የተቀጸል ጽጌ በዓል ተከበረ
መስከረም 11 ቀን 2005 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የሚከበረው የተቀጸል ጽጌ በዓል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መስከረም 10 ቀን 2005 ዓ.ም. በድምቀት ተከበረ፡፡
ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ አረጋውያን አርበኞች፤ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አባላትና ምእመናን በተገኙበት የተከበረው ይኸው በዓል ከቅዳሴ በኋላ በጸሎተ ወንጌል የተጀመረ ሲሆን የዕለቱ ተረኛ በሆነው በርዕሰ አድባራት ወገዳማት አዲስ ዓለም ደብረ ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያሬዳዊ ዜማ ቀርቧል፡፡ በተጨማሪም የአጫብር ወቆሜ ወረብ፤አንዲሁም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት መዘምራን ያሬዳዊ ዜማ ያቀረቡ ሲሆን በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
በመጨረሻም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል በሰጡት ቃለ ምዕዳን ‹‹ያሳለፍነው ወርኀ ነሐሴ የሰው ልቦና በሃዘን የተሰበረበት ጊዜ ነበር፡፡ መስከረም ሲጠባ በዚህ በዐውደ ምሕረት ተሰብስበን ታላቁን የመስቀል በዓል ተቀጸል ጽጌን እያከበርን እንገኛለን፡፡ ይህ በዓል የሚታወቀው በቤተ መንግሥት ነበር፡፡ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ የራሱ ጊዜ ሰላለው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በቤተ መንግሥት አደባባይ ይከበር የነበረው በዓል በዐውደ ምሕረት እንዲከበር አድርገውታል፡፡ አውደ ምሕረት የእግዚአብሔር ቃል የሚነገርበት ነውና፡፡›› በማለት የበዓሉን አከባበር ገልጸውታል፡፡
ወቅቱንም ለማመልከትና የደስታ ዘመን እንዲሆን በመመኘት ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ጀምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አበባ ለምእመናን በማበርከት መርሐ ግብሩ በጸሎት ተጠናቋል፡፡
ተቀጸል ጽጌ ማለት የአበባ በዓል ማለት ነው፡፡ ክረምቱ፤ ድጡ፤ ማጡ፤ ችግሩና ጨለማው ተወግዶ ምድር በልምላሜ የምታሸበርቅበት፤ በአበባ የምትደምቅበት ወቅት በመሆኑ፡፡ አንድም የዐፄ መስቀል በመባል ይታወቃል፡፡ ጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትና ቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ በዐፄ ዳዊትና በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ አማካይነት የገባበት ቀን በመሆኑ፡፡ ይህ ግማደ መስቀል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለማሳረፍ ቢሞከርም ከሦስት ዓመታት ጉዞ በኋላ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል” ተብሎ በታዘዘው መሠረት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ በግሸን ደብረ ከርቤ ለማኖር ችሏል፡፡
የተቀጸል ጽጌ በዓል የተጀመረው በ6ኛው ምዕተ ዓመት በዐፄ ገብረ መስቀል አማካይነት ሲሆን በዓሉ የሚከበረው የክረምቱ ማብቃት የሚያበስሩ አበቦች በሚፈኩበት ወር በመስከረም 25 ቀን ለንጉሡ የአበባ ጉንጉን /አክሊል/ በማበርከት ነበር፡፡ መስከረም 10 ቀን እንዲከበር የተወሰነው በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን ወደ ኢትዮጵያ ካመጡበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ነገስታቱ ልብሰ መንግስታቸውን በመልበስ፤ ካህናቱ ጥንግ ድርብ ለብሰው ዝማሬ በማቅረብ፤ ምዕመናን ፀአዳ ለብሰውና አሸብርቀው በዓሉ ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ እስከ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ማብቂያ ድረስ ሲከበር ቆይቷል፡፡ ደርግ ስልጣነ መንግሥቱን ሲቆናጠጥ ከሥልጣን እሰከተወገደበት እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ በዓሉ እንዲቋረጥ አድርጎታል፡፡ በ1984 ዓ.ም. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መንበረ ፓትርያርክ ሆነው እንደተሾሙ ቀድሞ የነበረውን ሥርዓት በመመለስ በየዓመቱ መስከረም 10 ቀን በመከበር ላይ ይገኛል፡፡