ዳግም ሥራኝ!

በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል

መስከረም ፯፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

በሰጠኸኝ ሳላመሰግን ባጣሁት ያማረርኩህ

ዝቅ ብዬ ሳላይ በበላዬ ያስጨነቅኩህ

በሰው ላይ ጣቴን የምቀስር

ወንድሜን በግፍ የማሳስር

አስታራቂ መስዬ የአንዱን ለአንዱ የነገርኩ

በሰላም በፍቅር ፈንታ ጸብ ጥላቻን ያፋፋምኩ

ነጠላዬን አስረዝሜ ማለዳ ከማደሪያ…

ዐሥራ አንደኛው ሰዓት ላይ ቆሜ ዛሬም  ኃጢአት ያናወዘኝ

ሥራየ ተዘበራርቆ ስባዝን ውዬ ስባዝን ያደርኩኝ

አጎንብሼ የምማትር የኃጢአት ሸክም ያጎበጠኝ

ለኔ ስትል ሰው መሆንክን የረሳሁኝ ውለታ

ግርፋት ሞትህን እንኳን ያላሰብኩኝ ለአፍታ

ዳግም ምጽአትህን ቸል ያልኩህ

የአዳምን ጩኸት ጮኸህ ጎንህን በጦር ተወግተህ

የከፈልከውን ዋጋ ከልብ ያላሰብኩኝ

በስም ብቻ የምኖር በደልን የካብኩኝ

ልቤ ከዓለም ሆኖ አገልጋይህ መስዬ

ከጠላት ጋር ውዬ ከእርሱ ጋር ተዋውዬ

በኃጢአት ወድቄ

በቂም ተሰንቄ

ለሰው’ማ አለሁ ለወጪ ለገቢ በዓይን እታያለሁ

በሰገነት ቆሜ ለክብርህ እዘምራለሁ

ይህን ቀሚሴን አስረዝሜዋለሁ

ጠዋት እና ማታ እመላለሳለሁ

በጎ እንደሚሠራ ጎንበስ ቀና እላለሁ

ግና…

የጽድቅ አበባዬ ጠውልጎ የኃጢአት ችግኜ አፈራ

አዝመራው ለምልሞ በለሱም የጎመራ

ለዓለም ሳጎበድድ  ጊዜዬን የጨረስኩ

በኃጢአት ብል ተበልቼ ባዶ ሆኜ የቀረሁ

ክርስትናዬን በነጠላ የሸፈንኩ

የራሴ ምሶሶ  እያለ ጉድፍ ለማውጣት የሮጥኩ

እኩይ ግብሬ ጸጽቶኝ በንስሓ ያልታጠብኩ

በተሰጠኝ የማልረካ ምስጋና የተሳነኝ

የራሴ ወርቅ ተቀምጦ  የሰው ነሐስ የሚያምረኝ

ለሰዎች ያለሁ መስዬ ከእቅፍህ የወጣሁኝ

አካሌ ከመቅደስ ልቤ ከዓለም የሆነብኝ

ጠፋ ብዬ የምፈልግ ራሴን ፈላጊ የሚያሻኝ

የተሰጠኝ መና ሰልችቶኝ የግብጽን ሽንኩርት የናፈቅኩ

የሚጠቅመኝን ትቼ የማይጠቅመኝን የፈለግኩ

እንደ ዴማስ ተማርኬ ዓለም ያስቀረችኝ

በውበቷ ገመድ ዐሥራ ተሰሎቄ የሳበችኝ

በቤትህ ውስጥ የጠፋሁ …ልጅህን ዳግም ሥራኝ!