‹‹ጊዜ ዕረፍታ ለሶልያና››
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ዕረፍት አደረሰን
በብዙአየሁ ጀምበሬ
በዕብራይስጥ ቋንቋ ሶልያና ማለት ጨረቃ ማለት ነው፤ ይህም መጠሪያ ለቅድስት ድንግል ማርያም ከተሰጡት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ‹‹ማርያም›› የሚለው ስም በዕብራይስጥኛ ማሪሃም ማለት ሲሆን ትርጉሙም ‹‹እመ ብዙኃን፤ የብዙዎች እናት›› ማለት ነው፤ በሌላም በኩል አበው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚከተለው ይገልጹዋታል፡፡
፩. ማርያም ማለት ‹‹መርሕ ለመንግሥተ ሰማያት፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት መሪ (መርታ የምታስገባ)›› ማለት ነው፡፡
ሕገ እግዚአብሔርን የጣሰው ጸጋ እግዚአብሔር የራቀው አዳም ወደ ቀድሞ ክብሩ እንዲመለስ ምክንያተ ድኅነት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ እኛ ክርስቲያኖች የእመቤታችንን አማላጅነት ተስፋ በማድረግ ወደ መንግሥተ ሰማያት እንገባለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ ድርሰቱ እንዲህ ብሏል ‹‹አልቦ ጸሎት፤ ወአልቦ ትንባሌ፤ እንበሌኪ ማርያም ዘየዐርግ ሉዓሌ፤ ያለ ማርያም አማላጅነት እና ተራዳኢነት ወደ ላይ (ወደ ሰማይ) የሚያርግ ጸሎትና ልመና የለም፡፡››
፪. ማርያም ማለት ጸጋ ወሀብት ማለት ነው፡፡
የእመቤታችን ወላጆች በጊዜው በመምከናቸው በሰው ዘንድ ተንቀው ነበርና ለእነርሱም በኀዘናቸው ጊዜ ስጦታ ሆና ተበረከተችላቸው፤ ፈጻሜው ግን አማላጅነቷን ተረድተው ቃል ኪዳኗን አምነው ለሚመጡ ምእመናን ሁሉ ሀብትና ጸጋ ትሆናቸው ዘንድ ተሰጥታለች፡፡
፫. ማርያም ማለት ፍጽምተ ሥጋ ወነፍስ፤ በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ማለት ነው፡፡
፬. ማርያም ማለት መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ፤ ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች የሆነች ማለት ነው፡፡ (ነገረ ማርያም ለግቢ ጉባዔያት የተዘጋጀ ገጽ ፪)
ከፍጡራን በላይ ናት ስንል በንጽሕናዋና ቅድስናዋ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተመረጠች፤ በማሕፀኗ እሳተ መለኮትን መያዝ የቻለች ስለሆነች ነው፡፡ እንዲሁም የስሟ የእያንዳንዱ ፊደል ትርጓሜ ተጠቅሷል፡፡
ማ– ማለት ማኅደረ መለኮት፤ ከአምላክ ዘንድ የተመረጠች የመለኮት ማደሪያ የሆነች ማለት ነው፡፡
ር– ማለት ርግብየ ይቤላ፤ ሰሎሞን ርግብየ ርግብየና ይላታልና፡፡
ያ– ማለት ያንቃዐዱ ኀቤኪ ኵሉ ፍጥረት፤ ፍጥረት ሁሉ ወደ አንቺ ዓይነ ኅሊናቸውን ይሰቅላሉ፤ አሕዛብ ሁሉ በፊትሽ ይማልላሉ፡፡ (መዝ. ፵፬፥፱)
ም– ማለት ምስአል ወምስጋድ ማለት ነው፤ እነሆ ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑኛል፡፡ (ሉቃ. ፩፥፵፰)
