እስራት

መምህር ቢትወደድ ወርቁ
መስከረም ፰፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ሰዎች በልዩ ልዩ ምክንያቶች በወኅኒ ቤት ይታሰራሉ፡፡ አንዳንዶች ወንጀል ፈጽመው፣ ያልታረመ ንግግር ተናግረው፣ በማታለል ተግባር ተሰማርተው፣ ሴት አስነውረው፣ ቤት ሰርስረውና የመሳሰሉትን እኩይ ተግባራትን ፈጽመው ሊሆን ይችላል፡፡ የሰው ልጆችም በሲኦል ወኅኒ ቤት ተጥለን ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት ስንሠቃይ የነበረው አባታችን አዳም ትእዛዘ እግዚአብሔርን ጥሶ፣ አምላክነትን ሽቶ፣ አትብላ የተባለውን በመብላቱ ነበር፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን አስመልክቶ ሲናገር ‹‹በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩት ነፍሳት ሰበከላቸው›› ይላል፡፡ (፩ኛጴጥ.፫፥፲፱)

በእኩያት ግብር ጸንተህ ብትታሰር የክፉ ግብርህ ውጤት ነውና ላያስደንቅ ይችላል፤ አያስገርምም፡፡ ክፉ ሥራ ሠርተን፣ የማይገባውን ፈጽመን፣ በወንጀል ሥራ ተሰማርተን ስንታሠር አካላችን ብቻ ሳይሆን ኅለናችንም ጭምር ይታሰራል፡፡ ወንጀል ፈጽመው ወደ ወኅኒ የተጣሉ ሰዎችም ብዙ ጊዜያቸውን  በጸጸት፣ በቁጭትና ሥር በሰደደ ኀዘን የሚያሳልፉትም ለዚያ ነው፡፡ አካላዊ እስር የሚፈጸምበት ወኅኒ ቤት ሰዎች በልዩ ልዩ ምክንያት ነፃነታቸው ተገፎ፣ እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ፣ አካላቸውና ኅሊናቸው በቦታ ተወስኖ የሚቆዩበት ስፍራና ሁኔታ ነው፡፡ ወኅኒ ቤት ውስጥ ምቾት የለም፤ ደስታና እንደ ፈቀዱት መኖር የለም፡፡ መጎሳቆልና ድብታም ዋነኛ መገለጫው ነው፡፡ ወኅኒ ቤት ሰዎች በአካል በአንድ ቦታ ተወስነው የልባቸውን እንኳን መናገር የማይችሉበት ስፍራ ነው፡፡ ወኅኒ ቤት ስትጣል ዘወትር የምታየው ነገር ተመሳሳይና አታካች ነው፡፡ አሳሪዎችህ የመረጡልህን እንጂ አንተ የመረጥከውን አታይም፤ አትሰማም፤ አታነብምም፡፡

ጥናቶችና በልዩ ልዩ ጊዜያት የተሠሩ ዘጋቢ ሥራዎች እንደሚያመለክቱትም በወኅኒ ቤት ያሉ ሰዎች ለሚጠቁበት የደም ግፊት፣ የጨጓራ፣ የአእምሮ መታወክና የመሳሰሉት ሕመሞች መነሻም ይኸው ሥር የሰደደ ጭንቀትና ውጥረት ነው፡፡ ትዕግሥት በማጣትና ራስን ባለ መግዛት ምክንያት ተነሣሥተን የምንፈጽማቸው ወንጀሎችና ስሕተቶች ውለው አድረው የሚያስከፍሉን ዋጋ ቀላል አይደለም፡፡ ሌሎች ደግሞ ባልፈጸሙት ወንጀል ባልሠሩት ክፉ ሥራ ወደ ወኅኒ ተወርውረው ብዙ ሥቃይ ይቀበላሉ፡፡

ከዚህም ባሻገር በሰዎች አሻጥርና የተንኮል ሥራም በሐሰት ተመስክሮባቸው ወኅኒ የገቡ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም ግብር ጸንተው በመኖር ኃጢአትን ሠርተውና ወንጀል ፈጽመው መከራን መቀበል እንደማይገባቸውና በግፍ ባልፈጸሙት ነገር እስርንና ሌሎች መከራዎችን ቢቀበሉ ግን ለክብር እንደሚሆንላቸው ሲያስተምር ‹‹ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጉዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር›› ብሏል፡፡ (፩ኛጴጥ.፬፥፲፭-፲፯)

