የመምህር አካለ ወልድ የሐዲስ ኪዳን የመጻሕፍት ትርጓሜ ት/ቤት የበግ ማድለብ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊደረግ ነው
መጋቢት 9 ቀን 2007 ዓ.ም
ከደሴ ማእከል
የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ከ20 በላይ የወረዳ ቤተ ክህነት ሲኖሩት፤ እነዚህም ብዛት ያላቸው ጥንታውያን ገዳማትና አድባራትን እንዲሁም የአብነት ት/ቤቶችን አቅፎ የያዘ ነው፡፡ ሀገረ ስብከቱ ካሉት ጥንታውያን የአብነት ት/ቤቶች የቦሩ ሥላሴ የመምህር አካለ ወልድ የሐዲስ ኪዳን የመጻሕፍት ትርጓሜ ት/ቤት አንዱ ነው፡፡
ት/ቤቱ በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በደሴ ወረዳ ቤተ ክህነት ቦሩ በሚባል ቀበሌ በቦሩ ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ ከደሴ የ10 ኪ.ሜ መንገድ ነው፡፡ ይህ ትምህርት ቤት በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ የቀለም ቀንድ ተብለው በሚጠሩት በዐራት ዓይናው በመ/ር አካለ ወልድ የተቋቋመ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የጠቀሙ ሊቃውንትን ሲያፈራ የነበረ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት 16 የሚደርሱ የሐዲሳት ትርጓሜ መጻሕፍት ተማሪዎችን ተቀብሎ በሀገረ ስብከቱ፣ በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል እና በጎ አድራጊ ምእመናን ድጋፍ እየተደረገላቸው እያስተማረ ይገኛል፡፡ ት/ቤቱ በአቅም ማነስና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ለብዙ ዓመታት ተዘግቶ የነበረ ሲሆን፤ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ቀናኢ በሆኑት በብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከፍተኛ ጥረት ካለፉት 9 ዓመታት ወዲህ እንደገና ተከፍቶ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መፋጠን የሚያግዙ ተተኪ አገልጋዮችን እያፈራ ይገኛል፡፡
ት/ቤቱ ቀድሞ ለብዙ ዓመታት እንዲዘጋ ያደረገውና አሁንም አገልግሎቱን እየተፈታተነው ያለውን መሠረታዊ የኢኮኖሚ ችግር ቀርፎ የተማሪዎችን ቁጥር እና የጉባኤያቱን ዓይነት በመጨመር ለቤተ ክርስቲያን ተተኪ አገልጋዮችን በማፍራት ሐዋርያዊ አገልግሎትን ለማጠናከር ይቻል ዘንድ በማኅበረ ቅዱሳን የደሴ ማእከል የቅዱሳት መካናት ማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ክፍል ከበጎ አድራጊዎች በተገኘ ድጋፍ የበግ ማድለብ ፕሮጀክት ቀርጾ ከደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ጋር የፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የውል ሰነድ መጋቢት 3 ቀን 2007 ዓ.ም ተፈራርሟል፡፡
በእለቱ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ቆሞስ አባ ገብረ ሥላሴ በላይ እና የሀገረ ስብከቱ ሰራተኞች የተገኙ ሲሆን፤ ገንቢና ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ሀሳቦች ተነስተው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ከሀገረ ስብከት፣ ከማኅበረ ቅዱሳን ደሴ ማእከል፣ ከት/ቤቱ፣ ከደብሩ ሰበካ ጉባኤና ከምእመናን የተውጣጡ ስድስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቋሟል፡፡
በአሁኑ ወቅት የመገልገያ ቁሳቁሶች ተገዝተው የበጎች ማድለቢያና ማቆያ ቤት መሠራቱን የደሴ ማእከል ጸሐፊ ዲ/ን ሰለሞን ወልዴ በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡
እንደ ጸሐፊው ገለጻ የፕሮጀክቱ ሙሉ ሥራ በሁለት ዙር የሚጠናቀቅ ሲሆን የመጀመሪያውን ዙር ቀሪ ሥራዎች በአጭር ቀናት ውስጥ በማጠናቀቅ የበግ ማድለቡ ሥራ እንዲጀመር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡የፕሮጀክቱን የመጀመሪያ ዙር ሥራ አጠናቆ አገልግሎት ለማስጀመርም ብር 135,993 /አንድ መቶ ሰላሳ አምስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ሶስት/ ብር እንደሚያስፈልግ ለማወቅ ተችሏል፡፡