‹‹ማርያም›› ማለት ከፍጡራን ሁሉ በላይ፤ ከፈጣሪ በታች (መልዕልተ-ኵሉ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ) የሆነች ፍጡር ማለት ነው፡፡ ይህም የተባለበት ምክንያት ዓለምን የፈጠረ እግዚአብሔር በእርሷ አድሮ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሥጋን ተዋሕዶ ስለተወለደ ነው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደች የአምላክ እናት ናት፤ ከሰው ወገን እንደ እርሷ ጸጋን የታደለ የለም፡፡
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታሪክ
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር፡፡ ዓለም ከተፈጠረ በኋላም አባ ሕርያቆስ ‹‹ድንግል ሆይ የነቢያት ምሳሌ እና ትንቢት ነሽ›› ብሎ በቅዳሴ ማርያም እንደተናገረው ቅዱሳን ነቢያት በልዩ ልዩ ምሳሌ እየመሰሉ፣ ትንቢት እየተናገሩ፣ ክብረ ድንግልናዋን እና ወላዲተ አምላክነቷን መስክረውላታል፡፡ በተለይ ከነቢያት መካከል ታላቁ ነቢይ ኢሳይስ «እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች» ብሎ ትርጉም በማያሻውና በማያሻማ የትንቢት ቃል ተናግሮላታል፡፡ (ኢሳ.፯፥፲፬)
የዘር ሐረግ
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትውልድ ይህ ነው፤ በጥሪቃና ቴክታ የተባሉ በእግዚአብሔር ያመኑ ባለጸጎች ነበሩ፤ ልጅ ግን አልነበራቸውም፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ቴክታ ሕልም አለመች፡፡ ለባሏም እንዲህ ስትል ነገረችው «በራእይ ነጭ ዕንቦሳ ከበረታችን ስትወጣ፤ ያችም ዕንቦሳን እየወለደች እስከ ፮ ትውልድ ስትደርስ ፮ኛይቱ ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃ ደግሞ ፀሐይን ስትወልድ አየሁ» አለችው፡፡ (ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ)
በጥሪቃም «ራእዩስ ደግ ነው፤ የሚፈታልን የለም እንጂ» አላት፡፡ በማግሥቱ ግን ለሕልም ፈቺ ሔዶ ነገረው፡፡ ሕልም ፈቺውም «እግዚአብሔር በምሕረቱ አይቷችኋል፤ በሣህሉ መግቧችኋል» ብሎ ደጋግ ልጆች እንደሚወልዱ፤ ፯ኛይቱ በጨረቃ መመሰሏ ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ደግ ፍጥረት እንደሚወልዱ፤ የፀሐይ ነገር ግን እንደ ንጉሥ ያለ ይሆናል አልተገለጸልኝም ብሎ ነገረው፡፡ (ነገረ ማርያም)
በጥሪቃም ለሚስቱ ሔዶ የሕልሙን ፍቺ ነገራት፡፡ በዚያም ወር የመጀመሪያዋ ሴት ልጅ ተፀነሰች፡፡ በተወለደች በ፰ኛው ቀን ስሟን ሄኤሜን አሏት፤ ወላጆቿም በሥርዓት አሳደጓት፡፡ እርሷም ለአቅመ ሔዋን ስትደርስ ባል አግብታ ሴት ልጅ ወለደች፤ የሄኤሜን ልጅም ዴርዴን ትባል ነበር፡፡ ዴርዴንም እንዲሁ አድጋ ቶና የምትባል ሴት ልጅ ወለደች፡፡ ቶና ደግሞ ሲካርን ወለደች፤ሲካርም ሔርሜላን ወለደች፤ ሔርሜላም በሥርዓት አድጋ ባል ካገባች በኋላ ሐና የተባለች ልጅ ወለደች፤ ሐና ማለትም በሃይማኖትና በምግባር የጸናች፤ በንጽሕና በቅድስና የኖረች ቡርክት ክብርት ልዕልት ማለት ነው፡፡ የሐና ወላጆች ልጃቸውን በሥርዓት አሳደጓት፡፡ ለአካለ መጠን ስትደርስም ኢያቄም የተባለውን ጻድቅ ሰው አጋቧት፡፡ ሐና ግን ልጅ መውለድ አልቻለችም፡፡ ስለዚህም ኢያቄም እና ሐና ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ፤ ልጅም ከሰጣቸው ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ እንዲሆን ለመስጠት ስእለት ተሳሉ፡፡ ከዚህም በኋላ ሐምሌ ፴ ኢያቄም ለሐና ራእይ አየ፤ ነጭ ርግብ ፯ቱን ሰማያት ሰንጥቃ ወርዳ በራሷ ስታርፍ በቀኝ ጆሮዋ ገብታ በማኅፀኗ ስታድር አየ፤ሐናም ለኢያቄም ፀምር ሲያስታጥቁህ መቋሚያህ አብባ አፍርታ ፍጥረት ሁሉ ሲመገባት አየሁ ብላ» ነገረችው፡፡
