ዜና ዕረፍት
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ በቀድሞው አጠራር ጎንደር ክፍለ ሀገር በአሁኑ በደቡብ ጎንደር ዞን በአንዳቤት ወረዳ ልዩ ስሙ አረጊት ኪዳነ ምሕረት ገዳም አካባቢ ከአባታቸው ከብላታ ፈንታ ተሰማና ከእናታቸው ከወ/ሮ ለምለም ገሠሠ በ ፲፱፻፴ ዓ.ም ተወለዱ፡፡
ዕድሜያቸው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ በአካባቢው ከሚገኙት ከመሪጌታ ላቀው ንባብና ዳዊት ከተማሩ በኋላ በአጭቃን ኪዳነ ምሕረት ደብር ምዕራፍና ጾመ ድጓ ተምረዋል። ከዚያም ትምህርታቸውን ለማስፋፋት ወደ ጎጃም ክፍለ ሀገር ሂደው ጐንጂ ቴዎድሮስ ገዳም ከመሪጌታ ወርቁ ሁለት ዓመት፤ ወደ ዋሸራ መንክር ኃይላ ቅድስት ማርያም በመሄድ ስመ ጥር ከነበሩት ከታላቁ ሊቅ ከመሪጌታ ማዕበል ፈንቴ ሁለት ዓመት፣ በጠቅላላው አራት ዓመት በመማር የቅኔ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡
ከዚያም ወደ ትውልድ ሀገራቸው ተመልሰው በደብረ ታቦር አውራጃ ልዩ ስሙ አጋጥ ጽዮን ደብር ከመሪጌታ ሙጬ ላቀ የምዕራፍ፥ የጾመ ድጓና የድጓ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በነበራቸው ከፍተኛ የትምህርት ፍላጐት ወደ አቋቋም ቤት በመግባት መነጒዘር ኢየሱስ በሚባለው ደብር ከመሪጌታ ሚናስ ለሁለት ዓመታት ያህል የአቋቋም ትምህርታቸውን ተምረዋል፡፡ በመቀጠል ቁት አቡነ አረጋዊ ደብር ከመሪጌታ ውብአገኝ ዝማሬ መዋሥዕት ተምረዋል። ከዚያም ከጥንቱ መምህራቸው መሪጌታ ሙጬ ላቀ ዘንድ እንደ ገና የድጓ ትምህርታቸውን በመከለስ ጽፈውና አመልክተው ከጨረሱ በኋላ፤ በቀድሞ አጠራር በጋይንት አውራጃ በታይ ጋይንት ወረዳ በምትገኘው ቅድስት ቤተ ልሔም የድጓ ትምህርት ማስመስከሪያ ወደ ሆነችው በመሄድ ለአራት ዓመታት ቆይተው የድጓ ትምህርታቸውን በሚገባ አጠናቀውና አስመስክረው በመምህርነት ተመርቀዋል።
ከዚህ በኋላ ቅዱስነታቸው ከነበራቸው የትምህርት ፍላጎት የተነሣ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቅዳሴና በማኅሌት እያገለገሉ ትርጓሜ ሐዲሳትንና አቡሻኽርን ተምረዋል። ዘመናዊ ትምህርታቸውን በቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ ተከታትለዋል። በተጨማሪም ለመምህራን የተዘጋጀውን የስብከት ዘዴ ትምህርት ለሁለት ዓመታት ተምረው በሠርተፊኬት ተመርቀዋል።
በ ፲፱፻፵፬ ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል የጎንደር ክፍለ ሀገር ሊቀ ጳጳስ መዐርገ ዲቁና ተቀብለዋል። ቅዱስነታቸው ሥርዓተ ምንኩስናን ከመምህርነት ጋር አጣምሮ ለመያዝ ያላቸው መንፈሳዊ ፍላጎት ከፍ ያለ ስለ ነበረና ቤተ ክርስቲያንን በሙሉ ኃይልና በሙሉ ጊዜ ለማገልገል የምንኩስና ሕይወት የበለጠ ተመራጭ መሆኑን ስላመኑበት፥ በደሴተ ጣና ካሉት ጥንታውያን ገዳማት አንዱ በሆነው በምኔተ አቡነ ሂሩተ አምላክ ዳጋ ቅዱስ እስጢፋኖስ አንድነት ገዳም ከመምህር ኃይለ ማርያም በ ፲፱፻፷፩ ዓ.ም መዐርገ ምንኩስናን፣ በዚሁ ዓ.ም.ደግሞ ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ የቅስና መዐርግ ተቀብለዋል።
ቅዱስነታቸው በነበራቸው ከፍተኛ መንፈሳዊ ሕይወት በባሕር ዳር አውራጃ ልዩ ስሙ በጋሾላ አቡነ ተጠምቀ መድኅን አንድነት ገዳም ገብተው የገዳሙን ሥርዓት እያጠኑ ለገዳማውያን በታዘዘው መሠረት በተግባረ እድ፣ በትምህርት፣ በጸሎተ ማኅበር፣ ለእንግዶች ማረፊያ ቤት በመሥራትና አቅመ ደካሞችን በመርዳት ለሁለት ዓመታት ገዳሙን አገልግለዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ከፍተኛ መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን በዋናነት የጀመሩት በማስተማር ሲሆን፤ የድጓ ትምህርታቸውን ካስመሰከሩ በኋላ ወደ ተወለዱበት ገዳም አረጊት ኪዳነ ምሕረት ሂደው ለሰባት ዓመታት ያህል ድጓ አስተምረዋል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቅዳሴና በማኅሌት ሰፊ አገልግሎት ሰጥተዋል። የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ ሆነው በአስተዳደሩበት ወቅት ለቤተ ክርስቲያኑ አገልጋዮች መኖሪያ ቤት፣ ለሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችም የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከነሙሉ ድርጅቱ አሠርተው ቤተ ክርስቲያኑ የነበረበትን ችግር እንዲቃለል አድርገዋል። ተጀምሮ የነበረውም የቤተ ክርስቲያኑ ሕንጻ እንዲጠናቀቅና በአካባቢው የሚገኙ ምእመናን በሰበካ ጉባኤ ተደራጅተው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ባላቸው በቂ የቤተ ክርስቲያን ዕውቀት፣ ባሳዩት መንፈሳዊ አገልግሎትና የሥራ ወዳድነት ቤተ ክርስቲያናችን ጥር ፲፫ ቀን ፲፱፻፸፩ ዓ.ም. ባደረገችው የ፲፫ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ በቅዱስ ሲኖዶስ፣ በካህናትና በምእመናን በከፍተኛ ድምፅ ተመርጠው የኡጋዴን አውራጃ ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ተሾመዋል።
በዚህም አውራጃ፡-
- በሱማሌ ጦርነት ፈርሰው የነበሩትን አብያተ ክርስቲያናት በማሠራትና በማሳደስ፣
- በጦርነቱ ምክንያት የተሸበረውንና የተደናገጠውን ሕዝብ በማጽናናት በሃይማኖቱ እንዲፀና፣ ሀገሩን እንዲወድ በማስተማር ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን ፈጽመዋል፡፡
ከዚያም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ በቀድሞ አጠራር ወደ ጎንደር ክፍለ ሀገር ተዛውረው የጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሁነው ተመድበዋል። ቅዱስነታቸው የጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሁነው ሲመደቡ ሀገረ ስብከቱ የራሱ ቢሮ አልነበረውም። የሊቀ ጳጳሱ መኖሪያ አርጅቶ ነበር። በሊቀ ጵጵስና ዘመናቸው የመንበረ ጵጵስናውን ሕንጻ ከማሳደሳቸውም በተጨማሪ ከአስራ ሰባት በላይ ክፍሎችና አንድ ሁለገብ አዳራሽ አስገንብተው መንበረ ጵጵስናው በክፍለ ሀገሩ ከሚገኙት የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የላቀ ደረጃ እንዲኖረው አድርገዋል። በወቅቱ እንዲህ ያለ የተሟላ መንፈሳዊ አስተዳደር ያለው ሀገረ ስብከት ስላልነበረ የእርሳቸው ሥራ በታላቅ አክብሮት ይነሣ ነበር።
ቅዱስነታቸው የጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ ባስመዘገቡት የሥራ ብቃት አምስት ጊዜ በብሔራዊ ደረጃ ከ፲፱፻፸፭ እስከ ፲፱፻፸፱ ዓ.ም. ድረስ በተከታታይ በአንደኛ ደረጃ ተሸልመዋል። ቅዱስነታቸው ቤተ ክርስቲያናችን ካፈራቻቸው ሊቃውንት አንዱ፥ ይልቁንም ታላቅ ጥረትና ትዕግሥት የሚጠይቀው የድጓ ሊቅና መምህር በመሆናቸው፤ በየቦታው ወድቀው ያለ ደጋፊ የነበሩትን የአብነት መምህራንን ያስታወሱና ከፍተኛ የሆነ የአብነት ትምህርት ቤት መስፋፋት እንዲከናወን አድርገዋል። በመሆኑም በክፍለ ሀገሩ ያሉ የአብነት መምህራን የወር ደመወዝ እንዲያገኙ በማድረግ ሊቃውንቱን አበረታተዋል። የአብነት ትምህርት ቤቶችና የሰንበት ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፉ የአራቱ ጉባኤ መምህራንና ተማሪዎች በቂ ቀለብ እንዲያገኙ አድርገዋል። በሀገረ ስብከታቸው በሚገኙ የዜማና የመጻሕፍት ትምህርት ቤቶች የሚማሩና የሚያስተምሩ መምህራንና ተማሪዎች የቀለብ ችግር ሲገጥማቸው፤ በእያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሁለትና ከሁለት በላይ ተማሪ በመደበኛነት እንዲያገለግልና ቀለብ እንዲያገኝ በማድረግ ለዘመናት ጎልቶ ይታይ የነበረውን ችግር አቃለዋል። በተጨማሪም ምእመናንን በሰበካ ጉባኤ በማደራጀትና በማጠናከር፣ በሀገረ ስብከቱ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሰበካ ጉባኤን በማቋቋምና በማጠናከር፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶችንም በማስፋፋት፣ ቅርሳ ቅርሶች በእንክብካቤ እንዲያዙ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ መንፈሳዊ መጽሔቶችና ጋዜጦች ለሕዝበ ክርስቲያን እንዲደርሱ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ መመሪያ ደንብ ቃለ አዋዲ በተግባር እንዲተረጐም አድርገዋል። በጎንደር ክፍለ ሀገር የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታደሱና በርከት ያሉ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ አድርገዋል። በተለይም በቀድሞው አጠራር በደብረ ታቦር አውራጃ በእስቴ ወረዳ፡-
፩.የአረጊት ኪዳነ ምሕረትን ቤተ ክርስቲያን በግላቸው አሠርተዋል።
፪. በዚሁ ወረዳ ውስጥ የምትገኘውን ደብረ ምሕረት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን የግል ገንዘባቸውን በማውጣት ቆርቆሮ እንድትለብስ አድርገዋል።
፫. መንፈሳዊ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ፣ የካህናት ማሠልጠኛ እንዲቋቋምና ካህናት በተግባረ እድ የሚሠለጥኑበት ትምህርት ቤት እንዲከፈት አድርገዋል።
ቅዱስነታቸው ምንም መተዳደሪያ ያልነበራቸው የአብነት መምህራን ሊቃውንት በክህነት ከሚያገኙት የግል ገንዘባቸው ደመወዝ እንዲቆረጥላቸው በማመቻቸት፤ ሳይሰለቹ ሳይቸገሩ ሙያቸውን ለትውልድ እንዲያስተላልፉ፣ የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞችም በትምህርት ሙያቸውን እንዲያሻሽሉ አድርገዋል። ከዚህም ሌላ ለአንድ የዜማ መምህር፣ ለአንድ የቅዳሴ መምህር፣ ለአንድ ዕቃ ቤት ጠባቂ በድምሩ ለሦስት ሰዎች ከራሳቸው ደመወዝ በመክፈል ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲያበረክቱ አድርገዋል።
ቅዱስነታቸው በየጊዜው በሚያሳዩት መልካም የሥራ ውጤት በ፲፱፻፸፪ ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ የሊቀ ጵጵስና ማዕርግ ተቀብለዋል፡፡ በቅዱስነታቸው ሊቀ ጵጵስና ዘመን ፵፫ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት ተተክለዋል፡፡ ፻፹፭ አብያተ ክርስቲያናት ተሠርተዋል። የልማት ሥራዎችን በተመለከተ የድጓ ምስክር በሆነችው በታላቋ ቅድስት ቤተልሔም፣ በእስቴ ወረዳ ሊጋባ ቅዱስ ሚካኤል የሞተር ወፍጮ በማስተከል፣ ለካህናትና ለመምህራን ደመዛቸውን እንዲችሉ በማድረግ፣ የተራቆቱ ቦታዎች በደን እንዲሸፈኑ በማስተባበር በርካታ የልማት ሥራዎችን ሠርተዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ቅድስት፣ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያንን ለ12 ዓመታት በፓትርያርክነት ሲመሩ የቆዩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ዐረፍተ ዘመን ገቷቸው ግንቦት ፳፰ ቀን ፲፱፻፹ ዓ.ም. በሞተ ሥጋ መለየታቸውን ተከትሎ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ መንበር ለመሰየም በተደረገው ምርጫ ነሐሴ ፳፪ ቀን ፲፱፻፹ ዓ.ም. በዕጩነት ከቀረቡት ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት መካከል፥ በቅዱስ ሲኖዶስ የተዘጋጁትን መመዘኛዎች በማሟላትና ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በመሆን ተመርጠዋል።
