ደብረ ምጥማቅ

 ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ግንቦት ፲፰፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች!  ለከበረው ጤንነታችሁ እንዴት አላችሁ? የበዓለ ሃምሣ ሳምንታት እንዴት ናቸው? ቤተ ክርስቲያን እየሄዳችሁ ታስቀድሳላችሁ? በሰንበታትስ ከወላጆቻችሁ ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያን ትሄዳላችሁ? ከሆነ በርቱ!

ልጆች! ይህ ወቅት ከምንም ጊዜ በላይ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጠጋት የሚያስፈልግበትና ስለ ሃይማኖታችንም አጥብቀን ማወቅ የሚገባን በመሆኑ ዘወትር ወደ ቤተ መቅደስ ሄደን በጸሎት ልንተጋ ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ፈተና ላይ በመሆኗ እኛም ከእርሷ መለየት የለብንም፤ እናንተ ሕፃናትም ይህንን በመረዳት ስለ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ስለ ሃይማኖት እንዲሁም ስለ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ማወቅ ስለሚያስፈልጋችሁ ተግታችሁ ተማሩ! መልካም!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ የምንነግራችሁ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደብረ ምጥማቅ በሚባል ገዳም ያደረገችውን ተአምር ነው፤ ልጆች ይገርማችኋል! ደብረ ምጥማቅ የተባለው ገዳም በግብጽ አገር የሚገኝ ሲሆን መነኮሳት በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት ፈጣሪን እያመሰገኑ እንዲሁም ለዓለም ሁሉ ሰላም እንዲሆን፣ ሰው በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፣ የሚያስፈልገውን ነገር ፈጣሪ ለሰው ልጆች እንዲሰጥ እየተማጸኑ የሚኖሩበት የነበረ ገዳም ነው፡፡

