ቤተ ክርስቲያን የምንላት ወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍጹምና ከማይነገር ፍቅሩ የተነሣ ሰው እስከ መሆን፣ ሰው ሆኖም በዚህ ዓለም ከኃጢአት በስተቀር እንደ ሰው መኖርን፣ ከዚያም በቀራንዮ ቅዱስ ሥጋውን እስኪቆርስላትና ክቡር ደሙን እስኪያፈስላት ድረስ የደረሰላትና የመሠረታት የምእመናን አንድነት (ጉባኤ) ናት፡፡ “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላእለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት” የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በወንጌል መሠረትነት በኢየሱስ ክርስቶስ ራስነት በምእመናን አካልነት የተመሠረተች ጉባኤ ናት፡፡
ቤተ ክርስቲያን ስንል የዚህ ዓለም ተጋድሏቸውን በድል አጠናቅቀው ወደ እግዚአብሔር የሄዱ ቅዱሳን (ሐዋርያት፣ ሰማዕታት፣ ሊቃውንት፣ …) እና ገና በዚህ ዓለም በተጋድሎ ላይ ያሉት የምእመናን አንድነት (ጉባኤ) ናት፡፡ በሰማይ ያለችው ቤተ ክርስቲያን (ጉባኤ) የዚህ ዓለም ጣጣቸውን ጨርሰው የሄዱ፣ ድል አድርገው የድል አክሊላቸውን ለመቀበል እርሱ የወሰነውን ጊዜ የሚጠባበቁ ቅዱሳን ኅብረት ስለሆነች አትናወጽም፤ ስለሆነም ሊቃውንት ይህችን ቤተ ክርስቲያን ድል አድራጊዋ ቤተ ክርስቲያን (Church Triumphant) ይሏታል፡፡ ገና በዚህ ዓለም በጉዞና በፈተና ላይ ያለችውን የአንዲቷ ቤተ ክርስቲያን አካል የሆነችውን ጉባኤ (ቤተ ክርስቲያን) ደግሞ ገና በተጋድሎ ላይ ያለች ቤተ ክርስቲያን (Church Militant) ይሏታል፡፡
በዚህ ዓለም ያለችው ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያት በባሕር ላይ በታንኳ እየሄዱ ሳለ ጌታችን አብሯቸው በመካከላቸውና በታንኳው ውስጥ እያለ፣ ነገር ግን በኃይለኛ ማዕበል ትናወጥ እንደ ነበረችው ታንኳ በተለያዩ ፈተናዎች ትናወጻለች፡፡ አንዳንድ ጊዜም በውስጧ ያለው ጌታ የማይሰማና የተዋት፣ መከራዋን እያየ ዝም ያላት፣ ባለቤት የሌላት እስክትመስል ድረስ በውስጧ ያሉና በተለያዩ ነገሮች ተጨንቀው የሚያማርሩና የሚያዝኑ ልጆቿም ሰሚ የሌላቸው የሙት ልጆች እስኪመስሉ ድረስ ባለቤቷ ኢየሱስ ክርስቶስ ዝም ይላል፡፡ ሐዋርያትንም “ስንጠፋ አይገድህምን?” እስኪሉ ያደረሳቸው ይህ ነበር፡፡ ማቴ. 8፡23-27
የአንዲቷ ቤተ ክርስቲያን አካል የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አምስተኛ ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ማረፋቸው ይታወቃል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የእርሳቸውን ነፍስ ከቅዱሳን ጋር ይደምርልን እያለች ተተኪውን ስድስተኛውን ፓትርያርክ የመምረጥ ከባድ ሥራ ደግሞ ከፊቷ ተደቅኗል፡፡ ይህ ሥራ ሂደቱና ውጤቱ ቢያንስ ቢያንስ ለሚመጡት የተወሰኑ ዓመታት በቤተ ክርስቲያናችን አካሄድ ላይ የራሱ የሆነ ተጽእኖ የሚኖረው መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማም በዚህ ታላቅ ወሳኝ ወቅት ላይ እያንዳንዳችን ምን ብናደርግ እንደሚሻል አጠንክረን እንድናስብ ሕሊናችንን ለማነሣሣት ያህል ነው፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የባለቤቷ የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ ስለሆነች ጠባቂዋና ተንከባካቢዋ እርሱ ራሱ ነው፡፡ ምንም እንኳ እርሱ በሚያውቀውና በተለያዩ ምክንያቶች እንድትፈተን ቢፈቅድም እንድትጠፋ ግን አይተዋትም፡፡ ይህ ማለት ግን በውስጧ ያሉ አባላት በጥርጥርና በልዩ ልዩ ፈተናዎች አይሰናከሉም ማለት ግን አይደለም፡፡ ምንም ቢሆን ግን ቤተ ክርስቲያን የራሱ የክርስቶስ አካሉ እንደ መሆኗ ራሷ የሆነ እርሱ ለአካሉ ለምእመናን የሚያስፈልገውን ያውቃል፣ ያዘጋጃል፣ ይሰጣል፡፡ ለዚህ ነው በጸሎተ ኪዳናችን ላይ “ዘይሁብ መርሐ ርቱዐ ለቤተ ክርስቲያን – ለቤተ ክርስቲያን ቅን መሪ የሚሰጥ” የተባለው፡፡
ነገር ግን ችግር የሚሆነው ቤተ ክርስቲያን የማን መሆኗን ዘንግተን ባለቤቷና ራሷ የሆነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ ራሱ የሚሆናትን ቅን መሪ እንዲሰጣት ከመጠየቅና ከመማጸን አልፈን እኛው ራሳችን መሪ እንስጥሽ ወደሚል ዝንባሌና አስተሳሰብ ስንሄድ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው እንደየ እውቀቱና አመለካከቱ ለክርስቶስ ሙሽራ ለሆነችው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን “እንዲህ ቢሆን፣ እገሌ ቢሆን፣ . . . ” ወደሚል ነገር መምጣት በሽታውን ሳይረዳ እንዲሁ በይመስላል መድኃኒት እንደሚያዝ ሰው መሆን ነው፡፡ በሽታውን ሳይመረምሩና ለመረዳት ጥረት ሳያደርጉ እንዲሁ በግምት፣ በአውቀዋለሁ ባይነትና በግዴለሽነት የሚታዘዘውን እንዲህ ያለውን መድኃኒት መውሰድ ምናልባትም ካለመውሰድ በባሰ ጤናን ሊያውክና ሕማምንም ሊያባብስ ይችላልና፡፡
ታዲያ መሥራቿና ባለቤቷ ኢየሱስ ክርስቶስ አካሉ ለሆነችው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ቅን መሪ እንዲሰጣት የእኛ ድርሻ ምን ቢሆን ይሻል ይሆን? ምንስ እናድርግ?
1. መሪ የመስጠቱን ሥራ ለራሱ ለእግዚአብሔር እንስጠው – እኛ ሳንሆን ራሱ ይምረጥልን
እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ መሪያቸውና ንጉሣቸው እግዚአብሔር ሆኖ በተለያዩ መሳፍንት አማካይነት ያስተዳድራቸው ነበር፡፡ መሳፍንቱም የባለ ሥልጣን ወግ ማዕረግ የሌላቸው ከሕዝቡ እንደ አንዱ ሆነው የሚስተዳድሩ፣ ጦርነት ሲሆንና አስፈላጊ በሚሆኑ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ብቻ የሚመሩ ነበሩ፡፡ ከሙሴ አንስቶ እሰከ ሳሙኤል ዘመን ድረስ ለ450 ዓመታት በዚህ ዓይነት ሁኔታ እየተመሩ ኖሩ፡፡ ሳሙኤልም ምስፍናና ክህነቱን ደርቦ ሕዝቡን አንደ ካህንነቱ ከእግዚአብሔር ጋር እያገናኘ፣ እንደ መሳፍንነቱ ደግሞ አስተዳደራዊ የሆኑ ጉዳዮቹን ያሰዳድራቸው ነበር፡፡ የሐዋ.13፡20-21
እነርሱ በዚህ ሁኔታ እየኖሩ ሳለ በአካባቢያቸው የሚኖሩ የተለያዩ አሕዛብ ደግሞ የራሱ የሆነ የንግሥና ሥርዓት፣ አፋሽ አጎንባሽ፣ ሠረገላና ሠራዊት፣ ሽቶ ቀማሚዎች፣ ወጥ ቤቶችና እንጀራ አበዛዎች ያሏቸው፣ ሕዝቡን የሚያስገብሩ ነገሥታት ነበሯቸው፡፡ እስራኤላውያን በአሕዛብ በመቅናት ንጉሣቸው እግዚአብሔር መሆኑ ቀርቶ እንደ ሌሎቹ ጎረቤቶቻቸው ከመካከላቸው አንዱን እነዲያነግሥላቸው በሳሙኤል በኩል ጠየቁ፡፡ በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው፡-
“በእነርሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን እንጂ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ስማ፡፡ ከግብጽ ካወጣኋቸው ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ትተው እንግዶች አማልክት በማምለካቸው እንደ ሠሩት ሥራ ሁሉ እንዲሁ በአንተ ደግሞ ያደርጉብሃል፡፡ . . . ለሕዝቡም በእናንተ ላይ የሚነግሠው የንጉሡ ወግ ይህ ነው ብለህ ንገራቸው፡- ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሰረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፣ . . . ሎሌዎቻችሁንና ገረዶቻችሁን ከከብቶቻችሁና ከአህዮቻችሁም መካከል መልካሞቹን ወስዶ ያሠራቸዋል፡፡ ከበጎቻችሁና ከፍየሎቻችሁ አሥራት ይወስዳል፤ እናንተም ባሪያዎች ትሆኑታላችሁ፡፡ በዚያም ቀን ለእናንተ ከመረጣችሁት ከንጉሣችሁ የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር አይሰማችሁም፡፡” 1 ሳሙ. 8፡10-18
