‹‹ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና›› /ኦ.ዘፀ.፲፭፥፳፮/
ዲያቆን ዘአማኑኤል አንተነህ
‹‹እርሱም አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ በፊቱም የሚበጀውን ብታደርግ ትእዛዙንም ብታዳምጥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ በግብጻውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና፡፡››/ኦ.ዘፀ.፲፭፥፳፮/
የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ፳፻፳ ከተስፋ ይልቅ ዓለም አቀፋዊ ስጋትን ይዞ መጥቷል፡፡ ፎሬየንስ የተሰኘው ድኅረ ገጽ አዲሱን ዓመት ‹‹መርዶ ነጋሪ፣ ጥቁር ዓመት›› ብሎ ገልጾታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱ ነው፡፡ ኖቭል ኮሮና ቫይረስ ብዙ ዓለም አቀፋዊ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን አምጥቷል፡፡
ኮሮና ቫይረስ መነሻው ቻይና ‹‹ሁቤይ›› ግዛት ይሁን እንጅ አሁን ላይ በርካታ ሀገራትን የቫይረሱ ተገዥ አድርጓቸዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በቫይረሱ እየተጠቁ ያሉ ሰዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ተላላፊ በሽታዎች ሁሌም ቢሆን ለዓለም ከባድ ስጋት ናቸው፡፡ ከዚህ በፊትም በታሪክ በ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ‹‹ያርሲን›› የሚባል ባክቴሪያ አውሮፓ ላይ ተከስቶ ወደ ሁለት መቶ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተውበታል፡፡
ቫይረሱ የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቃ ሲሆን ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ነው፡፡ በሽታው ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ ቢሆንም ከአንድ ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት፣ በዕድሜ የገፉ አረጋውያን እና ረዥም ጊዜ ከበሽታ ጋር የሚኖሩ ሰዎች የበለጠ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ቫይረስ ወለድ በሽታዎች ፈዋሽ መድኃኒት የላቸውም ለምሳሌ፡- ኤች አይ ቪ ኤድስን እና ሌሎችንም መጥቀስ እንችላለን፡፡
ኮሮና ለምን ተከሰተ?
ኮሮና የተከሰተበት ምክንያት በውል አይታወቅም፡፡ እንደ መነሻ የሚሰነዘሩ ሐሳቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡
፩. ፈረንጆች የማይበሉ እንስሳትን ሁሉ ስለሚበሉ ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጮች ናቸው፡፡ ጊንጡን፣ አይጡን፣ ጉርጡን እንዲሁም የተለያዩ የማይበሉ አዕዋፋት እና እንስሳትን ስለሚበሉ ለብዙ በሽታዎች ተጋላጮች ናቸው፡፡ ምክንያቱም እንስሳትን የቫይረሱ ተጠቂዎች አድርጓቸው ይኖራልና፡፡ ሳይንሱ እንደሚለው በሽታው ከሆስቱ የሚመጣ ነውና፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም እንዲበሉ የተፈቀዱ እንዳይበሉ የተከለከሉም አሉ፡፡ ‹‹ድፍን ሰኮና ያለው እና የማያመሰኳውን አትብሉ›› እንዲል ነብየ እግዚአብሔር ሙሴ፡፡ በዚህም ምክንያት በእነሱ የእንስሳት በሽታዎች የተለመዱ ናቸው፡፡
፪. የፀረ ተዋሕስያን በመጠቀም የሚደረግ ጦርነት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ጦርነት በአደጉት ሀገራት የተለመደ ነው፡፡ በመከላከል ስልት አንዱ የሚጠቀሰው ማይክሮቢያል ዋር ነው፡፡ አንድ ሀገር አንድን ሀገር ሲበልጠው የሚጠነስሰው ሳይንሳዊ ውጊያ ነው፡፡ ኮሮናም ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ኮሮናም ከላብራቶሪ ያመለጠ ነው ለማለት እርግጠኛ ባይኮንም ሊሆን ግን ይችላል፡፡
፫. የእግዚአብሔር ቁጣ /መቅሠፍት/ መዓት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ከሌሎችም ምክንያቶች ባለፈ ሰፊውን ቦታ የሚይይዝ ነው፡፡ በተለይም ይህ እምነት ያላቸው ሀገራት እና ሕዝቦች የሚያነሱት ምክንያት ነው፡፡
ከእግዚአብሔር ስንርቅ፣ ስመ እግዚአብሔርን መጥራት ስናቆም እግዚአብሔር በመዓት ይገሥጸናል፡፡ ነቢዩ ሚክያስ ‹‹ባልሰሙም አሕዛብ ላይ በቁጣ እና በመዓት እበቀላለሁ››/ት.ሚክ.፭፥፲፭/ እንዲል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢያሱም ‹‹እኛ እስከ ዛሬ ድረስ ከእርሱ ያልነጻንበት የፌጎር ኃጢአት ጥቂት ነውን በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ መቅሰፍት ወረደ፡፡››/መ. ኢያሱ. ፳፪፥፲፯/ እንዲል፡፡ በተጨማሪም ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ በቁጣህ አትቅሰፈኝ በመዓትህም አትገስጸኝ››/መዝ.፮፥፩/ እንዲል፡፡
ኮሮና ቫይረስን እንዴት እንከላከለው?
በመንፈሳዊ በኩል
በእምነት ውስጥ የሚኖር ሕዝብ እና ሃይማኖት ያለው ሀገር ምንጊዜም ክፉ ነገር ሲከሰት ወደ ፈጣሪው ይጮሀል፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት አምልኮተ እግዚአብሔር ትልቅ መሳሪያ ነው፡፡ ስለዚህ ምን እናድርግ?
ጸሎት መጸለይ
ሁሉም በገባው እና ባለው ሃይማኖት ፈጣሪውን መለመን አለበት፡፡ ሁሉም ሰው በያዘው ሃይማኖት በግሉም በማኅበርም መጸለይ አለበት፡፡ እግዚአብሔርም ይሰማናል፡፡ ቅዱስ ሙሴ ‹‹እርሱም አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ በፊቱም የሚበጀውን ብታደርግ ትእዛዙንም ብታዳምጥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ በግብጻውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና፡፡››/ኦ.ዘፀ.፲፭፥፳፮/ እንዳለ፡፡ እኛም የእግዚአብሔርን ትእዛዙን ከተከተልን ችግሩ መከራው ይቀላል፡፡
ምሕላ መያዝ
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በእግዚአብሔር ለሚያምኑ ሀገራት ምሕላ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ መ.ዜና መዋዕል ካልዕ ፳፥፱ ‹‹ክፉ ነገር፣ የፍርድ ሰይፍ ወይም ቸነፈር ወይም ራብ ቢመጣብን ስምህ ባለበት በዚህ ቤት እና በፊትህ ቆመን በመከራችን ወደ አንተ እንጮሀለን አንተም ሰምተህ ታድነናለህ፡፡›› እንዲል ለሁሉም ነገር በሕብረት ሆኖ ወደ ፈጣሪ መጮህ ይገባናል፡፡
ማዕጠንት ማጠን
በሀገራችን አንድ አባባል አለ፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ኅዳር ከታጠነ በሽታ የለም›› ይባላል፡፡ ስለዚህ ጸሎተ ዕጣን ተደግሞ ማዕጠንት በየቀኑ መታጠን አለበት፡፡ ‹‹ማዳን የእግዚአብሔር ነው››/መዝ.፫፥፰/ እንዲል፤
የቅዱሳንን እምነት እና ጸበል መጠቀም
በልዩነት በበሽታ፣ በተለይም በወረረሽኝ እና በተላላፊ በሽታዎች ቃል ኪዳን ለተገባላቸው ቅዱሳን የእነሱን እምነት መቀባት፣ጸበላቸውን መጠጣት፣ በጸበላቸው መጠመቅ ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡
ለአብነትም የአቡነ ሀብተ ማርያምን የቅዱስ ቂርቆስን፣የአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስን፣ የሰማዕቱ አባ ገብረ እንድርያስን፣ የአቡነ ሐራን እና የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ገድል ማንበብ፣ በቤታችን ማስነበብ ወረርሽኙን ለመከላከል ትልቅ መሳሪያ ነው፡፡
ቅዱስ ዳዊት ‹‹ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና›› እንዲል በመንገድህ ማለቱ በሕይወትህ ሲል ነው፣ መላእክቱን ማለቱ ቅዱሳንን ነው እንዲሁም ቅዱሳን መላእክትን ነው፡፡ ስለዚህ የቅዱሳኑን እምነት መቀባት፣ ጸበል መጠጣት፣ መልክአ መድገም፣ ገድል ማንበብ በሽታውን ለመከላከል መድኃኒት ነው፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪክ ነገሥታት የሚፈልጉትን ጉዳይ ለማስፈጸም ለታቦታት ቤተ አስገብተው መቅደሳቸውን ይሠሩ ነበር፡፡ ለአብነትም አባቶቻችን በአድዋ የቅዱስ ጊዮርጊስን ጽላት ይዘው ኢጣሊያንን ድል ነሥተዋል፡፡ እቴጌ ምንትዋብ ቁስቋም ማርያምን አሠርተው ብዙ ችግሮችን አልፈዋል፡፡ ሌሎች ነገሥታትም እንዲሁ፡፡ ስለዚህ ቅዱሳኑን መማጸን ተገቢም ትክክልም አዋጭም ነው፡፡
በሥጋዊ በኩል
የጤና ባለሙያን ምክር መቀበል /ማክበር/መተግበር
የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሮና ከመከሠቱ በፊት የማንቂያ ደብዳቤ/አለርት ሌተር/ እና ለባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ከተከሰተም በኋላ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት እና ሌሎችም አካላት ብዙ ሥራዎችን እየሰሩ ነው፡፡
የቫይረሱ ምልክቶች፡-
ከፍተኛ ትኩሳት፣ ሳል፣ እንደ ንፍጥ ያለ ፈሳሽ ነገር፣የጉንፋን ምልክት፣ጉሮሮ መከርከር፣ የሆድ ሕመም፣ የመገጣጠሚያ ሕመሞች እና የመተንፈስ ችግር ምልክቶች ሲሆኑ ምልክቶቹ ለመታየት ከሁለት እስከ ዐሥራ አራት ቀናቶችን ሊወስድ ይችላል፡፡
በባለሙያ ቫይረሱን ለመከላከል የተሰጡ ምክሮች፡-
- እጅን በሳሞና መታጠብ
- የግል ንጽሕናን መጠበቅ
- ምግብን አብስሎ መመገብ
- ከእንስሳት ጋር ንክኪ አለማድረግ
- ጭምብል መጠቀም
- ከሰዎች ጋር አለመጨባበጥ
- ትልልቅ ስብሰባዎችን መሰረዝ
- መስኮት መክፈት ወ.ዘ.ተ ለአብነት የሚጠቀሱ መከላከያ ዘዴዎች ናቸው፡፡
ንጽሕና መጠበቅ በቤተ ክርስቲያንም የሚገኝ አስተምህሮ ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ ‹‹ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው ከፈሳሹ ነገር ሲነጻ ስለመንጻቱ ሰባት ቀን ይቆጥራል፣ ልብሱንም ያጥባል፣ ገላውንም በምንጭ ውኃ ይታጠባል፣ ንጹሕም ይሆናል /ኦ.ዘሌ.፲፭፥፲፫/ እንዲል ንጽሕናን መጠበቅ ሳይንሳዊ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖትም የተደገፈ ነው፡፡
በሽታ የመከላከል አቅማችንን የሚጨምሩ ምግቦችን መመገብ
በሽታው በባሕርይ የመቋቋም አቅማቸው የወረዱ ሰዎችን የሚያጠቃ በመሆኑ አመጋገባችንን በተወሰነ መልኩ ማስተካከል፡፡
በቅርቡ ሲነገር እንደነበረው ማር፣ ጤና አዳም፣ ዝንጅብል፣ ፌጦ፣ ሽንኩርት፣ ሎሚ የመሳሰሉት በሀገራችን የዘመናዊ ሕክምና አገልግሎት ባልነበረበት ጊዜ መድኃኒትን ተክተው ይሠሩ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ተፈጥራዊ ቅመማ ቅመማት የኮሮና ቫይረስን እንደሚፈውሱ ‹‹ከአባቶች ሰምተናል›› በማለት አንዳንድ ሰዎች የአባቶችን ስም ለማጠልሸት እና ፈዋሽነታቸው ባልተረጋገጠ ሁኔታ ማኅበረ ምእመናንን ሲያደናግሩ ቆይተዋል፡፡ እነዚህን ነገሮች ብንጠቀም ጉዳት ባይኖረውም ጉዳዩን በማስተዋል መመርመር ግን ይገባል፡፡
ቫይረሱ ከ፳፮-፳፯ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ሙቀት መቋቋም የማይችል በመሆኑ ይሞታል፡፡ ስለዚህ እንደ ሻይ፣ሾርባ እና የመሳሰሉትን ትኩስ ነገሮች መጠቀም የቫይረሱን የመተላለፍ አቅም ይገድበዋል፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል ነውና የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ጉዳት የለውም፡፡
አለመጨነቅ
ገና ሊይዘን ይችላል በሚል መጨነቅ የለብንም፡፡ ምክንያቱም ጭንቀት በራሱ በሽታ ነውና፡፡ ተጨንቀንም የምንጨምረው ነገር ብዙ አይኖርምና፡፡
ሕግን ማክበር
ሌላው ከሕግ አንጻር በወረርሽኝ ደረጃ የተፈረጄ በሽታን ወደ ሌሎች ሆን ብሎ ማስተላለፍ እስከ ሞት ሊያስቀጣ ይችላል፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጄል ሕግ አንቀጽ ፭፻፲፬ (፩) ‹‹ማንም ሰው አስቦ በሰው ላይ ተላላፊ በሽታ ያሰራጨ ወይም ያስተላለፈ እንደሆነ ከዐሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ ነገር ግን በወረርሽኝ ደረጃ የተፈረጄ በሽታን ያስተላለፈ እንደሆነ ከሃያ ዓመት ጽኑ እስራት እስከ ሞት ሊያስቀጣ ይችላል፡፡›› ስለዚህ ማንኛውም በበሽታው ራሱን የሚጠራጠር እና በሽታው አለብህ ተብሎ የተነገረው ሰው ራሱን በለይቶ ማቆያ ክፍል ማኖር ይኖርበታል፡፡
