ዝክረ ልሳነ ሰብእ ቀዳማዊ

1. ግእዝ ምስለ ቤተ ክርስቲያን

ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ዘመናት የፈተና ገፈታ ቀማሽ በመሆን፣ ልጆቿን እያበረታታች ለሀገራዊ ሀብት መጠበቅም እስከ ሰማዕትነት እያበረከተች በየአድባራቱና ገዳማቱ ጠብቃ አሳድጋ ለዚህ ትውልድና ዘመን ካቆየቻቸው ዕሤቶች አንዱ ግእዝ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ቤተ መዘክር፣ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤት፣ ቤተ ክርስቲያን ግምጃ ቤት፣ ቤተክርስቲያን የሥልጣኔ ማዕከል፣ ቤተ ክርስቲያን ከተማ ሀገር በመሆን ስታገለግል ቆይታለች፡፡

ስለዚህም ነው በሀገሪቱ የታሪክና የመዛግብት ጥናት ላይ የረጅም እድሜ ልምድ ያላቸው ፕሮፌሰር ሪቻድ ፓንክረስት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱ ባህል ጠባቂ ናት ሲሉ በውዳሴ ዘጽድቅ የሚመሰክሩላት፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የግእዝን ሥነ ጽሑፍ ሆነ ቋንቋ እንደሚከተለው ጠብቃ አስረክባናለች፡፡

በየጉባኤያቱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ማዕከለ ትምህርት በመሆን ለዘመናት ሕዝቡን አገልግላለች፡፡ በራሷ ባሕላዊ ሥርዓተ ትምህርት ዜማውን ቅኔውን ትርጓሜ መጻሕፍቱን በዚሁ ቋንቋ ስታስተላልፍ ቆይታለች፡፡ እነዚህም ትምህርቶች የሚከናወኑበትን ትምህርት ቤት ከቤተክርስቲያኗ ዐውደ ምሕረት ዙሪያ በተዘጋጁ የመቃብር ቤቶች፣ ዙሪያውን  በተሠሩ ጎጆች አልያም በዙሪያዋ በተተከሉ ዐጸዶች አትሮንሷን ዘርግታ፣ አዘጋጅታ፣ ዜማውን አሰምታ፣ ግሱን አስገስሳ ምስጢሩን አብራርታ አስተላልፋለች፡፡ ይህንንም ስታደርግ ለደቀመዛሙርቱ ከሰንበቴው ከደጀ ሰላሙ ረድኤት እያሳተፈች ነው፡፡

በሊቃውንት የሊቃውንት፣ የፍቅር ሀገር፣ ሕይወተ ክርስትና፣ ፍሬ በረከት ስላላቸውና ዘወትር ቃለ እግዚአብሔርን በመናገር፣ ደቀ መዝሙር ሲያጠፋ ሲያርሙ ሲሳሳት ሲያስተካክሉ፣ የተበላሸውን ሲያቀኑ ባሳለፉት ድካም ሀብተ ታሪክን አውርሰዋል፡፡ የደረሷቸውን ቅኔያት፣ የጻፏቸውን መጻሕፍት ዜና መዋዕላቱን ጭምር ሲደጉሱ፣ ሲኮትቱ የተሻለ ቅርጸ ፊደልን ሲያወርሱን ወዘተ ነፍሳቸውን ከሥጋቸው አብልጠው በመኖራቸው ነው፡፡ በመሆኑም ዳዊቱን እየደገሙ፣ መጻሕፍትን እየተረጎሙ ያብራሩበትም በዚሁ ልሳን ነው፡፡ በዚህ ሳይወሰኑ ሌትም ቀንም እንቅልፍ አጥተው ከማኅሌቱ፣ ከሰዓታቱ፣ ከጉባኤ ቤቱ ሳይለዩ ስለ ነገዋ ቤተ ክርስቲያን በመጨነቅ ያስተማሩትን ደቀ መዛሙር «ኦ ወልድየ ጽንዐ በጸጋሁ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘኅዱር ላዕሌከ በመንፈስ ቅዱስ» ልጄ ሆይ አድሮብህ ባለው በመንፈስ ቅዱስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋው ጽና ምከር አስተምር ብለው የቃል አደራ በመስጠት በየአህጉሩ ሲያሰማሩ ቆይተዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ጸሎታቸውን ለሀገር በሱባኤ ሲያደርሱ ኖረዋል፡፡