እንደ ልመናቸው ንጉሥ ሰጣቸው፣ ሳኦልን አነገሠላቸው፡፡ ሆኖም እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደ ነገራቸው ብዙም ሳይቆይ ንጉሦቻቸው ለሕዝበ እስራኤል ዋናው የጥፋታቸው መሪዎች በመሆን የጥፋታቸውን ጎዳና ደኅና አድርገው ጠርገውላቸዋል፡፡ በንጉሥ ሰሎሞን ኃጢአት ምክንያት በልጁ በሮብአም ዘመን አንድ የነበረው ሕዝብ ከሁለት ተከፈለ፤ አሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ተብሎ በሰሜን፣ ሁለቱ ነገድ ደግሞ በደቡብ የይሁዳ መንግሥት ተብሎ በ928 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ዳግመኛ አንድ ላይሆኑ ተለያዩ፡፡
ቀጥሎም የአሥሩ ነገድ ንጉሥ የነበረው ኢዮርብዓም በግዛታቸው በስሜንና በደቡብ ጫፍ ላይ በዳንና በቤቴል ጣዖት አቁሞ ከዚያ በፊት ይደረግ እንደ ነበረው ሕዝቡ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ በታቦተ ጽዮን ፊት በቤተ መቅደሱ መሥዋዕት አቅርቦ አምላኩን እግዚአብሔርን አዘክሮ እንዳይመለስ በዚያው በሰሜኑ ግዛት ብቻ ተገድቦ እንዲቀር ለማድረግ ሲል ባቆማቸው ጣዖታት ሕዝቡን እግዚአብሔርን ከማምለክ ጣዖት ወደ ማምለክ እንዲያዘነብል አደረገው፡፡ ከዚሁም ጋር ንጉሣቸው ኢዮርብዓም እንደ ሕጉ መሠረት ካህናትን ከሌዋውያን ሳይሆን ሌዋውያን ካልሆኑት መካከል ለራሱ የሚመቹትን ካህናት ናቸው ብሎ መረጠ፣ በዓል የሚከበርበትን ቀን ለወጠ፣ በአጠቃላይ በኦሪቱ የተሰጠውን ነገር ሁሉ ገለባበጠው፡፡
እስራኤላውያን አስቀድሞ የንጉሥ አንግሥልን ምርጫቸው ምን እንደሚያስከትል በግልጽ እንደ ተነገራቸው ሆነባቸው፡፡ የሰሜኑ ግዛት የአሥሩ ነገድ ነገሥታት ኢዮርብዓም በጀመረው ከእግዚአብሔር የመለየትና ጣዖት የማምለክ የጥፋት ጎዳና እየገፉበት ሄዱ፡፡ ከዚያም በኋላ እነ አክአብና ኤልዛቤል ክህደቱና ኃጢአቱ፣ ግፉና ዓመጹ መሥፈሪያውን ቶሎ እንዲሞላ እያቻኮለው ሄደ፡፡ በዚያ የጥፋት ቁልቁሊት በፍጥነት በመቀጠል የእስራኤል መንግሥት ለሁለት በተከፈለ በ210 ዓመት (በ718 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ) በአሶራውያን ተማርከው ተወሰዱ፡፡ 2 ነገ. ምዕ. 17 ከዚያ በኋላ የአሥሩ ነገድ ነገር የውኃ ሽታ ሆኖ ቀረ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አሥሩ ነገድ መማረክ ይነግረናል እንጂ ከዚያ በኋላ የት እንደ ደረሱና ምን እንደ ሆኑ አይነግረንም፡፡ በመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ከምርኮ ስለ መመለሳቸው የተጻፈላቸው በኋላ የተማረኩት ሁለቱ ነገድ ናቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ከተነገሩና ምሥጢራቸው ካልተፈታ ታሪኮች አንዱ ይህ የአሥሩ ነገድ ጉዳይ ነው፡፡ እንግዲህ ያ የወደዱትና ጓጉተውና ሽተው የለመኑት የንጉሥ አንግሥልን ጥያቄ ነገር ፍጻሜያቸው እንዲህ አሳዛኝ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በዚሁ ንጉሥ የማንገሥ ጉዳይ ነቢዩ ሳሙኤል ከእግዚአብሔር ፊት በተናቀው በሳኦል ፋንታ የሚቀባውን ሊፈልግ ወደ ቤተ ልሔም ሄዶ ወደ እሴይ ቤት ገብቶ በዚያ የነበሩትን የእሴይን ልጆች ተራ በተራ ሲያልፉ ዓይኑ ኤልያብ ላይ አርፎ ነበር፡፡ ኤልያብ በሰው አስተሳሰብ መልከ መልካምና ተክለ ቁመናው የሚስብ ስለነበር ነቢዩ ሳሙኤል እርሱን ሲመለከት “በእውነት እግዚአብሔር የሚቀባው በፊቱ ነው” አለ፡፡ እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፡- “ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፣ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው፡፡ ሌሎቹም የእሴይ ልጆች እነ አሚናዳብ፣ ሣማን፣ … በፊቱ አለፉ፡፡ ሆኖም እነዚያ ሁሉም “ይህን ደግሞ እዘለግታ አትይ” የሚል ተግሣጽ አከል ነገር የተናገረው ለዚህ ነበር፡፡ እንግዲህ እንዲህ ያሉ ታላላቅ አባቶች እንኳ እግዚአብሔር ያዘጋጀውንና የመረጠውን ለማወቅ ይህን ያህል የሚቸገሩና ለዚህ ጥሪ የማይሆኑ ብዙ ሰዎችን አጣርተው (በፊታቸው አሳልፈው) መተው ያለባቸው ከሆነ ለእኛማ ምን ያህል ከባድ ይሆን?
ይህ ማለት እኛ መሥራት ያለብንን ሥራ መሥራት የለብንም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ቤተ ክርስቲያንን በአባትነት የሚመራ፣ ለመንጋው ታማኝ የሆነና መንጋውም የሚወደውና የሚያፈቅረው፣ ምንደኛ ያይደለ እረኛ፣ ጌታ ሳይሆን አገልጋይ፣ ለራሱ ሥልጣንና ክብር ሳይሆን ለእግዚአብሔር ክብር የሚቀና፣ ውስብስብ የሆነውን ዓለም በመስቀል ተደግፎ የሚሻገርና የሚያሻግር�ግዚአብሔር አልመረጠውም” እየተባሉ በፊቱ አለፉ፡፡ እግዚአብሔር የመረጠው አባቱ እንኳ ሳይቀር ለዚህ ይሆናል ብሎ ያላሳበው፣ ከዚህም የተነሣ ከመሥዋዕቱ ጥሪና ከበዓሉ ሥርዓት ለይቶ በጎችን እንዲጠብቅ በዱር የተወው ዳዊት ነበር፡፡
የሰው የምርጫ መለኪያና የእግዚአብሔር የምርጫ መለኪያ ምን ያህል የተራራቁና የተለያዩ እንደ ሆኑ እናስተውል፡፡ ሌላው ቀርቶ ክህነት ከምስፍና ደርቦ የያዘው ታላቁ ነቢይ ሳሙኤል እንኳ ኤልያብን ሲያየው ገጽታውን በመመልከት ብቻ ወዲያዉኑ ደስ ብሎት “በእውነት እግዚአብሔር የሚቀባው በፊቱ ነው” እስኪል ያደረሰው በውጫዊ ነገር በመሳቡና በመመሰጡ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ጊዜ “ኢትርአይ ግርማ ርእየቱ ለኤልያብ – የኤልያብን ፊቱን የቁመቱንም �� ቤተ ክርስቲያንን የሚመራ፣ ራሱ ግን በእግዚአብሔር የሚመራ ሰው ማግኘት ለሰው ከባድ ስለሆነ ነው ሁሉን ለሚያውቀው ለእርሱ መተው ከሁሉም የተሻለ አማራጭ የሚሆነው፡፡ ራሱ ባለቤቱም ይህን ሲያስተምረን “መኑ እንጋ ገብር ምእምን ወጠቢብ ዘይሠይሞ እግዚኡ ውስተ ኩሉ ቤቱ ከመ የሀቦሙ ሲሳዮሙ በጊዜሁ – ምግባቸውን በየጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ልባምና ታማኝ ባሪያ ማን ነው?” ሲል የጠየቀው እንዲህ ያሉ ታማኝ አገልጋዮችን (ጌቶችን አላለም) ማግኘት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሲያስተምረን ነው፡፡ ማቴ. 24፡45
ቅዱሳን ሐዋርያት በይሁዳ ቦታ የሚተካና ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ገብቶ የሚቆጠር ሰው ሊመርጡ ሲሉ ሁለት ሰዎችን አቀረቡና ከሁለቱ አንዱን እግዚአብሔር እንዲመርጥላቸው ዕጣ ጣሉ፡፡ ዕጣውም ለማትያስ ወደቀ፡፡ ታዲያ ሐዋርያት እንዲህ ምርጫውን ለእግዚአብሔር ከሰጡ እኛ ለእርሱ የማንሰጥበት ምክንያት ምን ይሆን? የሐዋ. 1፡21-26
ስለሆነም እኛ እያንዳንዳችን እግዚአብሔር እንዲመርጥልን ጉዳዩን ለእርሱ እንስጥ፡፡ ቀድሞዉኑ እግዚአብሔርን “አንተ የሚሆነውን ቅን መሪ ስጠን” ብለን ሙሉ ፈቃዳችንን ሳንሰጠውና ሳንለምነው እኛው “እንዲህ ቢሆን፣ እገሌ ቢመጣ . . .” እያልን እርሱም ለራሳችን ሃሳብ ከተወን በኋላ የምርጫችንን ስናገኝ እንደገና መልሰን ‘እንዴት እንዲህ ዓይነት ሰው ሰጠኸን?’ ብለን ለመናገር እንዴት እንችላለን?
