‹‹ጌታችን በመለከት ድምጽ ዐረገ›› (መዝ. ፵፮፥፭)
ሰኔ ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
ነቢዩ ዳዊት ለመዘምራን አለቃ የቆሬ ልጆች አስቀድሞ በመንፈሰ ትንቢት ‹‹አምላካችን በዕልልታ፥ ጌታችንም በመለከት ድምጽ ዐረገ፥ ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ፤ ዘምሩ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ›› በማለት እንደተናገረ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን ፈጽሞ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ በዐርባኛው ቀን ዐርጓል፤ እኛም ይህንን ቃል በማሰብና በማክበር የጌታችንን የዕርገት በዓል ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን አመላካች በመሆኑ በዝማሬ እና በዕልልታ እናከብር ዘንድ ይገባል፡፡ (መዝ.፵፮፥፭)
የጌታቸን ዕርገት እንደ ኤልያስ እንደ ሄኖክ እንደሌሎቹም ቅዱሳን ሳይሆን በገዛ ሥልጣኑ ነው፤ ሌሎች ግን አጋዥ አሥነሽ ይሻሉና፡፡ የእርሱም ማረግ በነቢያት የትንቢት መጽሐፍት የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ በመሆኑም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ በ፵ኛው ቀን በክብር በምስጋና ዐርጓል፡፡ በ፵ኛው ቀንም የተነሣበትም ምክንያት አዳም በ፵ ቀን አግኝቶ ያጣትን ልጅነት እንደተመለሰለት ለማጠየቅ፣ ጌታችን በረቀቀ ጥበቡ ሐዋርያትን ለማጽናት፣ አይሁድም ዕርገቱ ከትንሣኤው አስከትሎ ወዲያው ቢሆን ምትሐት እንጂ የእግዚአብሔር ሥራ እንደሆነ ስለማይቀበሉ በሞቱ ሞትን ድል አድረጎ የተነሣው ወልደ እግዚአብሔር መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ መሆኑን እንዲረዱ ለማድርግ እንዲሁም ከአሕዛብ ወገን የሆኑት እስራኤላውያን (አይሁድ) በተሠራላቸው የንስሓ ሥርዓት በክርስቶስ አምላክነት አምነው እንዲመለሱ ለማድረግ ነው፡፡ በዘመነ ሥጋዌ ከአይሁድ ወገን በጌታችን አምነው የዳኑ ብዙዎች ነበሩና፡፡
በዕርገቱም ዕለት ሐዋርያት በተሰበሰቡበት እንዲህ አላቸው፤ ‹‹እነሆ፥ እኔ የአባቴን ተስፋ ለእናንት እልካለሁ፤ እናንተ ግን ከአርያም ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀመጡ፡፡›› ከዚያም እስከ ቢታንያ መውጫ ድረስ ወሰዳቸውና ባከራቸው፡፡ እየራቃቸውም ሄደ፤ በደመናም ወደ ሰማይም ዐረገ፡፡ በአባቱ ቀኝም ተቀመጠ፤ ሐዋርያቱም ሰገዱለት፤ እጅግም ደስ ብሏቸው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፡፡ አምላካቸውን እግዚአብሔርንም ዘወትር በምስጋና ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡ (ሉቃ.፳፬፥፵፱-፶፪፣ማር.፲፮፥፲፱)
ጌታችንም ለአዳም የገባለትን ቃል ከፈጸመ በኋላ ወደ መንግሥተ ሰማይ የማረጉ በምድራዊ ሕይወታችን የሚገጥመንን ሁሉ ችግርና መከራ ተቋቁመን በክርስቲያናዊ ሕይወት ኖረን በከበረ ሞት መንግሥተ ሰማያትን እንደምንወርስ ያመለክታል፡፡ እርሱ በመሠረተልንም የድኅነት መንገድ በመጓዝ በዳግም ምጽአቱ በቀኙ እንደምንቆም ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን ሰጥቶናል፡፡
