ዐበይት አናቅጽ እና ዐሥራው
መምህር በትረማርያም አበባው
ጥር ፳፭ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? የእግዚአብሔር አምላካችን ስም የተመሰገነ ይሁን! ባለፈው የትምህርታችን ክፍለ ጊዜ ስምንቱን ስለ አዕማድ አስተምረናችሁ ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ለሰጠናችሁ መልመጃ ምላሽና አምስቱ አዕማድን እንመለከታለን፤ በጥሞና ተከታተሉን!
የመልመጃ ጥያቄዎች
የሚከተሉትን ግሦች አዕማድ አውጡ!
፩ኛ) ሰቀለ….ሰቀለ
፪ኛ) ወደሰ….አመሰገነ
፫ኛ) ኮነነ……ገዛ
መልሶች፦ ፩) ሰቀለ… ሰቀለ
ግእዝ | አማርኛ | |
አድራጊ | ሰቀለ | ሰቀለ |
ተደራጊ | ተሰቅለ | ተሰቀለ |
አስደራጊ | አስቀለ | አሰቀለ |
ተደራራጊ | ተሳቀለ | ተሰቃቀለ |
አደራራጊ | አስተሳቀለ | አሰቃቀለ |
፪) ወደሰ.. አመሰገነ
ግእዝ | አማርኛ | |
አድራጊ | ወደሰ | አመሰገነ |
ተደራጊ | ተወደሰ | ተመሰገነ |
አስደራጊ | አወደሰ | አስመሰገነ |
ተደራራጊ | ተዋደሰ | ተሰቃቀለ |
አደራራጊ | አስተዋደሰ | ተመሰጋገነ |
፫) ኮነነ…ገዛ
ግእዝ | አማርኛ | |
አድራጊ | ኮነነ | ገዛ |
ተደራጊ | ተኮነነ | ተገዛ |
አስደራጊ | አኮነነ | አስገዛ |
ተደራራጊ | ተኩዋነነ | ተገዛዛ |
አደራራጊ | አስተኩዋነነ | አገዛዛ |
ውድ አንባብያን! የጥያቆዎችን መልሶች በትክክል አግኝታችኋል ብለን ተስፋ እያደረግን ወደ ዛሬው ትምህርታችን እናልፋለን፡፡
ዐበይት አናቅጽ
ዐበይት አናቅጽ የሚባሉት ዓረፍተ ነገር ማሰር የሚችሉ የዓረፍተ ነገር መቋጫዎች ሲሆኑ እነዚህም ቀዳማይ አንቀጽ፣ ካልኣይ አንቀጽ (ትንቢት አንቀጽ) እና ትእዛዝ አንቀጽ ናቸው። ከእነዚህ ጋር አያይዘን ምንም እንኳ ቁጥሩ ከዐበይት አናቅጽ ባይሆንም በአረባብ አንድ ላይ ስለሚገሠሥ ዘንድ አንቀጽንም እንመለከታለን። ቀዳማይ አንቀጽ የሚባለው ያለፈ ነገርን የሚያመለክት አንቀጽ ሲሆን፣ ካልኣይ አንቀጽ ደግሞ ትንቢትን ወይም ወደፊት የሚደረግን ድርጊት የሚገልጽ ነው። ትእዛዝ አንቀጽ ደግሞ እንደ ስሙ ትእዛዝን የሚያመለክት አንቀጽ ነው። ዘንድ አንቀጽ ብቻውን ማሠሪያ መሆን የማይችል ሲሆን ወደ አማርኛ በሚተረጎምበት ጊዜ ‹ዘንድ› የሚለውን ቃል አስከትሎ የሚተረጎም ነው። ለምሳሌ ‹‹ይኩን›› ቢል በአማርኛ ሲተረጎም ‹ይሆን ዘንድ› ተብሎ ይተረጎማል።