በወቅቱ በመራጭነት የተሳተፉት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ የአጠቃላይ መንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ ከየሀገረ ስብከቱ የሰበካ ጉባኤ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተወካዮችና ከቀደሙት የአንድነት ገዳማትና አድባራት ተወካዮች በድምሩ ፻፱ መራጮች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ መካከል ፻፩ ድምፅ አግኝተው በከፍተኛ ድምፅ በመመረጥ ነሐሴ ፳፱ ቀን ፲፱፻፹ ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው ተሹመዋል። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በሀገር ቤት በመንበራቸው የቆዩት ለሦስት ዓመታት ሲሆን የተቀሩትን ዓመታት በስደትና ከስደት ተመልሰው በሀገር ቤት ነው። በእነዚህ ጊዜያት የተለያዩ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ አከናውነዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ሁነው የተሾሙበት ወቅት ሀገራችን ታላቅ ፈተና ላይ የነበረችበት ወቅት ነው። በአንድ በኩል አገሪቱን የሚመራው መንግሥት የሚከተለው ርእዮተ ዓለም እግዚአብሔር የለሽ መሆኑ ቤተክርስቲያን ራሷን በራሷ እንድትደግፍ ግድ ብሎአት ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ጦርነት ታላላቆቹንና ጥንታውያን ገዳማትና አድባራት የጦርነት ቀጠና በማድረጋቸው፥ ምእመናንና ካህናት ከባድ አደጋ ላይ ነበሩ። በዚህ ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ቤተክርስቲያን ራሷን በራሷ የምትችልበትን መንገድ በከፍተኛ ደረጃ እንድታስብበት፥ ካህናቱም ከመንፈሳዊው አገልግሎት ጎን ለጎን በተለያዩ የሙያ ሥራዎች አገራቸውን የሚጠቅሙበትን ልምድ እንዲቀስሙ፥ ባለፉት ቅዱሳን አባቶች የተጀመረው የሰበካ ጉባኤ ማደራጀትና የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ እንቅስቃሴ በሰፊው እንዲከናወን አድርገዋል። ቅዱስ ፓትርያርኩ በዚህ ሳይወሰኑ፥ በወቅቱ መንግሥትና በሰሜኑ ክፍል በነበሩ ታጣቂዎች መካከል ይካሄድ የነበረውን የእርስ በእርስ ጦርነት በሰላም እንዲቋጭ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል። ይኸውም በሀገር ውስጥ ያሉትን የሃይማኖት መሪዎችን በማስተባበር የሰላም ጥሪ ለሁለቱም አካላት አቅርበዋል። በሥልጣን ላይ ለነበረው መንግሥት ቅዱስነታቸው በአካል ተገኝተው የሰላሙን መልእክት ያቀረቡ ሲሆን፤ በበረሃ ለነበሩት ታጣቂ ኃይሎች ደግሞ በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ተወካይ እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል እንዲደርስ አድርገዋል።
ቅዱስነታቸው ታላላቆቹ የትግራይ ገዳማትና አድባራት እንዲሁም የትግራይ ክፍለ ሀገር ሕዝብ በችግር ላይ በነበረበት ወቅት ቤተ ክርስቲያን የበኩሏን እርዳታ እንድታደርግ መመሪያ ሰጥተዋል። ቅዱስነታቸው የታላቂቱ ገዳም የርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵሱም ጽዮን ካህናት እጅግ ከባድ ችግር ላይ በነበሩበት ወቅት፥ ለቤተ ክርስቲያኒቱ እድሳት በሚል ስም ለካህናቱ እገዛ እንዲውል አንድ መቶ ሺ ብር፣ አንድ ተሳቢ የጭነት መኪና እና አንድ ፒክ አፕ መኪና እንዲሰጥ አድርገዋል። በዚህም ምክንያት በወቅቱ ከነበረው መንግሥት ጋር ለማጋጨት፥ «ገንዘቡን የላኩት ለአኵሱም ጽዮን ሳይሆን ለወያኔ ነው» በሚል ከፍተኛ ፈተና ተነሥቶባቸው ነበር።
ቅዱስነታቸው በወቅቱ ሀገራችን ምንም እንኳ በልዩ ልዩ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ተወጥራ የነበረች ብትሆንም፤ በተለያዩ አህጉረ ስብከቶች ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ፥ የሰላም ግንባታ ማስተማሪያ በማዘጋጀት፣ ሰባክያነ ወንጌልን ከማሰማራት ጋር የገንዘብና የንዋየ ቅድሳት ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ቅዱስነታቸው በዘመነ ፕትርክናቸው ከስደት በፊት የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማስፋፋትና ለማጠናከር በመንፈሳዊ ትምህርታቸውና ዕውቀታቸው፣ በምንኩስና ሕይወታቸው የተመሰከረላቸውን ስድስት ኤጲስ ቆጶሳት በ1983 ዓ.ም. በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በአንብሮተ እድ ሾመዋል።
