የቀኝ ዐይን – ድንግል ማርያም

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

አፍጣኒተ ረድኤት ማርያም በጊዜ  ምንዳቤ ወአጸባ ለዐይን እምቀራንባ፤ አንቲ ውእቱ ረዳኢተ ያዕቆብ በቤተ ላባ፤ በኩሉ ኅሊናሃ ወበኩሉ አልባባ፤ዘኢታፈቅረኪ ነፍስ ትሠሮ እምሕዝባ፡፡

 የነገረ ማርያም ሊቅ(Marian Doctor)እየተባለ የሚጠራው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ እመቤታችንን በብዙ ምሳሌ እየመሰለ፣ እየተረጎመና እያመሰጠረ ብዙ ጊዜ አመስግኗታል፡፡ ምንም እንኳን እኛ የምናውቀው የምስጋና ድርሰቱ ለጸሎት የምንጠቀምበት ውዳሴ ማርያም ቢሆንም ከትርጓሜና ከስብከቶቹ ውጪ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ስንኝ ያላቸው የምስጋና ድርሰቶችን(Hymns) መድረሱን ታሪክ ጸሐፊው ሶዝመን መዝግቦልናል፡፡ ከነዚህ የምስጋና ድርሰቶቹ መካከልም ‹‹በእንተ ልደት››(On Nativity) እና ‹‹በእንተ ቤተ ክርስቲያን››(On the Church)በተባሉ ትልልቅ ድርሰቶቹም እመቤታችንን ደጋግሞ ያመሰግናታል፡፡

በተጠቀሱት ሁለቱም ድርሰቶቹ እመቤታችንን ለማመስገን ከተጠቀመባቸው ምሳሌዎች ውስጥ አንዱ “ዐይን” ነው፡፡ ሊቁ ስለ ቤተክርስቲያን በደረሰው የምስጋና መዝሙሩ ውስጥ እንዲህ ይላታል፤ ‹‹ዐይን ጥርት የሚለው ከፀሐይ ብርሃን ጋር ተዋሕዶ ከብርታቷ ኃይልን ከውበቷም ነጸብራቅን ሲቀበል ነው፤ በዚህ ጊዜ በግለቷ ይሰነገላል፣ያበራል፤ በውበቷም ያጌጣል፤… ልክ እንደዚሁ ማርያም ዐይን ናት፤ብርሃን (ጌታ) ማደሪያውን በእርሷ አዘጋጀና መንፈሷን ጽሩይ አደረገ፤አሳቦቿን አጠራ፣ኅሊናዋንም ንጹሕ አደረገ፤የድንግልናዋንም ክብር አበራው ››/Hymns on the Church, 36, 1-2/፡፡ ሊቁ በዚሁ ድርሰቱ ውስጥ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ፤ ‹ለዚህ ዓለም ሁለት ዐይኖች ተሰጡት፤ ማየት ያልተቻላት የግራ ዐይን ሔዋን ስትሆን፣ የምታበራው የቀኝ ዐይን ደግሞ (እመቤታችን) ማርያም ናት፡፡በማታየው በጨለማዋ ዐይን ምክንያት መላው ዓለም ጨለመ፤ ስለዚህም ሰዎች በጨለማ ጥላ ውስጥ ሆነው ሲዳብሱ ያገኙት ሁሉ አምላክ ፣ ሐሰቱም እውነት መሰላቸው፡፡ነገር ግን ዓለም እንደገና በሌላ ዐይኑ ባበራና (ባየና) ሰማያዊው ብርሃንም በዚች ዐይን ሰሌዳ ውስጥ ባንጸባረቀ ጊዜ ሰዎችም ቀድሞ ያገኙትን(ያመለኩትን) የኑሮአቸው ውድቀት(የባሕርያቸው መጎስቆል) መሆኑን ተረድተው ወደ ማንነታቸው ተመለሱ (አንድነታቸውን አገኙ)›› ይላል /Ibid, 37, 5-7/::

 

በዚህ መሠረት የእመቤታችን ልደት ዓለም ማየት የጀመረበት ዕለት ነው ማለት ነው፡፡ በርግጥም በነገረ ማርያም መጽሐፋችን ላይ እንደተገለጸው እመቤታችን በቴክታና በጥሪቃ(ሰባተኛ ቅድመ አያቶቿ) በታየው ሕልም መሠረት ዓለምን ሰፍኖበት ከነበረው ድቅድቅ የኃጢኣት ጨለማ እፎይታ የሰጠችው ጨረቃ እርሷ ናት፡፡ በጨለማ ሲያዩት የሚያስፈራውና ሌላ ሌላ የሚመስለው ጉቶው፣ ቁጥቋጦው ፣ ድንጋዩ ፣ ጉብታው….ሁሉ ተራ ነገር መሆኑ የተጋለጠባት፤ ሰዎችም የሰገዱለት ሁሉ አምላክና ጌታ መሆኑ ቀርቶ ድንጋይ ጉብታ መሆኑን ማየት የጀመሩባት፣ ከደገኛው ፀሐይ ክርስቶስ መውጣት በፊት ከረጂሙ ዘመን ጨለማ ጭንቀት የተገላገልንባት ጨረቃ፣ ብርሂት የቀኝ ዐይን እመቤታችን ማርያም ናት፡፡ ስለዚህም ልደቷን የጨለማችን መገፈፍ፣ የዐይናችን ማየት፣ የብርሃናችንም መውጣት ነውና በፍጹም ደስታ እናስበዋለን፤ እናከብረዋለንም፡፡

