የጎንደር መካነ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን
ነሐሴ 1 ቀን 2006 ዓ.ም.
እንዳለ ደምስስ
ክፍል ሦስት
የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርና ሰበካ ጉባኤ እንቅስቃሴ
በጎንደር በአራት ቦታዎች ላይ የትርጓሜ መጻሕፍት ጉባኤ ቤቶች ይገኛሉ፤ ትምህርትም በተጠናከረ ሁኔታ ይሰጥባቸዋል፡፡ ነገር ግን ለቤተ ክርስቲያን ባለውለታ የሆኑት የመምህር ኤስድሮስ ወንበር በልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ታጥፏል፡፡ ይህንን ገጽታ ለመቀየርና የመምህር ኤስድሮስን ወንበር ወደነበረበት ለመመለስ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርና ሰበካ ጉባኤው ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ጉባኤ ቤቶቹን ዳግም ወደነበሩበት ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ የነበረ ቢሆንም ለፍጻሜ ሳይበቃ ወደ ደቡብ ጎንደር ተቀይረው ሄዱ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ተግባራዊ ባይሆንም በቅርቡ አንድ ውጤት ላይ ለመድረስ ጠንክረው እንደሚሰሩ አስተዳደሩና ሰበካ ጉባኤው ይገልጻሉ፡፡ ወደፊት ሊሰሩ ከታቀዱ ሥራዎች መካከል አንዱ የጉባኤ ቤቱን ጥንት ወደነበረበት መመለስ ይገኝበታል፡፡
ከታቀዱት የልማትና የአገልግሎት ሥራዎች መካከል ቅድሚያ የሚያደርጉት ቤተ ክርስቲያኗ ሙሉ አገልግሎት መስጠት የምትችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት በመሆኑ፤ ካህናቱ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ በትምህርት ብቃታቸውን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶበት እንደሚሠራ ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም ብቃት ያላቸው መምህራንን በማዘጋጀት፤ ከማኅበረ ቅዱሳን ጎንደር ማእከል ጋር በመተባበር በወንጌል ትምህርት በቂ ልምድ እንዲኖራቸው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡
“በልደታ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጥላ ዘቅዝቆ መለመን አይቻልም፡፡ ምእመናን ሳይሳቀቁ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው በነፃነት ጸሎት አድርሰው፤ ቡራኬ ተቀብለው እንዲሄዱ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥረናል ለማለት እንችላለን፡፡ ምእመናንን በልመና ማሳቀቅ አይገባም፤ አስበውና ደስ ብሏቸው ነው መሥጠት የሚኖርባቸው” በማለት የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሰብሳቢ ዲያቆን ሙሉቀን ብርሃኑ ይገልጻሉ፡፡
በቤተ ክርስቲያኗ አገልገሎት አይቋረጥም፤ ሊቃውንቱም የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ጠብቀው ያገለግላሉ፡፡ ለአብነት ተማሪዎች ቤት ተሰጥቷቸው፤ የመብራትና ውኃ ተከፍሎላቸው በመማር ላይ ይገኛሉ፡፡ በእንተ ስማ ለማርያም በሚሰማሩበትም ወቅት ምእመናን ስለሚያውቋቸው ያላቸውን ሰጥተው ይሸኗቸዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኗ ጽ/ቤት በእያንዳንዱ አገልጋይ ካህን ስም ፋይል ከፍቶ የንስሐ ልጆቻቸውን ስም ዝርዝር እንዲያስመዘግቡ ተደርጓል፡፡ እያንዳንዳቸው የንስሐ ልጆቻቸውን በአግባቡ በመያዝና በመምከር፤ ቢያንስ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከንስሐ ልጆቻቸው ጋር እንዲገናኙ በማድረግ፤ በየቤታቸው እየተገኙ ጸሎት አድርስው፤ ጠበል ረጭተውና አስተምረው የመመለስ ግዴታ እንዳለባቸው በመረዳት ይህንኑ በተግባር ላይ እያዋሉት ይገኛሉ፡፡ አስተዳደሩም ይከታተላል፡፡ የንስሐ አባቶቻቸው የሚፈለግባቸውን ሓላፊነት ካልተወጡና የሥነ ምግባር ችግር እንዳለባቸው ካረጋገጡ ምእመናን ወደ ጽ/ቤት በመምጣት ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ አስተዳደሩም ችግሩን ለመፍታት ጥረት ከማድረግ አንስቶ አስተዳደራዊ እርምጃ ይወስዳል፡፡