በዚሁ የፕትርክና ዘመናቸው በውጭ ሀገራት፦
- በምዕራብ ጀርመን ልዩ ልዩ ከተሞች፤
- በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል።
- በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ በአካል በመገኘት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲጠናከር አድርገዋል።
- አስቀድሞ በሀገረ እስራኤል እና በኢትዮጵያ መካከል ተቋርጦ የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዳግም እንዲቀጥል አድርገዋል።
- በግሪክ አቴንስ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ በሀገሪቱና በኢትዮጵያ እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናቱ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር አድርገዋል።
በውጭ ሀገር ባደረጉዋቸው ሐዋርያዊ ጉዞዎች በየሀገራቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማጽናናት ቃለ ቡራኬና ቃለ ምዕዳን በመስጠት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲጠናከር አድርገዋል።
የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ የስደት ታሪክ በ፲፱፻፹ ዓ.ም. በሀገራችን ኢትዮጵያ ከተደረገው የመንግሥት ለውጥ ጋር የተያያዘ ነው። በወቅቱ በትረ ሥልጣኑን የተረከበው ገዢው የኢሕአዴግ መንግሥት ከቅዱስነታቸው ጋር መሥራት እንደማይፈልግ በተለያዩ መንገዶች የሚያደርገው ፖለቲካዊ ጫና እየተባባሰ በመምጣቱና ቅዱስነታቸው በሕይወት እያሉ አዲስ ፓትርያርክ እንዲሾም በማድረጉ ወደ ሀገረ ኬንያ በመሰደድ፤ አስከፊው የስደት ሕይወት የሚጠይቀውን ሁሉ እየተጋፈጡ በዚያ ለአምስት ዓመታት ብዙ ጸዋትወ መከራ ተቀብለዋል።
በመቀጠልም ቅዱስነታቸው በፈቃደ እግዚአብሔር ወደ ሰሜን አሜሪካ ያቀኑት ወደ ዋሺንግተን ሲያትል ነበር። ከዚያም በካናዳ፣ በዋሽንግተን ዲሲ፣ በአትላንታ፣ በዴንቨርና በኦሃዮ ግዛቶች ማረፊያቸውን እያደረጉ፤ በመላው ሰሜን አሜሪካ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን አከናውነዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በአብዛኛው ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በጸሎት፣ በጾም (በሃያ አራት ሰዓት አንድ ጊዜ ብቻ በመመገብ) እና ለምእመናን ትምህርተ ወንጌል፣ ቃለ ምዕዳን እና ቃለ ቡራኬ በመስጠት ነበር። በተለይም ቅዱስነታቸው ለስብሐተ ማኅሌት በነበራቸው ልዩ ፍቅር፥ የማኅሌት አገልግሎት በሚኖር ጊዜ ከሁሉ ቀድመው በመገኘት በፍጹም ትጋትና ተመስጦ ሥርዓተ ማኅሌቱን ይመሩ ነበር።
ቅዱስነታቸው በስደት በነበሩባቸው ዓመታት፦
- በሰሜን አሜሪካ ከ፻፹ በላይ አብያተ ክርስቲያናት እንዲመሠረቱ በማድረግ፤
- በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራልያና ኒውዚላንድ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት እንዲመሠረቱ በማድረግ ቤተ ክርስቲያን እንድትሰፋ አድርገዋል።