 

ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምን የምናስታውሰውም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ብዙ በማመስገኑ ብቻ ሳይሆን ግሩም አድርጎ በማመስጠሩና እንዲህ ያለ ልዩ ልዩ ነገር በማምጣቱም ጭምር ነው፡፡ ለነገሩ ሰው የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ከሆነ በኋላ ይህን ሁሉ ማድረጉ አያስደንቅም፡፡ የሆነው ሆኖ የእርሱን ያህል በልዩ ልዩ ሕብረ-አምሳል ያመሰገናት ያለ አይመስልም፡፡ሊቁ በልደት ድርሰቱም‹‹እናትህ አስደናቂ ናት፤ ጌታ ወደ እርሷ ገባና አገልጋይ ሆነ፤ እየተናገረ ገብቶ በእርሷ ውስጥ ግን ዝም አለ፤ ወደ እርሷ በነጎድጓድ ድምፅ ገብቶ በእርሷ ውስጥ ጸጥታን አሳደገ፤ የዓለሙ እረኛ ገብቶ በግ ሆኖ ተወለደ፤ እንደ በግም ‹ባ› እያለ ተገለጠ ››/On Nativity, 11, 6/ እያለ አስደናቂነቷን እየደጋገመ ይናገርላታል፡፡አንድ ብቻ ጨምሬ ወደ በዓሉ ልመለስ ፤ቅዱሱ ሊቅ ጌታን እንዲህ ይለዋል፤ ‹‹አንተና እናትህ ብቻ ተወዳዳሪ የሌላችሁ ውቦች ናችሁ፤ በአንተ ላይ ምንም ምን ትንታ(mark) በእናትህም ላይ እንከን(stain) የለም››/Carmina Nisibena, 27,8/፡፡ምንኛ ግሩም ምስጋና፣ እንዴትስ ያለ ፍቅር፣ እንደምንስ ያለ መረዳት ነው? መብቃት ነዋ! መብቃት! ከሌላ ከምን ይገኛል? እርሱ ካልገለጸ፡፡

 

ከቅዱስ ኤፍሬም ሌሎች ድርሰቶች የተነሣሁትና ርእሴንም በእርሱ ምስጋና ያደረግሁት እንዲሁ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ውዳሴ ማርያም እየተጣጣለና ድርሰቱም የእርሱ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ነው (ምነው በሆነና ነበር) ፤ ወይም ደግሞ እርሱ ስለ ሌላ የደረሰውን የእኛ ሰዎች የማርያም ምስጋና ነው ብለው ነው እንጂ እርሱስ እንዲህ አይልም መባል ስለተጀመረ እርሱ ስለ እርሷ ከደረሰዉ ወደ ግእዝ የተተረጎመዉ ትንሽ መሆኑንና ከላይ ለምሳሌነት ካቀርብኳቸው በላይ በውዳሴ ማርያም ምን አዲስ ነገር አለ ለማለት ነው፡፡ ይህችን ታህል ጥቆማ ከሰጠሁ ቦታውም ጊዜውም የጽሑፉም ዓላማ በዚህ ጉዳይ ላይ መከራከር አይደለምና ወደ እናታችን በዓለ ልደት በረከት ላምራ፡፡

 

በርግጥም ፍጹም ልዩ

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማይጠረጠር መልኩ ከፍጥረት ሁሉ ልዩ ናት፡፡ በድንግልና ላይ እናትነት፣ በክብረ ድንግልና ላይ ክብረ ወሊድ፣ በድንጋሌ ሥጋ ላይ ድንጋሌ ነፍስና ድንጋሌ ኅሊና የተሰጠው ከእርሷ በቀር ማንም የለም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ምንም እንኳ ‹‹በልቧ ትጠብቀው ነበር››/ሉቃ.2፡51/ ተብሎ እንደተጻፈው አትናገረው እንጂ ከፍጥረት ወገን እንደ እመቤታችን እርሱን ለማወቅ የተቻለው ፍጥረት የለም፡፡ ሊቁ ኦሪገን በሉቃስ ወንጌል ትርጓሜው ላይ እንደገለጸው ስለ አምላክ ፍጥረት ሊያውቀው የሚቻለው የመጨረሻው የእውቀት ደረጃ ላይ የደረሰችው እመቤታችን ብቻ ናት፡፡ እንደ እርሱ ትርጓሜ እመቤታችን ፍጡር ለፈጣሪው ክብር ሊጨምርለት እንደማይቻለው እያወቀች  ‹‹ተዐብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር – ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች›› ያለችው ፍጡር ሊረዳው የሚቻለው የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሳ በዚያ መጠን ማመሰገኗን ስትገልጽልን ነዉ ይላል፡፡በርግጥም በዚህ መጠን ከርሷ በላይ ሊደርስ የሚቻለው እንዴት ሊኖር ይችላል? ይህ የሚያመለክተውም ገና በምድር ሳለች ለፍጥረት የሚገባው ለዚህ የመጨረሻ ብቃት ከደረሰች ከዚህ ዓለም ከሔደች በኋላማ ይልቁንም እንዴት ያለውን የተወደደውንና ከፍጥረት ሁሉ የላቀውን ምስጋና ታቀርብልን ይሆን? ምን ጥርጥር አለው? ልዩ የሆነውን ልታቀርብ የሚቻላት ልዩ እናት፡፡

 

ለዚህም የበቃችው ራሷን ለሰው በሚቻለው ከፍተኛው መጠን እንደምትጠብቅ አስቀድሞ የሚያውቅ ፈጣሪ እርሱም ደግሞ ጠበቃትና ከፍጥረት ወገን ልዩ ሆነች፡፡ ቀድም ብለን የተመለከትናቸው የቅዱስ ኤፍሬም ጥቅሶች የሚያረጋግጡልንም ይህንኑ ነው፡፡ ብርሂት የሆነች ዐይን ለሰውነት መብራት የምትሆነው የፀሐይ ብርሃን ሲዋሐዳት እንደሆነው ሁሉ እርሷም በራሷ ብርሃነ ዐይን ንጽሐ ሥጋ ወኅሊና ላይ የብርሃን ጌታ ብርሃን የተባለ ጸጋዉን አሳድሮ ንጽሕናዋን ወደር የለሽ አደረገዉ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ርብቃ ለይስሐቅ የታጨችበትን የሚናገረዉ አንቀጽ ላይ ‹‹ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች››/ዘፍ. 24፣16/ የሚለውን ሲተረጉም ‹ወንድ የማያውቃት› የሚለውን ለሥጋ ድንግልናዋ ከሰጠ በኋላ ‹ድንግልም ነበረች› ያለው ደግሞ ለመደጋገም ሳይሆን በኅሊናዋም ያልባከነች የተጠበቀች ነበረች ሲል ነው ይላል፡፡ ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለችው ድንግል ርብቃ ድንገት(ለርሷ) ያገኘችውና ማንነቱን እንኳ በውል የማታውቀው ሽማግሌ (የአብርሃም መልክተኛ) ቤተሰቦቿን በጠየቀው መሠረት ወላጆቿ ጠርተው ‹‹ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን?›› ብለው በጠየቋት ጊዜ ሳታንገራግር ‹‹እሔዳለሁ›› አለች፤ መሰስ ብላም ተከተለችው፡፡/ዘፍ 24፣58/ እመቤታችን ግን የከበረ መልአክ ተገለጾ ሲያነጋግራት እንኳ የልቡናዋ በር ለወሊድ አልተንኳኳም፡፡ ለልማዱ ሴት ልጅ ‹‹ትጸንሻለሽ፣ ትወልጃለሽ›› ቢሏት ምንም ብትመንን መልአክ ተገልጾ ከነገራት ‹‹ይህ እንዴት ይሆናል?›› ልትል አትችልም፤ እንዴት እንደሚሆንማ ጠንቅቃ ታውቃለችና፡፡ እመቤታችን ከነዚህ ሁሉ ልዩ ስለሆነች ‹‹እፎኑ ይከውነኒ ዝንቱ›› ስትል ፈጽሞ በታተመና እርሱን በሚያልፍ ኅሊና መልአኩን አስጨነቀችው፡፡

 

እርሱም‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም›› የምትል ጥቅስ አግኝቶ ፈተናዉን ተገላገለ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በዚህ ጥቅስ ተረትታ ብሥራቱን ስትቀበልም ‹‹ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ- እንዳልከው ይሁንልኝ›› ያለች አንት እንዳልከው የአምላኬ ፈቃዱ ሆኖ እንበለ ዘርዕ፣ እንበለ ሩካቤ ከሆነና ተጸንሶ የሚወለደውም እርሱ ከሆነ ይሁን ይደረግ አለች እንጂ ለሌላው ነገርማ ኅሊናዋ እንደታተመ ነው የቀረው፡፡‹‹ ልጄ ሆይ ስሚ፣ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽን የአባትሽንም ቤት እርሽ፣ ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፤ እርሱ ጌታሽ ነውና›› (መዝ 44÷12) ሲል አባቷ ዳዊት በትንቢት እንደተናገረው እርሷ ከሔዋናዊ ጠባይ ተለይታለችና፡፡ ሰሎሞንም‹‹ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ፤ ነውርም የለብሽም፤ ልቤን በፍቅር አሳበድሽው….›› ያለው ለዚህ  ነበር፡፡

 

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ‹‹የታተመች ደብዳቤ›› ያላትም ለዚህ ነው/ኢሳ 28 ፤ 12/፡፡ ምክንያቱም ለልማዱ ደብዳቤ ከተጻፈ በኋላ ይታሸጋል፡፡ ስለ እርሷ የተነገረው ግን  ከታተመ ወይም ከታሸገ በኋላ ተጻፈበት የሚል ነው፡፡ አብ በድንግልና አትሞ ሲያበቃ በውስጧ አካላዊ ቃልን የጻፈባት ማንበብ የሚችሉም(እሥራኤል) ማንበብ የማይችሉም(አሕዛብ) እናነበው ዘንድ አንችልም ታትሟልና (በድንግልና በንጽሕና በክብር በምስጢር) አሉ ብሎ የተናገረላት ደብዳቤ እርሷ ናትና፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጸጋ ለተሰጣቸው ሰዎች ብሥራት ሊያደርስ ሲመጣ ይህ የመጀመሪያው አልነበረም፤ ይሁን እንጂ ለዳንኤልም ሆነ ለጻድቁ ካህን ለዘካርያስ ለእርሷ እንዳደረገው ለእነርሱ መች አደረገ? እነርሱ እጅ ነሱት ሰገዱለት እንጂ እርሱ መቼ እጅ ነሳ ሰገደላቸው? ከዚህ በላይ ልዩ መሆን በእውነት ወዴት ይገኛል፡፡

 

ፍጹም ልዩ መሆኗን ለማስረገጥ ያህል አንድ ነገር ብቻ ላክል፡፡ የጥንቶቹ የቤተክርስቲያን ሊቃዉንት ጌታ ለሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቋት ዘንድ  የሰጠው ሁለት ጊዜ ነው ይላሉ፡፡ አንደኛው ብዙ ጊዜ ሲጠቀስ የምንሰማው ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጠው ነው፡፡ይህም ‹‹በጎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ እና ግልገሎቼን አሰማራ››/ዮሐ 21፣15-17/የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከዚህ ቀደም ብሎ በመስቀል ላይ የሰጠው ነው፤ በመስቀል ላይ ጌታ ለዮሐንስ ‹‹እነኋት እናትህ›› ሲል የሰጠው እርሷን ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንንም ነው ይላሉ፡፡

 

በእነዚህ ሊቃዉንት ትርጓሜ መሠርት  ሁለቱም ራሳቸውን የቻሉ ምስጢራትን ይዘዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሕጋዊ ስለነበር(በጋብቻ የተወሰነ ማለት ነው) የተሰጠውም አደራ ይህንኑ የሚመለከትና በጎቹን እስከ ገላግልቶቻቸው(ምእመናን) የሚመለከት ነው፡፡ጌታ በወንጌል ‹‹በጎቼ ድምጼን ይለያሉ›› እንዳለው እነዚህ ድምጽ እንጂ ቃል መለየት የማይቻላቸው ምእመናን ናቸው፡፡  የቅዱስ ዮሐንስ ግን ከዚህ ሁሉ በእጅጉ ይለያል፡፡ምክንያቱም እመቤታችን ራሷ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ብቻ ሳትሆን የፍጹማን ደናግልም ምሳሌ ናት፡፡ ስለዚህ ከድምጽ ያለፈ ቃላትን ምስጢራትን መለየት የሚቻላቸው ፍጹማንን የሚመለከተው አደራ የተሰጠዉ ለበቃው ብቻ ሳይሆን ለፍጹሙ ድንግል ለዮሐንስ ነዉ፡፡ ስለዚህ እመቤታችንን መግፋት ቤተክርስቲያንን መግፋት ነው፡፡እርሷንም በቤቱ ማስተናግድ የሚቻለው ዮሐንስን የመሰለ ንጹሕ ድንግል ነው፡፡

 

ቅዱስ  ቅዱስ አትናቴዎስ እንደሚለው ጌታ የሰጠው ድንግሊቱን ለድንግል፣ ድንግሉንም ለድንግል፤ ንጹሕንም ለንጹሕ ነው፡፡ መላእክት ሲጠብቋት ከኖሩ በኋላ መልአክ ለመሰለ ሰው ሰጣት እንጂ ለሌላ አልተሰጠችም፤ ሊቀበላት የሚቻለውም የለም፡፡በተለይ ኦሪገን ይህንኑ በተረጎመበት አንቀጹ ስለ ቅዱሱ ብቃት ሲናገር  ለእርሷም ‹‹እነሆ ልጅሽ›› አላት እንጂ ‹‹ልጅ ይሁንሽ›› አላላትም፤ ምክንያቱም ዮሐንስ በዚያ የመከራና የጭንቀት የፍርሃት ቀን በዕለተ ስቅለት ሳይፈራ ሳይሰቀቅ በእግረ መስቀሉ የተገኘው ቅዱስ ጳዉሎስ ‹‹እኔም አሁን ሕያዉ ሆኜ አልኖርም፤ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል›› /ገላ 2፣20/ እንዳለዉ ዮሐንስ ራሱን ክዶ ስለነበር ለራሱ እየኖረ አይደለምና በእርሱ የሚኖረው ጌታ ነው፡፡ ‹‹አነሆ ልጅሽ›› ያላትም በእርሱ አድሬ ያለሁት እኔ ነኝ ማለቱ ስለሆነ ከእርሷ ሰው ከሆነ በኋላ ለማንም አልሰጣትም፤ በዮሐንስ አድሮ የተቀበላትም ራሱ ነው፤ ከዚያ በኋላ እርሷን ሊቀበል የሚቻለው የለምና ይላል፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው እንኳንስ የእርሷን ነገር ለመንቀፍ ቀርቶ ለማመስገንም ትሰጠው ዘንድ ከፈለገ እንደ ዮሐንስ ራሱን በንጽሕና ይጠብቅ ፣ራሱንም ፈጽሞ ይካድ ባይ ነው፡፡

 

የአሁኖቹ ሰዎች እርሷን ባይቀበሉ፣ በእርሷ አማላጅነት ባያምኑ ለምን እንደነቃለን? እነዚህ በትንሽ ነገር እንኳን መታመን የማይቻላቸው የእርሷን ነገር ይረዱ ዘንድ ታላቁንና ሰማያዊውን ምስጢር ማን አደራ ሊሰጣቸው ይችላል? አንዳንድ የዋኃን ደግሞ መሠርይ ተሐድሶዎች ስለ እርሷ የዘመሯቸውን መዝሙር ተብየ ዘፈኖች እየተመለከቱ ይታለላሉ፡፡ ይህ መናፍቃኑ ስለ እርሷ የሚሉትን መንገድ የተከተለ በእነርሱ ወዝ የታሸ ስለሆነ ተወዳጅ መሥዋዕት አይደለም፡፡ በኦሪት አንበሳው፣ ተኩላው፣ ቀበሮው፣ … የመሳሰለው  አውሬ የገደለውን ሁሉ እንኳን ለመሥዋዕት ልናቀርበው ቀርቶ ልንበላውም የተከለከለ ነው፡፡ ይህም ማለት በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱት አውሬዎች የተባሉት (አጋንንት፣ ርኩሳን መናፍስት፣ መናፍቃን፣…. ደሙን ያፈሰሱትን ወይም በእነርሱ) የተሰዋውን ሁሉ እንኳን ለእግዚኣብሔር ማቅረብ ለእኛም መንካት መርከስ ነው ማለት ነው፡፡ ‹አውሬ የቧጨረውንም አትንካ› የሚል ንባብም ይገኛል፤ ይህ ሁሉ ከእነርሱ የተነካካውን በዚህ ዓለም የዘፈንና የረከሰ መንፈስ የጎሰቆለውን ምንም ለዐይንህ ቢያምርህ (በዘፈን ላደገ ሁሉ የእነርሱ የሚያምረው መሆኑ አይጠረጠርም) ፈጽመህ አትንካ ተብለን ታዘናልና መልከስከስ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ግጥሙ በኑፋቄ ዜማው በዘፈን ርኩሰት የተቧጨረ ርኩስ ነውና፡፡እርሷ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ የቤተክርስቲያናችንም ስጦታ ስለሆነች በእውነት ልዩ ናትና ይህን በመሰለ መልኩ የተቧጨረውን አናቀርብም፡፡

 

እንግዲህ ዛሬ ተወለደች የምንለው ይህችን ልዩ ድንግል ነው፡፡ስለዚህም የእርሷን በዓለ ልደት ማክበር ከዚህ ሁሉ በረከት መሳተፍ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር በእርሷ በኩል ለባሕርያችን ያደረገውንም ክብር ማወቅና መቀበል ጭምር ነው፡፡

 

ከበዓሉ ምን እናገኛለን? የእርሷስ በዓል አልበዛምን?

አንዳንድ ሰዎች በእኛ ቤተክርስቲያን የጌታ በዓል አንሶ የእመቤታችን የበለጠ፤ እኛም ከርሱ ይልቅ ለርሷ የምናደላ የሚመስላቸው ቁጥራቸው በርከት ማለት ጀምሯል፡፡ ያለማወቅ ነውና አይፈረድባቸውም፡፡ ለነቀፋም የተሰለፉ ስለሆነ በ‹ምሰለ ፍቁር ወልዳ-ከተወደደው ልጇ ጋራ› በምንለው ሥዕል ውስጥ እንኳን በሥዕሉ መጠን እየመሰላቸው ጌታ ያነሰ የሚመስላቸው ማስተዋል የራቃቸው ስለሆኑ በእነርሱ አንገረምም፡፡በቤተ ክርስቲያናችን ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ድረስ ከእናቱ ጋር መሰደዱን፣ ከኅዳር ፲፬ ጀምሮ እስከ ልደቱ ይወርዳል ይወለዳል ሲሉ ትንቢት የተናገሩ የነቢያትን ጾም እየጾምን እርሱን እናስባለን፡፡ ከልደት እስከ ዐቢይ ጾም ድረስም በሥጋዌ፤ በአንድነት በሦስትነት መገለጡ አስተርእዮ እየተባለ ይታሰባል ይሰበካል፡፡ ከዚያም ዐቢይ ጾም ይገባል፤ ሁለንተናችን እርሱን በማሰብ ይሰበሰባል፤ ቃለ እግዚአበሔሩም ይህንኑ ያዘክራል፡፡ በትንሣኤውም ሃምሳ ቀናትን እንደ አንድ ቀን እንደ ዕለተ ትንሣኤው በመቁጠር ትንሣኤውን እንሰብካለን፡፡ ከዚህ በማስከተልም ርዕደተ መንፈስ ቅዱስን በዓለ ጰራቅሊጦስን በጾም እናከብራለን፡፡በየወሩም በዓለ እግዚእ፣ መድኃኔዓለም፣ ኢየሱስ፣ አማኑኤል…. እያልን ከዘጠኙ ዓበይትና ከዘጠኙ ንዑሳን በዓላት በተጨማሪ በየአጥቢያቸው የሚታሰቡት ትዝ አይሏቸውም፡፡ ሌላው ቀርቶ በየሳምንቱ ሁለት ቀናትን (ረቡዕ እና አርብ) በጾም ሁለት ቀናትን (ቀዳሚትንና እሑድን) በበዓል ለክርስቶስ መታሰቢያ የሰጠች ብቸኛ ቤተ ክርስቲያን የእኛይቱ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ብቻ መሆኗን አያስተውሉም፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ የማርያም በዓል ከጌታ በዓል ይበልጣል ማለትን ምን ዓይነት አለማስተዋል ልንለው እንችላለን? ቢሆንስ በቅዱሳን በዓል ዋናው ተከባሪ ተመሰጋኝ ማን ሆነና ነው ይሄ ሁሉ ጩኸት? ስለዚህ በዚህም ስም አደረግነው በዚያ እግዚአብሔር በአከበራቸው ቅዱሳን ስም እስካደረግነው ድረስ በዓሉ ሁሉ የእግዚአብሔር ነው፡፡

 

የእመቤታችን በዓለ ልደትም በዚሁ መንፈስ የሚከበር በዓል ነው፡፡ነቢዩ ኢሳይያስ ቀደም ብሎ ‹‹ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ-ከእሴይ ሥር ወይም ግንድ በትር ትወጣለች››/ኢሳ 11፤6/ ብሎ ስለ ልደቷም ተናግሮላታል፡፡ ይህንንም ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ዘቀዳሚት ድርሰቱ፤ ‹‹ በትረ ሃይማኖት ዘኢትጸንን ምስማኮሙ ለቅዱሳን-የቅዱሳን መደገፊያቸው ግያዝ የሱነማዊቷን ልጅ ከሞት ያስነሣባት ዘንድ ከነቢዩ ከኤልሳ ተቀብሎ እየተጠራጠረ እንደወሰዳት ያይደለሽ ጽነት ጥርጣሬ የሌለብሽ የሃይማኖት በትር አንቺ ነሽ›› ብሎ ተርጎሞልናል፡፡ አባ ጀሮምም ይህን የነቢዩን ትንቢት በትር ከግንዱ ላይ ተስተካክሎ የሚወጣ ግዳጂ ለመፈጸም የሚፈልግ ስለሆነ የእመቤታችን ልዩ መሆን ያሳያል ይላል፡፡

 

በርግጥም ሊቃውንቱ እንዳሉት ለቅዱሳን መደገፊያ ለአጋንንት ለመናፍቃን ደግሞ ማባረሪያ የሆነች በትር፤ ድንግል ማርያም፡፡ስለዚህ የእርሷን በዓል ማክበር ከዚህ ጥርጣሬ ከሌለው በረከት መሳተፍ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአጠቃላይ የበዓላት ይልቁንም በክርስትና ጥቅማቸው ምንድን ነው የሚለውን እንመልከትና እንፈጽም፡፡

 

በዓላትን በብዛት እንድናከብር ያዘዘን እግዚአብሔር ነው፡፡የምናከብራቸውም ዝም ብለን አይደለም፡፡በተለይም በብሉይ ኪዳን በዓላት ብዙ የመሥዋዕት እንስሳትን ማቅረብና መሠዋት በጥብቅ የሚፈጸም ትእዛዝ ነበረ፡፡ የዚያ ሁሉ መሥዋዕትም ዓላማ ሥርየተ ኃጢኣትን ማስገኘት ነበር፡፡/ዘሌ ፲፯፣፲፩/ በአጭሩ በዓላቱን የማክበሩ ዓላማ ሥርየተ ኃጢኣትን ማሰገኘት ነው ማለት ነው፡፡በዚህ መሠረታዊ ምክንያት በእያንዳንዱ የኦሪት በዓል እጅግ ብዙ የመሥዋዕት እንስሳት ይቀርቡ ነበር፡፡በኦሪት በየዕለቱ ሁለት ሁለት ጠቦቶች፣ በየሰንበቱ ሁለት ተጨማሪ የበግ ጠቦቶች፣በየመባቻው ደግሞ ለየዕለቱ ከሚቀርበው በተጨማሪ ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግ፣ ሰባት የአንድ ዓመት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ፍየል ይቀርብ ነበር፡፡ የዓመታዊ በዓላት ደግሞ ከዚህ ሁሉ ይለያል፡፡ለምሳሌ የዳስ በዓሉን ብቻ ብንመለከት ከዕለቱ፣ ከሰንበቱና ከመባቻው እንዲሁም በፈቃድ ከሚቀርቡት በተጨማሪ 73 ወይፈኖች፣ 136 አውራ በጎችና ጠቦቶች፣ 10 አውራ ፍየሎች ይቀርቡ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ግን የእህሉን ቁርባንና ሌላውን መሥዋዕት(ለኃጢኣት ፣ ለበደል፣….የሚባሉትን) ሳይጨምር ነዉ/ዘጸ ፳፱፣፴፰፣ ዘሌ ፳፬፣፭-፱፣ ዘኁ ፳፰፣፱-፲፭፣ዘኁ ፳፱/፡፡

 

‹‹ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና››/ዕብ 10፣1 / ተብሎ እንደተጻፈ እነዚህ ሁሉ ግን ምሳሌዎች ነበሩ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም።ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።›› /ዕብ 5፣ 12-15/ እንዳለው ሊቃውንቱ ለእኛ ወተት ወተቱን እየመገቡ ጠንካራውን ምግብ አላቀረቡልንም ነበር፡፡ አሁን ግን እስኪ ይህን እንኳ እንሞክረው፡፡

 

በኦሪት እንደተጻፈው በፋሲካ የሚሠዋው ልዩ የድኅነት መሥዋዕት በግ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡‹‹በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ። እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ›› /ዮሐ 1፣ 26/።ተብሎ ተጽፎአልና፡፡በሌሎቹ በዓላት የምናቀርባቸው ደግሞ ቀደም ብለን እንዳየነው ወይፈኑ፣ አውራ በጉ፣ ፍየሎቹ(ወንድም ሴትም ነው የሚቀርበው)፣ ሌላው ሁሉ የማን ምሳሌ ነው ማለታችን አይቀርም፡፡ ይህ ሁሉ የበዓል መሥዋዕት የቅዱሳን ምሳሌ ነው፡፡ ‹‹እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፥ ወደ አሕዛብም በተንኸን›› /መዝ 44፣12/ ተብሎ ትንቢትም ተነግሮላቸዋልና።ጌታም በወንጌል ‹‹ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ።እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል›› /ማቴ 23፣35/ ሲል እንደተናገረው ቅዱሳን ለእምነታቸው መሥዋዕት ሆነው ቀርበዋል።ደማቸውንም አንዱ እንደ ፍየል፣ ሌላው እንደ ወይፈን፣ ሌላውም እንደ አውራ በግ አፍስሰዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ የመሥዋዕት ዓይነቶች ለተለያየ የኃጢኣት ማስተሥረያ እነደነበሩት እነዚህም ድኅነትን ለመፈጸም ከተሰዋው በግ ከጌታ በኋላ ለምናምን ሁሉ ሥርየተ ኃጢኣትን እናገኝ ዘንድ የሚማልዱ ስለኛም ጭምር ደማቸውን ያፈሰሱ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የሌላው ጊዜ የመሥዋዕት እንስሳ የፋሲካቀውን በግ ሊተካው እንደማይችልና የመሥዋዕቱም ዓይነት ፈጽሞ የተለያየ እንደ ሆነው ሁሉ የቅዱሳኑ መሥዋዕትነትና ሰማዕትነትም እንዲሁ የተለያየ መሆኑና የእነርሱም የጌታችንንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሊተካ የማይችል መሆኑ ሊዘነጋ አይገባውም፡፡እርሱ ኃጢኣትህ ተሠረየልህ(ሽ) እያለ ይቅር ሲል እነርሱ ግን የሚያስተሠርዩልን እየጸለዩ ነውና፡፡ ከዚህ በመለስ ግን የጥንቶቹ ሊቃውንት እንደተረጎሙልን የእነርሱ ተጋድሎና ሰማዕትነት የእኛ የሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች መሥዋዕቶች ናቸው፤ ስለእነርሱም ሥርየተ ኃጢኣትን እንቀበላለን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል  ››/ዕብ 4፣6/ ሲል የተናገረዉው ይህን የሚያረጋግጥልን ነው፡፡

 

ቀደም ብለን እንዳየነው የመሥዋዕቱ እንስሳት የበዙት ለእሥራኤል ለኃጢኣታቸው አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነው ሁሉ በሐዲስ ኪዳን ለምንኖር ለእኛም ብዙ ቅዱሳን መኖራቸው ይጠቅመናል፣ ኃጢኣታቸንም ያስተሠረይልናል፡፡ የመሥዋእቱ እንስሳት በሙሉ የተቆጠሩና የታወቁ እንደሆነው ሁሉ ቅዱሳኑም ምን ቢበዙም እንዲሁ የታወቁና የተቆጠሩ ናቸው፡፡

 

ዳዊት አባታችን ‹‹ዘይኌልቆሙ ለክዋክብት በምልኦሙ፣ ወይጼዉዖሙ ለኩሎሙ በበአስማቲሆሙ- ክዋክብትን በምልዓት ይቆጥራቸዋል፣ ሁሉንም በየስማቸዉም ይጠራቸዋል››/መዝ 146፣4/ ሲል እንደተናገረዉ ክዋክብት የተባሉ ቅዱሳን ሁሉ በእርሱ ዘንድ በባለሟልነት በቃል ኪዳን የታወቁ በመሥዋዕትነትም የተቆጠሩ ናቸዉ፡፡ ያ ሁሉ የ መሥዋዕት እንስሳ ፣ የጧቱና የሰርኩ፣ የሰንበቱና የመባቻዉ፣ የዓመት በዓላቱ፣ የየግለሰቡ የኃጢኣቱ፣ የበደሉ፣ የመንጻቱ፣…በዓይነት በዓይነት እንደሚታወቅ በእርሱም ዘንድ ተቀባይነት እንዳለዉ ሁሉ የየዕለቱ ቅዱሳንም እንዲሁ ይተወቃሉ፤ ጸሎታቸዉና ምልጃቸዉም በእርሱ ዘንድ የከበረ ነዉ፡፡ እመቤታችን ደግሞ ከነዚህ ሁሉ በግንባር ቀደምነት የምትጠራ ልዩ መሥዋዕታችን ናት፡፡በሁለተኛዉ ክፍለዘመን መጨረሻ የነበረዉ የሰረዴሱ መልይጦን/Melito of Sardis/  በፋሲካ መዝሙሩ ላይ እመቤታችንን የመሥዋዕቱን በግ የወለደችልን ንጽሕት ሴት በግ (fair ewe) ይላታል፡፡ ስለዚህ የእመቤታችን በዓለ ልደት ከብሉይ ኪዳን ሰዎች የተሻለ ሥርየተ ኃጢኣት የምናገኝበት ነዉና ከነዚያ በተሻለ በዓላችንን መንፈሳዊ አድርገን እናክብር፤ ከመንፈሳዊ በረከትም እንካፈል፡፡የደራሲዉንም ምስጋናና ምልጃ በመሰለ ምስጋና እንዲህ እንበላት፤‹‹ምንተኑ አዐስየኪ ዕሴተ፤በእንተ ኩሉ ዘገበርኪ ሊተ፤ማርያም ሠናይት ዘታፈቅሪ ምሕረተ፤ሶበሰ ተታአቀቢ ዘዚኣየ ኃጢኣተ፤ እምኢሐየዉኩ አሐተ ሰዓተ›› እያልን ለእርሷ በሚገባ ምስጋና እናመስግናት፡፡ ከዚህ የወጣ ሰዉ በመጀመሪያ እንደተመለከትነዉ ብርሂት ቀኝ ዐይኑን እንደገና እያሳወረ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ እኛስ ለባሕርያችንን መመኪያ እርሷን የሰጠንን እግዚአብሔርን ‹‹ብርሂት የቀኝ ዐይን ድንግል ማርያምን ›› በዚህ ዕለት የሰጠኸን፣ ከዚህ ዓለም የድንቁርናና የኃጢኣት ጨለማም የገላገልከን ክብር ምስጋና ለአንተ ይሁን፤ አንተ ለመረጥካትና ላከበርካት ለእናትህም ምስጋና ይድረሳት እያልን አፋችንን ሞልተን እናመሰግናለን፡፡ ቀይ ዕንቁ እምነት ገንዘባቸዉ ያልተሰረቀባቸዉ ወይም በአዉሬዉ ዲያብሎስ ያልተቧጨሩት ሁሉ አብረዉን ያመሰግናሉ፡፡ ቀኝ ዐይናችን ሆይ ዛሬም በአንቺ ብርሃን እናያለንና እናመሰግንሻለን፡፡ እንኳን አንቺን አባትሺን አብርሃምን የሚባርኩት እንደሚባረኩ ልጂሽ አስቀድሞ በሙሴ በኩል በኦሪት ነግሮናልና፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