መነኮሳት አባቶች በትሕትናና በፍቅር መልካም ምግባር እየሠሩ በዚያ ገዳም ይኖሩ ነበሩ፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንም እጅግ አድርገው ያፈቅሯት ነበር፤ ምክንያቱም አምላክን የወለደች ናትና እንዲሁም እናት ትሆነን ዘንድ ልጇ ፈጣሪያችን ኢየሱሰ ክርስቶሰ በቅዱስ ዮሐንስ አማካኝነት ‹‹እናት ትሁናች›› ብሎ ሰጥቶናልና መነኮሳቱ በጸሎት ይማጸኗት ነበር፤ ልዩ ፍቅር ስለነበራቸው እነርሱም እርስ በእርስ ስለሚዋደዱና ስለሚከባበሩ የእግዚአብሔር ቸርነት ከእነርሱ ጋር ነበር፤ ጌታችን በትምህርቱ ‹‹…እኔ እንደ ወደድኳችሁ እርስ በእርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት…›› በማለት እንዳስተማረው እርስ በእርሳቸው ይዋደዱ ነበር፤ (ዮሐ.፲፭፥፲፪) ሌላውንም ሰው ይወዱ ነበር፤ እግዚአብሔር ያለበት ደግሞ ፍቅር አለ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆቸ! ታዲያ በዚህ ደብረ ምጥማቅ በሚባል ገዳም ባለች ቤተ ክርስቲያን አንድ ጊዜ ምን ሆነ መሰላችሁ? ከግንቦት ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱሳን መላእክት አጅበዋት በብርሃን መርከብ ሆና በቤተ ክርስቲያኑ ጉልላት ላይ ተገለጠችላቸው፤ ሱራፌል ማዕጠንታቸውን ይዘው እያጠኑ ቅዱሳን እየመጡ ለእርሷ ሲሰግዱላት ደብረ ምጥማቅ በሚባለው ገዳም ላሉት መነኮሳት እንዲሁም ለምእመናን ሁሉ ታየቻቸው፤ ይገርማችኋል ልጆች! ምእመናን፣ አባቶች እንዲሁም መነኮሳት እየሰገዱለላትና እያመሰገኗት እርሷም እየባረከቻቸው አምስት ቀን ያህል እያዩት ቆየች፤ ይህም ለመነኮሳትና ለምእመናን መገለጥና መባረክ በየዓመቱ ሆነ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እመቤታችን ለሚጠራት በበረከት ትገለጣለች፤ የልቡን ፍላጎት ታሟላለች፤ መነኮሳቱ መልካም ሕይወት ነበራቸው፤ ይፋቀሩም ነበር፤ ስለዚህ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በብርሃን መርከብ ላይ ሆና ተገልጣ ባረከቻቸው፤ መልካም ልጆች ሆነን፣ ትሕትናን ይዘን፣ ታዛዦች ሆነን፣ ሰዎችን የምንወድ፣ በጾም በጸሎት የበረታን ከሆንን እመቤታችን ዛሬም ትባርከናለች፤ በሕይወታችን ቅንና ታዛዥ እንሁን፤ የምንማረው ትምህርት እውቀት ይገለጥልናል፤ ማስተዋል ጥበብ ይሰጠናል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን በዓል በየዓመቱ ግንቦት ፳፩ ቀን ታከብረዋለች፤ በዚያ ዘመን ለነበሩ ክርስቲያኖች ተገልጣ እንደ ባረከቻቸው እኛንም እንድትባርከን ሊቃውንት፣ አበውና ምእመናን በማኅሌት፣ በሰዓታት ጸሎት፣ በሥርዓተ ቅዳሴው ፈጣሪያችን እመቤታችንን እያመሰገኑ ያድራሉ፤ ይውላሉ፤ ልጆች! ያን ጊዜ እመቤታችን ትገለጥበት በነበረው ቤተ ክርስቲያን የነበረው ጽላት (ታቦት) ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ የተባሉ ደገኛ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ወደ አገራችን ኢትዮጵያ መጥቶላቸው ቤተ ክርስቲያን ሠሩላት፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምእመናን ወደዚህ ሥፍራ እየተጓዙ ብዙ በረከትን ያገኛሉ፤ ችግር የገጠማቸው፣ የታመሙ፣ ነገሮች አልስተካከል ያላቸው ምእመናን ወደዚህች ገዳም ሄደው በጾም፣ በጸሎት ሁነው እመቤታችንን ሲማጸኗት ምላሽ ትሰጣቸዋለች፤ የልባቸው ደርሶ፣ ለልመናቸው ምላሽ አግኝተው፣ እንባቸው ታብሶ፣ ኀዘናቸው ተወግዶና ደስ ብሏቸው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! መልካምነት ለራስ ነው፤ መልካምና ቅን ልጆች ከሆንን በምድር ላይ ስንኖር ሕይወታችን ይባረካል፤ ደግሞ ከዚህ ዓለም ወደ ማያልፈው ዓለም ስንሄድ የክብር ሕይወት እናገኛለን፤ የክብር መንግሥቱን ያወርሰናል፤ ስለዚህ ልጆች! ሰዎችን የምናከብር፣ የምንወድ፣ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለአገራችን ሰላም እንዲሆን የምንጸልይ ታዛዦች እንሁን! ይህንን በጎ ምግባራችንን ሰዎች ሳይሆኑ እግዚአብሔር ይመለከታል፤ ከዚያም በክብር ከፍ ያደርገናል፤ መነኮሳቱ መልካም ሕይወት ስለ ነበራቸው እመቤታችን ተገለጸችላቸው፤ ባረከቻቸው፤ የእነርሱ መልካም ሕይወት ለሌላውም በረከት ሆነ፤ ልጆች! የእኛ መልካም መሆን ለቤተ ሰብ ከዚያም ለአገር ይተርፋል፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከቱን ታድለን፤ አሜን! ቸር ይግጠመን!

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ግንቦት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በኢትዮጵያ