ነቢዩ ዳዊትም እንደተናገረው ጌታችን በመለከት ድምጽ እንዳረገና አባቱ ቀኝም እንደተቀመጠ ሁሉ እኛም በምጽአት ቀን ቅዱሳን መላእክት በንፍሐተቀርን ወይም የመለከትን ድምጽ ሲያሰሙ በክብር ተነሥተን የመንግሥቱ ወራሽ እንደምንሆን ነግሮናል፡፡
በጽድቅ ሥራ የኖሩ ሰዎች ደግሞ መንግሥተ ሰማያትን የመውረስ ክብር ሲያገኙ ከመላእክት ጋር አንድ ሆነው እግዚአብሔር አምላክን በማመስገን በግዛቱ ለዘለዓለም ይኖራሉ፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ዐይን ያላየው፥ ጆሮም ያልሰማው፥ በሰውም ልቡና ያልታሰበ እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ነው›› ሲል ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ተናግሯል፡፡ (፩ኛ ቆሮ. ፪፥፱)
ሐዋርያውም በራእዩ ስላየውም ስለ አንድ በክርስቶስ ስላመነና እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ስለተነጠቀ ሰው እንዲህ ሲል ገልጿል፤ ‹‹ያን ሰው አውቀዋለሁ፤ በሥጋው ይሁን በነፍሱ እንጃ፥ እግዚአብሔር ያውቃል፡፡ ወደ ገነትም ነጥቀው ወሰዱት፤ በዚያም ሰው ሊናገረው የማይችለውን የማይተረጎም ነገር ሰማ፡፡ ስለዚህም እንደዚህ ባለው እመካለሁ፤ በመከራዬ እንጂ በራሴስ አልመካም፡፡›› (፪ኛቆሮ.፲፪፥፫-፭)
እኛም በዓይናችን ባናየው በጆሮአችንም ባንሰማውም መንግሥተ ሰማያት በእግዚአብሔር መንግሥት መኖር በመሆኑ አምላካችን ጋር የመኖር ተስፋን ሰንቀን በተስፋ እንኖራለን፡፡
ጌታችን ኢየሱስም ስለ መንግሥተ ሰማያት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ዳግመኛም መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ የተቀበረች ወርቅን ትመስላለች፤ ሰውም አግኝቶ ሠወራት፤ ከደስታውም የተነሣ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያችን እርሻ ገዛት፡፡ ዳግመኛም መንግሥተ ሰማያት ክቡር ዕንቊን ትመስላለች፡፡ ዋጋዋም ብዙ የሆነ አንዲት ዕንቊን በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት፡፡ ዳግመኛም መንግሥተ ሰማያት በባሕር ውስጥ የተጣለችውን፥ የዓሣ ወገንን ሁሉ የሰበሰበችውን መረብ ትመስላለች፡፡ በሞላችም ጊዜ ወደ ዳር አወጡአት፤ ተቀምጠውም መልካም መልካሙን መርጠው ወደ ሣጥናቸው ጨመሩ፤ መጥፎውን ግን ጣሉት፡፡›› (ማቴ.፲፫፥፵፬-፵፰)
እንደ ዓሣ በመረቡ የሚሰበሰቡትም የእግዚአብሔር ሕዝብ ናቸው፡፡ ሕዝበ እግዚአብሔር ደግሞ ፈጣሪያቸውን ይፈራሉ፤ ይታዘዛሉ፤ በሕጉ ይመራሉ፤ ትእዛዛቱን ይፈጽማሉ፤ በጎ ሥራን እንጂ ኃጢአትን አይፈጽሙም፡፡
ነገር ግን በዚህ ጊዜ አብዛኛው ሰው እግዚአብሔርን አይፈራም፤ ሕጉንም ይተላለፋል፤ ትእዛዛቱን አይፈጽምም፤ በድፍረትም ክፋትና በደልን ይፈጽማል፤ በጎ ሥራን እንደ ድክመት ወይንም እንዳለማወቅ ይቆጥራል፡፡ ስለዚህም ይህ እጅጉን ትልቅ ጥፋት መሆኑን ዐውቀን በንስሓ ወደ አምላካችን ልንመለስ ይገባል፡፡ የጌታችንን የዕርገት በዓልም ስናስብና ስንዘክር የእርሱን ነገረ ድኅነት በማሰብና ለመንግሥተ ሰማያት የበቃን ለመሆን በመዘጋጀት ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ መንግሥተ ሰማይትን እንድንወርስ ይርዳን፤ አሜን፡፡