ዐሥራው የሚባሉት ደግሞ ከቀዳማይ አንቀጹ ላይ ካልኣይ አንቀጽን፣ ዘንድ አንቀጽን እና ትእዛዝ አንቀጽን የሚያስገኙልን ፊደላት ናቸው። እነዚህም ‹ይ፣ ት፣ እ፣ ን› ናቸው። እነዚህም በግእዝ ማለትም ‹የ፣ ተ፣ አ፣ ነ› ሆነው ወይም በራብዕ ማለትም ‹ያ፣ ታ፣ ኣ፣ ና› እና ከላይ በመጀመሪያ ባለው መልኩ በሳድስ ሊገኙ ይችላሉ። መደበኛው ሳድሳቸው ማለትም ‹ይ፣ ት፣ እ፣ ን› ነው። ሌላው በአመል የሚወጣ ነው። ይህን ወደፊት እንመለከተዋለን። ‹ይ› ለሦስተኛ መደቦች ለውእቱ፣ ለውእቶሙ እና ለውእቶን ዝርዝር ይሆናል። ‹ት› ከሦስተኛ መደቦች ለይእቲ እና ለሁለተኛ መደቦች ለአንተ፣ ለአንትሙ፣ ለአንቲ እና ለአንትን ይሆናል። ‹እ› ለአነ ብቻ ይሆናል። ‹ን› ለንሕነ ብቻ ይሆናል። ለምሳሌ ውእቱ ሰበከ የሚለውን ግሥ በዐበይት አናቅጽ እና በዘንድ ስንገልጸው እንደሚከተለው ይሆናል።
ግእዝ=አማርኛ
ቀዳማይ አንቀጽ=ሰበከ=አስተማረ
ካልኣይ አንቀጽ=ይሰብክ=ያስተምራል
ዘንድ አንቀጽ=ይስብክ=ያስተምር ዘንድ
ትእዛዝ አንቀጽ=ይስብክ=ያስተምር
አስተውሉ! ለምሳሌ ከላይ ያለውን ብንመለከት ሰበከ ቀዳማይ አንቀጽ ነው። የዚህ ካልአይ አንቀጹ ይሰብክ ‹ይ› ን እንደጨመረ ከዚያ ‹ሰ› ባለችበት ግእዝ መሆኗ ‹ብ› እና ‹ክ› ወደ ሳድስ ፊደል እንደተለወጡ፤ በዘንድ እና በትእዛዝ አንቀጽ ጊዜ ደግሞ አሥራው ‹ይ› እንዳለ ሆኖ ‹ሰ› ስ ‹በ› ብ ‹ከ› ክ ወደ ሳድስ ተቀይረዋል። ይህ የፊደላት ቅርጽ በስምንቱ አርእስተ ግሥ እና በቆመ፣ በገብረ፣ በሤመ እና በነደ፣ ምን ይመስላል የሚለውን ቀጥለን እንመልከት።
በቅደም ተከተል መጀመሪያው ቀዳማይ አንቀጽ፣ ቀጥሎ ያለው ካልአይ አንቀጽ፣ ከዚያ ሦስተኛ ላይ ያለው ዘንድ አንቀጽ ሲሆን መጨረሻ ላይ ያለው ደግሞ ትእዛዝ አንቀጽ ነው። ዘንድ አንቀጽና ትእዛዝ አንቀጽ የሚለያዩት በሁለተኛ መደቦች ጊዜ ነው እንጂ በሌላው ተመሳሳይ የሆሄያት ቅርጽና ንባብ አላቸው። ካልአይ አንቀጽ ጠብቆ ይነበባል። ማለትም ቅድመ መድረሻው ይጠብቃል። ለምሳሌ ይቀትል ካለው ‹ት› ይጠብቃል ማለታችን ነው።
፩) ቀተለ ገደለ
ይቀትል- ይገድላል
ይቅትል- ይገድል ዘንድ
ይቅትል- ይግደል
፪) ቀደሰ- አመሰገነ
ይቄድስ- ያመሰግናል
ይቀድስ- ያመሰግን ዘንድ
ይቀ ድስ- ያመስግን
፫) ተንበለ- ለመነ
ይተነብል-ይለምናል
ይተንብል-ይለምን ዘንድ
ይተንብል-ይለምን
፬) ባረከ አመሰገነ
ይባርክ-ያመሰግናል
ይባርክ-ያመሰግን ዘንድ
ይባርክ-ያመስግን
፭) ዴገነ-ተከተለ
ይዴግን-ይከተላል
ይዴግን-ይከተል ዘንድ
ይዴግን-ይከተል
፮) ክህለ-ቻለ
ይክህል/ይክል ይችላል
ይክሀል- ይችል ዘንድ
ይክሀል-ይቻል
፯) ጦመረ-ጻፈ
ይጦምር-ይጽፋል
ይጦምር-ይጽፍ ዘንድ
ይጦምር-ይጻፍ
፰) ማሕረከ-ማረከ
ይማሐርክ-ይማርካል
ይማሕርክ-ይማርክ ዘንድ
ይማሕርክ-ይማርክ
፱) ቆመ-ቆመ
ይቀውም-ይቆማል
ይቁም-ይቆም ዘንድ
ይቁም-ይቁም
