የጎንደር መካነ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን
ሐምሌ 16 ቀን 2006 ዓ.ም.
እንዳለ ደምስስ
ክፍል ሁለት
ጥምቀት
በጎንደር ጥምቀትን አስመልክቶ ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር የሚወርዱበትና የሚመለሱበት ሦስት ዓይነት ሥርዓት ይገኛሉ፡፡ እነዚህም እየተፈጸሙ እስከ ዛሬ ድረስ ደርሰዋል፡፡
በዐፄ ገብረ መስቀል የነበረው ሥርዓት ታቦታት ከመንበራቸው ይወጣሉ፤ ወደ ጥምቀተ ባሕር ወርደው ሕዝቡን ባርከው በእለቱ ተመልሰው ወደ መንበራቸው ይገባሉ፡፡ በንጉሥ ላሊበላ ዘመን ደግሞ ቀድሞ የነበረው ሥርዓት ተቀይሮ ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው ወደ ወንዝ በመውረድ አድረው በመጡበት መንገድ እንዲመለሱ ተደረገ፡፡ ሦስተኛው በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን የተጀመረ ነው፡፡ በዋዜማው ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር በመውረድ ያድራሉ፡፡ አድረው ወደ መንበራቸው ሲመለሱ ግን ወደ ጥምቀተ ባሕር በወረዱበት ሳይሆን በሌላ መንገድ አገሩንና ሕዝቡን እየባረኩ እንዲመለሱ ተደረገ፡፡
ሦስቱንም ሥርዓት ዛሬ በጎንደር እንመለከታለን፡፡ የመጀመሪያው እንደ ዐፄ ገብረ መስቀል ሥርዓት ከመንበሯ ወጥታ ሕዝቡን ባርካ በዕለቱ ወደ መንበሯ የምትመለሰው የጎንደር በዓታ ለማርያም ናት፡፡ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ቅዱስ ኡራኤል በ22 ወጥቶ በእለቱ ሕዝቡን ባርኮ ወደ መንበሩ በክብር ይገባል፡፡ እንደ ዐፄ ላሊበላ ታቦታት ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር በመውረድ አድረው በመጡበት መንገድ መመለስን 8ቱ ዐፄ ፋሲል ባሰራው ጥምቀተ ባሕር የሚወጡት ታቦታት ናቸው፡፡ እንደ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ሥርዓት ታቦታት ወደ ጥምቀተ ባሕር በወረዱበት ሳይሆን በሌላ መንገድ ወደ መንበሯ የምትመለሰው ታቦት በጎንደር ውስጥ ብቸኛዋ የልደታ ለማርያም ታቦት ናት፡፡
መምህር ኤስድሮስ፡-
በቤተ ክርስቲያኗ ከአንድ መቶ ሃምሳ በላይ የአቋቋምና የትርጓሜ መጻሕፍት መምህራን ነበሩባት፡፡ የአቋቋም መምህራንና ጉባኤው አሁንም ድረስ ሳይቋረጥ የቀጠለ ቢሆንም የትርጓሜ መጻሕፍት መምህራን ግን ድርቡሽ ቤተ ክርስቲያኗን ካወደመና ንዋያተ ቅድሳትን ዘርፎ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ ከሔደ በኋላ ወንበሩ እንደታጠፈ ነው፡፡ የመምህር ኤስድሮስ የትርጓሜ ወንበር ታጥፎ ወደ ሠለስቱ ምዕት ቤተ ክርስቲያን ተወስዷል፡፡
የጎንደር ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ዐራት ዓይና የነበሩት መምህር ኤስድሮስ የትርጓሜ መጻሕፍትን ወንበር ዘርግተው በማስተማር ታላላቅ ሊቃውንትን ያፈሩባት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለውለታ የሆነች ናት፡፡
መምህር ኤስድሮስ በልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን የትርጓሜ መጻሕፍትን ጉባኤ ተክለው ወንበር ዘርግተው በማስተማር የተለያዩ የቤተ ክርስቲያንን መጽሕፍት እየመረመሩ ለተማሪዎቻቸው በቂ እውቀት እያስጨበጡ ተመርቀው ይወጣሉ፡፡ ከደቀመዛሙርቱም መካከል የቻለ ወንበር ዘርግቶ በማስተማር፤ ሌሎቹ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማገልገላቸውን ይቀጥላሉ፡፡
በቤተ ክርስቲያናችን ሁለት ዓይነት የአተረጓጎም ሥልቶች ይገኛሉ፡፡ እነሱም የላይ ቤትና የታች ቤት ትርጓሜ በመባል ይታወቃሉ፡፡ የትርጓሜ መጻሕፍትን በምሥጢር ካበለጸጓቸው መምህራን አንዱ መምህር ኤስድሮስ ሲሆኑ፤ የታች ቤት ትርጓሜ መሥራችም ናቸው፡፡
