‹‹የሱራፌል አምሳላቸው ቅዱስ ያሬድ››
እግዚአብሔር አምላክን ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ በመንበሩ ፊት ቆመው እንደሚያመሰግኑ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያለ በመላእክት ቋንቋ ፈጣሪውን በማመስገኑ እና ዜማውን ከእነርሱ በመማሩ በመጽሐፈ ስንክሳር ‹‹አምሳሊሆሙ ለሱራፌል፤ የሱራፌል አምሳላቸው›› ተብሏል፡፡ እርሱም፤ ‹‹ሃሌ ሉያ ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እመላእክት ግናይ እንዘ ይብሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር መልዐ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሓቲከ፤ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን! ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር፤ የምስጋናህ ስፋት ሰማይና ምድርን መላ፤ እያሉ ሲያመሰግኑ ከመላእክት የሰማሁት ምስጋና ምንኛ ድንቅ ነው?›› በማለት ዜማውን የተማረው ከመላእክት መሆኑን በድርሰቱ መስክሯል፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ግንቦት፤ ኢሳ.፮፥፫)
በ፭፻፭ ዓ.ም ሚያዝያ ፭ ቀን በአክሱም ከተማ ከአባቱ ከአብዩድ (ይስሐቅ) እና ከእናቱ ታውክልያ (ክርስቲና) የተወለደው ቅዱስ ያሬድ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ እናቱ ታውክሊያ ከአጎቱ ከአባ ጌዴዎን ዘንድ እንዲማር ብትወስደውም በመጀመሪያ እንዳሰበቸው አልሆነላትም፡፡ ለበርካታ ዓመታት ትምህርት ሊገባው እንዳልቻለና የመምህሩ ቁጣና ግርፍያ ስለበረታበት በወቅቱ ከመምህሩ ቤት ሸሽቶ መጥፋቱን ቅዱሳት መጻሕፍት ይገልጻሉ፡፡
ቅዱስ ያሬድ በተጓዘበት መንገድ ማይክራ በሚባል ስፍራ ዛፍ በማየቱ በሥሩ ለማረፍ ቁጭ እንዳለ ወደ ላይ በተመለከበት ጊዜ ትል ወደ ዛፉ ሲወጣ ትኩረቱን ሳበው፡፡ ትሉ ወደ ላይ መውጣት ባለመቻሉ ያለመሰልቸት መሞከር ነበረበት፤ ከብዙ ጥረት በኋላ ዛፉ ላይ መድረሱን በመመልከቱ ቅዱስ ያሬድ በትሉ ትጋት ተገረመ፡፡ ይህን ጊዜ የከበደው ምሥጢር እንደሚገለጽለት በማመን ወደ መምህሩ ተመልሶ ይቅርታ ጠይቆ ትምህርቱን መቀጠል ችሏል፡፡ እግዚአብሔር አምላክም የ፹፤፩፣ የሊቃውንት እንዲሁም ሌሎች ቤተ ክርስቲያን የተቀበለቻቸውን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ገለጸለት፡፡ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ ዲቁና መዓርገ ከማግኘቱም ባሻገር መምህር ጌዲዬን ሲሞቱ በእርሳቸው ምትክ ማሰተማሩን ቀጥሏል፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነናም ቅዱስ ያሬድን ከኤዶም ገነት ሦስት አዕዋፍ በሰው አንደበት አናገሩት፡፡ በ፭፻፴፬ ዓ.