- በእነዚህ አህጉረ ስብከት ያለውን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማጠናከር ጥር ፲፫ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳትን በዋሽንግተን ዲሲ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል። ጥር ፳ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. በካናዳ ቶሮንቶ መንበረ ብርሃን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አራት ኤጲስ ቆጶሳትን በአንብሮተ እድ ሹመዋል። እንዲሁም ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም. በኦክላንድ ካሊፎርኒያ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ካቴድራል ሰባት ኤጲስ ቆጶሳትን በአንብሮተ እድ ሹመዋል።
- በጊዜው በሀገር ውስጥ ከነበረው ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር የነበረው አለመግባባት የበለጠ እንዳይሰፋ በማሰብ ቅዱስነታቸው አንድም ጊዜ በጉዳዩ ዙሪያ ለጋዜጠኞች መግለጫ ባለመስጠት ከባቴ አበሳና የትዕግሥት ባለቤት መሆናቸውን አስመስክረዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከሚወዷት ቅድስት ሀገራቸው ኢትዮጵያና ከሚወዱት ሕዝባቸው ተለይተው ለሃያ ስድስት ዓመታት በሐዋርያዊ አገልግሎትና በጸሎት ቆይተዋል። በእነዚህ ዓመታት ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት፣ ስለ ሀገራቸው ሰላም፣ ፍትሕና ደኅንነት ያለማቋረጥ በመጸለይና ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ዘወትር ተስፋ በማድረግ አምላካቸውን ይማፀኑ ነበር፡፡
በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ተቋቁሞ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ሲሠራ የነበረው የሰላምና የአንድነት ጉባኤ ሦስት የሰላምና የአንድነት ጉባኤያትን ቢያከናውንም በወቅቱ ፈቃደ እግዚአብሔር ስላልሆነ ሊሳካ አልቻለም ነበር፡፡ አራተኛው የሰላምና አንድነት ጉባኤ ከመካሄዱ በፊት በእግዚአብሔር ፈቃድ በሀገራችን ኢትዮጵያ የመጣውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ፤ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾሙት ክቡር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር የቤተ ክርስቲያን አንድነት መመለስ ቁልፍ ተግባር መሆኑን በማመን፥ በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል ዕርቀ ሰላም እንዲወርድ ለቅዱስ ሲኖዶስ ባቀረቡት ማሳሰቢያ መነሻነት በጉዳዩ ላይ የመከረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ዕርቀ ሰላሙ እንዲከናወን በብፁዐን አባቶች የሚመራ ልዑክ ሰይሟል። በዚህም መነሻነት በቅዱስ ሲኖዶስ መካከል የነበረው ልዩነት በአራተኛው የሰላምና የአንድነት ጉባኤ ተወግዶ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ሲታወጅ፤ ሐምሌ ፳፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. ክቡር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ወደ ሀገረ አሜሪካ በተጓዙበት አውሮፕላን ቅዱስነታቸውን በስደት ከነበሩት ብፁዐን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ይዘው ተመልሰዋል። በዚህም ክቡር የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት መመለስ ያበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በቤተክርስቲያኒቱ ታሪክ ሁልጊዜ ሲታወስ ይኖራል። ቅዱስነታቸው በመንበረ ፕትርክናቸው ሁነው ከዚህ ዓለም ድካም እስካረፉበት ቀን ድረስ ስለ ሀገራቸው፣ ስለ ቤተ ክርስቲያንና ስለ ሕዝብ አንድነት ሲጸልዩ፣ ሲባርኩ ቆይተዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ፡-
- ሰባት ዓመት በድጓ መምህርነት፣
- ለበርካታ ዓመታት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቅኔ ማኅሌትና በቅዳሴ አገልግሎት፣
- በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በመሆን፤
- በሊቀ ጵጵስና ከ ፲፱፻፸፩ ዓ.ም. ጀምሮ ፲፱፻፹ ዓ.ም. ድረስ በኡጋዴንና በጎንደር አህጉረ ስብከት፣
- በፕትርክና ከ፲፱፻፹ እስከ ፳፻፲፬ ዓ.ም. ቤተ ክርስቲያንንና ሕዝበ ክርስቲያንን ለበርካታ ዓመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የተሰጣቸውን ሐዋርያዊ ኃላፊነትና አደራ በታላቅ ብቃትና በመንፈሳዊ ተጋድሎ ተወጥተዋል። በዚህም በቤተክርስቲያናችን የመንበረ ፕትርክና ታሪክ ለ፴፸ ዓመታት ሐዋርያዊና አባታዊ አገልግሎት በመስጠት ረጅሙ አገልግሎት ሁኖ ተመዝግቧል።
- ቅዱስነታቸው እጅግ በጣም ትጉህና ጠንካራ ለእውነት የቆሙና ላመኑበት ጉዳይ እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት ለመክፈል የማይሳሱ፣ ከልጅነታቸው ጊዜ ጀምሮ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸውን በመንፈሳዊ ተልእኮ፣ በንጽሕናና በቅድስና ያገለገሉ፣ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታቸውን ቅድስት ሀገራቸውን ኢትዮጵያን የሚወዱ፣ ሥጋዊ ምቾት በሚበዛበት የምዕራቡ ዓለም ኑረው ለሥጋዊ ጥቅም ያልተንበረከኩ፣ በምናኔና በልግስና ሕይወት የኖሩ ቅዱስ አባት ነበሩ።
- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ከስደት የተመለሱት ሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ በሚታሰብበት ዕለት መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። አሁንም ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ በሚዘከርበት ዕለት የካቲት ፳፭ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፈው ወደማያልፈው ዓለም ተሻግረዋል።
የቅዱስነታቸው አስከሬን በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተወስዶ ጸሎተ ፍትሐት ሲደረስበትና ሲቀደስበት ካደረ በኋላ ፡-
- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
- በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት፣ የፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ተወካዮች፤
- ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፥
- የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የየመምሪያው፣ የየድርጅቱና የመንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ኃላፊዎች፣
- የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣
- ከመላው የአኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ እህጉረ ስብከት የተወከሉ ኃላፊዎች፤
- መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ዲፕሎማቶችና የውጭ አህጉር ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፤
የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት መጋቢት ፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም. ሥርዓተ ቀብራቸው በአዲስ አበባ መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በክብር ተፈጽሟል።
እግዚአብሔር አምላካችን የብፁዕ ወቅዱስ አባታችንን ነፍሳቸውን ለወዳጆቹ ቅዱሳን፣ ጻድቃንና ሰማዕታት ባዘጋጀው መካነ ዕረፍት በክብር ያሳርፍልን፤ እኛንም ያጽናን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
መጋቢት ፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም.
አዲስ አበባ