መምህር ኤስድሮስ መጸሕፍትን በመመርመር የሚታወቁ በመሆናው አንድ ወቅት ወደ ጣና ገዳማት ሔደው ከ300 በላይ መጻሕፍትን ለማንበብ ችለዋል፡፡ መጻሕፍቱን በማንበባቸው ቀድሞ በነበራቸው እውቀት ላይ በመጨመር እስከዚያ ጊዜ ድረስ ለተማሪዎቻቸው ያስተማሩት ትምህርት በቂ እንዳልነበር ተረዱ፡፡ በዚህም ምክንያት ከዚህ ቀደም አስተምረዋቸው፤ ለወጡ ደቀ መዛሙርቶቻቸው መልእክት በመላክ “የጎደለን ምሥጢር አለ” በማለት እንዲሰበሰቡ አደረጉ፡፡
በርካቶቹ የመምህራቸውን ጥሪ ተቀብለው ቢመጡም፤ ጌታ ዮናስ የተባሉት ደቀመዝሙራቸውና ሌሎች ግን እርስዎ ልዩ ትርጓሜ ከመጨመርዎ በፊት አስተምረውናል በማለት በመምህር ኤስድሮስ ተሻሻለ የተባለውን አንድምታ ትርጓሜ ለመማር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ እንደ ምክንያትነት ያስቀመጡት “ኢተወለድነ እምዝሙት፤ እኛ ከዝሙት አልተወለድንም፡፡ ከመጀመሪያው ጉባኤ ተምረን ተመርቀን ወጥተናልና አንመለስም” በማለታቸው ነው፡፡
ጥሪያቸውን ተቀብለው ለመጡት ደቀመዛሙርቶቻቸው ከጣና ገዳማት ከመጻሕፍት ያገኙትን እውቀት ሳይቆጥቡ ያላስተማሩትን እየጨመሩ ምሥጢሩን አስፋፍተው፤ ያጠረውን እያስረዘሙ፤ የረዘመውን እያሳጠሩ አስተማሯቸው፡፡
የመምህር ኤስድሮስን ጥሪ ተቀብለው በመምጣት እንደገና አስፋፍተው ያስተማሩትን “የታች ቤት ትርጓሜ” ሲባል፤ ጥሪያቸውን ሳይቀበሉ የቀሩትና እነ ጌታ ዮናስ በቀጣነት ያስተማሩት ጥንታዊው ትርጓሜ ደግሞ “የላይ ቤት ትርጓሜ” ተብሎ ለሁለት ተከፈለ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በጎንደር ተስፋፍቶ የሚሰጠው የታች ቤት ትርጓሜ ሲሆን፤ በጎጃምና አካባቢው ደግሞ የላይ ቤት ትርጓሜ በስፋት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ /የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ.ም. ገጽ194፤ ዝክረ ሊቃውንት፤ በመልአከ ምክር ከፍያለው መራሒ፤ 2003 ዓ.ም./
አለቃ ገብረ ሃና፡-
ከልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ጋር ተያይዞ ስማቸው ከሚነሱ ሊቃውንት መካከል አለቃ ገብረ ሃና አንዱ ናቸው፡፡ በዓታ ለማርያም ወንበር ዘርግተው አቋቋም እያስተማሩ ወደ ልደታ ለማርያም እየመጡም ያገለግሉ ነበር፡፡ አለቃ ገብረ ሃና ለልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን አንድ ከበሮ ራሳቸው አሰርተው በስጦታ አስገብተው ስለነበር ወደ ቤተ ክርስቲያኗ በሚመጡበት ወቅት አገልግሎት ይሰጡበታል፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ በልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን የሚገኝ ሲሆን፤ “የአለቃ ገብረ ሃና ከበሮ” እየተባለም ይጠራል፡፡ ከበሮው በቅርስነት የተያዘና በክብር እንዲቀመጥ በመደረጉ ለዓመታዊ ክብረ በዓል ካልሆነ በቀር ለአገልግሎት አይወጣም፡፡
የድርቡሽ ጦር ጠባሳ፡-
የድርቡሽ ጦር በተለይም በጎንደር በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ያደረሰው ከፍተኛ ውድመት በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የራሱን ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡ አባቶች ታርደዋል፤ ተሰደዋል፤ ንዋያተ ቅድሳት ተዘርፈዋል፤ ተቃጥለዋል፡፡ ከፍተኛ ውድመት ከደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ የልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡
ቤተ ክርስቲያኗን ድርቡሽ ከማፍረሱ በፊት ምን ትመስል እንደነበር መገመት ይከብዳል፡፡ ነገር ግን የንጉሥ ኢያሱ ዜና መዋዕል እንደሚነግረን “ዐፄ ዮስጦስ ልደታ ለማርያም የምትባል ረጅም ፤ ከፍ ያለች ፤ ከከፍታዋ የተነሳ ከርቀት የምትታይ ቤተ ክርስቲያን ሠሩ” እያለ ይነግረናል፡፡
