‹‹ወደ አንተ የጮኹሁትን የልመናዬን ቃል ስማ›› (መዝ.፳፯፥፪)
ካለፈው የቀጠለ…
ነሐሴ ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
መሪር በሆነችው በዚህች ዓለም ስንኖር እኛ ሰዎች ብዙ ችግርና ፈተና ሲያጋጥመንም ሆነ ለተለያዩ ሕመምና በሽታ ስንዳረግ እንዲሁም ለአደጋ ስንጋለጥ ስሜታችንን አብዛኛውን ጊዜ የምንገልጸው በዕንባ ነው፡፡ በተለይም አንድ ሰው የተጣለ መስሎ ሲሰማው በኃጢአቱ ምክንያት ቅጣት እንደመጣበት ሲያስብ ያለቅሳል፡፡ ጸጋ እግዚአብሔር እንደተለየው እግዚአብሔርም በጠላቶቹ እጅ አሳልፎ እየሰጠው እንደሆነ ሲያስብ ወደ ለቅሶ የሚያስገቡ መንፈሳዊ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህም እጅግ ያዝናል፤ ያለቅሳልም፡፡ አንዳንዴ በፀፀት እና በንስሓ ውስጥ ሆኖ ያለቅሳል፤ አንዳንዴ ደግሞ እግዚአብሔርን እየወቀሰ ያለቅሳል፡፡
ነቢዩ ዳዊትም ፈተናና በችግሩ ጊዜ ያደረገው ይሄንኑ ነው፡፡ እንዲህም ብሏል፤ ‹‹አቤቱ ለምን ርቀህ ቆምህ? በመከራም ጊዜ ለምን ትሠወራለህ›› (መዝ.፲፥፩) አንዳንዴ እግዚአብሔር ሰው እንዲጣል ሳይሆን ለመንፈሳዊ ጥቅም መከራዎችን እንድንቀበል ፈቃዱ ይሆናል፡፡ አምላካችን ከልጆቹ አንዱ በዓለም ደስታ ምክንያት መዳኛ ዕንባዎች ከዓይኑ ደርቀው ሊመለከት ይችላል፡፡ በመሆኑም ከዓይኖቹ ዕንባን ሊያወጣለት ከዚያም በኋላ ዓይነ ልቦናውን ሊያጠራለት ሲፈልግ የሚቀበለውን መከራ ለበጎ ያስብለታል፡፡ ሌላው ቀርቶ እግዚአብሔር ከቅዱሳን መከራን አይከለክልም፡፡ በመዝሙርም ‹‹የፃድቃን መከራቸው ብዙ ነው፤ እግዚአብሔር ከሁሉ ያድናቸዋል›› ተብሎ ተጽፏል፡፡ (መዝ.፴፬፥፲፱) ቅዱሳኑ መከራ እንዲቀበሉ ያደርጋል፡፡ ከዚያም ይህ መከራ ከፍተኛ መንፈሳዊ ውጤት ላይ ሳይደርስ ከዚህ መከራ ያድናቸዋል፤ (ያወጣቸዋል)
ስለዚህ መከራና ለቅሶን በሁለት ዓይነት ሊከፈሉ ይችላሉ፤ አንደኛው ዓለማዊ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መንፈሳዊ ነው፡፡ የሰውን ሀብቱን ዝናውን ሥልጣኑን የሚጎዳ ዓለማዊ ፈተና /መከራ/ መጥቶበት በዓለም ባጣቸው ነገሮች የነበረውን ደስታ እያሰበ በማዘን ሊያለቅስ ይችላል፡፡ ምናልባት ለጉዳቱ እግዚአብሔር ምክንያት የሆነ ይመስል በእግዚአብሔር ላይ ሊያጉረመርም የተከፋም ሊሆን ይችላል፡፡ የዚህ ሰው ለቅሶ ኃጢአት ነው፡፡ ለቅሶው ከመሻቱ ጋር አብሮ የሚያልፈው ዓለም የነበረውንና ያለው ጽኑ ፍቅር እና በውስጡም የነበረውን ስሜት ይጠቁማል፡፡ (፩ኛዮሐ.፪፥፲፮) የዓለምን ደስታ በፈቃዱ የናቀ ሰው ግን በእነዚህ ነገሮች ልቡ አይነካም፡፡ ነገር ግን ‹‹እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔርም ነሳ፤ የአግዚአብሔርም ስም የተባረከ ይሁን›› በማለት ይጸናል፡፡ (ኢዩ.፩፥፳፩)