እግዚአብሔር ይመርጥ ዘንድ አባቶቻችንም እንደ ሐዋርያት በዕጣ ቢያደርጉት መንፈሳዊም ሐዋርያዊ ትወፊትም ነውና ያስመሰግናቸዋል፤ ለማንኛውም ሰው ቢሆን ውጤቱን ለመቀበልም የተመቸ ይሆናል፡፡ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የፓትርያርክ አመራረጥ ሂደት ላይ መራጮች የሚመርጡት የመጨረሻዎቹ ሦስት ዕጩዎች እስኪቀሩ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ከሦስቱ አንዱ የሚመረጠው ስማቸው ተጽፎ በመንበር ላይ ይቀመጥና ቅዳሴ ተቀድሶ ሲያበቃ የአምስት ዓመት ሕፃን ልጅ ፊቱ ተሸፍኖ አንድ የተጠቀለለ ወረቀት ያነሣል፣ ወረቀቱ ይገለጥና እዚያ ላይ የተጻፈው ስም አዲሱ ፓትርያርክ ይሆናል፡፡ አሁን ዐቃቤ መንበር ሆነው የተመረጡት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ ደግሞ ይህም ብቻ አይበቃም እያሉ ነው፡፡ ሦስቱንም ዕጩዎች እግዚአብሔር ባይፈልጋቸው በማለት አራተኛ የእግዚአብሔር ሰም የተጻፈበት ወረቀት አብሮ ተጠቅልሎ ሊቀመጥ ይገባል እያሉ ነው፡፡ ይህ በጥንትም በቤቱ ክርስቲያኒቱ በሆነ ዘመን ላይ የነበረ አሠራር ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ስም የተጻፈበት ወረቀት ከወጣ ሦስቱንም እግዚአብሔር አልፈለጋቸውም ማለት ስለሆነ ሂደቱ እንደገና ይጀምራል ማለት ነው፡፡
የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት በራሳቸው ተመርተው እገሌ ፓትርያርክ ካልሆነ እያሉ የመረጡባቸው ጊዜያት ለቤተ ክርስቲያናቸው እጅግ ከባድ የሆኑ ውድቀቶችን አስከትለውባቸዋል፡፡ ለምሳሌም ከ1946-1956 ዓ.ም. (እኤአ) 115ኛ ፓትርያርክ ተደርገው የተመረጡት አቡነ ዮሳብ ካልአይ በዚህ ዓይነት ሁኔታ የተመረጡ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በፓትርያርኮቿ የአመራር ታሪክ እጅግ በጣም መራር የሚሉት ፈተና የገጠማት በእርሳቸው ዘመን ነበር፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የሚሆነውን እረኛ ራሱ እግዚአብሔር እንዲመርጥ ዕድል የሚሰጠውን አሁን ያለውን የፓትርያርክ መምረጫ መስፈርት በ1957 ያወጡት ከዚያ ሁሉ ስህተታቸው በመማር ነበር፡፡ እንዲህ ባለ በመንፈሳዊ መንገድ ሲመርጡ ደግሞ ታላቁን ቅዱስ አባት ቄርሎስ 6ኛን (ከ1959-1971) እና የቅርቡን አቡነ ሺኖዳን (1971-2012) አግኝተዋል፡፡ ስለዚህ ራሳቸው ሲመርጡና እግዚአብሔር እንዲመርጥ ዕድል ሲሰጡ ውጤቱ ምን እንደሆነ በተደጋጋሚ በተግባር አይተውታል፡፡
ስለሆነም በእኛም የፓትርያርክ የምርጫ ሂደት ወደ ምርጫ ከመገባቱ በፊት ከሁሉም አስቀድሞ እንዲህ ዓይነት ለእግዚአብሔር ቦታ የሚሰጥ መንፈሳዊነትና ቀኖናዊነት ያለው የምርጫ ሕግ ሊወጣ ይገባዋል፡፡ በምርጫው ሂደት በአንድ በኩል የተለያየ ዓላማና ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እጃቸውን እንዳያስገቡ በመካላከልና በመጠበቅ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር እንዲመርጥልን የልባችንን በር እንክፈትለት፣ መንገዱንም አንዝጋበት – “አርኁ ኆኃተ መኳንንት ወይባእ ንጉሠ ስብሐት – እናንተ መኳንንት በሮችን ክፈቱ፣ የክብርም ንጉሥ ይግባ” እያለ ይጣራል፡፡ መዝ. 23፡9
2. ምን ጊዜም ለመንፈሳዊነትና ለቀኖናዊነት ቅድሚያውን እንስጥ
ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊት አካል ናት፣ አካልነቷም የክርስቶስ ነው፡፡ በርግጥ ይህን መንፈሳዊነት ለመጠበቅ አስተዳደራዊና መዋቅራዊ አሠራር የሚያስፈልግ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ግን ቅድሚያ ሊሰጠው ብቻ ሳይሆን ምን ጊዜም ታላቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን ኅብረት (Communion of Saints) የመሆኗ ነገር ነው፡፡ አንድ የቤተ ክርስቲያን አባት (ፓትርያርክ) በአስተዳደራዊ ችሎታውና አሠራሩ የተዋጣለት ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን መንፈሳዊነት ከተለየው ቤተ ክርስቲያንን እንደ አንድ ዓለማዊ ተቋም ወይም ድርጅት ሊያስመስላት ይችል እንደሆነ እንጂ ቤተ ክርስቲያን አያሰኛትም፤ ቤተ ክርስቲያንን “ቤተ ክርስቲያን” የሚያሰኛት በውስጧ ያለው መዋቅር፣ የሰው ኃይል፣ የገንዘብ መጠን፣ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት፣ . . . ሳይሆን ከእግዚአብሔርና ከቅዱሳን ጋር ያላት ኅብረትና አንድነት ነው፡፡ እነዚያ አያስፈልጉም ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው፣ ዋናውና መሠረቱ አይዘንጋ ለማለት እንጂ፡፡
ቤተ ክርስቲያንን በፓትርያርክነት የሚመራ አባት ይቅርና በቅስና ደረጃ ካሉት ጀምሮ በተለያየ ደረጃ ያሉት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና አባቶች በእውቀት ከሌላው ተሽለውና ልቀው መገኘት እንጂ አንሰው ወደ ኋላ መቅረትና ቤተ ክርስቲያንን ማሳፈርና ማስናቅ የለባቸውም፡፡ ከመንፈሳዊው ባሻገር በሳይንሱም በጣም የተማረ የነበረ አንድ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ በአንድ የሳይንቲስቶች የጥናት ጉባኤ ላይ ተገኝቶ ንግግር ሲያደርግ “እስከ ግድግዳው ድረስ ከእናንተ ጋር እኩል እናያለን፣ ከዚያ ባሻገር ያለውንና እናንተ የማታዩትን ደግሞ እኛ ብቻ እናያለን” እንዳለው መናገር የሚችሉ አባቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ሆኖም ግን ለቤተ ክርስቲያን አባትነት ዋናው መለኪያ እንዲህ ያለው ዓለማዊ ጥበብና እውቀት አይደለም፡፡ ይህ ሲኖርና ከመንፈሳዊነት ላይ ሲደረብ በእጅጉ የሚጠቅም ሙሉ ጌጥ ይሆናል፡፡ ብቻውን ግን የትም አያደርስም፡፡
አንድ የቤተ ክርስቲያን አባት በቋንቋ ችሎታውና በዲፕሎማሲው ቤተ ክርስቲያንን ከሌላው ዓለም ጋር ማስተዋወቁ መልካም ነገር ነው፡፡ ሆኖም ግን ከእግዚአብሔር ጋር እስካላገናኘንና ከቅዱሳን ጋር ያለውን የመንፈስ አንድነት እስካልጠበቀ ድረስ ከሌሎች መንግሥታትና ድርጅቶች ጋር ስላገናኘን በዚህ ብቻ ቤተ ክርስቲያን ልትጠቀም አትችልም፡፡ ስለዚህ ምን ጊዜም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊነት መጠበቁና ማስጠበቁ ላይ ነው፡፡
እያንዳንዳችንም በመጀመሪያ ከክርስቶስ ጋር አብረን በቤተ ክርስቲያን ሳንሠራና የአካሉ አንድ ክፍል (ብልት) ሳንሆን ስለ አካሉ በማሰብና በመናገር ብቻ ራሳችንንም ቤተ ክርስቲያንንም ልንጠቅም አንችልም፡፡ ጌታችን “እኔ የወይን ግንድ ነኝ፣ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ” እንዳለ በመጀመሪያ ከግንዱ ያልተቆረጥን ስለመሆናችን እናስብ፡፡ ተቆርጦ የወደቀና ከግንዱ ውጭ የሆነ ክብርና ምስጋና ይግባውና ጌታችን በቅዱስ ቃሉ እንደ ተናገረው “በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል፣ ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሏቸዋል፣ ያቃጥሏቸውማል” ብላል፡፡ በአንጻሩ በእርሱ ለሚኖሩት ደግሞ እንዲህ ይላል፡- “በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ፤ ይሆንላችሁማል፡፡” ዮሐ. 15፡1-7
ምድራዊ የሆኑ መሥፈርቶችን ዋና ጉዳዮች በማድረግ መሠረታዊ የሆነውን ፈሪሃ እግዚአብሔርን፣ ሃይማኖተኛነትን፣ ቅንነትን፣ ትሑትነትን፣ ወዘተ ችላ በማለት የምናደርገው ነገር እንዳይኖር ወደ ራሳችን መመለስ ያለብን ትክክለኛ ጊዜ ላይ ያለን ይመስላል፡፡ ጌታችን “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥቱንና ጽድቁን ሹ ፈልጉ፣ ሌላው ሁሉ ይጨመርላችኋል” ያለው ለዚህ ነው፡፡ ማቴ. 6፡33 የእግዚአብሔርን መንግሥት፣ ጽድቅን የሚሻ ሰው ወድቆ አይወድቅም፣ ተሻግሮ ያሻግራል፣ ጸሎቱ ይጠቅማል፡፡ በተቃራኒው ምድራዊ የሆነ እውቀት፣ ችሎታ፣ ልምድ፣ . . . ላይ የምንመሠረት ከሆነ ግን በአሸዋ ላይ እንደ ተሠራው ቤት አንድ ነገር ሲነካው ፈጥኖ ይወድቅና በውስጡ የተጠለሉበትን ሁሉ ጉዳት ያደርስባቸዋል፡፡ ስለሆነም ከውጭ ሰዎች ጋር መነጋገር ስለመቻሉ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት መነጋገር ስለመቻሉ፣ ከቅዱሳን ጋር ኅብረት ያለውና እኛንም ወደዚያ የሚመራን ስለመሆኑ ቅድሚያ ሰጥተን እናስብ፡፡ መንፈሳዊ የሆነውን ነገር ስንመኝና ስንፈልግ የልባችንን መሻት የሚያይ እግዚአብሔር እንደ ፈቃዱ የሆነ መሻታችንን ተመልክቶ የተመኘነውን አይነሳንም፡፡ ነገር ግን ምኞታችን ምድራዊና ኃላፊ ጠፊ ስለሆነው ነገር ከሆነ “ወወሀቦሙ ለፍትወቶሙ – እግዚአብሔር ለፈቃዳቸው አሳልፎ ሰጣቸው” እንደ ተባለው ለዚያው ለተመኘነው ነገር አሳልፎ ይሰጠናል፡፡
3. ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅመውን ሃሳብ ብቻ ለመከተል ቁርጥ ሕሊና ይኑረን
ሃሳባችንንና ድርጊታችንን የሚመራው ገዢ ሃሳብ ሐዋርያዊትና ቅድስት ለሆነችው ቤተ ክርስቲያናችን ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም የሚለው እንጂ ግለሰባዊ ወይም ቡድናዊና አካባቢያዊ (ጎጣዊ) ጥቅማ ጥቅም ስሌት ሊሆን አይገባውም፡፡ በእውነቱ ከሆነ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ለአንድ ክርስቲያን የሚገባ አይደለም፣ ሃይማኖት ከማጣት የሚመጣ ክፉ ደዌ ነው፡፡ በየጎጡና መንደሩ የምናስብና ሃሳባችን ሁሉ በዚህ የሚቃኝ ከሆነ ስለ አንዲት ቤተ ክርስቲያን በጋራ ማሰብ እንዴት ይቻለናል? ጌታችን “እርስ በርሷ የምትከፋፈል ቤት አትጸናም” በማለት እንደ ነገረን ለሁላችንም የሚጠቅም ነገር ለማግኘት እንዴት አንችላለን?