ነሐሴ ፯ በዕለተ እሁድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተፀነሰች፡፡ በ፱ኛው ወር ግንቦት ፩ ቀን እመቤታችን ድንግል ማርያም ነቢያት የተናገሩላት ትንቢት ይፈጸም ዘንድ በአምስት ሺህ አራት መቶ ሰማንያ አምስት ዓመተ ዓለም ከሐና እና ከኢያቄም በፈቃደ እግዚአብሔር ተወለደች፡፡ በ፰ኛው ቀንም ስሟን ማርያም ብለው ሰየሟት፤ በዚህ ዓለም ካሉት ምግቦች ሁሉ ጣፋጭ «ማር» በመሆኑ፤ በገነት ካሉት ምግቦች ደግሞ «ያም»ን የሚያህል ጣፋጭ ባለመኖሩ ሁለቱን ቃል በማጣመር (አንድ በማድረግ) «ማርያም» አሏት፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአባትና እናቷ ቤት ሦስት ዓመት ድረስ ከተቀመጠች በኋላ ኢያቄምና ሐናም የተሳሉትን ስእለት አስታውሰው ለቤተ ክርስቲያን ሰጧት፤ የሕይወት መጠጥና የሰማይ ኅብስት እየተመገበች ፲፪ ዓመት በቤተ መቅደስ ኖረች፡፡ ፲፭ ዓመት ሲሞላት ግን አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና ከቤተ መቅደስ ትውጣልን በማለት ተነሱባት፡፡ ካህኑ ዘካርያስም ይህን ሰምቶ እመቤታችንን ጠየቃት «ኦ ወለተ እስራኤል እፎ ትፈቅዲ ትንበሪ፤ ልጄ እንደምን ሆነሽ ልትኖሪ ትወጂያለሽ?» አላት፡፡ እርሷም «ከእግዚአብሐር በታች ያለኸኝ አባት አንተ ነህ፤ በዚያውም ላይ እናት አባቴ አደራ ያሉህ አንተን ነው፤ ወደ እግዚአብሔር አመልክትልኝ» አለችው፡፡ ዘካርያስም ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ከነገደ ይሁዳ ሚስቶቻቸው የሞቱባቸውን ወንዶች በትራቸውን በመሰብሰብ ጸልዮበት እንዲያድርና ምልክትም እንደሚያሳየው ነገረው፡፡ በተሰበሰቡት በትሮች ሲጸልይ አድሮ በማግሥቱ በትሮቹን አውጥተው ሲያዩ የዮሴፍ በትር አብባና አፍርታ ተገኘች፡፡ ከበትሩ ጫፍ ላይ «ኦ ዮሴፍ ወልደ ዳዊት ዕቅባ ለማርያም ፍህርትከ፤ ዮሴፍ ሆይ እጮኛህ ማርያምን ጠብቃት፤» የሚል ጽሑፍም አገኙ፤ ርግብም መጥታ በራሱ ላይ አርፋበታለች፤ ስለዚህም ዮሴፍ እንዲጠብቃት ተወሰነ፤ ቤተ ዘመዷም በመሆኑ በኋላም እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም ወደ ግብፅ ወርዳ ስትሰደድ ዮሴፍም አብሮ ተሰዶ፤ መከራዋን ይቀበላል፤ልቦናዋንም ያረጋጋልና እግዚአብሔር በረቀቀ ጥበቡ ዮሴፍ እንዲጠብቃት አደረገ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ነገር ግን ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከሴትም ተወለደ፡፡›› ብሎ እንደመሰከረው እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን የያዘው ቀነ ቀጠሮ በደረሰ ጊዜ ድንቅ በሆነው ምሥጢረ ሥጋዌ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ሰማያትና ምድር የማይወሰኑትን ጌታ በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ወለደችልን፡፡ ሊቁ አባ ሕርያቆስ ‹‹ድንግል ሆይ የሕይወት ምግብን እና መጠጥን ስላስገነሽልን እናከብርሻለን፤ ከፍ ከፍ እናደርግሻለን›› ብሎ እንዳመሰገናት እኛም የድንግልን ክብረ ልዕልናዋን እንናገራለን፤ ከፈጣሪ በታች፤ ከፍጡራን ሁሉ በላይ መሆኗን እየመሰከርን እናመሰግናታለን፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም ‹‹እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል››፤ብላ በመንፈስ ቅዱስ አሰምታ እንደተናገረችው በሦስቱ ዓለማት የሚኖሩ ሰማያውያን መላእክት፤ በገነት የሚኖሩ ጻድቃን በምድር የሚኖሩ ሕያዋን ደቂቀ አዳም ያመሰግኗታል፡፡
ስደት
ጌታችን ከመወለዱ በፊት ከፅንሰቱ እስከ ዳግም ምጽአቱ ድረስ ስለሚሠራው ሥራ አስቀድሞ በነቢያቱ እያደረ ትንቢት አናግሯል፡፡ መልአኩም ለዮሴፍ ብላቴናውን ሄሮድስ ሊገድለው አንደሚሻ ሲነግረው የሚሸሽበትን ቦታ ሳይቀር ‹‹ተንሥእ ንሣእ ሕፃነ ወእሞ ወሑር ውስተ ብሔረ ግብፅ›› ተነስተህ እናቱንና ብላቴናውን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ በማለት ለስደቱ ግብፅን እንደመረጣት ነግሮታል (ማቴ.፪፥፲፫) ከደቂቅ ነቢያት አንዱ ሆሤዕም ጌታችን ወደ ግብፅ እንደሚሰደድ ‹‹እምግብፅ ጸዋዕክዎ ለወልድየ፤ ልጄን ወደ ግብፅ ጠራሁት›› ሲል ልዑለ ቃል ኢሳይያስ ደግሞ ‹‹ወይወርድ እግዚእነ ውስተ ምድረ ግብፅ እንዘ ይጼዐን ዲበ ደመና ቀሊል፤ጌታችን በፈጣን ደመና (በእመቤታችን ጀርባ) ተጭኖ ወደ ግብፅ ይወርዳል›› በማለት ተናግሯል፡፡ (ሆሴ. ፲፩፥፩ ኢሳ. ፲፱፥፩)
ግብፃውያንና ኢትዮጵያውያንም ለጌታችን ፍቅር ከምንም በላይ ይሳሱ ስለነበር በስደታቸው ጊዜ ተቀብለው በማሳረፍና አንዳንዶቹም ቤታቸውን በመልቀቅ አስተናግደዋቸዋል፡፡ (ድርሳነ ዑራኤል) ብዙዎቹ እርሱን ለማየትም በቅተዋል፡፡
ሦስት ዓመት ከስድስት ወር በኋላም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእናት አባቷ ቤት ሦስት ዓመት፤ በቤተ መቅደስ ዐሥራ ሁለት ዓመት፤ በዮሴፍ ቤት ዘጠኝ ወር፤ ከጌታ ጋራ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር፤ በቤተ ዮሐንስ ዐሥራ አምስት ዓመት በአጠቃላይ ስድሳ አራት ዓመት በዚህ ምድር ኖራለች፡፡
ዕረፍት
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር፡፡ ዓለም ከተፈጠረ በኋላም ቅዱሳን ነቢያት በተለያዩ ምሳሌዎች እየመሰሉ፣ ትንቢት እየተናገሩ፣ ክብረ ድንግልናዋን እንዲሁም የአምላክ እናት መሆኗን መስክረዋል፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በምድር ላይ በአይሁድ ክፋት ብዙ መከራና ኃዘን ካሳለፈች በኋላ በዘመነ ሉቃስ ጥር ሃያ አንድ ቀን በስድሳ ዐራት ዓመቷ ወደ ዘለዓለም ደስታ ትገባ ዘንድ ዐርፋለች፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ወዳጄ ሆይ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ ነይ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ፤ ዝናሙም አልፎ ሄደ፡፡ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፤ የዜማም ጊዜ ደረሰ፤ የቍርየውም ቃል በምድር ላይ ተሰማ›› በማለት ተናግሯል፡፡ (መኃ.፪፥፲-፲፬)