ም. ሕዳር ፮ ቀን፤ ወደ ሰማይ ከእነርሱ ጋር ተነጥቆ ቅዱሳን መላእክቱ እግዚአብሔርን ልዩ በሆነ ጣዕመ ዝማሬ ሲያመሰግኑ ሊሰማ ችሏል፡፡ አዕዋፉም የሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ሱራፌልን ማኅሌት አስተማሩት፤ ወደ ምድርም በተመልሰ ጊዜ በአክሱም ጽዮን ውስጥ በታላቅ ቃል አመስግኗል፡፡ ዜማውም እንዲህ የሚል ነበር፤ ‹‹ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ፤ ለአብ ምስጋና ይገባል፤ ለወልድ ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል፡፡ የጽዮን ደገኛዋ ሰማይን ፈጠረ፡፡ዳግመኛም እንዴት መሥራት እንዳለበት የድንኳንን አሠራር ለሙሴ አሳየው፤ አስተማረው›› ቅዱስ ያሬድ ይህን ዜማ አርያም ብሎ ጠራው፡፡
በ፭፻፴፰ ዓ.ም. ታህሳስ ፩፤ በዕለተ ሰኞ ምህላ ይዞ እሰከ ታህሳስ ፮፤ ቀዳሚት ሰንበት ጨረሰ፤ ይህች ዕለትም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል አንደተሰቀለ ሆነ ከቅዱሳን መላእክት ጋር የተገለጸለት ነበር፡፡
ቅዱስ ያሬድ ጌታ የተገለጸለትን የመጀመሪያውን ሳምንት ‹ስብከት› ብሎ ሰይሞታል፤ በሳምንቱም እንደገና በብርሃን አምሳል ስለተገለጸለት ያን ዕለት ‹ብርሃን› ብሎ ሰየመው፤ በሶስተኛው ሳምንት እንዲሁ በአምሳለ ኖላዊ ስለተገለጸለት ‹ኖላዊ› ብሎ ሰየመው፡ በመጨረሻም ሳምንት በአምሳለ መርዓዊ ሲገለጽለት ዕለቱን ‹መረዓዊ› ብሎ ሰይሞታል፡፡
ቅዱስ ያሬድ የደረሳቸው የዜማ መጻሕፍት ድጓ፤ ጾመ ድጓ፤ ምዕራፍ፤ ዝማሬና መዋሥዕት ናቸው፡፡ ከእነርሱም ውስጥ ትልቁ ድጓ ነው፤ በውስጡ የዮሐንስ፤ አስተምህሮና ፋሲካም ይዟል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በንባባት ብቻ ይቀደስባቸው የነበሩትን ፲፬ቱ ቅዳሴያት በዜማ ደርሷል፤ ዝማሬውም በ፭ ተከፍለውም ኅብስት፤ ጽዋዕ፤ መንፈስ፤ አኮቴትና ምሥጢር ተብለው ተሰይመዋል፡፡
‹‹በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ከዓመት እስከ ዓመት ድረስ በየክፍለ ዘመኑ በክረምትና በበጋ፣ በመጸውና በጸደይ፣ በአጽዋማትና በበዓላት፣ በሰንበታት እንዲሁም በመላእክት በዓል፣ በነቢያትና በሐዋርያት፣ በጻድቃንና በሰማዕታት እና በደናግል በዓል የሚደረስ ቃለ እግዚአብሔር በሦስት ዜማዎች ማለትም በግእዝ፣ በዕዝልና በአራራይ ደረሰ፡፡ የሰው ንግግር፣ የአዕዋፍ፣ የእንስሳትና የአራዊት ጩኸት ሁሉ ከእነዚህ ከሦስቱ ዜማዎች አይወጣም፡፡›› (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ግንቦት)