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ”ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፣ . . . እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፣ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ ሃሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን” በማለት በብርቱ የተማጸነው፡፡ ይህ በሽታ በየትኛውም የሥልጣንም ሆነ የትምህርት ደረጃ ያሉ ሰዎችን ሊጸናወት የሚችል ክፉ ደዌ እንደ ሆነ ስለተረዳ ነው፡፡ ፊል. 2፡3-5 “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ” ሲል አሳሰበን፡፡ እስኪ ይህን የእግዚአብሔር ጽኑ ማሳሰቢያ ስለ እግዚአብሔር ብለን ቆም ብለን እናስተውለው፡፡ ይህ ማለት እያንዳንዱ ለራሱ መንደር ወይም ጎጥ የሚጠቅመውን ብቻ እያሰላ ከዚያ አንጻር የሚሄድ ከሆነ ውጤቱ ብቻ ሳይሆን አስተሳሰቡ በራሱ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና በአበው ቀኖና የተወገዘ ነው፡፡ እንዲህ የሚያስብ ሰው በቤተ ክርስቲያን አንድነት በሰው ልጅ ወንድማማችነትና እኩልነት የማያምን ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ይህ ዓይነት አስተሳሰብ ከእኛ ይርቅ ዘንድ በቅዱሳት መጻሕፍት እንዲህ ምክርና ተግሣጽ የተሰጠበት ጉዳይ ቢሆንም በብዙዎቻችን ዘንድ እንደ መልካም ሃሳብ ተቆጥሮ በልቡናችን ተንሰራፍቶና ተደራጅቶ የተቀመጠ መሆኑ ነው፡፡
ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ የሆነችው የአርሜንያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በ1995 (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር) በተካሄደው የፓትርያርካቸው ምርጫ ላይ የተካፈሉ መራጮች ከመምረጣቸው በፊት ከዚህ በታች የተመለከተውን ቃለ መሀላ እንዲፈጽሙ ያደረገችው ለዚህ ነበር፡፡ ቃለ መሀላው እንዲህ ይላል፡-
“እኔ ከዚህ በታች የፈረምኩት፣ ካቶሊኮስ (እነርሱ ፓትርያርካቸውን ካቶሊኮስ ነው የሚሉት – ዓለም አቀፋዊ አባት ለማለት) ለመምረጥ በቤ/ክ የተወከልኩት፣ ከፊታችን ባለው የመላዋ አርሜንያውያን ካቶሊኮስ ምርጫ ላይ በጥንቃቄና በማስተዋል፣ ያለ አድልዎ፣ ለቦታው ይሆናል የምለውን ሰው ብቻና ያለ ምንም ግላዊ ፍላጎት፣ እገሌ ቢሆን ከሚል ነገር ራሴን አርቄና ነጻ አድርጌ፣ ከውስጤ ማንኛውንም ዓይነት ክፋትና ተንኮል፣ ጥላቻ፣ ቅናትና ምቀኝነት ወይም የዝምድናም ሆነ የጓደኛነት ትስስር ወይም ቅርበት አርቄ፣ ለክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እረኛና ታማኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ ይሆናል ብዬ የማስበውን ብቻ የምመርጥ መሆኔን በቅዱስ ወንጌሉ ፊት በኃያሉ በእግዚአብሔር ስም እምላለሁ፡፡
“ተስፋዬ በሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ ቃል እንደ ገባሁት ባላደርግ ግን ራሴን ለመንፈሳውያን ወንድሞቼ ወቀሳ አጋልጣለሁ፣ በዚህም ዓለምም ሆነ በሚመጣው ዓለም በታላቁ የፍርድ ቀን በእግዚአብሔር ፊት እጠየቅበታለሁ፡፡ ቃለ መሀላዬን ለመግለጽ ፍትሐዊ ምርጫ ይሆን ዘንድ የመድኃኒታችንን ቅዱስ ወንጌልና መስቀሉን አስማለሁ፡፡ አሜን፡፡”
አንዳችን ስለ ሁላችን ብናስብ፣ ለአንዲቷ ቤተ ክርስቲያን ስለሚበጀው ብናስብ፣ በጎ ሃሳብን ከምንም ነገር በላይ እንደ ተወደደ መሥዋዕት አድርጎ የሚቀበለው እግዚአብሔር ለሁላችንም የሚጠቅመውን መልካም ነገር ያደርግልናል፡፡ አይሁድ የሰሎሞን ቤተ መቅደስ ስለ ታነጸበት ቦታ እንዲህ የሚል አፈ ታሪክ አላቸው፡፡ ሁለት ወንድማማቾች እርሻቸውን የሚያርሱትና አዝመራውን የሚካፈሉት በጋራ ነበር፡፡ ታላቁ ቤተሰብ ያለው ሲሆን ታናሹ አልነበረውም፡፡ እኩል ከተካፈሉ በኋላ ታናሹ እኔ ብቻዬን ነኝ፣ ወንድሜ ግን ቤተሰብ አለው፣ ስለዚህ እርሱ ከእኔ ይልቅ የበለጠ ያስፈልገዋል እያለ ከእህሉ ከፍሎ ሌሊት ማንም ሳያየው ተሸክሞ እየወሰደ በታላቅ ወንድሙ ጎተራ ይጨምርና ይመለስ ነበር፡፡ ታላቁ ደግሞ ለራሱ እኔ ቤተሰብ መሥርቻለሁ፣ ወንድሜ ግን ገና ብዙ ነገር ይጠብቀዋል፣ ስለዚህ ለእርሱ የበለጠ ያስፈልገዋል እያለ እንዲሁ ሌሊት ተሸክሞ ወስዶ ማንም ሳያየው ከታናሽ ወንድሙ ጎተራ ጨምሮ ይመለስ ነበር፡፡ ሁለቱም ከጎተራቸው ከወሰዱለት በኋላ ጠዋት ሲያዩት ተመልሶ ሞልቶ ስለሚያገኙት ነገሩ ይገርማቸው ነበር፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲኖሩ አንድ ሌሊት ላይ ታናሹም ተሸክሞ ወደ ታላቁ ጎተራ ሊጨምር ሲሄድ፣ ታላቁም እንዲሁ ወደ ታናሹ ጎተራ ሊጨምር ተሸክሞ ሲሄድ መንገድ ላይ ተገናኙ፡፡ ሁለቱም ሸክማቸውን አውርደው ተቃቅፈው ተላቀሱ፡፡ መሥዋዕት ሲሠዋበትና ሕዝቡ አምልኳቸውን ሲፈጽሙበት የኖሩት የብሉይ ኪዳኑ ቤተ መቅደስ የታነጸበት ቦታ የተሠራው እነዚህ ሁለቱ ወንድማማቾች የተገናኙበት ቦታ ላይ ነው ይላሉ፡፡ እኛ እንዲህ ብንተሳሰብ እግዚአብሔር እርሱ የሚመሰገንበትን እኛም በፍቅር አንድ የምንሆንበትን መንፈስ ይሰጠናል፡፡
ለራሳችንና የእኛ ወገን ለምንለው ብቻ እንድንጠቀም፣ የእኛ ወገን ወይም ቡድን ወይም አካባቢ ብቻ ቀዳሚ ወይም የተለየ ተጠቃሚ እንዲሆን በማስላት የምንሠራው ሥራ ግን ራሳችንንም አይጠቅምም፡፡ ስለሆነም እንኳን በክርስትና ሃይማኖት እኖራለሁ ለሚል ሰው ቀርቶ በፖለቲካ እንኳ እየተጠላ ያለውን እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ እግዚአብሔር ከውስጣችን እንዲያወጣልንና ነጻ እንዲያደርገን እንለምነው፡፡ ለሁላችንም የሚጠቅመወን ለቤተ ክርስቲያን የሚበጀውን በአንድ ልብ ለማሰብ እንሞክር፡፡
4. ወደ እግዚአብሔር እንጸልይ
ነቢዩ ዳዊት “ወከዐው ልበክሙ ቅድሜሁ – ልባችሁን (ሃሳባችሁን፣ ልመናችሁን) በፊቱ አፍሱ (ንገሩት፣ ግለጡለት)” እንዳለ ጸሎት ጭንቀታችንንና ሃሳባችንን ለአባታችን ለእግዚአብሔር የምንገልጥበት ልዩ ሀብት ነው፡፡ ከእኛ በላይ ለእኛ የሚያስፈልገንን የሚያውቅ፣ ከአባታዊ ቸርነቱ የተነሣ የሚጠቅመንን እንጂ የሚጎዳንን የማይሰጥ እርሱን በጸሎት እንጠይቀው፡፡ ድካማችንን የሚያውቅ እርሱ በጸሎት ወደ እርሱ እንደንጠይቀው በቅዱሳት መጻሕፍት በተለያየ መንገድ ደግሞ ደጋግሞ አስተምሮናል፡፡ “ለምኑ፣ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፣ ታግኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፣ ይከፈትላችሁማል፡፡ የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፣ የሚፈልግም ያገኛል” በማለት ደጋግሞ ካስተማረ በኋላ በምሳሌ ደግሞ እንዲህ አለ፡- “አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማናችሁም ልጁ እንጀራ ቢለምነው እርሱም ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ደግሞ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን? ወይስ እንቁላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?” ሉቃ. 11፡9-13
