የቃል ኪዳኑ ታቦት
ኅዳር፤፳፻፲፫ ዓ.ም
ነቢዩ ሙሴ ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ጸልዮና ጹሞ ዐሥርቱ ቃላት የተጻፈበትን ጽላት ከእግዚአብሔር ከተሰጠው በኋላ የቃል ኪዳኑን ታቦት ‹ታቦተ ጽዮንን› እንደሠራት መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል፡፡ ታቦተ ጽዮን ከማይነቅዝ እንጨት የተሠራችበት ምክንያት የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ንጽሕና ለማመልከት ነው፡፡ በውስጥም በውጪም በጥሩ ወርቅ የተለበጠች መሆኗ ደግሞ የእመቤታችን ድንግል ማርያም ቅድስናዋንና በሁለት ወገን ድንግል የመሆኗ ምሳሌ ነው፡፡
በኦሪት ዘፀአት ላይ እንደተጻፈውም እግዚአብሔር አምላክ ነቢዩ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ታቦተ ጽዮን ርዝመቷ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቷ አንድ ክንድ ተኩል እንዲሆን ተደርጋ ተሠርታለች፤ ይህም ለጽላቱ መቀመጫ በስፋትም ሆነ በቁመት እንዲመች ተደርጎ የተቀረጸ ነው፡፡ ‹‹ከጥሩ ወርቅም የሥርየት መክደኛውን በቃል ኪዳን ታቦቷ ላይ በርዝመቷና በወርደዋ ልክ ሠራ›› እንዲል፤ በውስጥም በውጪም በጥሩ ወርቅ ተለብጦ በዙሪያዋም የወርቅ አክሊል አለ፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ዙፋን ተምሳሌት ነው፡፡ ‹‹ካህናት ታቦተ ጽዮንን ለመሸከም እንዲረዳቸውም በአራቱም መዓዘናት በወርቅ የተሠሩ ቀለበቶችንና በእነርሱም ውስጥ የሚገቡ ሁለት መሎጊያዎችን አሏት፡፡ የሥርየት መክደኛውን እንዲጋርዱት አድርጎም ጥሩ ከሆነ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ኪሩቤልን ሥሎ በሥርየት መክደኛው ግራና ቀኝ አስቀመጣቸው፡፡ እነዚህ በጥሩ ወርቅ የተሠሩት ሁለቱ ኪሩቤል ፊታቸው ወደ ሥርየት መክደኛው ሆኖ እርስ በእርሳቸው እንዲተያዩ ተደርገው የተሠሩ ናቸው፡፡ በዚህ በሥርየት መክደኛው በሁለቱ ኪሩቤል መካከል እግዚአብሔር ለሙሴ እየተገለጠ ያነጋግረው ነበር፤ ለሕዝቡም በደመና ዐምድ ይታያቸው ነበር፡፡ (ዘፀ.፳፬፥፲-፳፪)
ታቦተ ጽዮን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት፤ የመለኮት ማደሪያ ለመሆን በቅታለችናም ትመሰገናለች፡፡ ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ጽዮን ከተማ ባስመጣበት ወቅት በታቦቷ ፊት በሙሉ ኃይሉ በደስታ እየዘለለ ለእግዚአብሔር በዝማሬ ምስጋና አቅርቧል፡፡ ‹‹ለንጉሥ ዳዊትም “እግዚአብሔር የአቢዳራ ቤት የነበረውን ሁሉ ስለ እግዚአብሔር ታቦት ባረከ” ብለው ነገሩት፡፡ ዳዊትም ሄዶ የእግዚአብሔርን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በደስታ አመጣት፡፡ ከእርሱም ጋር የእግዚአብሔርን ታቦት የተሸከሙ ሰባት መሰንቆ የሚመቱ መዘምራን ነበሩ፡፡ በሬዎችንና በጎችን ይሠዉ ነበር፡፡ ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት በገና ይደረድር ነበር›› እንዲል፤ ነቢዩ ዳዊት በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት የተቀኘው ለሰው ልጆች ሆሉ የመዳናችን ምክንያት የሆነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሲያመስገን ነው፡፡ (፪ሳሙ.፮፥፲፪-፲፬)
