‹‹ያለ ደግ ልጆች ያላስቀረን እግዚአብሔር ይመስገን!›› ብፁዕ አቡነ ሉቃስ
ሐምሌ ፳ ቀን፣ ፳፻፰ ዓ.ም
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ይህ ‹‹ያለ ደግ ልጆች ያላስቀረን እግዚአብሔር ይመስገን!›› የሚለው ኃይለ ቃል ከብፁዕ አቡነ ሉቃስ ቃለ ምዕዳን የተወሰደ ሲኾን፣ ይኸውም ማኅበረ ቅዱሳን በጀት በመመደብና ምእመናንን በማስተባበር ለገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ያደረገውን ድጋፍና ያመጣውን ውጤት ለቤተ ክርስቲያን አባቶችና ለበጎ አድራጊ ምእመናን ለማሳወቅ ሐምሌ ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በግዮን ሆቴል በንግሥት ሳባ አዳራሽ ባዘጋጀው ልዩ መርሐ ግብር የተናገሩት ነው፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ሑመራ፣ የሰሜን ሱዳንና የግብጽ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማሳተሚያ ድርጅት የበላይ ሓላፊ፤ የዐሥር ገዳማት አበ ምኔቶችና እመ ምኔቶች፤ የአብነት መምህራንና ደቀ መዛሙርት፤ የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚዎችና የልዩ ልዩ ክፍሎች አገልጋዮች፤ በጎ አድራጊ ምእመናንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሉቃስ በዕለቱ ቃለ ምዕዳን ሲሰጡ “ጸግወኒ እግዚኦ ውሉደ ቡሩካነ ወኄራነ እለ ይትኤዘዙ ለከ፤ አቤቱ ለአንተ የሚታዘዙ፣ የተባረኩ፣ ቸር የኾኑ ልጆችን ስጠኝ፤” የሚል ኃይለ ቃል ጠቅሰው “ያለ ልጆች ያላስቀረን፤ ታዛዥና ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ ልጆችን የሰጠን እግዚአብሔር አምላክ የተመሰገነ ይኹን!” በማለት በየገዳማቱ በጾም በጸሎት ተወስነው፣ በሥራ ተጠምደው የሚኖሩ አባቶች መነኮሳትንና መነኮሳይያትን፤ ለገዳማትና ለአብነት ት/ቤቶች መስፋፋት ልዩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ ላይ የሚገኙ ምእመናንንና ይህንን አገልግሎት የሚያስተባብረውን ማኅበረ ቅዱሳንን አመስግነዋል፡፡
መርሐ ግብሩ በብፁዕነታቸው ጸሎት ከተከፈተ በኋላ በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል መዘምራንና በመምህር ወልደ ገብርኤል ይታይ ወቅታዊ ይዘት ያላቸው ያሬዳውያን ዝማሬያት ቀርበዋል፡፡
ዲያቆን ብርሃኑ አድማስም “ንገሩ” በሚል ኃይለ ቃል የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮና ታሪክ፤ የቅዱሳት መካናትን ጠቀሜታና አስተዋጽኦ፤ እንደዚሁም ያሉባቸውን ችግሮች ለሌሎች በማስረዳት ቤተ ክርስቲያናችንን ከልዩ ልዩ ችግር ነጻ ማድረግና የገዳማትንና የአብነት ትምህርት ቤቶችን ህልውና ማስጠበቅ እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ‹ምርጥ ተሞክሮ› በሚል ርእስ ያሳተመው፤ ልዩ ልዩ ጉዳዮችን የሚዳስሰው የኤሌክትሮኒክስ ጋዜጣም በብፁዕ አቡነ ሉቃስ ቡራኬ ተመርቋል፡፡
ከዐሥሩ ገዳማት ከመጡ አበ ምኔቶችና እመ ምኔቶች መካከልም ከፊሎቹ ስለየገዳሞቻቸው ኹኔታና አገልግሎት እንደዚሁም ስለሚያከናውኗቸው ልማታዊ ሥራዎች የልምድ ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡
ማኅበሩ ምእመናንን በማስተባበር ካሠራቸው ተግባራት መካከልም በደብረ ሐይዳ አቡነ ቶማስ ገዳም የተገነባው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በውሃ እጥረት ምክንያት የተበተኑ መነኮሳትና የአብነት ተማሪዎች ወደ ገዳሙ እንዲመለሱና ቍጥራቸውም እንዲጨምር ማድረጉን የገዳሙ አባቶች መስክረዋል፡፡