ስለዚህ ብንለምነው የማይሰለቸን፣ ይልቁንም ሳንለምነው ከምንቀር ብንለምነው የሚወድ ቸር አባት እግዚአብሔር እያለን እንዴት የምንሻውን እናጣለን? ሆኖም ስንለምነው ፈቃዱን አውቀን በቅዱሳት መጻሕፍት በታዘዝነው መሠረት ይሆን ዘንድ፣ እንደ ታዘዝነው ለመሆን እንድንችልም ራሳችንን በሚቻለን እያዘጋጀን ሊሆን ይገባል፡፡ እንዲህ ከሆነ ሁሉንም በእኩል ዓይን የሚያይ፣ የወንጌል የመዳን ጸጋ ለሰው ሁሉ እንዲደርስ የሚተጋ፣ በጎቹን በትጋት የሚጠብቅና ስለ አንዲቷ በግ መባዘን ዕረፍት የሚያጣ ደግ እረኛ ይሰጠን ዘንድ ይችላል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ “አንብር ለነ ኖላዌ ኄረ ዲበ መንበሩ – በመንበሩ ላይ ቸር እረኛ አስቀምጥልን (አምጣልን)” ብለን የምንጸልየውን ጸሎት ተቀብሎ ቅን መሪ ይስጠን፡፡ አሜን፡፡
(ጸሎተ ኪዳን – ዘሠርክ)
ነሐሴ 18 ቀን 2004 ዓ.ም.
በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ
ቤተ ክርስቲያን የምንላት ወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍጹምና ከማይነገር ፍቅሩ የተነሣ ሰው እስከ መሆን፣ ሰው ሆኖም በዚህ ዓለም ከኃጢአት በስተቀር እንደ ሰው መኖርን፣ ከዚያም በቀራንዮ ቅዱስ ሥጋውን እስኪቆርስላትና ክቡር ደሙን እስኪያፈስላት ድረስ የደረሰላትና የመሠረታት የምእመናን አንድነት (ጉባኤ) ናት፡፡ “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላእለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት” የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በወንጌል መሠረትነት በኢየሱስ ክርስቶስ ራስነት በምእመናን አካልነት የተመሠረተች ጉባኤ ናት፡፡
ቤተ ክርስቲያን ስንል የዚህ ዓለም ተጋድሏቸውን በድል አጠናቅቀው ወደ እግዚአብሔር የሄዱ ቅዱሳን (ሐዋርያት፣ ሰማዕታት፣ ሊቃውንት፣ …) እና ገና በዚህ ዓለም በተጋድሎ ላይ ያሉት የምእመናን አንድነት (ጉባኤ) ናት፡፡ በሰማይ ያለችው ቤተ ክርስቲያን (ጉባኤ) የዚህ ዓለም ጣጣቸውን ጨርሰው የሄዱ፣ ድል አድርገው የድል አክሊላቸውን ለመቀበል እርሱ የወሰነውን ጊዜ የሚጠባበቁ ቅዱሳን ኅብረት ስለሆነች አትናወጽም፤ ስለሆነም ሊቃውንት ይህችን ቤተ ክርስቲያን ድል አድራጊዋ ቤተ ክርስቲያን (Church Triumphant) ይሏታል፡፡ ገና በዚህ ዓለም በጉዞና በፈተና ላይ ያለችውን የአንዲቷ ቤተ ክርስቲያን አካል የሆነችውን ጉባኤ (ቤተ ክርስቲያን) ደግሞ ገና በተጋድሎ ላይ ያለች ቤተ ክርስቲያን (Church Militant) ይሏታል፡፡
በዚህ ዓለም ያለችው ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያት በባሕር ላይ በታንኳ እየሄዱ ሳለ ጌታችን አብሯቸው በመካከላቸውና በታንኳው ውስጥ እያለ፣ ነገር ግን በኃይለኛ ማዕበል ትናወጥ እንደ ነበረችው ታንኳ በተለያዩ ፈተናዎች ትናወጻለች፡፡ አንዳንድ ጊዜም በውስጧ ያለው ጌታ የማይሰማና የተዋት፣ መከራዋን እያየ ዝም ያላት፣ ባለቤት የሌላት እስክትመስል ድረስ በውስጧ ያሉና በተለያዩ ነገሮች ተጨንቀው የሚያማርሩና የሚያዝኑ ልጆቿም ሰሚ የሌላቸው የሙት ልጆች እስኪመስሉ ድረስ ባለቤቷ ኢየሱስ ክርስቶስ ዝም ይላል፡፡ ሐዋርያትንም “ስንጠፋ አይገድህምን?” እስኪሉ ያደረሳቸው ይህ ነበር፡፡ ማቴ. 8፡23-27
የአንዲቷ ቤተ ክርስቲያን አካል የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አምስተኛ ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ማረፋቸው ይታወቃል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የእርሳቸውን ነፍስ ከቅዱሳን ጋር ይደምርልን እያለች ተተኪውን ስድስተኛውን ፓትርያርክ የመምረጥ ከባድ ሥራ ደግሞ ከፊቷ ተደቅኗል፡፡ ይህ ሥራ ሂደቱና ውጤቱ ቢያንስ ቢያንስ ለሚመጡት የተወሰኑ ዓመታት በቤተ ክርስቲያናችን አካሄድ ላይ የራሱ የሆነ ተጽእኖ የሚኖረው መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማም በዚህ ታላቅ ወሳኝ ወቅት ላይ እያንዳንዳችን ምን ብናደርግ እንደሚሻል አጠንክረን እንድናስብ ሕሊናችንን ለማነሣሣት ያህል ነው፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የባለቤቷ የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ ስለሆነች ጠባቂዋና ተንከባካቢዋ እርሱ ራሱ ነው፡፡ ምንም እንኳ እርሱ በሚያውቀውና በተለያዩ ምክንያቶች እንድትፈተን ቢፈቅድም እንድትጠፋ ግን አይተዋትም፡፡ ይህ ማለት ግን በውስጧ ያሉ አባላት በጥርጥርና በልዩ ልዩ ፈተናዎች አይሰናከሉም ማለት ግን አይደለም፡፡ ምንም ቢሆን ግን ቤተ ክርስቲያን የራሱ የክርስቶስ አካሉ እንደ መሆኗ ራሷ የሆነ እርሱ ለአካሉ ለምእመናን የሚያስፈልገውን ያውቃል፣ ያዘጋጃል፣ ይሰጣል፡፡ ለዚህ ነው በጸሎተ ኪዳናችን ላይ “ዘይሁብ መርሐ ርቱዐ ለቤተ ክርስቲያን – ለቤተ ክርስቲያን ቅን መሪ የሚሰጥ” የተባለው፡፡
ነገር ግን ችግር የሚሆነው ቤተ ክርስቲያን የማን መሆኗን ዘንግተን ባለቤቷና ራሷ የሆነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ ራሱ የሚሆናትን ቅን መሪ እንዲሰጣት ከመጠየቅና ከመማጸን አልፈን እኛው ራሳችን መሪ እንስጥሽ ወደሚል ዝንባሌና አስተሳሰብ ስንሄድ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው እንደየ እውቀቱና አመለካከቱ ለክርስቶስ ሙሽራ ለሆነችው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን “እንዲህ ቢሆን፣ እገሌ ቢሆን፣ . . . ” ወደሚል ነገር መምጣት በሽታውን ሳይረዳ እንዲሁ በይመስላል መድኃኒት እንደሚያዝ ሰው መሆን ነው፡፡ በሽታውን ሳይመረምሩና ለመረዳት ጥረት ሳያደርጉ እንዲሁ በግምት፣ በአውቀዋለሁ ባይነትና በግዴለሽነት የሚታዘዘውን እንዲህ ያለውን መድኃኒት መውሰድ ምናልባትም ካለመውሰድ በባሰ ጤናን ሊያውክና ሕማምንም ሊያባብስ ይችላልና፡፡
ታዲያ መሥራቿና ባለቤቷ ኢየሱስ ክርስቶስ አካሉ ለሆነችው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ቅን መሪ እንዲሰጣት የእኛ ድርሻ ምን ቢሆን ይሻል ይሆን? ምንስ እናድርግ?