ካሳለፍናቸው ታሪኮች ትምህርት መውሰድ፣ ተሞክሮ መውሰድ
ኢትዮጵያ ብዙ ሥቃዮችን አሳልፋለች፡፡ አዲስ መከራም አዲስ ደስታም የለም ስለዚህ የድሮ አባቶቻችን ወረርሽኝ ሲመጣ እንዴት አድርገው አለፉት ብሎ መመርመር መጠየቅ ይገባል፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሠራት አለበት
ኮሮና የማይመለከተው የለም ሁሉም የድርሻውን ወስዶ መስራት ካልቻለ ልንቋቋመው አንችልም፡፡ ትልልቅ የዓለም ሀገራት ጠንካራ የጤና ፖሊሲ እና ቴክኖሎጅ ያላቸውም እንኳን በጣም እየተፈተኑ ነው፡፡
እየሳቁ አለቁ እንዲሉ በሕመሙ መቀለድ አያዋጣም፡፡ ለቫይረሱ ሚዲያዎች ቋሚ የአየር ሰዓት እና ዐምድ መመደብ አለባቸው፡፡ ነጻ የስልክ መስመሮችን በመክፈት እና በአግባቡ በማስተዋወቅም ኅብረተሰቡ ያልገቡትን ጉዳዮች እንዲጠይቅ እና ግንዛቤውን እንዲያሰፋ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አስፈላጊ ነው፡፡
በገጠሩም በከተማውም የሚዲያ አካላት እና ሌሎችም በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መረጃ መስጠት ይኖርብናል፡፡
የተያዙትን ሰዎች አለማግለል
አጋጣሚውን ተጠቅሞ የተያዙትን ማግለል ተገቢ አይደለም፡፡
አጋጣሚውን ተጠቅሞ ገቢያን አለመጨመር
አጋጣሚውን ተጠቅሞ የዋጋ ንረቱን መጨመርም ተገቢ አይደለም፡፡
ቅድመ መከላከሉ ላይ መስራት
ኮሮና የመተላለፍ አቅሙ የመተላለፍ አቅሙ ከፍተኛ ሲሆን ገዳይነቱ ግን ዝቅተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ቫይረሱን ለመከላከል የቅድመ መከላከል ሥራ መሥራት ይኖርብናል፡፡ መከላከሉም ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል፡፡
ቀደም ሲል በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የአየር መንገዱ ኢንዱስትሪ ቢሊዮን ዶላሮችን ማጣቱን ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር አስታውቋል፡፡ የሰዎች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ተገቷል፡፡ እግር ኳስ ሳይቀር ለቫይረሱ እጁን ሰጥቷል፡፡
ኮሮና የታንዛንያው ፕሬዘዳንት ከተቀናቃኞቻቸው ጋር የእግር ሠላምታ እንዲለዋወጡ አስገድዷቸዋል፡፡ ቅዱስ ሙሴ እንዳለን የእግዚአብሔርን ቃል ብንፈጽም ኖሮ ይህ ሁሉ መንጫጫት ባልነበር፡፡ ለእግዚአብሔር የሚበጀውን ብናደርግ ኖሮ ይህ ሁሉ መንጫጫት ባልነበር፡፡ ትእዛዙን ሰምተን ብንፈጽም ኖሮ ይህ ሁሉ መንጫጫት ባልነበር፡፡ ሥርዓቱን ሁሉ ብንጠብቅ ኖሮ ይህ ሁሉ መንጫጫት ባልነበር፡፡ አሁንም በንስሓ ሳሞና ታጥበን እግዚአብሔርን እንለምነው የመጣው ቁጣ ፣ በሽታ ይመለሳል እርሱ እግዚአብሔር ይመልሰዋል፡፡ ‹‹እርሱም አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ በፊቱም የሚበጀውን ብታደርግ ትእዛዙንም ብታዳምጥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ በግብጻውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና፡፡››/ኦ.ዘፀ.፲፭፥፳፮/ እንዳለን፡፡
ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር ነች፤ ስለዚህ ይህን የአምልኮተ እግዚአብሔር ሥርዓት ተጠቅሞ በሽታውን መከላከል አዋቂነት እንጅ ቂልነት አይደለም፤ ለሌሎች ሀገራትም ይህን መልእክት ማስተላለፍም ይገባል፡፡