፲) ሤመ-ሾመ
ይሠይም-ይሾማል
ይሢም-ይሾም ዘንድ
ይሢም-ይሹም
፲፩) ገብረ-ሠራ
ይገብር-ይሠራል
ይግበር-ይሠራ ዘንድ
ይግበር-ይሥራ
፲፪) ነደ-ነደደ
ይነድድ-ይነዳል
ይንድድ-ይነድ ዘንድ
ይንድድ-ይንደድ
የአንድ ግሥ አርእስቱ ከታወቀ አርእስቱን መስሎ እንደሚረባ አስተውሉ። የዴገነ፣ የጦመረ እና የባረከ ቤቶች ከካልኣይ አንቀጽ እስከ ትእዛዝ አንቀጽ ተመሳሳይ የሆሄያት አወቃቀር ያላቸው ሲሆን ካልኣይ አንቀጹ በአነባበብ ይለያል። ይሄውም ይባርክ ሲል ‹ር› ጠብቆ ይነበባል። በዘንድ እና በትእዛዝ ያለው ‹ይባርክ› ግን ‹ር› ላልቶ ይነበባል። የዴገነ እና የጦመረም ይህንኑ ይመስላል። ይህ ከላይ ያየነው በውእቱ ሲዘረዘር ነው። በዐሥሩም መራሕያን ሲዘረዘር ደግሞ እንደሚከተለው ነው።
፩) ውእቱ-ቀደሰ አመሰገነ
ይቄድስ-ያመሰግናል
ይቀድስ- ያመሰግን ዘንድ
ይቀድስ-ያመስግን
፪) ውእቶሙ ቀደሱ አመሰገኑ
ይቄድሱ-ያመሰግናሉ
ይቀድሱ-ያመሰግኑ ዘንድ
ይቀድሱ-ያመስግኑ
፫) ይእቲ ቀደሰት-አመሰገነች
ትቄድስ-ታመሰግናለች
ትቀድስ-ታመሰግን ዘንድ
ትቀድስ-ታመስግን
፬) ውእቶን ቀደሳ- አመሰገኑ (ሴቶች)
ይቄድሳ-ያመሰግናሉ
ይቀድሳ-ያመሰግኑ ዘንድ
ይቀድሳ-ያመስግኑ
፭) አንተ ቀደስከ-አመሰገንክ
ትቄድስ-ታመሰግናለህ
ትቀድስ-ታመሰግን ዘንድ
ቀድስ-አመስግን
፮) አንትሙ ቀደስክሙ አመሰገናችሁ
ትቄድሱ-ታመሰግናላችሁ
ትቀድሱ-ታመሰግኑ ዘንድ
ቀድሱ-አመስግኑ
፯) አንቲ ቀደስኪ- አመሰገንሽ
ትቄድሲ-ታመሰግኛለሽ
ትቀድሲ-ታመሰግኚ ዘንድ
ቀድሲ-አመስግኚ
፰) አንትን ቀደስክን- አመሰገናችሁ (ሴቶች)
ትቄድሳ-ታመሰግናላችሁ
ትቀድሳ-ታመሰግኑ ዘንድ
ቀድሳ-አመስግኑ
፱) አነ ቀደስኩ- አመሰገንኩ
እቄድስ-አመሰግናለሁ
እቀድስ-አመሰግን ዘንድ
እቀድስ-ላመስግን
፲) ንሕነ ቀደስነ- አመሰገንን
ንቄድስ-እናመሰግናለን
ንቀድስ-እናመሰግን ዘንድ
ንቀድስ-እናመስግን
የሌሎች አርእስተ ግሦች ይህንን መስሎ ይዘረዘራል። በሁለተኛ መደቦች ማለትም በአንተ፣ በአንትሙ፣ በአንቲ፣ በአንትን ትእዛዝ ጊዜ አሥራው እንደሌለ አስተውል። በን ሕነ ጊዜ አሥራው ‹ን› በአነ ጊዜ አሥራው ‹እ› እንደሆነም አስተውል። በውእቱ፣ በውእቶሙ እና በውእቶን ጊዜ አሥራው ‹ይ› እንደሆነ እና በይእቲ እና በሁለተኛ መደቦች ደግሞ አሥራው ‹ት› እንደሆነም አስተውል።
የመልመጃ ጥያቄዎች
የሚከተሉትን ቃላት ከቀዳማይ እስከ ትእዛዝ አንቀጽ ዘርዝር።
፩) ኖመ-ተኛ (ቆመ)
፪) ጠበ-ብልሃተኛ ሆነ (ነደ)
፫) ሠምረ-ወደደ (ገብረ)
፬) ዘገበ-ሰበሰበ (ቀተለ)
፭) መነነ-ናቀ (ቀደሰ)
፮) ናፈቀ-ተጠራጠረ (ባረከ)
፯) ፄወወ-ማረከ (ዴገነ)
፰) ሞቅሐ-አሰረ (ጦመረ)