የተስፋው ቃል
በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል
ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
በአንዲት ፍሬ ቅጠል ሕይወትን አጥቼ
ርስቴን ተነጠኩ የሞት ሞትን ሙቼ
በግዞት ተነዳሁ በድቅድቅ ጨለማ
ወደ ፍዳ መንደር ወደ ሞት ከተማ
የተስፋውንም ቃል በልቤ ቋጥሬ
ለዲያቢሎስ ግብር ሆንኩት ጋሻ አጃግሬ
የባርነት ቀንበር ፍላፃው በርትቶ
በበርባኖስ መሃል ብርሃኔ ጠፍቶ
የመከራው ዘመን በእኔ ላይ አድርቶ
ዙሪያዬን ተብትቦኝ ሆነብኝ ድሪቶ
እሾህ አሜከላው ነግሦብኝ ሠልጥኖ
የጽድቅ ሥራዬም የመርገም ጨርቅ ሆኖ
ነፍሴ ብትቃጠል ሥጋዬም ቢጠፋኝ ከመሬት ተቀብሮ
፭፼፭፻ ዘመን ድምጼን ከፍ አድርጌ አሰማሁ እሮሮ
ትንቢቱ ተነግሮ ግዜው ተፈጽሞ
ያ . . . የተስፋው ቃል ነጋሪት ጐስሞ
የምሥራች ዜና ድኅነትን አብሥሮ
ሕይወትን ሊሰጠኝ ሞትን በሞት ሽሮ
በድንግል ማኅፀን ሥጋን ተዋሕዶ
ከሰው ልጆች አንሶ ራሱን አዋርዶ
መንበረ ጸባኦት ማደሪያውን ትቶ
ተገኘ ቤተ ልሔም ከበረት ተኝቶ