ነቢዩም አስቀድሞ በመንፈስ በትንቢት እግዚአብሔር አምላክ ጊዜ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማደሪያ ትሆነው ዘንድ እንደመረጣት ከእርሷም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነሥቶ እንደሚወለድ ያውቃልና በዝማሬ አመስግኗል፡፡ ‹‹ዳዊትና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ በዜማ መሣሪያዎች በበገና በመሰንቆ፥ በከበሮና በነጋሪት፥ በጸናጽልና በዕንዚራ በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ያመሰግኑ ነበር›› እንዲል፡፡ (፪ሳሙ.፮፥፭)
በሐዲስ ኪዳንም የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተመስግናለች፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በእናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ማኅጸን ሳለ የእመቤታችን የሰላምታ ድምጽ በመስማቱ እንደ ነቢዩ ዳዊት በደስታ ዘሏል (ሰግዷል)፡፡ (ሉቃ.፩፥፵፬)
ታቦተ ጽዮን በዘመናት ያደረገቸው ተአምር ብዙ ነው፡፡ እስራኤል የዮርዳኖስን ባሕር ለመሻገር በተቸገሩ ጊዜ ነቢዩ ኢያሱ እግዚአብሔር አምላክ በነገረው መሠረት ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት ይዘው በሕዝቡ ፊት ወደዮርዳኖስ እንዲሄዱ ነገራቸው፤ እነርሱም እንደታዘዙት አደረጉ፤ ታቦቱን የተሸከሙት የካህናቱ እግሮች በውኃው ዳር ሲጠልቁ ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ፤ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ጸንተው ቆመው ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ እስራኤል ሁሉ በደረቅ መሬት ተሻገሩ፡፡ (ኢያ. ፫፥፩-፲፯)
እስራኤላውያን በመካከላቸው የቃል ኪዳኑ ታቦት በያዙ ቁጥር በጦርነታቸው ሁል ጊዜ ያሸንፉ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ልዑል እግዚአብሔር ሕዝበ እስራኤል ስለበደሉት እንዲሁም የኤሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በደላቸውና ክፋታቸው ስለበዛ ታቦተ ጽዮን ተማርካ ወደ ፍልስጥኤም ሄደች፡፡ በዚያም አሕዛብ በቤተ ጣዖቶቻቸው ባስቀመጡት ጊዜ ዳጎን የተባለውን የአሕዛብን ጣዖት ቀጥቅጣ አጥፍታዋለች፡፡ በዚያ በአሕዛብ ምድርም ልዩ ልዩ ተአምራትን እያደረገች ፍልስጥኤማውያንን ስለአስጨነቀቻቸው የፍልስጥኤማውያን አለቆች የቃልኪዳኑን ታቦት ልዩ ልዩ ገጸ በረከቶችን አስይዘው ወደመጣችበት በሠረገላ አድርገው በክብር ሸኝተዋታል፡፡ በዚህም ለእስራኤል ትልቅ ደስታ አጎናጽፋቸዋለች፡፡ (፩ኛ.ሳሙ. ፭፥፩-፲፭)
ሀገራችን ኢትዮጵያም የተባረከች ሀገር ናትና በንግሥተ ሳባ አማካኝነት ለታቦተ ጽዮን መቀመጫ እንድትሆን የእግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኗል፡፡ ይህም እንዲህ ነበር፤ ንግሥተ ሳባ የንጉሥ ሰሎሞንን ጥበብ ለማድነቅ ምድረ እስራኤል ድረስ ተጓዘች፤ እርሱንም በእንቈቅልሽ ፈተነችው፤ እርሱም በጥበቡ ሁሉን መለሰላት፤ ለስድስት ወራትም በእስራኤል ተቀመጠች፡፡ በዚህም ጊዜ ውስጥ ከጠቢቡ ሰሎሞን ቀዳማዊ ምኒልክን ፀነሰች።