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሐዋርያት ሊቀብሩዋት በአጎበር አድርገው ወደ ጌቴሴማኒ ይዘው በመሄድ ላይ ሳሉ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና ‹‹ከዚህ አስቀድሞ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስን ያልተነሣውን ተነሣ፤ ያላረገውን ዐረገ እያሉ ሲያውኩንና ሲያስቸሩን ኖረዋል፤ አሁን ደግሞ እርሷ ተነሣች፤ ዐረገች፤ እያሉ ያውኩን አይደለምን? በእሳት አስከሬኗን እናቃጥለው›› ብለው ተሰብስበው ሄዱ፤ ከመካከላቸውም ታውፋንያ የሚብለው አይሁዲዊ ተራምዶ የእመቤታችንን አስከሬን አጎበሩን ጨበጠው፤ የታዘዘ መልአክ በሰይፍ ሁለት እጁን ሲሰይፈው እጁ ከአጎበሩ ላይ ተንጠልጥሎ ቀረ፡፡ ነገር ግን በሐዋርያት ጸሎት እጆቹን በተአምራት ተቀጥለው እንደቀድሞው ሆነውለታል፤ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ በደመና ነጥቆ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት፤ ሆኖም ሐዋርያት ዮሐንስን እመቤታችን ‹‹እንደ ምን ሆነች?›› ብለው ሲጠይቁት ‹‹በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር ናት‹‹ ብሏቸዋል፡፡ ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ ይህን ሁሉ ክብር አይቶ እኛስ አናይምን?›› ብለው በነሐሴ መጀመሪያ ጾም ያዙ፤ ሁለት ሱባዔ ጾመው በዐሥራ አራተኛው ቀን ሥጋዋን አምጥቶ ሰጥቷቸው ቀብረዋታል፡፡ (ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ)
ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድም ‹‹ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኵሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው፤ የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል›› በማለት አድንቋል፡፡ ከገቡ ከማይወጡበት ሰማያዊ ሀገር፣ ስደት፣ መከራ፣ ኃዘን ከሌለባት ሀገር፣ ቅዱሳን ሩጫቸውን ጨርሰው አክሊል ከሚቀዳጁበት ሥፍራም ከተወደደ ልጇ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ትኖራለች፡፡ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ለዛቲ ብእሲት ሠረቀ ላዕሌሃ ብዕለ ጸጋሁ ለአብ ወአግዓዛ እምእኩይ ውስተ ሠናይ እሞት ውስተ ሕይወት፤ በድንግል ማርያም ላይ የአብ የባለጸግነቱ ብዛት ተገለጠ፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከክፉ ዓለም ወደ በጎ ዓለም አሸጋግሯታልና፤›› ያለውም ይህንን ያመለክታል፡፡ ይህም በዓለ ዕረፍት ታላቅ በረከት የምናገኝበት በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፤ የእመቤታችን ረድኤት በረከት አይለየን፤ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር