የሻጮችና የለዋጮች ወንበር የሞላው ቤተ መቅደስ
በሕግና ዕቅበተ እምነት አገልግሎት ማስተባበሪያ
መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
ጥንቱን ለልማዱ የቤተ መቅደስ መሠራት ምክንያቱ ሰዎችን ለመቀደስ፣ ሕያዊት ነፍስ የተሰጠቸው ሥጋዊ ደማዊ ፍጥረት ሁሉ ጸሎቱን አድርሶ መሥዋዕቱን አቅርቦ ከእግዚአብሔር ምሕረት ሊቀበልበት አልነበረምን? ‹‹ለዘለዓለም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይኖራሉ›› ብሎ የመረጠው የነገሥታት ንጉሥ የእግዚአብሔር ልዩ ሥፍራ ነው ቤተ መቅደስ፡፡ መቅረዙና ጠረጴዛው የመሥዋዕቱም ኅብስት ነበረበት፤ የወርቁ ማዕጠንት፣ ሁለንተናዋም በወርቅ የተለበጠች የኪዳን ጽላት፣ በውስጧም መናን የተሸከመችው መሶበ ወርቅና ክህነት የጸናባት የአሮን በትር እንዲኖሩ ታዝዞ ነበር፡፡ በምድራውያን ሰዎች መካከል እንደ ምሰሶ የሚቆመው ካህን ገብቶ የሚያጥንበት ይህ ቤተ መቅደስ ምንኛ የከበረ ነው? ለሰዎች ሁሉ ራዕይን አይቶ የሚነግራቸው ባለ ራዕይ ነቢይ የማይታጣበት፣ ሊቀ ካህናቱ የሚደገፈው ያቁም፣ ንጉሡ የሚደገፈው በለዝ የሚባሉት ምሰሶዎች የሚገኙበትም ነው፡፡ ያዕቆብ እንዳለው ይህ ቤተ መቅደስ የሰማይ ደጅ ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ (፩ኛ ነገ. ፱÷፫፣ ዕብ. ፱÷፪፣ ዘፍ. ፳፰÷፲፯)
እግዚአብሔር በሚያድርበት ስፍራ የሚኖሩ ብፁዓን ናቸው፡፡ ከምድር ወደ ሰማይ መውጫው በር ላይ እንዲያገለግሉ የተፈቀደላቸውም ንዑዳን ክቡራን ናቸው፡፡ ያዕቆብ በራዕይ አይቶ ‹‹ይህ ሥፍራ ምን ያስፈራል››ብሎ አስፈርቶ አስገርሞ ነገረን፡፡ ዘመኑ ደርሶ በተሠራ ጊዜም ካህናቱ ቆሞ ማገልገል እስኪሳናቸው ድረስ ቤተ መቅደሱን የእግዚአብሔር ክብር ሞልቶት ነበር፡፡ (፩ኛ ነገ. ፰÷፲፩)
ነገር ግን እንደዚያ የሚያስፈራ ክብር የነበረውን ያንን ቤተ መቅደስ የአይሁድ ካህናት በክብር እንዳይኖር የሌቦች ዋሻ የወንበዴዎችም ጋሻ አደረጉት፡፡ በመጨረሻም ናቡከደነፆር አቃጠለው፤ ናቡዛርዳን አፈረሰው፤ ባቢሎናውያን ሳይገባቸው ገብተው አረከሱት፤ መሠዊያውንም አፈረሱት፤ ኤልዛቤል በቤተ ጣዖት ለወጠችው፤ አክዓብ የሚስቱን የኤልዛቤልን ፈቃድ ለመፈጸም ሲል ችላ አለው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ጊዜው ሲደርስ በኤልያስ፣ በኤርምያስ አድሮ ክብሩን መለሰው፡፡ ሰይጣን አሁንም በምድር ላይ ለእግዚአብሔር ማደሪያ እንዲኖረው አይፈልግም፤ የሰዎችም ልብ የሚያርፍበት ሥፍራ እንዲኖር አይሻምና፡፡ ጽርዓዊው አንጥያኮስ መጥቶ ሊቀ ካህናቱን አልዓዛርን በእሳት አቃጥሎ አራት መቶ ሺህ እስራኤላውያንን አሳድዶ በመግደል የቀሩትንም አሳምኖ የዘሩባቤልን ቤተ መቅደስ ሥዕለ ፀሐይ አቆመበት፡፡ የአሳማ ሥጋንም መሥዋዕት አድርጎ አቀረበበት፡፡ እንደ ገና እግዚአብሔር ለቤቱ ይቀናልና መቃብያንን አስነሥቶ አደሰው፡፡ (የዮሐንስ ወንጌል አንድምታ ፲÷፳፪)
ይህን ሁሉ ለምን እንደምተርክ ታውቃላችሁ? የእግዚአብሔር መቅደስ በአሕዛብ እጅ ቢፈርስም በዘመነ ክርስቶስ የሆነውን ያህል ርኵሰት ግን አላጋጠመውምና እሱን ልብ እንድትሉልኝ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው በሆነበት ወራት የአገልግሎት ተራ ደርሷቸው ከእስራኤላዊነትም በላይ ሌዋዊነትን ከሌዋዊነትም በላይ ከአሮን ወገን የሆኑ አንዳንዶቹ ቤተ መቅደሱን ለክብሩ እንደሚገባ አልጠበቁትም ነበር፡፡ ንጉሡ ዳዊት ተመኝቶ ያልደረሰበትን፣ ሰሎሞን ከገባዖን በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ እግዚአብሔርን ያየበትን፣ ሐና ከኀዘኗ የተጽናናችበትን፣ ሳሙኤል ለክህነት የተመረጠበትን ይህን ቅዱስ ስፍራ ለፈቃደ ሥጋቸው ያደሩ በፍቅረ ንዋይ የሰከሩ ሰዎች ይዘው አበላሹት፡፡
በማስመሰል ጸሎት የመበለታቱን ገንዘብ የሚዘርፉበት፣ ወርቁን ለብር ብሩን ለወርቅ የሚለውጡበት፣ ርግቡን ዋኖሱን የሚሸጡበት፣ በሬና ላም የሚያሥሩበት ሆኗል፡፡ ፍርድ የሚጣመመው ጉቦ የሚበላው ከቤተ መንግሥት ይልቅ በክፉ ሰዎች የማይገባ ሥራ የሚሠራበት ይህ ቤተ መቅደስ ሆኖ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ሳለ ነው ቤተ መቅደሱን የሚቀድሰው ኢየሱስ ክርስቶስ የደረሰው፡፡ ገብቶ አየው የሻጮችና የለዋጮች ወንበር ሞልቶታል፤ ጸሎቱ ቀርቷል፤ መሥዋዕቱ ታጉሏል፤ ክህነት ዋዛ ፈዛዛ ሆኗል፡፡ ናቡከደነፆር ሳይመጣ፣ ናቡዛርዳንም ሳይኖር፣ ኤልዛቤል ሳትነሣ፣ አክዓብም ሳይበረታ፣ አንጥያኮስ ጦር ሳያነሣ ቤተ መቅደሱ በራሳቸው በካህናቱ እጅ ክብሩን ለቀቀ፡፡ ይሄ ይባስ! አሕዛብ ሳይመጡ ራሳቸው የአብርሃም የይስሐቅ ልጆች ካረከሱት የአሮን ልጆች ግብረ ክህነትን አቁመው የንግድ ቦታ ካደረጉት ማን ሊደርስለት ነው?
ደግሞ የሚገርመው ነገር አስመሳይነታቸው ነው፤ ‹‹ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛው ቀን እሠራዋለሁ›› ቢላቸው ይህን ቤተ መቅደስ ሠርቶ ለመጨረስ የወሰደው ጊዜ ዓርባ ዓመት ነው፡፡ አንተ ግን በሦስት ቀን እሠራዋለሁ ትላለህ ብለው ጌታን ከሰሱት፡፡ እነሱ አፍርሰውት ሳለ ልባቸው እያወቀው አፋቸው ግን ከንቱ ነገርን ይናገር ነበር፡፡ (ዮሐ. ፫÷፲፱)
ወገኖቼ ሆይ! ቤተ መቅደስ የሰማይ ደጅ ናት በዚህ ስፍራ እንድንቆም ዕድሉን ካገኘን ለቦታው እንደሚገባ ሆነን እንኑር እንጂ ኃጢአት እየሠራን እግዚአብሔርን እያስቀየምን ለምእመናን የሰማዩን ደጅ ለምን እንዘጋባቸዋለን?
በዚህ ቦታ ቆመው የሚጽናኑ ብዙዎች ናቸውና ሰዎች መጽናናትን እንዳያገኙ ቦታውን ለምን እናረክስባቸዋለን? የእግዚአብሔር ዐይኖች ያሉት በዚህ ቤተ መቅደስ ላይ ነውና ዐይኖቹ እያዩን ኃጢአት ብንሠራ መልካም ነውን?
የእግዚአብሔር ፊቱ ወደዚህ ነው፡፡ ዓለም በፊቱ አይደለችም፡፡ ይህ እኛ የቆምንበት ቤት ግን በፊቱ ነውና በዚህ ሥፍራ ታመው የተፈወሱ፣ አጋንንትን ድል የነሡ፣ ረክሰው የተቀደሱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ማርያም ለጌታ የቀባችው ሽቱ ያለው በዚህ ሥፍራ ነው፡፡ ቬሮኒካ መልክአ ትስብእትን ያየችበት፣ ፊቱን የጠረገበት ጨርቅ የሚታይበት፣ ታቦት ዘዶርም የምትገኝበት፣ የብርሃን አዳራሽ ይህ ቤተ መቅደስ ነው፡፡ ‹‹እንተ ደም ይውኅዛ›› ለዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ይፈሳት የነበረችውም ሴት ዳሳው የተፈወሰችበት ልብሱ፣ ሰብአ ሰገል የገበሩለት ሥረወጥ ቀሚሱ አይሁድ ዕጣ የተጣጣሉበት እጄጠባቡ፣ ለአራት መደብ አድርገው የተካፈሉት መጎናጸፊያው የሚገኘው በዚህ ይህ ቤተ መቅደስ ነው፡፡ እኛ እጅ ላይ መድረሱን አይታችሁ አታቃሉት፡፡ ሐዋርያት ጌታን የተገነዘበት ሰበኑን፣ የተወጋበት ጦሩን፣ የተሰቀለበት መስቀሉን፣ ዑራኤል ደሙን የቀዳበት ጽዋውን ያኖሩልን እዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ ነው፡፡
ጌታ በሥጋነት በደምነት የሚሰጥበት፣ ጴጥሮስ የሚሰብክበት ጽርሐ ጽዮናችን፣ ጳውሎስ የሚያስተምርበት አርዮስፋጎሳችን፣ እስጢፋኖስ ህሉና ሥላሴን አይቶ የሚያደንቅበት መንበረ ጸባዖታችን ይህ ቤተ መቅደስ ነው፡፡ ስለሆነም ሥጋዊ ፈቃዳችንን የምንፈጽምበት የንግድ ሥራ ወደ ቤተ መቅደስ እንዳይገባ ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡
አይሁድ ይህን ሲያደርጉ ቢያገኛቸው በጅራፍ እየገረፈ አስወጣቸው፡፡ የሚሸጡትንና የሚለውጡትንም ገለባበጠባቸው፡፡ በዚህም ለኃጢአት ምክንያት የሆናቸውን ሁሉ አስወገደላቸው፡፡ እኛም ቤተ መቅደስ በተባለው ሰውነታችን ውስጥ ተደብቀው ምክንያተ ኃጢአት እየሆኑ ያስቸገሩንን ፍትወታት እኩያትን በቃሉ ገርፎ ያርቅልን ዘንድ የቤተ መቅደስን ክብር ልንጠበቅ፣ ቤተመቅዱስን የሚቀድሰውን የክርስቶስን ትእዛዝ ልናከብር፣ ፈቃዱንም ልንፈጽም ይገባናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቤተ መቅደስን የሚቀድሳት ቤተ መቅደስ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ሥጋውን ደሙን ተቀብለን ቤተ መቅደስ የተባለ ሰውነታችንን ሁልጊዜ ከኃጢአት ተግተን መጠበቅ ይኖርብናል፡፡