ለደብረ ገሪዛን ካስዋ ጕንዳጕንዶ ማርያም ገዳም ገቢ ማስገኛ ይኾን ዘንድ በአዲግራት ከተማ የተገነባው ሕንፃም ሌላው የማኅበረ ቅዱሳንና የበጎ አድራጊ ምእመናን ተሳትፎ ውጤት ሲኾን፣ ይህም በመቅኑን እጥረትና በልዩ ልዩ ችግር የቀዘቀዘው ገዳም ተመልሶ እንዲሰፋ ማስቻሉንና የአብነት ትምህርት ለመስጠት መልካም አጋጣሚ ማስገኘቱን የገዳሙ አበ ምኔት ተናግረዋል፡፡
የሚዛን ደብረ ከዋክብት አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሴቶች ገዳም እመ ምኔትም ገዳሙ ከባንክ ፩.፰ (1.8) ሚሊዮን ብር ተበድሮ ባስገነባው ሕንፃ ከ፩ኛ – ፱ኛ (ከ1ኛ – 9ኛ) ክፍል ድረስ ዘመናዊ ትምህርት እያስተማረ እንደኾነና ሌሎችንም የልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ፤ ማኅበረ ቅዱሳንም የሕንፃውን ዲዛይን ከመሥራት ጀምሮ ድጋፍ እንዳደረገላቸው ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ያልተጠናቀቁ ሕንፃዎች መኖራቸውንና ከተበደሩት ገንዘብም አብዛኛው አለመመለሱን አስታውሰው ለዚህም የምእመናን ድጋፍ እንዳይለያቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአቃቂ ደብረ ገነት አቡነ ሳሙኤል ገዳምም በማኅበሩ ድጋፍ የልብስ ስፌት መኪናና ጣቃ ጨርቅ፤ አንድ ተሽከርካሪ፣ እንደዚሁም ላሞችና የቤት ክዳን ቆርቆሮ ርዳታ ማግኘቱን፤ የገዳሙ መነኮሳይያትም በዘማናዊ ልብስ ስፌትና በእንስሳት ርባታ በሚያገኙት ገቢ ወላጅ የሌላቸውንና ረዳት ያጡ ልጆችን በመከባከብና በማስተማር ላይ እንደሚገኙ እመ ምኔቷ አስረድተዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ በጎንደር አቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል የቅኔ ጉባኤ ቤት የቅኔ ደቀ መዝሙር የኾነው፤ ከዩኒቨርሲቲ በዲግሪ መርሐ ግብር ከተመረቀ በኋላ ማኅበሩ ባዘጋጀው የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ነጻ የትምህርት ዕድል በማግኘቱ ሥራውን ትቶ ወደ አብነት ትምህርት ቤት የገባው ዲያቆን እንዳልካቸው ንዋይና ከኢትዮጵያ የሁለት ዓመት ሕፃን እያለ ከወላጆቹ ጋር ወደ ካናዳ አገር የሔደው፤ የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ያዘጋጀውን የአብነት ትምህርት ቤት ሥርዓተ ትምህርት የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም በፌስ ቡክ ተመልክቶ በትምህርቱ በመማረኩ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባቱን ትቶ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ የአብነት ትምህርት መከታተል የጀመረው የቀድሞው ሔርሞን ተስፋዬ የአሁኑ ዘድንግል በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ቅኔ አበርክተዋል፡፡
ባለዲግሪው የቅኔ ተማሪ ዲያቆን እንዳልካቸው ስሜቱን ሲገልጽም “ከአሁን በፊት አነጋጋሪ የነበረው የእኔ ወደ አብነት ትምህርት ቤት መግባት ዜና በወንድሜ በሔርሞን ታሪክ ተሸፍኗል፤ ለወደፊትም ወደ አብነት ትምህርት ቤት የሚገቡና የሁለታችንንም ታሪክ የሚያስረሱ ሌሎች ወንድሞቻችንም እንደሚበዙ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲል አስተያየት ሰጥቷል፡፡
የአፍ መፍቻ ቋንቋው እንግሊዝኛ የኾነውና በጥረቱ የአማርኛም የግእዝም ቋንቋዎች ተናጋሪ መኾን የቻለው የቀድሞው ዘመናዊ ተማሪ የአሁኑ የቅኔ ደቀ መዝሙር ኢትዮ ካናዳዊው ዘድንግል ደግሞ ለአማርኛ አዲስ መኾኑን በሚመሰክሩ ቃላቱ “እግዚአብሔር ቢፈቅድልኝና ቢሳካልኝ ቅኔ ካስመሰከርሁ በኋላ አቋቋም ተምሬ በውጭው ዓለም በማኅሌት ለማገልገልና በካናዳና በአካባቢው የሚኖሩ ወጣቶችን የአብነት ትምህርት ለማስተማር ዐሳብ አለኝ” በማለት የወደፊት ርእዩን አስገንዝቧል፡፡
በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያም የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ዓለም ፀሐይ መሠረት ማኅበረ ቅዱሳን ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ካለባቸው ችግር አኳያ ከፍተኛ ትኵረት ሰጥቶ ምእመናንን በማስተባበር በሚገኘው ድጋፍና በተፈጥሮ ሀብቶች በመታገዝ ቅዱሳት መካናቱ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ልዩ ልዩ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው “በቤተ ክርስቲያናችን ከሚገኙ ብዙ ሺሕ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ቍጥር አንጻር ኹሉንም ተደራሽ ለማድረግ አልተቻለም፤ በአሁኑ ሰዓትም የዕለት ጕርስ እንኳን የማያገኙ አባቶችና እናቶች ያሉባቸው ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፡፡ ስለዚህም ለወደፊቱ ከማኅበሩና ከምእመናን ከዚህ የበለጠ አገልግሎት ይጠበቃል” ብለዋል፡፡
በመጨረሻም በአባታዊ ምክራቸውና በጸሎታቸው ከማኅበሩ ጎን የማይለዩትን ብፁዕ አቡነ ሉቃስንና ሌሎችንም የቤተ ክህነትና የየገዳማት አባቶችን፤ በጎ አድራጊ ምእመናንን፤ በየጊዜው ርዳታ የሚያደርገውን የአሜሪካ ማእከልን፤ እንደዚሁም ለመርሐ ግብሩ መሳካት ልዩ ልዩ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የማኅበረ ቅዱሳን ልዩ ልዩ ማእከል አባላትን፤ በዕለቱ የተገኙ የዐሥሩን ገዳማት አበ ምኔቶችንና እመ ምኔቶችችን ወ/ሮ ዓለምፀሐይ መሠረት ማኅበሩን ወክለው ምስጋና ካቀረቡ በኋላ በብፁዕ አቡነ ሉቃስ ጸሎተ ቡራኬ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ኾኗል፡፡
በተያያዘ ዜና ዋና ክፍሉ በደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት ለሚገኙት ለደብረ ገነት ቀቀማ ቅድስት ማርያም እና ደብረ ዓሣ አባ ዮሐኒ ገዳማት የምግብ ድጋፍ ማድረጉን የመቀሌ ማእከል ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቋል፡፡
በድጋፍ መርሐ ግብሩም የገዳማቱ መነኮሳት፣ የዋናው ማእከልና የመቀሌ ማእከል አባላት ተገኝተዋል፡፡
የመቀሌ ማእከል ዋና ጸሐፊ አቶ ሐጋዚ አብርሃ እንደ ገለጹት ሁለቱ ጥንታውያን ገዳማት ካለባቸው የምግብ ችግር አኳያ ቅድሚያ የተሰጣቸው ሲኾን፣ ለሁለቱ ገዳማትም በአጠቃላይ የሃያ ኩንታል ጤፍ እና ሥንዴ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡
ከዚህ በፊትም በዚሁ ሀገረ ስብከት በሕንጣሎ ውጅራት ወረዳ ለምትገኘው ቅድስት አርሴማ ገዳም ተመሳሳይ ድጋፍ መደረጉን አቶ ሐጋዚ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በአካባቢው በተከሠተው ድርቅ ምክንያት የገዳማቱ መነኮሳት በደረሰባቸው ረኃብ በዓለ ትንሣኤን ሳይቀር ጥሬ ቆርጥመው ማሳለፋቸውንና የዕለት ጕርስ ለማግኘት በመቸገራቸውም በዓታቸውን ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን የቀቀማ ቅድስት ማርያም ገዳም አበምኔት መምህር አባ ሠርፀ ድንግል እና የደብረ ዓሣ አባ ዮሐኒ ገዳም አበ ምኔት መምህር አባ ተክለ አብ አብርሀ ይናገራሉ፡፡
በዚህ ዓመት የተከበረውን የትንሣኤ በዓልን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በተዘጋጀው መርሐ ግብርም ይህ የገዳሙ ኹኔታ መዘገቡን የመቀሌ ማእከል አስታውሷል፡፡
ለወደፊቱም “ገዳማት ለቤተ ክርስቲያን ህልውና መሠረት ናቸው፤ ጳጳሳቱ፣ መነኮሳቱ፣ ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ምንጫቸው ገዳማት ናቸው፡፡ ከኹሉም በላይ ገዳማት ከእግዚአብሔር ምሕረትን የሚለምኑ፣ ዘወትር በጾም በጸሎት የሚተጉ አባቶች መኖሪያዎች ናቸውና ኹሉም ሕዝበ ክርስቲያን ገዳማትን ቢደግፍ መልካም ነው” ሲሉ የገዳሙ አባቶችና እናቶች ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ፡፡