ምእመናን ሓላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በማድረግ ረገድ ለካህናት ብቻ የተተወ ባለመሆኑ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር መምህራንን በመመደብ፤ ትምህርተ ወንጌል የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት አንድ ክርስቲያን በክርስትና ሕይወት ውስጥ እስካለ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡ ምእመናን ሓላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታ ነው፡፡ አሥራት በኩራት ከማውጣት አንስቶ ንስሐ በመግባት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን በመቀበል በሕይወታቸው ለሌሎች አርአያ የሚሆኑ ምእመናን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው በመጨመር እየፈሩ ነው፡፡
የልማት እቀዶች፡-
የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር የልማት ሥራዎችን በመሥራት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በ400 ሺህ ብር የዳቦ መጋገሪያ ማሽን አስገብቷል፤ ሦስት ቋት ያለው ወፍጮና አንድ ማበጠሪያ በመትከል አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ ዙሪያ ሰፊ ቦታ ስላለ ባለ አራት ፎቅ ሁለገብ ሕንፃ በመሥራትና በማከራየት ራሷን የምትችልበት ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያኗን በአዲስ መልክ በጥሩ ዲዛይን ለማነጽ በብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የመሠረት ድንጋይ ተጥሏል፡፡ ለታቦቱ ማረፊያ የሚሆን ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ ምእመናን ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉም ይጠበቃል፡፡ የጎንደር መምህራን ኮሌጅ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች አዳራሽ ለመገንባት ለቤተ ክርስቲያኗ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ተፈቅዶላቸው ግንባታውን በማጠናቀቅ አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡
የጠበሉ ቦታን በማስተካከል ምእመናን ሳይቸገሩ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ በማመቻቸት የግንባታ ሥራው ይከናወናል፡፡
የልደታ ለማርያም የጥምቀተ ባሕር ቦታ ለሙስሊሞች ተሰጥቶ ስለነበር ከፍተኛ ችግር ተከስቶ ቆይቷል፡፡ በተለይም በ2001 ዓ.ም. የተፈጠሩት ግጭቶች አስቸጋሪ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ የችግሩ አሳሳቢነት ቀጥሎም ጥምቀተ ባሕሩ ከሙስሊሞች ተወስዶ ለአንድ ጀርመናዊ ባለ ሀብት ተሰጠ፡፡ ነገር ግን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እና በከተማው ወጣቶችና ምእመናን ብርቱ ጥረት ሳይሳከላቸው ቀርቷል፡፡
ቦታው የቤተ ክርስቲያን ሃብት በመሆኑ የልማት ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ በማመን ፕሮፖዛል በማዘጋጀት ለአማራ ክልላዊ መንግሥት ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ቀርቦ ውሳኔ እንዲሰጥበት ወደ ጎንደር ከተማ አስተዳደር አስተላልፎት በመታየት ላይ ይገኛል፡፡
ቦታው 46 ሺህ ካሬ ሜትር የሚገመት ሲሆን፤ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርና ሰበካ ጉባኤው ይህን ሥፍራ ለጥምቀተ ባሕርና ለልማት ለማዋል ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በቦታውም የግእዝ ቋንቋ ትምህርት ቤት፤ ሁለገብ ሕንፃ፤ የአረንጓዴ መናፈሻ፤ የኪነ ጥበብ ማእከል፤ መዋኛ ገንዳ፤ ሁለገብ የመሰብሰቢያ አዳራሽና ሌሎችንም ያቀፈ እንዲሆን ተደርጎ ዲዛይኑን በማዘጋጀት ለከተማ አስተዳደሩ ገብቷል፡፡ የሚመለከተው አካል ያጸድቀዋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