መጽሐፍ በግፍ ያለምንም ጥፋት የታሠሩ ሰዎች እንደነበሩ ያስተምረናል፡፡ ብእሴ እግዚአብሔር ቅዱስ ዮሴፍ የጲጥፋራን ሚስት ‹‹አስነውርሃል›› ተብሎ ባላደረገው ባላሰበውም ይልቁንም በተቃወመውምና ‹‹በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ›› በማለት ሴቲቱን ገሥፆ ሳለ በሐሰት መስክራ ወደ ወኅኒ እንዲወረወር አድርጋዋለች፡፡ (ዘፍ.፴፱፥፩-፲፭) በቅዱሳት መጻሕፍት ታሪካቸው የተጻፈልን ብዙዎቹ ቅዱሳን በግፍ ታስረዋል፤ በወኅኒ ሳሉም ተደብድበዋል፤ ተሠቃይተዋልም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ›› ብሎ መናገሩ ይህን ያስረዳናል፡፡ (ዕብ.፲፩፥፴፮)

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በአይሁድ እጅ በግፍ ተይዞ እንደታሠረ መጽሐፍ ያስተምረናል፡፡ ‹‹አስረውም ወሰዱት፤ ለገዢውም አሳልፈው ሰጡት›› ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ (ማቴ.፳፯፥፪) ቅዱሳን ሐዋርያትም እውነትን ስለመሰከሩ፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ስላስተማሩ፣ ግፍን ስለተቃወሙና ሕሙማንን ስለፈወሱ በወኅኒ ተጥለው ታስረዋል፡፡ (የሐዋ.፲፪፥፭፣፲፮፥፳፫)

በአባቶቻችን የገድላት መጻሕፍትም ውስጥ ቅዳሳት አባቶቻችንና ቅዱሳን እናቶቻችን በግፍ ታስረው ብዙ መከራዎችን እንደተቀበሉ ተጽፎልናል፡፡ በዓለም ታሪክም በሐሰት ተመስክሮባቸው ሌሎች ለፈጸሙት ስሕተትና ወንጀል ሰለባ ሆነው፣ በወኅኒ ተወርውረው በወኅኒ ሳሉ በግፍ የሞቱ፣ በረኃብ ተመተው አንጀታቸው ተጣብቆ ተጎሳቁለው ያለፉ፣ ብዙ ሊሠሩበት የሚችሉበትን ውሱን ዕድሜ በወኅኒ ያሳለፉ፣ በወኅኒ ሳሉ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ብዙዎች ናቸው፡፡ በተሳሳተ ክስ፣ በሐሰት ምስክርነት፣ በተጣመመ ፍርድ በወኅኒ ተወርውረው ዕድሜያቸውን ከጨረሱ በኋላም ንጽሕናቸው ተረጋግጦ ‹‹የታሠራችሁት በስሕተት ነው!›› ተብለው ነጻ የተደረጉም ብዙ ናቸው፡፡ አካል ሲታሰር ሌሎችን ሊጠቅምበት የሚችልበት የታሳሪ እውቀት፣ ጥበብና ጊዜም አብሮ ይታሠራል፡፡ የታሳሪ ሕፃናት ልጆች ይጎሳቆላሉ፤ ወላጆች ጧሪ ቀባሪ ያጣሉ በስተርጅናቸውም እያዘኑ ይኖራሉ፡፡ የዘመድ አዝማድ መንከራተትም በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ እውነተኛ ሰዎች ይታሰራሉ፤ እውነት ግን አትታሰርም፡፡ እውነት ጊዜዋን ጠብቃ ታሳሪዎችዋን ነጻ ስታወጣ ተጸጽተው ንስሓ ገብተው ካልተመለሱ ደግሙ አሳሪዎችዋን ታስራለች፡፡ በግፍ የሚያስሩና ለንጹሓን መታሰር በልዩ ልዩ መንገድ ምክንያት የምንሆን ሰዎች መታሰራችን ከፍ ሲልም ከእስር በሚበልጥ ነገር መቀጣታችን አይቀሬ ነው፡፡ እውነት ተናግረው፣ ስለ እውነት ቆመው፣ እስርና እንግልትን ፈርተው የተሰደዱ ሰዎች ቢኖሩም ወኅኒ ቤት ተጥለው የሚቀበሉትን ያክል መከራ ባይቀበሉም ከአገር ከወገን ከቤተ ሰብም ርቆ መኖርም ራሱን የቻለ መከራ ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ኃጢአት ሲሠራ ነፃነቱን እንደሚያጣ ይነግረናል፡፡ ክፉ ሥራ ሠርተን እግዚአብሔርን ስናሳዝን የክፉ ሥራችንና የሰይጣን እስረኞች እንሆናለን፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን አስመልክቶ ‹‹ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነውና›› በማለት ማስተማሩም ይህን እውነት ያስረዳናል፡፡ (፪ኛጴጥ.፪፥፲፱) ለሱስና ለስካር የምትሸነፍ ከሆንክ የሱስና የስካር ባሪያ ነህ፤ የወሬና የሐሜት ሱስ ካለብህም የእነርሱ ባሪያ ነህ፤ ጎጥህ የጎሳ፣ ማንነትህ ገንዘብህ የዚህ ዓለም፣ ክብርህና ዝናህ የከበቡህ ዘመድ አዝማዶችህና ባልንጀሮችህ ከእግዚአብሔር ከአምላክህ ከበለጡብህ የዘርህ የጎጥህ የክብርህና የዝናህ የዘመድ አዝማዶችህ እስረኛ ነህ፡፡ ንስሓ ያልገባህበት ማናቸውም ኃጢአትና በደል እስረኛ ያደርግሃል፡፡ በሕይወት ዘመንህ ለፈጸምከው ክፉ ሥራና ስሕተት እስረኛ እንዳትሆን ልትጠነቀቅ ይገባል፡፡