ደቀ መዛሙርቱ ሀገረ ሙላዳቸውን በመተው ደበሎ ለብሰው፣ ቁራሽን ተማምነው፣ አኮፋዳቸውን ከሰሌን አዘጋጅተው፣ ዳዊታቸውን በትከሻቸው አንግበው በትምህርተ ቤተክርስቲያን ዘመናቸውን ያቆዩ ተማሪዎችም ባለውለታ መሆናቸው የማይዘነጋ ነው፡፡ እድሜ ሳይገድባቸው ገና በልጅነት እድሜያቸው ጥሬ እየቆረጠሙ በውርጭ እየተነሡ ሀገር ለሀገር በመዞር ምስጢር ሲሸምቱ የአባቶቻቸውን ትውፊት በቃል በመጽሐፍ ያስተላለፉ ደቀ መዛሙርቱም እነዚሁ ናቸው፡፡ እነዚህም በሌሊት እየተነሡ ከመምህራቸው እግር ሥር ሆነው በብርዱ፣ በቁሩ ሲቀደሱ ሲያስቀድሱ፣ የሌሊቱን ዝናብ ታግሰው ሳይታክቱ በመምህራቸው ጓሮ በትጋት የተማሩባቸውን ጉባኤያት እያስታወሱ ሲያስተላልፉ ኖረዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ያለኀፍረት ራሱን ዝቅ አድርጎ በምእመናን ደጃፍ ዐረፍ ብሎ የተገኘውን እየተዘከሩ ወደ ጉባኤው ሲመለሱ እያዜሙ፣ ቅኔውን እየቆጠሩ፣ ወንዙን እየተሻገሩ፣ ተራራውን እየወጡ፣ እየወረዱ የአራዊቱን ድምጽ እየሰሙ፣ ተፈጥሮን እየቃኙ፣ ምስጢርን እያዩ ያዩትንም በቅኔው እየቀመሙ ለነባር ሲያስተላልፉ ቆይተዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ለክብረ በዓሉ ያለውን ቀለም በአፋፍ ላይ ሆነው እየቀጸሉ በጎጆአቸው ሌሊቱን ሲያዜሙ በራሳቸው ቋንቋ «አዛኘን» እስኪ በልልኝ  በመባባል እየተሳሳሉ ለዘመናት ትምህርቱን አስተላልፈዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን መምህራቸውን በእርሻ፣ በማሳ፣ በሥራ እየረዱ ነው፡፡

 
ምዕመናን ለሃይማኖታቸውና ለሀገራቸው ባላቸው ፍቅር ሃይማኖታቸውን ከቤተ ክርስቲያን አጣምረው ኖረዋል፡፡ በባህል ግንባታውም ተሳትፈዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ተማሪንም ከመሶባቸው ማዕድ ሳይሰስቱ እየመገቡ ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡ ቤተክርስቲያን እንድትገለገል ጧፉን መጋረጃውን አሥራቱን ሲያስገቡ ባደረጉት አስተዋፅኦ የቤተ ክርስቲያኗ ሀብቷ እንዲህ ሊተላለፍ ችሏል፡፡ ዋዜማ እየደገሱ ቁመት ሲያስቆሙ ዕድሞ ሲያስከብሩ ኖረዋል፡፡

2. የግእዝ ቋንቋ እንዲያድግ ለምን አስፈለገ?