1. መሪ የመስጠቱን ሥራ ለራሱ ለእግዚአብሔር እንስጠው – እኛ ሳንሆን ራሱ ይምረጥልን
እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ መሪያቸውና ንጉሣቸው እግዚአብሔር ሆኖ በተለያዩ መሳፍንት አማካይነት ያስተዳድራቸው ነበር፡፡ መሳፍንቱም የባለ ሥልጣን ወግ ማዕረግ የሌላቸው ከሕዝቡ እንደ አንዱ ሆነው የሚስተዳድሩ፣ ጦርነት ሲሆንና አስፈላጊ በሚሆኑ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ብቻ የሚመሩ ነበሩ፡፡ ከሙሴ አንስቶ እሰከ ሳሙኤል ዘመን ድረስ ለ450 ዓመታት በዚህ ዓይነት ሁኔታ እየተመሩ ኖሩ፡፡ ሳሙኤልም ምስፍናና ክህነቱን ደርቦ ሕዝቡን አንደ ካህንነቱ ከእግዚአብሔር ጋር እያገናኘ፣ እንደ መሳፍንነቱ ደግሞ አስተዳደራዊ የሆኑ ጉዳዮቹን ያሰዳድራቸው ነበር፡፡ የሐዋ.13፡20-21
እነርሱ በዚህ ሁኔታ እየኖሩ ሳለ በአካባቢያቸው የሚኖሩ የተለያዩ አሕዛብ ደግሞ የራሱ የሆነ የንግሥና ሥርዓት፣ አፋሽ አጎንባሽ፣ ሠረገላና ሠራዊት፣ ሽቶ ቀማሚዎች፣ ወጥ ቤቶችና እንጀራ አበዛዎች ያሏቸው፣ ሕዝቡን የሚያስገብሩ ነገሥታት ነበሯቸው፡፡ እስራኤላውያን በአሕዛብ በመቅናት ንጉሣቸው እግዚአብሔር መሆኑ ቀርቶ እንደ ሌሎቹ ጎረቤቶቻቸው ከመካከላቸው አንዱን እነዲያነግሥላቸው በሳሙኤል በኩል ጠየቁ፡፡ በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው፡-
“በእነርሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን እንጂ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ስማ፡፡ ከግብጽ ካወጣኋቸው ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ትተው እንግዶች አማልክት በማምለካቸው እንደ ሠሩት ሥራ ሁሉ እንዲሁ በአንተ ደግሞ ያደርጉብሃል፡፡ . . . ለሕዝቡም በእናንተ ላይ የሚነግሠው የንጉሡ ወግ ይህ ነው ብለህ ንገራቸው፡- ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሰረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፣ . . . ሎሌዎቻችሁንና ገረዶቻችሁን ከከብቶቻችሁና ከአህዮቻችሁም መካከል መልካሞቹን ወስዶ ያሠራቸዋል፡፡ ከበጎቻችሁና ከፍየሎቻችሁ አሥራት ይወስዳል፤ እናንተም ባሪያዎች ትሆኑታላችሁ፡፡ በዚያም ቀን ለእናንተ ከመረጣችሁት ከንጉሣችሁ የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር አይሰማችሁም፡፡” 1 ሳሙ. 8፡10-18
እንደ ልመናቸው ንጉሥ ሰጣቸው፣ ሳኦልን አነገሠላቸው፡፡ ሆኖም እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደ ነገራቸው ብዙም ሳይቆይ ንጉሦቻቸው ለሕዝበ እስራኤል ዋናው የጥፋታቸው መሪዎች በመሆን የጥፋታቸውን ጎዳና ደኅና አድርገው ጠርገውላቸዋል፡፡ በንጉሥ ሰሎሞን ኃጢአት ምክንያት በልጁ በሮብአም ዘመን አንድ የነበረው ሕዝብ ከሁለት ተከፈለ፤ አሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ተብሎ በሰሜን፣ ሁለቱ ነገድ ደግሞ በደቡብ የይሁዳ መንግሥት ተብሎ በ928 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ዳግመኛ አንድ ላይሆኑ ተለያዩ፡፡
ቀጥሎም የአሥሩ ነገድ ንጉሥ የነበረው ኢዮርብዓም በግዛታቸው በስሜንና በደቡብ ጫፍ ላይ በዳንና በቤቴል ጣዖት አቁሞ ከዚያ በፊት ይደረግ እንደ ነበረው ሕዝቡ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ በታቦተ ጽዮን ፊት በቤተ መቅደሱ መሥዋዕት አቅርቦ አምላኩን እግዚአብሔርን አዘክሮ እንዳይመለስ በዚያው በሰሜኑ ግዛት ብቻ ተገድቦ እንዲቀር ለማድረግ ሲል ባቆማቸው ጣዖታት ሕዝቡን እግዚአብሔርን ከማምለክ ጣዖት ወደ ማምለክ እንዲያዘነብል አደረገው፡፡ ከዚሁም ጋር ንጉሣቸው ኢዮርብዓም እንደ ሕጉ መሠረት ካህናትን ከሌዋውያን ሳይሆን ሌዋውያን ካልሆኑት መካከል ለራሱ የሚመቹትን ካህናት ናቸው ብሎ መረጠ፣ በዓል የሚከበርበትን ቀን ለወጠ፣ በአጠቃላይ በኦሪቱ የተሰጠውን ነገር ሁሉ ገለባበጠው፡፡
እስራኤላውያን አስቀድሞ የንጉሥ አንግሥልን ምርጫቸው ምን እንደሚያስከትል በግልጽ እንደ ተነገራቸው ሆነባቸው፡፡ የሰሜኑ ግዛት የአሥሩ ነገድ ነገሥታት ኢዮርብዓም በጀመረው ከእግዚአብሔር የመለየትና ጣዖት የማምለክ የጥፋት ጎዳና እየገፉበት ሄዱ፡፡ ከዚያም በኋላ እነ አክአብና ኤልዛቤል ክህደቱና ኃጢአቱ፣ ግፉና ዓመጹ መሥፈሪያውን ቶሎ እንዲሞላ እያቻኮለው ሄደ፡፡ በዚያ የጥፋት ቁልቁሊት በፍጥነት በመቀጠል የእስራኤል መንግሥት ለሁለት በተከፈለ በ210 ዓመት (በ718 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ) በአሶራውያን ተማርከው ተወሰዱ፡፡ 2 ነገ. ምዕ. 17 ከዚያ በኋላ የአሥሩ ነገድ ነገር የውኃ ሽታ ሆኖ ቀረ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አሥሩ ነገድ መማረክ ይነግረናል እንጂ ከዚያ በኋላ የት እንደ ደረሱና ምን እንደ ሆኑ አይነግረንም፡፡ በመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ከምርኮ ስለ መመለሳቸው የተጻፈላቸው በኋላ የተማረኩት ሁለቱ ነገድ ናቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ከተነገሩና ምሥጢራቸው ካልተፈታ ታሪኮች አንዱ ይህ የአሥሩ ነገድ ጉዳይ ነው፡፡ እንግዲህ ያ የወደዱትና ጓጉተውና ሽተው የለመኑት የንጉሥ አንግሥልን ጥያቄ ነገር ፍጻሜያቸው እንዲህ አሳዛኝ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በዚሁ ንጉሥ የማንገሥ ጉዳይ ነቢዩ ሳሙኤል ከእግዚአብሔር ፊት በተናቀው በሳኦል ፋንታ የሚቀባውን ሊፈልግ ወደ ቤተ ልሔም ሄዶ ወደ እሴይ ቤት ገብቶ በዚያ የነበሩትን የእሴይን ልጆች ተራ በተራ ሲያልፉ ዓይኑ ኤልያብ ላይ አርፎ ነበር፡፡ ኤልያብ በሰው አስተሳሰብ መልከ መልካምና ተክለ ቁመናው የሚስብ ስለነበር ነቢዩ ሳሙኤል እርሱን ሲመለከት “በእውነት እግዚአብሔር የሚቀባው በፊቱ ነው” አለ፡፡ እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፡- “ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፣ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው፡፡ ሌሎቹም የእሴይ ልጆች እነ አሚናዳብ፣ ሣማን፣ … በፊቱ አለፉ፡፡ ሆኖም እነዚያ ሁሉም “ይህን ደግሞ እግዚአብሔር አልመረጠውም” እየተባሉ በፊቱ አለፉ፡፡ እግዚአብሔር የመረጠው አባቱ እንኳ ሳይቀር ለዚህ ይሆናል ብሎ ያላሳበው፣ ከዚህም የተነሣ ከመሥዋዕቱ ጥሪና ከበዓሉ ሥርዓት ለይቶ በጎችን እንዲጠብቅ በዱር የተወው ዳዊት ነበር፡፡
የሰው የምርጫ መለኪያና የእግዚአብሔር የምርጫ መለኪያ ምን ያህል የተራራቁና የተለያዩ እንደ ሆኑ እናስተውል፡፡ ሌላው ቀርቶ ክህነት ከምስፍና ደርቦ የያዘው ታላቁ ነቢይ ሳሙኤል እንኳ ኤልያብን ሲያየው ገጽታውን በመመልከት ብቻ ወዲያዉኑ ደስ ብሎት “በእውነት እግዚአብሔር የሚቀባው በፊቱ ነው” እስኪል ያደረሰው በውጫዊ ነገር በመሳቡና በመመሰጡ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ጊዜ “ኢትርአይ ግርማ ርእየቱ ለኤልያብ – የኤልያብን ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ” የሚል ተግሣጽ አከል ነገር የተናገረው ለዚህ ነበር፡፡ እንግዲህ እንዲህ ያሉ ታላላቅ አባቶች እንኳ እግዚአብሔር ያዘጋጀውንና የመረጠውን ለማወቅ ይህን ያህል የሚቸገሩና ለዚህ ጥሪ የማይሆኑ ብዙ ሰዎችን አጣርተው (በፊታቸው አሳልፈው) መተው ያለባቸው ከሆነ ለእኛማ ምን ያህል ከባድ ይሆን?