ቅዱስ ያሬድ ከብሉይና ከሐዲስ እንደዚሁም ከሊቃውንትና ከመነኮሳት የተውጣጣውን መንፈሳዊ ድርሰቱን በዘመኑ ከነበረው ከንጉሥ ገብረ መስቀል ፊት ቆሞ ዘምሯል፡፡ በዚያን ዕለትም ንጉሡ በድምፁ በመማረኩ የተነሣ ልቡናው በተመስጦ ተሠውሮበት የሚያደርገዉን ባለማወቅ የቅዱስ ያሬድን እግር በጦር ወጋው፤ ከቅዱስ ያሬድ እግር ደምና ውኃ ፈሰሰ፤ ነገር ግን ማኅሌቱን እስኪፈጽም ድረስ ሕመሙ አልተሰማውም ነበር፡፡
ንጉሡም ያደረገዉን ሁሉ ባወቀ ጊዜ ደነገጠ፤ ጦሩንም ከእግሩ ነቅሎ ‹‹ስለፈሰሰው ደምህ ዋጋ የምትፈልገዉን ሁል ለምነኝ›› እያለ ተማጸነው፡፡ ቅዱስ ያሬድም ‹‹ላትከለክለኝ ማልልኝ›› ብሎ ቃል ካስገባው በኋላ ወደ ገዳም ሔዶ ይመነኩስ ዘንድ እንዲፈቅድለትና እንዲያሰናብተው ለመነው፡፡ ንጉሡም ከእርሱ እንዲለይ ባይፈልግም መሐላዉን ማፍረስ ስለከበደው እያዘነ አሰናበተው፡፡
ቅዱስ ያሬድ በአክሱም ጽዮን ቤተ መቅደስ በታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ፡- ‹‹ቅድስት ወብፅዕት ስብሕት ወቡርክት ክብርት ወልዕልት አንቀጸ ብርሃን መዐርገ ሕይወት፤ ፈጽሞ የከበርሽና የተመሰገንሽ፣ ከፍ ከፍም ያልሽ፣ የብርሃን መውጫ የሕይወት ማዕረግ የሆንሽ›› እያለ አንቀጸ ብርሃን የተባለውን የእመቤታችን ምስጋና እስከ መጨረሻው ድረስ ደረሰ፡፡ ይህንን ጸሎት ሲያደርስም አንድ ክንድ ያህል ከመሬት ከፍ ብሎ ይታይ ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ ሰሜን አገር ሔዶ (ሰሜን ተራሮች አካባቢ) በጾምና በጸሎት ተወስኖ ሥጋውን እጅግ እያደከመ ኖሮ ገድሉን በዚያው ፈጸመ፡፡ በገድለ ቅዱስ ያሬድ እና በመጽሐፈ ስንክሳር የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እንደዘገቡት በተወለደ በ፸፭ ዓመቱ በሰሜን ተራራ ውስጥ ደብረ ሐዊ ከሚባል ገዳም ግንቦት ፲፩ ቀን ዐርፏል፡፡ ሰው ‹ዐረፈ› ሲባል ሞትን ብቻ ሳይሆን እንደነ ሄኖክ ከዚህ ዓለም በሕይወት እያሉ ተሠውሮ መኖርንም ያመለክታል፡፡ ‹‹ገድሉን በሰሜን አገር ፈጸመ›› የሚለውም ታሪካዊ መረጃ ደግሞ መሠወሩን ብቻ ሳይሆን መሞቱንም ሊያመለክት ይችላል፡፡ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን መምህራን እንደተናገሩት ስለመቀበሩ ምንም ዓይነት ማስረጃ አልተገኘም፡፡ ቅዱስ ያሬድ ተሠወረ እንጂ ሞተ ተብሎ አይነገርለትም፡፡ ለዚህም ማስረጃ እርሱ በተሠወረበት ተራራ እስከ አሁን ድረስ የከበሮ (የማኅሌት) ድምፅ ይሰማል፤ የዕጣን መዓዛ ይሸታል፡፡ ይህም ቅዱሱ ከሰው ዓይን ተሠውሮ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንደሚገኝ አመላካች ነው፡፡(መጽሐፈ ስንክሳር፣ ግንቦት ፲፩)
እግዚአብሔር አምላክም ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጥቶታልና በአባታችን በቅዱስ ያሬድ ጸሎት ይምረን እና በረከቱም ከእኛ ጋር ለዘለዓለም ይኖር ዘንድ ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