ንግሥተ ሳባ ከእስራኤል ቆይታዋ ስትመለስ የፀነሰችው ልጅ ተወልዶ አባቱን ለመጠየቅ የመጣ ልጁን መለየት ያስችለው ዘንድ ሰሎሞን የጣት ቀለበት ሰጣት። እርሷም ያንን ይዛ በመመለስ ላይ እንዳለች ባህረ ኤርትራን ተሻግራ ከሀገሯ ድንበር ከሐማሴን አውራጃ ማይበላ የተባለ ቦታ ላይ ስትደርስ ቀዳማዊ ምኒልክን ወለደችው። በመናገሻ ከተማዋ አክሱምም ወስዳ በሥርዓት አሳደገችው፤ ፳፪ ዓመት ሲሞላው ግን የአባቱን ማንነት አጥብቆ ይጠይቃት ስለነበር ብዙ ሹማምንትና ወታደሮችን አስከትላ እርሷን የወሰዳትን ነጋድራስ ታምሪንን አደራ ብላ ወደ ኢየሩሳሌም ላከችው። ታምሪንም በጋዛ በኩል አድርጎ ኢየሩሳሌም ወሰደው፡፡ መልኩም አባቱን ይመስል ስለነበረ ብዙ የንጉሥ ሰሎሞን ሠራዊቶች እና ሕዝቡ ንጉሣቸው ሰሎሞን የመጣ መስሏቸው ይሰግዱለት ነበር፡፡ ንጉሡ ሰሎሞን ስለዚህ ነገር ሲሰማ ወጥቶ በሚመለከትበት ጊዜ የእርሱ ልጅ እንደሆነ በመልኩ መመሳሰል ብቻ ዐወቀ፤ በፍቅርም ተቀብሎ አቅፎ ሳመው፤ ከእርሱ ጋርም አስቀመጠው፡፡
ከዚህም በኋላ ጠቢቡ ሰሎሞን ባዘዘው መሠረት ሊቀ ካህኑ ሳዶቅ የእስራኤልን ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖትና ሥርዓት ለሦስት ዓመታት አስተማረው፤ ቀዳማዊ ምኒልክ ከአባቱ ጥበብን ተማረ። ነገር ግን ከጥቂት ዓመታት በኋላ አባትና ልጅ በመልክ ይመሳሰሉ ነበርና ሁለቱም በየተለያየ ቦታ ለየብቻ ሲንቀሳቀሱ ሕዝቡ ለሁለቱም እየሰገደ እጅ እየነሳና እየተምታታ ተቸግሮ ስለነበር እስራኤላውያን ቀዳማዊ ምኒልክ ወደ ሀገሩ እንዲመለስ ንጉሣቸውን እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፡፡ ‹‹ለሁለት ንጉሥ መገዛት አንችልም ወይ አንተ ንግሥናህን ልቀቅና ውረድና እሱን አንግሠው፤ ካልሆነ ግን ወደ እናቱ ሀገር ስደደው›› በሚል ሞገቱት፤ ንጉሥ ሰሎሞን ግን አንድ ልጁን በሀገሩ ነግሦ ከእርሱ ጋር እንዲኖር እጅጉን ይፈልግ ነበርና ሊያነግሠው ቢሻም የእግዚአብሔር ፈቃድ አልሆነም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቀዳማዊ ምኒልክ ወደ እናቱ ሀገር ሄዶ መንገሥ እንደሚፈልግ በመናገሩ የተነሣ ወደ ኢትዮጵያ መሄድ እንዳለበት በቁርጠኝነት አሳወቀ፡፡ ንጉሡም ‹‹ልጄን ወደ መጣበት እንዲመለስ እንደጠየቃችሁኝ አደርጋለሁ። ነገር ግን ወደ ሀገሩ ስሸኘው ብቻውን አይሆንም፡፡ የእኔ የበኵር ልጅ ከዚህ እንደሚሄድ ሁሉ የእናንተም የበኵር ልጆችና ካህናት አብረውት ወደ ኢትዮጵያ ይሄዳሉ›› ብሎ አዘዘ፡፡ በዚህም መሠረት ቀዳማዊ ምኒልክ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ አብረውት አንድ ሺ ሁለት መቶ እስራኤላውያን የበኵር ልጆች፣ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት በአዛርያስ የሚመሩ ሌዋውያን ካህናትም አብረውት ለጉዞ ተነሡ፡፡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትንና ሌሎች በርካታ ቁሳቁሶችን ይዘውም ነበር።
ነገር ግን ታቦተ ጽዮንን አዛርያስና ካህናቱ ተማክረው ቀዳማዊ ምኒልክ እንኳን ሳይሰማ በምሥጢር ይዘዋት ሊመጡ ተስማሙ፡፡ ዕቅዳቸውን ለማሳካት በታቦተ ጽዮን አምሳያ ሌላ ታቦት አዘጋጅተው ለመሄድ በሚነሡበት ዕለት ሌሊትም ወደ ቤተ መቅደስ ይዘውት ሄዱ፡፡
ከቤተ መቅደስ ሲደርሱም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበርና የቤተ መቅደሱ በር ተከፍቶ እና ውስጡም በብርሃን ተሞልቶ ታቦተ ጽዮንም ከመንበሯ በመነሣት ከፍ ብላ አገኟት። በዚህም የአምላክን ፈቃድ ተረድተውና እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በፍጥነት ይዘዋት ወጡ፡፡ በአምሳያዋ የሠሩትንም ቅርፅ በመንበሩ ላይ አስቀምጠው ሄዱ። መንገድ በጀመሩም ጊዜ በኢየሩሳሌም ታላቅ ንውፅውፅታ ሆነ፤ በከተማይቱም መዓት የወረደ ይመስል ነበር።
ሕዝበ እስራኤል ጋር በሐዘንና በለቅሶና ሸኗቸው፡፡ ንጉሥ ይህን ሲመለከት በመጨነቅ ሊቀ ካህኑን ሳዶቅን ጠራውና ‹‹የዚህ ልጅ ጉዞ አስጨነቀኝ፤ ቀድሞ ከእናቱ ጋር በተገናኘሁበት ሌሊት በሕልሜ ፀሐይ ከእስራኤል ወጥታ ስትጠልቅ እንደገናም ደግሞ በሌላ ሀገር ሰማይ ስታበራ ተመልክቼ ነበር። አሁን ደግሞ እንደምታየው ሆነ፤ እናም ነገሩ ከታቦተ ጽዮን ጋር የሚገናኝ መሰለኝ፤ እባክህ ወደ ቤተ መቅደስ ሂድና ደኅንነቷን አረጋግጥልኝ፤›› ብሎ ላከው፤ ሳዶቅም ገሥግሦ ቤተ መቅደስ ሲደርስ ታቦተ ጽዮንን ከመንበሯ ላይ አጣት፤ በግንባሩ ወደ መሬት ተደፋ።
ንጉሥ ሰሎሞን ሳዶቅን ልኮት ሳይመለስ ስለቆየ ያጋጠመውን እንዲያዩ መልእክተኞችን ላከ፤ እነርሱም ከነበረበት ሲደርሱ ወድቆ አገኙት፤ እርሱንም በጠየቁት ጊዜ ስለሆነው ነገር ነገራቸው፡፡ እነርሱም ያዩትንና የሰሙትን ሁሉ ለንጉሡ ነገሩት፤ ንጉሡ ሰሎሞንም እጅግ ተቈጣ፤ ወታደሮቹንም ጠርቶ ታቦተ ጽዮንን የወሰዷትን ኢትዮጵያውያን እንዲከተሏቸውና ታቦቷን እንዲያስመልሱ እነርሱን ደግሞ እንዲፈጇቸው አዘዘ፤ ነገር ግን ‹‹ባሕረ ኤርትራን ተሻግረው አልፈው ከሆነ እንዲተዋቸው ነገራቸው። እርሱ ግን ማቅ ለብሶ ታቦተ ጽዮን ከእነርሱ እንደተወሰደባቸው መሪር ለቅሶን እያለቀሰ እግዚአብሔርን ይለምን ነበር።
የንጉሡ ወታደሮች በፍጥነት ቢጓዙም ቀዳማዊ ምኒልክ እና አዛርያስ ታቦተ ጽዮንን ይዘው ሲጓዙ እጅግ ፍጣን ስለበር ሊደርሱባቸው አልቻሉም። መጽሐፈ ክብረ ነገሥት ይህንን ሲጠቅስ ‹‹ከመሬት አንድ ክንድ ያህል ከፍ ብለው ይሄዱ ነበር›› በማለት ይገልፀዋል። ባሕረ ኤርትራን ከተሻገሩና ግብፅ ከደረሱ በኋላ ዕረፍትን ባደረጉ ጊዜ አዛርያስ ለቀዳማዊ ምኒልክ ታቦተ ጽዮንን ይዘዋት እንደመጡ ነገረው፡፡ አያይዞም ‹‹አንተም ብትሻ ታቦቷንም ወደ ሀገሯ ልመልሳት ብትል አትችልም፤ አባትህ ሰሎሞንም ሊወስዳት ቢመጣ አይሆንለትም›› አለው። ከቦታ ቦታ ይዣት እንቀሳቀሳለው ቢልም ያለ ፈቃዷ ምንም እንደማያደርግና ሁሉ ነገር በአምላክ መልካም ፈቃድ እንደሚፈጸም ነገረው። ቀዳማዊው ምኒልክም ይህን ሲሰማ ተደሰተ፤ ሕዝቡና ሠራዊቱ በሙሉ ልዑል እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ከግብፅ ምድር ወጥተው እስከ ኢትዮጵያ በታላቅ እልልታና ሆታ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ።
ኅዳር ፳፩ ቀን አክሱም በደረሱ ጊዜም እናቱ ንግሥተ ሳባ ተቀበለችው፤ ደስታና እልልታውን ተመልክታ ያገኙት ነገር እንዳለ ብትጠይቀው ታቦተ ጽዮንን እንዳመጧት ነገራት፡፡ የእርሷም ደስታ እጥፍ ድርብ ሆነ። ታቦቷንም በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስቀመጡአት፡፡
ከዚያም ዘመን ጀምሮ በየዓመቱ ኅዳር ፳፩ ቀን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙ ታላላቅ ተአምራትን በማሰብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ታከብራለች፡፡
ምንጭ፤ ‹‹ክብረ ነገሥት ከገጽ ፳፩-፶፭››በ፲፱፺፬ ዓ.ም. የታተመ፤ ተርጓሚ ሥርግው ገላው