የሩስያው ፕሬዝዳንት ለሀገራቸው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምስጋና አቀረቡ

ግንቦት 3/2004 ዓ.ም.

በስንሻው ወንድሙ

የሩስያ ፕሬዝዳንት ዴሚትሪ ሜድቬዴቭ የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሀገሪቱ ዜጎች ዘንድ መንፈሳዊ ሥርዐት እንዲጐለብት ለምታደርገው እንቅስቃሴ ከሁለት ሳምንት በፊት ምስጋና ማቅረባቸውን ዘ-ጋርዲያን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡

 

የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ሚያዝያ 7 ባደረጉት ንግግራቸው የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱ ሕዝቦች ባሕልና ወጋቸውን ከሃይማኖት ሥርዐት ጋር ጠብቀው እንዲቆዩ ለአደረገችው አስተዋጽኦ ምስጋና ማቅረባቸውን ዘገባው አመልክቶ ፕሬዝዳንቱ «ይህን የሐሴት ቀን ከእናንተ ጋር በማሳለፌ ደስታ ተሰምቶኛል፤ በሀገሪቱ ውስጥ ሃይማኖታዊ ሥርዐት እንዲሰፍን ለምታደርጉት እንዲሁም በሕዝቡ ዘንድ ሰላም እንዲሰፍንና መጪውን ትውልድ በበጐ ሥነ ምግባር ለመቅረጽ ለምታካሂዱት እንቅስቃሴ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እወዳለሁ» ሲሉ መናገራቸውንም ዘግቧል፡፡

 

ፕሬዝዳንቱ አክለው የበዓሉ መከበርና ሥርዐቱን የጠበቀ መሆን ለሰላምና ለመቻቻል እንዲሁም መንፈሳዊ እሴቶችን ከማጎልበት አንፃር አርአያ የሚሆን ተግባር ነው ማለታቸውን የዘገበው ጋዜጣ የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱ ሕዝቦች ጠባቂ ናት ያሉት ፕሬዝዳንቱ ላለፉት በርካታ መቶ ዓመታት ጠብቃ ያቆየችውን የሀገር አንድነትን የመጠበቅ ሓላፊነት አሁንም አጠናክራ እንድትቀጥል መጠየቃቸውን ዘገባው አስፍሯል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከቤተ ክርስቲያኗ የተሰጠ ምላሽ አልተካተተም፡፡