ዘመነ ትንሣኤ
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሚያዚያ ፲፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ከሚከበርበት ዕለተ እሑድ አንሥቶ እስከ የሚቀጥለው እሑድ ያሉት ቀናት ለእያንዳንዳቸው ዕለታት ስያሜ ተሰጥቷቸው ፍቅሩን እያሰብን ውለታውን እያስታወስን እናዘክራቸዋለን፡፡
የትንሣኤ ማግሥት/ ሰኞ ማዕዶት (ሽግግር) ወይም ፀአተ ሲኦል
ነፍሳት ከሲኦል እሥራት ነጻ መውጣታቸው እንዲሁም ከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገራቸው የሚታሰብበት ዕለት ነው፡፡ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለ፶፻፭፻ (አምስት ሺህ አምስት መቶ) ዘመን በሲኦል እስራት፣ በጠላት ዲያቢሎስ ግዛት የነበሩትን ነፍሳት ነጻ አውጥቶ አዳምና ልጆቹን ወደ ቀድሞ ርስታቸው የመለሰበት ዕለት መታሰቢያ ነው፡፡ ይህቺን ዕለት አጥተን የነበረውን ነጻነት ማግኘታችንን፣ ባርነቱ ቀርቶ ዳግመኛ ልጆች መሆናችንን፣ ሰላም ይናፍቁ የነበሩ አዳምና ልጆቹ ሰላማቸው ታውጆ፣ ጭንቀታቸው ርቆ፣ በደስታ ወደ ገነት መመለሳቸውን እናስብበታልን፡፡
ማክሰኞ /ማግ ሰኞ/ ቶማስ
ጌታችን መነሣቱን ለቅዱሳን ሐዋርያተ በገለጸ ጊዜ በቦታው ሐዋርያ ቶማስ አልነበረምና የጌታንን ትንሣኤ ሲነግሩት ካላየሁ አላምንም በማለቱ ጌታችን እርሱ ባለበት ዳግመኛ ለሐዋርያ ተገለጸ፤ ቅዱስ ቶማስንም ‹‹..ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንክ እንጂ ያላመንክ አትሁን›› አለው፡፡ ( ዮሐ.፳፥፳፯) ቅዱስ ቶማስም የእጆቹን ጣቶች ጌታችን በዕለተ ዓርብ ሌንጊኖስ በተባለ ጭፍራ በወጋው ጎኑ ሰደደ፤ የዚህን ጊዜ እጁ ኩምትር አለች፤ ቅዱስ ቶማስም ‹‹ጌታዬ አምላኬ›› ብሎ መስክሯል፡፡ የዚህን ድንቅ ተአምራት መታሰቢያ ከትንሣኤ ማግሥት ባለው ሰኞ ማግሥት ይታሰባል፡፡
ረቡዕ /አልዓዛር/
አልአዛር ማለት ‹እግዚአብሔር ረድቷል› ማለት ነው፤ ጌታችን ከሞት ያስነሣው የማርያና የማርታ ወንድም ነው፤ በቢታንያ ይኖር የነበረው የጌታችን ወዳጅ አልዓዛር ታሞ ሞተ፤ በዚህን ጊዜ ጌታችን በዚያ ሥፍራ አልነበረምና እንደ አምላክነቱ ባለበት ቦታ ሆኖ የወዳጁ አልዓዛርን መሞት አወቀ፤ ደቀ መዛሙርቱንም ‹‹ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል፤ ላነቃው እሄዳለሁ›› አላቸው፤ ወደ ቢታንም መጣ ከሞተ ዐራት ቀን የሆነውን አልዓዛርን ከመቃብር አስነሳው፤ ጌታችን ይህን ድንቅ ተአምር ማድረጉን በዚህ ወቅት ታሰባል፡፡ (ዮሐ.፲፩፥፲፩-፵፬)
ሐሙስ ፡-አዳም ሐሙስ
አዳም በበደለ ጊዜ በደሉን አምኖ ንስሓ ገባ፤ ተጸጸተ፤ እግዚአብሔርን መበደሉንና ትእዛዙን መጣሱን አምኖ ለብዙ ዓመት ሲያለቅስ ኖረ፤ ጠላትም አስጨንቆ ገዛው፤ የዕዳ ደብዳቤ አጽፎ ‹አዳም ገብሩ ለዲያቢሎስ፣ ሔዋን ዓመቷ ለዲያቢሎስ› የሚል የዕዳ ደብዳቤ አጻፋቸው፤ አዳምም ስለበዱሉ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ጌታችንም የአዳምን መጸጸትና መመለስ ተቀብሎለት አምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ኪዳን ገባለት፤ ይህም ዕለት በዚህ ቀን ይታሰባል፤ አዳም ሐሙስ መባሉ ለዚህ ነው፡፡
ዓርብ፡- ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
በዚህ ዕለት የሚታሰበው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክቡር ደሙ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንደመሠረተ ነው፡፡ በሐዋርያት ሥራ ላይ ቅዱስ ሉቃስ ‹‹…እግዚአብሔር በደሙ የዋጃትን ቤተክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመ ….›› በማለት እንደገለጸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው፡፡ (የሐ.ሥራ ፳፥፳፰) ይህ ዕለት የዚህ መታሰቢያው ነው፡፡
ቅዳሜ ፡-ቅዱሳን አንስት
ከመቶ ሃያው ቤተሰብ መካከል ሰላሣ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ናቸው፤ የትንሣኤውን ብሥራት ሰምተዋልና ‹‹..መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው፤ እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤ እንደተናገረ ተነሥቷልና፤ በዚህ የለም የተኛበትን ሥፍራ ኑና እዩ……በፍርሃትና በታላቅ ደስታም ፈጥነው ከመቃብር ሄዱ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ሊያወሩ ሮጡ፤ እነሆም ኢየሱስ አገኛቸውና ‹‹ደስ ይበላችሁ›› አላቸው እነርሱም ቀርበው ሰገዱለት ፡፡….›› (ማቴ.፳፰፥፭-፱) ከትንሣኤ በዓል በኋላ ያለው ቅዳሜ የጌታችንን ትንሣኤ ያበሠሩና የመሰከሩ ቅዱሳን አንስት የሚታሰቡበት ዕለት በመሆኑ ቅዱሳን አንስት ይባላል፡፡
እሑድ:- ዳግም ትንሣኤ
ጌታችን ዐሥሩ ደቀ መዛሙርት ባሉበት ቅዱስ ቶማስ ባልነበረበት ተገልጦ ስለነበር ቅዱስ ቶማስ ባለበት በዚህች ዕለት በዝግ ቤት ሳሉ ተገልጾላቸዋል፤ ‹‹..ከስምንት ቀን በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ደግመው በውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ቶማስን “ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን” አለው፡ቶማስም ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት፡፡›› (ዮሐ.፳፥፳፮-፳፰) በዚህም የተነሣ ይህ ዕለት ዳግም ትንሣኤ ተብሏል፡፡
መልካም ዘመነ ትንሣኤ!!!