ባህል በቋንቋ ይለካል፡፡ እምነቶች ሥነ ሕዝብ ማኅበራዊ መሠረቶች /ዐምዶች ልምዶች ዕውቀቶች ሁሉ በቋንቋ አሉ፡፡ በአደጋ ላይ ያለ ቋንቋ ማለትም በአደጋ ላይ ያለ ዕውቀት አሳሳቢ፤ ባህል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ስለ አገባብ የሚታወቀው ዕውቀት ካፀፀ መሠረት የለሽ ድካምን ያስከትላል፡፡

በመሆኑም ቋንቋ የኅብረተሰብእ /የአንድ ሕዝብ አካል ነው፡፡ ስለ ሕይወት ባህል ልምድ የሚፈስ ዕውቀት ሁሉ ትርጉም የሚኖረው በራስ ቋንቋ በሚገኝ ዕውቀት እንጂ የተጻፈን በመቀበል አለመሆኑ ደግሞ የራስ ቋንቋን ማወቅ ወሳኝ መሆኑን ያሳያል፡፡ ልሳናት በአባቶች ቅድመ አያቶች ቀሩ ማለት የልጆች ሀገራዊ አንደበታቸው ማንነት የሚጠብቁበት ኃይል ጠፋ ማለት ነው፡፡ የእኛ ማንነትና ታሪካችን ያለው የተቆራኘው በብዙ መንገድ ከቋንቋችን /ከግእዝ ጋር ነውና ያለበትን ደረጃ ልንመረምርና ልናስተውለው ይገባል፡፡ ሌላው ይቅርና መለያችን ልዩነታችን እንኳን በቋንቋችን ሰዋስው አገባብ ሊታወቅ ይችላል፡፡ ቋንቋችን ካልተጠበቀ የሚተላለፈው ዕውቀት ትውፊት ባለበት ይቆማል፡፡ አብሮ አስሮ የያዘቸውን እውቀቶች ፍልስፍናዎች ሁሉ ይዞ ይጠፋል፡፡ ነገር ሁሉ በአዲስ ይጀምራል፡፡ ሥር የሌለው በአሸዋ የተገነባ ሕንፃን ይመስላል፡፡ የሌሎች የባህል ጎርፍ በመጣ ጊዜ በቀላሉ ይወድቃል፡፡ ቋንቋን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን እንደገና ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ በስደት፣ በዝርፊያ በዓለም ዙሪያ በየቦታው ያሉትን የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች ሊመረምሩ የሚችሉ ልጆች ሊተኩ ያስፈልጋል፡፡ የተበረዘውን ማቅናትና የጠፋውን ታሪክ መፈለግ፣ የተለየንን የጥበብ ምንጭ ፍለጋ መውጣት መውረድ ያስፈልጋል፡፡ ሊጠፉ የተቃረቡትንም መጠበቅና ብሎም ዘመኑ ባፈራቸው መሳሪያዎች ተጠቅሞ በመቅረጽ ለትውልዱ ማስተላለፍ ትልቁ ኃላፊነት ይኸው ነው፡፡

አፍሪካውያን ዛሬ ቋንቋቸውን ለመጠበቅ የሚያደክማቸው ለብዙ ዘመናት በተሰላ እቅድ ሥር ተጽዕኖ በመውደቃቸውና በሌላኛው የቅኝ ግዛት መንገድ ማለፋቸው ነው። እንዳልነው ይህ ችግር ደግሞ ዛሬም ከአፍሪካ ምድር ስላልተወገደ በአደጋ ላይ የነበሩ ዕውቀቶች ሁሉ ጠፍተዋል፡፡ መፍቀርያነ ባህል አፍረንጅም በመብዛታቸው ነባሩ/ የአከባቢው መንፈሳዊውም ሆነ ቁስ አካላዊው ዕውቀት እየተረሳ መጥቷል፡፡ ይህንን እየተረሳ ያለ ሀብት ደግሞ ለመጠበቅ ልምዱ ያላቸው ወላጆችና ሽማግሌዎች አስረካቢ ሕፃናት ተረካቢ ሊሆኑለት ይገባል፡፡ እንግሊዘኛቸውን ሲናገሩ በማበላሸታቸው የሚስቁ ይቅርታ የሚጠይቁትን ወጣቶችን ልብ አማርኛን ግእዝን ግን በማበላሸታቸው ግን ይቅርታ የማይጠይቁትን አእምሮ ሊያጠቁት ይችላሉ፡፡ በዚያውም ላይ የውጪውን ቋንቋ በመጠቀም የአንደበታቸው አርአያነት ብቻ ሳይሆን መልዕክቱ የተዛባ እየሆነ መጥቷል፡፡