ከልደታ ለማርም ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጋር ስማቸው ከሚነሱ ነገሥታት መካከል ዐፄ ዮስጦስ፤ ንጉሥ ዐጽመ ጊዮርጊስ፤ ንጉስ ተክለ ሃይማኖትና ዐፄ በካፋ ይገኙበታል፡፡ ቤተ ክርስያኗን በተለያዩ ዘመናት በማሠራት ይታወቃሉ፡፡
የዐፄ ዮስጦስ የንግሥና ዘመን በአጭርነቱ ከሚጠቀሱት ውስጥ የሚደመር ሲሆን፤ ለአምስት ዓመታት በንግሥና በቆዩባቸው ዘመናት በርካታ ቤተ ክርስቲያንና አገርን የሚጠቅሙ ሥራዎች ለመሥራት ጥረዋል፡፡ ነገር ግን በዙሪያቸው የነበሩ ተቀናቃኞቻቸው ሊያጠፏቸው ሌት ተቀን ያደቡ ስለነበር አባ እንጦንስ ቤተ ክርስቲያን ሔደው አስቀድሰው እንደተመለሱ ከምግብ ጋር መርዝ ሰጥተዋቸው የካቲት 12 ቀን 1708 ዓ.ም. አርፈው በማግሥቱ የካቲት 13 ቀን ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡ መቃብራቸውም በልደታ ማርያም ቤተ ክርስቲያንና በቤተልሔሙ መካከል ከቤተ ክርስቲያኑ ተጠግቶ ይገኛል፡፡ የልደታ ቤተ ክርስቲያንን ቅጥርና ደጀ ሰላም በማሠራት ላይ እያሉ በመሞታቸውም ዐፄ በካፋ ቅጥሩን አሠርተው አጠናቀውታል፡፡
በድርቡሽ ወራራ የልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት ወደ ጣና ደሴቶች እንደተወሰዱ የሚነገር ሲሆን፤ የት እንዳሉ ግን ማወቅ አልተቻለም፡፡ ሳይወሰዱ የተረፉትም እንደ ብራና፤ ተአምረ ኢየሱስ፤ የደብሩን ታሪክ በተለይም የንጉሱን ታሪክ የሚናገር ስንክሳር የመሳሰሉት መጻሕፍት ዛሬም ድረስ በቤተ ክርስቲያኗ ይገኛሉ፡፡
ድርቡሽ በጎንደር ውስጥ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን አፍርሷል፤አቃጥሏል፤ ንዋየ ቅድሳትን ዘርፏል፡፡ ነገር ግን የድርቡሽ ጦር የልደታ ለማርያምና የቁስቋም አብያተ ክርስቲያናት ደጀ ሰላምን ማፍረስ ግን አልተቻለውም፡፡
አሁን ያለው ቤተ ክርስቲያን እንዴት ታነጸ?
የልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያንን የቀድሞ ገጽታ ከፍርስራሹና ሙሉ ለሙሉ ካልወደቁት ቆመ ብእሲ በመነሳት መገመት አይቻልም፡፡ ድርቡሽ ቤተ ክርስቲያኗን ሲያወድም ቅጥሩን ግን ማፍረስ ሳይችል ቀርቶ እስከ ዛሬ ድረስ ከነደጀ ሰላሙ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ያለው ግድግዳ የጥንቱ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗን ድርቡሽ ካፈረሰ በኋላ መቃረቢያ ተሰርቶላት ለረጅም ዘመናት በዚያ ሲቀደስ ነበር፡፡ ይህ አሁን አገልግሎት እየሰጠ ያለው ቤተ ክርስቲያን በ1970ዎቹ ውስጥ የታነጸ ነው፡፡
በወቅቱ ቤተ ክርስቲያኗን ያሠሩት በዓታ ለማርያም ሲያገለግሉ የነበሩ ቄስ አቡሐይ የሚባሉ አባት ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ ገጽታ እየፈረሰ መሆኑን በመረዳታቸው ምእመናንን ሰብስበው ላሰራው በማለት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ በወቅቱ የነበሩት የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርና ምእመናን ከለከሏቸው፡፤ እሳቸው ግን ተሰፋ ባለመቁረጥ አስተዳደሩንም ሆነ ምእመናንን ለማሳመን ባደረጉት ተከታታይ ጥረት ተፈቅዶላቸው አሳንጸዋል፡፡ በዚህ ወቅት በርካታ ፈተና ገጥሟቸዋል፤ ብዙም ደክመውበታል፡፡ የዓፄ ዮስጦስና የመምህር ኤስድሮስ ታላቅ ሥፍራ ፈርሶ መቅረት የለበትም በሚል በቁጭት ተነሣስተው ለፍጻሜ ለማብቃት ችለዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑን ማሠራት ብቻ ሳይሆን ለቤተ መቅደሱ ልዩ ድምቀት የሆኑትን ቅዱሳት ሥዕላትን በማሣል አስረክበዋል፡፡