ይህ ማለት እኛ መሥራት ያለብንን ሥራ መሥራት የለብንም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ቤተ ክርስቲያንን በአባትነት የሚመራ፣ ለመንጋው ታማኝ የሆነና መንጋውም የሚወደውና የሚያፈቅረው፣ ምንደኛ ያይደለ እረኛ፣ ጌታ ሳይሆን አገልጋይ፣ ለራሱ ሥልጣንና ክብር ሳይሆን ለእግዚአብሔር ክብር የሚቀና፣ ውስብስብ የሆነውን ዓለም በመስቀል ተደግፎ የሚሻገርና የሚያሻግር፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚመራ፣ ራሱ ግን በእግዚአብሔር የሚመራ ሰው ማግኘት ለሰው ከባድ ስለሆነ ነው ሁሉን ለሚያውቀው ለእርሱ መተው ከሁሉም የተሻለ አማራጭ የሚሆነው፡፡ ራሱ ባለቤቱም ይህን ሲያስተምረን “መኑ እንጋ ገብር ምእምን ወጠቢብ ዘይሠይሞ እግዚኡ ውስተ ኩሉ ቤቱ ከመ የሀቦሙ ሲሳዮሙ በጊዜሁ – ምግባቸውን በየጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ልባምና ታማኝ ባሪያ ማን ነው?” ሲል የጠየቀው እንዲህ ያሉ ታማኝ አገልጋዮችን (ጌቶችን አላለም) ማግኘት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሲያስተምረን ነው፡፡ ማቴ. 24፡45
ቅዱሳን ሐዋርያት በይሁዳ ቦታ የሚተካና ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ገብቶ የሚቆጠር ሰው ሊመርጡ ሲሉ ሁለት ሰዎችን አቀረቡና ከሁለቱ አንዱን እግዚአብሔር እንዲመርጥላቸው ዕጣ ጣሉ፡፡ ዕጣውም ለማትያስ ወደቀ፡፡ ታዲያ ሐዋርያት እንዲህ ምርጫውን ለእግዚአብሔር ከሰጡ እኛ ለእርሱ የማንሰጥበት ምክንያት ምን ይሆን? የሐዋ. 1፡21-26
ስለሆነም እኛ እያንዳንዳችን እግዚአብሔር እንዲመርጥልን ጉዳዩን ለእርሱ እንስጥ፡፡ ቀድሞዉኑ እግዚአብሔርን “አንተ የሚሆነውን ቅን መሪ ስጠን” ብለን ሙሉ ፈቃዳችንን ሳንሰጠውና ሳንለምነው እኛው “እንዲህ ቢሆን፣ እገሌ ቢመጣ . . .” እያልን እርሱም ለራሳችን ሃሳብ ከተወን በኋላ የምርጫችንን ስናገኝ እንደገና መልሰን ‘እንዴት እንዲህ ዓይነት ሰው ሰጠኸን?’ ብለን ለመናገር እንዴት እንችላለን?
እግዚአብሔር ይመርጥ ዘንድ አባቶቻችንም እንደ ሐዋርያት በዕጣ ቢያደርጉት መንፈሳዊም ሐዋርያዊ ትወፊትም ነውና ያስመሰግናቸዋል፤ ለማንኛውም ሰው ቢሆን ውጤቱን ለመቀበልም የተመቸ ይሆናል፡፡ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የፓትርያርክ አመራረጥ ሂደት ላይ መራጮች የሚመርጡት የመጨረሻዎቹ ሦስት ዕጩዎች እስኪቀሩ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ከሦስቱ አንዱ የሚመረጠው ስማቸው ተጽፎ በመንበር ላይ ይቀመጥና ቅዳሴ ተቀድሶ ሲያበቃ የአምስት ዓመት ሕፃን ልጅ ፊቱ ተሸፍኖ አንድ የተጠቀለለ ወረቀት ያነሣል፣ ወረቀቱ ይገለጥና እዚያ ላይ የተጻፈው ስም አዲሱ ፓትርያርክ ይሆናል፡፡ አሁን ዐቃቤ መንበር ሆነው የተመረጡት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ ደግሞ ይህም ብቻ አይበቃም እያሉ ነው፡፡ ሦስቱንም ዕጩዎች እግዚአብሔር ባይፈልጋቸው በማለት አራተኛ የእግዚአብሔር ሰም የተጻፈበት ወረቀት አብሮ ተጠቅልሎ ሊቀመጥ ይገባል እያሉ ነው፡፡ ይህ በጥንትም በቤቱ ክርስቲያኒቱ በሆነ ዘመን ላይ የነበረ አሠራር ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ስም የተጻፈበት ወረቀት ከወጣ ሦስቱንም እግዚአብሔር አልፈለጋቸውም ማለት ስለሆነ ሂደቱ እንደገና ይጀምራል ማለት ነው፡፡
የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት በራሳቸው ተመርተው እገሌ ፓትርያርክ ካልሆነ እያሉ የመረጡባቸው ጊዜያት ለቤተ ክርስቲያናቸው እጅግ ከባድ የሆኑ ውድቀቶችን አስከትለውባቸዋል፡፡ ለምሳሌም ከ1946-1956 ዓ.ም. (እኤአ) 115ኛ ፓትርያርክ ተደርገው የተመረጡት አቡነ ዮሳብ ካልአይ በዚህ ዓይነት ሁኔታ የተመረጡ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በፓትርያርኮቿ የአመራር ታሪክ እጅግ በጣም መራር የሚሉት ፈተና የገጠማት በእርሳቸው ዘመን ነበር፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የሚሆነውን እረኛ ራሱ እግዚአብሔር እንዲመርጥ ዕድል የሚሰጠውን አሁን ያለውን የፓትርያርክ መምረጫ መስፈርት በ1957 ያወጡት ከዚያ ሁሉ ስህተታቸው በመማር ነበር፡፡ እንዲህ ባለ በመንፈሳዊ መንገድ ሲመርጡ ደግሞ ታላቁን ቅዱስ አባት ቄርሎስ 6ኛን (ከ1959-1971) እና የቅርቡን አቡነ ሺኖዳን (1971-2012) አግኝተዋል፡፡ ስለዚህ ራሳቸው ሲመርጡና እግዚአብሔር እንዲመርጥ ዕድል ሲሰጡ ውጤቱ ምን እንደሆነ በተደጋጋሚ በተግባር አይተውታል፡፡
ስለሆነም በእኛም የፓትርያርክ የምርጫ ሂደት ወደ ምርጫ ከመገባቱ በፊት ከሁሉም አስቀድሞ እንዲህ ዓይነት ለእግዚአብሔር ቦታ የሚሰጥ መንፈሳዊነትና ቀኖናዊነት ያለው የምርጫ ሕግ ሊወጣ ይገባዋል፡፡ በምርጫው ሂደት በአንድ በኩል የተለያየ ዓላማና ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እጃቸውን እንዳያስገቡ በመካላከልና በመጠበቅ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር እንዲመርጥልን የልባችንን በር እንክፈትለት፣ መንገዱንም አንዝጋበት – “አርኁ ኆኃተ መኳንንት ወይባእ ንጉሠ ስብሐት – እናንተ መኳንንት በሮችን ክፈቱ፣ የክብርም ንጉሥ ይግባ” እያለ ይጣራል፡፡ መዝ. 23፡9
2. ምን ጊዜም ለመንፈሳዊነትና ለቀኖናዊነት ቅድሚያውን እንስጥ
ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊት አካል ናት፣ አካልነቷም የክርስቶስ ነው፡፡ በርግጥ ይህን መንፈሳዊነት ለመጠበቅ አስተዳደራዊና መዋቅራዊ አሠራር የሚያስፈልግ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ግን ቅድሚያ ሊሰጠው ብቻ ሳይሆን ምን ጊዜም ታላቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን ኅብረት (Communion of Saints) የመሆኗ ነገር ነው፡፡ አንድ የቤተ ክርስቲያን አባት (ፓትርያርክ) በአስተዳደራዊ ችሎታውና አሠራሩ የተዋጣለት ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን መንፈሳዊነት ከተለየው ቤተ ክርስቲያንን እንደ አንድ ዓለማዊ ተቋም ወይም ድርጅት ሊያስመስላት ይችል እንደሆነ እንጂ ቤተ ክርስቲያን አያሰኛትም፤ ቤተ ክርስቲያንን “ቤተ ክርስቲያን” የሚያሰኛት በውስጧ ያለው መዋቅር፣ የሰው ኃይል፣ የገንዘብ መጠን፣ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት፣ . . . ሳይሆን ከእግዚአብሔርና ከቅዱሳን ጋር ያላት ኅብረትና አንድነት ነው፡፡ እነዚያ አያስፈልጉም ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው፣ ዋናውና መሠረቱ አይዘንጋ ለማለት እንጂ፡፡
ቤተ ክርስቲያንን በፓትርያርክነት የሚመራ አባት ይቅርና በቅስና ደረጃ ካሉት ጀምሮ በተለያየ ደረጃ ያሉት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና አባቶች በእውቀት ከሌላው ተሽለውና ልቀው መገኘት እንጂ አንሰው ወደ ኋላ መቅረትና ቤተ ክርስቲያንን ማሳፈርና ማስናቅ የለባቸውም፡፡ ከመንፈሳዊው ባሻገር በሳይንሱም በጣም የተማረ የነበረ አንድ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ በአንድ የሳይንቲስቶች የጥናት ጉባኤ ላይ ተገኝቶ ንግግር ሲያደርግ “እስከ ግድግዳው ድረስ ከእናንተ ጋር እኩል እናያለን፣ ከዚያ ባሻገር ያለውንና እናንተ የማታዩትን ደግሞ እኛ ብቻ እናያለን” እንዳለው መናገር የሚችሉ አባቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ሆኖም ግን ለቤተ ክርስቲያን አባትነት ዋናው መለኪያ እንዲህ ያለው ዓለማዊ ጥበብና እውቀት አይደለም፡፡ ይህ ሲኖርና ከመንፈሳዊነት ላይ ሲደረብ በእጅጉ የሚጠቅም ሙሉ ጌጥ ይሆናል፡፡ ብቻውን ግን የትም አያደርስም፡፡
አንድ የቤተ ክርስቲያን አባት በቋንቋ ችሎታውና በዲፕሎማሲው ቤተ ክርስቲያንን ከሌላው ዓለም ጋር ማስተዋወቁ መልካም ነገር ነው፡፡ ሆኖም ግን ከእግዚአብሔር ጋር እስካላገናኘንና ከቅዱሳን ጋር ያለውን የመንፈስ አንድነት እስካልጠበቀ ድረስ ከሌሎች መንግሥታትና ድርጅቶች ጋር ስላገናኘን በዚህ ብቻ ቤተ ክርስቲያን ልትጠቀም አትችልም፡፡ ስለዚህ ምን ጊዜም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊነት መጠበቁና ማስጠበቁ ላይ ነው፡፡
እያንዳንዳችንም በመጀመሪያ ከክርስቶስ ጋር አብረን በቤተ ክርስቲያን ሳንሠራና የአካሉ አንድ ክፍል (ብልት) ሳንሆን ስለ አካሉ በማሰብና በመናገር ብቻ ራሳችንንም ቤተ ክርስቲያንንም ልንጠቅም አንችልም፡፡ ጌታችን “እኔ የወይን ግንድ ነኝ፣ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ” እንዳለ በመጀመሪያ ከግንዱ ያልተቆረጥን ስለመሆናችን እናስብ፡፡ ተቆርጦ የወደቀና ከግንዱ ውጭ የሆነ ክብርና ምስጋና ይግባውና ጌታችን በቅዱስ ቃሉ እንደ ተናገረው “በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል፣ ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሏቸዋል፣ ያቃጥሏቸውማል” ብላል፡፡ በአንጻሩ በእርሱ ለሚኖሩት ደግሞ እንዲህ ይላል፡- “በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ፤ ይሆንላችሁማል፡፡” ዮሐ. 15፡1-7
ምድራዊ የሆኑ መሥፈርቶችን ዋና ጉዳዮች በማድረግ መሠረታዊ የሆነውን ፈሪሃ እግዚአብሔርን፣ ሃይማኖተኛነትን፣ ቅንነትን፣ ትሑትነትን፣ ወዘተ ችላ በማለት የምናደርገው ነገር እንዳይኖር ወደ ራሳችን መመለስ ያለብን ትክክለኛ ጊዜ ላይ ያለን ይመስላል፡፡ ጌታችን “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥቱንና ጽድቁን ሹ ፈልጉ፣ ሌላው ሁሉ ይጨመርላችኋል” ያለው ለዚህ ነው፡፡ ማቴ. 6፡33 የእግዚአብሔርን መንግሥት፣ ጽድቅን የሚሻ ሰው ወድቆ አይወድቅም፣ ተሻግሮ ያሻግራል፣ ጸሎቱ ይጠቅማል፡፡ በተቃራኒው ምድራዊ የሆነ እውቀት፣ ችሎታ፣ ልምድ፣ . . . ላይ የምንመሠረት ከሆነ ግን በአሸዋ ላይ እንደ ተሠራው ቤት አንድ ነገር ሲነካው ፈጥኖ ይወድቅና በውስጡ የተጠለሉበትን ሁሉ ጉዳት ያደርስባቸዋል፡፡ ስለሆነም ከውጭ ሰዎች ጋር መነጋገር ስለመቻሉ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት መነጋገር ስለመቻሉ፣ ከቅዱሳን ጋር ኅብረት ያለውና እኛንም ወደዚያ የሚመራን ስለመሆኑ ቅድሚያ ሰጥተን እናስብ፡፡ መንፈሳዊ የሆነውን ነገር ስንመኝና ስንፈልግ የልባችንን መሻት የሚያይ እግዚአብሔር እንደ ፈቃዱ የሆነ መሻታችንን ተመልክቶ የተመኘነውን አይነሳንም፡፡ ነገር ግን ምኞታችን ምድራዊና ኃላፊ ጠፊ ስለሆነው ነገር ከሆነ “ወወሀቦሙ ለፍትወቶሙ – እግዚአብሔር ለፈቃዳቸው አሳልፎ ሰጣቸው” እንደ ተባለው ለዚያው ለተመኘነው ነገር አሳልፎ ይሰጠናል፡፡
3. ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅመውን ሃሳብ ብቻ ለመከተል ቁርጥ ሕሊና ይኑረን
ሃሳባችንንና ድርጊታችንን የሚመራው ገዢ ሃሳብ ሐዋርያዊትና ቅድስት ለሆነችው ቤተ ክርስቲያናችን ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም የሚለው እንጂ ግለሰባዊ ወይም ቡድናዊና አካባቢያዊ (ጎጣዊ) ጥቅማ ጥቅም ስሌት ሊሆን አይገባውም፡፡ በእውነቱ ከሆነ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ለአንድ ክርስቲያን የሚገባ አይደለም፣ ሃይማኖት ከማጣት የሚመጣ ክፉ ደዌ ነው፡፡ በየጎጡና መንደሩ የምናስብና ሃሳባችን ሁሉ በዚህ የሚቃኝ ከሆነ ስለ አንዲት ቤተ ክርስቲያን በጋራ ማሰብ እንዴት ይቻለናል? ጌታችን “እርስ በርሷ የምትከፋፈል ቤት አትጸናም” በማለት እንደ ነገረን ለሁላችንም የሚጠቅም ነገር ለማግኘት እንዴት አንችላለን?
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ”ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፣ . . . እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፣ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ ሃሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን” በማለት በብርቱ የተማጸነው፡፡ ይህ በሽታ በየትኛውም የሥልጣንም ሆነ የትምህርት ደረጃ ያሉ ሰዎችን ሊጸናወት የሚችል ክፉ ደዌ እንደ ሆነ ስለተረዳ ነው፡፡ ፊል. 2፡3-5 “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ” ሲል አሳሰበን፡፡ እስኪ ይህን የእግዚአብሔር ጽኑ ማሳሰቢያ ስለ እግዚአብሔር ብለን ቆም ብለን እናስተውለው፡፡ ይህ ማለት እያንዳንዱ ለራሱ መንደር ወይም ጎጥ የሚጠቅመውን ብቻ እያሰላ ከዚያ አንጻር የሚሄድ ከሆነ ውጤቱ ብቻ ሳይሆን አስተሳሰቡ በራሱ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና በአበው ቀኖና የተወገዘ ነው፡፡ እንዲህ የሚያስብ ሰው በቤተ ክርስቲያን አንድነት በሰው ልጅ ወንድማማችነትና እኩልነት የማያምን ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ይህ ዓይነት አስተሳሰብ ከእኛ ይርቅ ዘንድ በቅዱሳት መጻሕፍት እንዲህ ምክርና ተግሣጽ የተሰጠበት ጉዳይ ቢሆንም በብዙዎቻችን ዘንድ እንደ መልካም ሃሳብ ተቆጥሮ በልቡናችን ተንሰራፍቶና ተደራጅቶ የተቀመጠ መሆኑ ነው፡፡
ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ የሆነችው የአርሜንያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በ1995 (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር) በተካሄደው የፓትርያርካቸው ምርጫ ላይ የተካፈሉ መራጮች ከመምረጣቸው በፊት ከዚህ በታች የተመለከተውን ቃለ መሀላ እንዲፈጽሙ ያደረገችው ለዚህ ነበር፡፡ ቃለ መሀላው እንዲህ ይላል፡-
“እኔ ከዚህ በታች የፈረምኩት፣ ካቶሊኮስ (እነርሱ ፓትርያርካቸውን ካቶሊኮስ ነው የሚሉት – ዓለም አቀፋዊ አባት ለማለት) ለመምረጥ በቤ/ክ የተወከልኩት፣ ከፊታችን ባለው የመላዋ አርሜንያውያን ካቶሊኮስ ምርጫ ላይ በጥንቃቄና በማስተዋል፣ ያለ አድልዎ፣ ለቦታው ይሆናል የምለውን ሰው ብቻና ያለ ምንም ግላዊ ፍላጎት፣ እገሌ ቢሆን ከሚል ነገር ራሴን አርቄና ነጻ አድርጌ፣ ከውስጤ ማንኛውንም ዓይነት ክፋትና ተንኮል፣ ጥላቻ፣ ቅናትና ምቀኝነት ወይም የዝምድናም ሆነ የጓደኛነት ትስስር ወይም ቅርበት አርቄ፣ ለክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እረኛና ታማኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ ይሆናል ብዬ የማስበውን ብቻ የምመርጥ መሆኔን በቅዱስ ወንጌሉ ፊት በኃያሉ በእግዚአብሔር ስም እምላለሁ፡፡ “ተስፋዬ በሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ ቃል እንደ ገባሁት ባላደርግ ግን ራሴን ለመንፈሳውያን ወንድሞቼ ወቀሳ አጋልጣለሁ፣ በዚህም ዓለምም ሆነ በሚመጣው ዓለም በታላቁ የፍርድ ቀን በእግዚአብሔር ፊት እጠየቅበታለሁ፡፡ ቃለ መሀላዬን ለመግለጽ ፍትሐዊ ምርጫ ይሆን ዘንድ የመድኃኒታችንን ቅዱስ ወንጌልና መስቀሉን አስማለሁ፡፡ አሜን፡፡”