የአእምሮ መታወክ ዋነኛው መነሻም ሰዎች በፈጸሙት ስሕተት ምክንያት ከሰዎች በሚደርስባቸው መገለል፣ የስም መጥፋት ክብርና ጥቅም ማጣት የሚገቡበት ውጥረት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ለረጅም ጊዜ የሠሩትን ስሕተት እያሰላሰሉ መቆየትንና የዚያ እስረኛ መሆን የሥነ ልቡና ባለሙያዎቹ ‘አባዜ’ በማለት ይጠሩታል፡፡ ይህም አእምሮአዊ ሁኔታ ድብታን ይወልዳል፡፡ እያደገ ሲሄድም ፍጹም ወደሆነ የአእምሮ መናወጥ ያድጋል፡፡ ለዚህ መድኃኒቱ ምንድነው? ያልን እንደሆነ ንስሓ ነው፡፡ ንስሐ ስንገባ አእምሮአችን ይታደሳል፤ ነጻነትን እናገኛለን፤ ከኅሊና ወቀሳና ከሰሳም እንድናለን፡፡ ያለፈው ስሕተታችንን መማሪያ እንጂ መማረሪያ አናድርገው፡፡

የሰዎችን ክፉ ንግግር፣ ፍርድ፣ ማሽሟጠጥና ሐሜት ከመመልከት ይልቅ ከተመለስክ የማይበቀልህን ደግሞም በምሕረትና በርኅራኄ ዓይኑ የሚመለከትህን ፈጣሪህን ተመልከት፡፡ በማናቸውም የውድቀት ሁኔታ ውስጥ ብትሆን እግዚአብሔር ይፈልግሃልና እንደሚፈልግህ አውቀህ ፈልገው፡፡ የደረሰብህንና እየደረሰብህ ያለውን ጫና ትቋቋም ዘንድ ኃይል እንዲያስታጥቅህ በጽኑ ለምነው የሚያደርግልህን ተአምራት ትመለከታለህ፡፡ ነቢዩ “በተከበበ ከተማ የሚያስደንቅ ምሕረቱን የገለጠ እግዚአብሔር ይመስገን” ብሎ እንደተናገረ ማለት ነው፡፡ (መዝ .፴፩፥፳፩) አንተም በከበቡህ ሰዎችና ክፉ ጸጸቶች መካከል የሚያስደንቅ ምሕረቱን ታይ ዘንድ መንገድ ያለው አምላክህ ምሕረቱን ይገልጥልህ ዘንድ ተግተህ ለምነው፡፡

የአምላካችን እግዚአብሔር ቸርነትና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፤ አሜን!