርቅ የብርና የንሐስ የመዳብና የወርቅ ሣጥን አዘጋጅተን እንላክለት›› በማለት ከተስማምተውና በክብር በሥነ ሥርዓት በሠረገላና በግመል ካስጭኑ በኋላ ስናር ድረስ አምጥተው ባስረከቧቸው ጊዜ ኢትዮጵያውያን በታላቅ ዝማሬ እያጨበጨቡና እያሸበሸቡ በግንባራቸው እየሰገዱ በክብር በደስታ ተቀበሉት፤ ያችም የተከበረች ዕለት መስከረም ፳፩ ነበረች፡፡
ከዚያም በኋላ ግማደ መስቀሉ ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ ሳይደርስ በድንገት ዓፄ ዳዊት ስናር ላይ ዐረፉ፡፡ የግድም በዚያው በስናር መቆየት አስፈለገው፡፡ የዳግማዊ ዳዊት ልጅ ዘርዐ ያዕቆብ አባታቸውን ተክተው እንደነገሡ ወደ ስናር ሄደው ግማደ መስቀሉን ከሌሎቹ ንዋየ ቅድሳት ጋር አምጥተው በመናገሻ ከተማቸው በደብረ ብርሃን ላይ ቤተ መቅደስ ሠርተው ለማስቀመጥ ጥረት አደረጉ፡፡ ያን ጊዜም ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ ወዳጄ ዘርዐ ያዕቆብ ሆይ፥ መስቀሌን በመስቀልኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ›› የሚል ራእይ አዩ፡፡ ንጉሡም በኢትዮጵያ አውራጃዎች ሁሉ መስቀለኛ ቦታ በመፈለግ በመጀመሪያ በሸዋ በደርሄ ማርያም ከዚያም በመናገሻ ማርያም ቀጥሎም በወጨጫ መስቀሉን አሳርፈውት ነበር፡፡ ሆኖም ግን የመጨረሻውን ቦታ እስኪያገኙ እግዚአብሔር አምላክ በራእይ እየደጋገገመ ‹‹መስቀሌን በመስቀልኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ›› ይላቸው ነበር፡፡ እርሳቸውም ቦታው ስላልተገለጠላቸው መስቀሉን ይዘው መላ ኢትዮጵያን ዞሩ፤ በዚህም ሀገራችን በግማደ መስቀሉ ተባረከች።
አምላካቸው ምሥጢሩን ይገልጥላቸው ዘንድም ዓፄ ዘርዐ ያዕቆብ ለሰባት ቀናት ያህል ሱባዔ ገቡ፤ በዚያም ራእይ ተገልጦ ‹‹መስቀለኛውን ቦታ የሚመራህ ዓምድ ብርሃን ይመጣል›› አላቸው፡፡ ከሱባኤያቸው በዓት እንደወጡ መስቀለኛውን ቦታ የሚመራ ዓምደ ብርሃን ከፊታቸው መጥቶ ቆመ፡፡ በዚያ መሪነት ወደ ወሎ ክፍለ ሀገር አምባሰል አውራጃ ውስጥ ግሸን ከምትባል ቦታ መርቶ አደረሳቸው፡፡ ግሽን የተባለችውም አምባ በጥበበኛ የቀረጸችና የተዋበች መስቀልኛ ቦታ ሁና ስለአገኟት በልባቸው ደስ ተሰኙ፡፡ በዚያችም አምባ ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርተው መስቀሉንና ሌሎች ንዋየ ቅድሳቱን በየማዕረጋቸው የክብር ቦታ መድበው አስቀመጧቸው፡፡
ከእነርሱም መካከል ጌታ በዕለተ ዓርብ ለብሶት የነበረው ቀይ ልብስ ከሮም የመጣ ከለሜዳ፣ ከአፍርጌ ሀገር የመጣው ሐሞት የጠጣበት ሰፍነጉ፣ ቅዱስ ዮሐንስ የሳለው የኲርዓተ ርዕሱ ስዕል፣ ቅዱስ ሉቃስ የሳለው የእመቤታችን ስዕል፣ የበርካታ ቅዱሳን አጽምና በኢየሩሳሌም ውስጥ ከልዩ ልዩ ቅዱሳት መካናት የተቆነጠረ የመሬት አፈር፣ የዮርዳኖስ ውሃ፣ በግብጽ ውስጥ ከሚገኙት ታላላቅ ገዳማት የተቆነጠረ አፈር ይገኙበታል፡፡ ዓፄ ዘርዐ ያዕቆብም የንዋየተ ቅዱሳቱን ዝርዝር ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለግሸን ካህናት መስከረም ፳፩ ቀን ፩፻፬፻፵ ዓ.ም. ላይ አሳወቁ፡፡ ግማደ መስቀል በመጀመሪያ ከእስክንድርያ ስናር የገባው መስከረም ፲ ቀን ሲሆን ወደ ኢትዮጵያም የገባው በመስከረም ፳፩ ቀን ነው፡፡ በዚህም ዕለት ግሸን አምባ ገብቶ ቤተ መቅደስ ተሠርቶለት ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል፡፡
በዘመኑ የነበሩት የኢትዮጵያ ጳጳሳት አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤል ከንጉሡ ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ጋር በኅብረት በግሸን ደብር ሱባዔ ገቡ፤ በሱባዔአቸውም መጨረሻ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ‹‹ይህች ቦታ እኔ ተወልጄ ያደኩባትን ኢየሩሳሌምን ትሁን፤ የተሰቀልኩባትን ቀራንዮን ትሁን፤ የተቀበርኩባትንም ጎልጎታን ትሁን፤ በዚች ቦታ እየመጣ የሚማፀነውን ሁሉ ቸርነቴ ትጎበኘዋለች፤ ጠለ ምህረቴም አይለይባትም›› አላቸው፤ በዚያ ለተገኙት ምእመናን ሁሉ በጽሑፍ አሳወቁ፤ በኋላም የግማደ መስቀሉንና የንዋየ ቅዱሳትንም ዝርዝር ታሪክ የያዘውን መጽሐፈ ጤፉት ብለው ሰይመው ድንጋጌውን ሁሉ በመዘርዘር ለግሸን እግዚአብሔር አብ አበረከቱ፡፡
ዐፄ ዘር ያዕቆብም ለንግሥት እሌኒ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ቤተ መቅደስ እንድትሠራ አዘው የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ አሳንጻ ጥር ፳፩ ቀን ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ፤ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብም ይህችን ደብር ‹ደብረ ከርቤ› ብለው በመሰየም ‹‹እንኳንስ ሰው የሠገረ ቆቅ፤ የበረረ ወፍ እንዳይገደል ዳሯ እሳት መካከሏ ገነት ትሁን›› ብለው ደንብና ሥርዓት በመጽሐፈ ጤፉት ውስጥ አጽፈዋል፡፡ በዚያም ይህንም ተከትሎ የነገሡ የኢትዮጵያ ነገሥታትና የተሾሙ ጳጳሳት መሳፍንትና መኳንንት ልዩ ልዩ ንዋየ ቅድሳትንና መጻሕፍትን የወርቅንና የብር ጻሕል ጽዋን መስቀልን የመሳሰሉትን ሥጦታ አበርክተዋል።
በየዓመቱ መስከረም በባተ በ፳፩ኛው ቀንም በግሸን ደብር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ከበረከተ መስቀሉና ከቅዱሳን አፅም በረከት ለማገኘት ከየክፍለ ሀገራቱ እየመጡ ያከብራሉ፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር ከበረከተ መስቀሉ ያሳትፈን፤ አሜን፡፡