ሌላውም ደግሞ እጅግ ከባድ የሆነ ፈተናና ጫና ሲደረግበት የዓለምን ከነቱነት በመረዳት ሌላውን ዓለም ይመኛል፡፡ ይህ እውነት መንፈሳዊ ሰው ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይርቀው በመፍራት፣ ጌታንም እያሳዘነ መሆኑን በማሰብ የሚያለቅስ ከሆነ በዓለም መከራ ውስጥ ለጊዜው ሊተወው ይችላል፡፡ የዚህ ሰው ለቅሶ የሚሆነው መንፈሳዊ ነው፡፡ ከንስሓ፣ ከትሑት ልቦና ኃጢአትንም ከማመን ጋር የተዋሐደ ነው፡፡ በልቡም ‹‹የሆነብኝ ሁሉ በኃጢአቴ ምክንያት ከሚገባኝ በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡ ለእኔም እንደ ምስኪኑ አልዓዛር መከራዬን /ፍርዴን/ በምድር መፈጸሜ መልካም ነው›› ይላል፡፡ (ሉቃ. ፲፮፥፳፯) ከመዝሙረኛው ጋር እንዲህ እያለም ይዘመራል፡፡ ‹‹ሥርዓትህን እማር ዘንድ ያስጨከነኝ መልካም ሆነልኝ፡፡›› (መዝ.፻፲፱፥፸፩) እነዚህ ዕንባዎች በፊቱ እንደ ደስታ መዓዛ ይቀበላቸዋል፡፡ የማያለቅሱለትም መንፈሳዊ ተነሣሽነታቸውንም ይቀበላል፡፡
ነገረ ግን ፈተናዎች ከዲያብሎስም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሰው ድክመቱን በመረዳት ረድኤት እግዚአብሔርን በመጠየቅ ያነባል፡፡ ራሱን ከዚህ የውጊያ ኃይል ጋር አነፃፅሮ ደካማ መሆኑን በተረዳ ጊዜ መንፈሳዊ ዕንባ ይቀርበዋል፡፡ እንዳይወድቅ ይፈራልና፡፡ የጠላቱ ሐሳብ ሊያረክሰው ይችል ይሆናልና ያለቅሳል፡፡ ስለልቡ ንጽሕና፣ ሐሳብ እና ስሜት በመጠንቀቅ ያለቅሳል፡፡ የእግዚአብሔርንም ጸጋ ከእርሱ ጋር እንዲሆን በዕንባ ይጠይቃል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን በላከው መልእክት ውስጥ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፡፡›› (ዕብ.፲፪፥፬)
እንግዲህ ዕንባ ደም እስከ ማፍሰስ የሚያዳርገው ተጋድሎ አካል ነው፡፡ የተጋደለው ሰውም ‹‹ወደ አንተ የጮኹሁትን የልመናዬን ቃል ስማ›› ይላል፡፡ እንዲሁም ‹‹አትጣለኝ፤ ያላንተ አንዳች ላደረግ አልችልምና›› እያለ ይማጸናል፡፡ (መዝ.፳፯፥፪፣ ዮሐ.፲፯፥፯)
ክርስቲያናዊ ሕይወት በችግርና መከራ የተሞላች መሆኗ ለዚያም መፍትሔ ከአምላካችን እግዚአብሔር ዘንድ በምንሻበት ጊዜ ከልብ የመማጸናችን ድጋፍ ዕንባ ስለመሆኑ እውነታ በዚህ እንረዳለን፡፡ ጸሎታችን ወደ ፈጣሪያችን የሚደርስልንም በለቅሶ ስንለምነው እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ይህም ዘወትር ልንተገብረውና የሕይወታችን አንዱ አካል ልናደርገው የሚገባ ነገር ነው፡፡
በተለይም አሁን ካለንበት ወቅታዊ የሀገራዊና የቤተ ክርስቲያን ችግር እንዲያወጣን ከልብ በመነጨ ዕንባ ወደ እግዚአብሔር ልንጮህ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሀገራችንም ከዚያም አልፎ ተርፎ ዓለማችን በጥላቻ የተሞላች መሆኗ፣ በእርስ በርስ ጦርነት መታወካችን፣ ሰላም አጥተን የምንሠቃየው እንዲሁም አብረን መኖር እስኪያቅተን ድረስ መቻቻል የተሳነን ጊዜ ላይ መድረሳችን ሊያስጨንቀን ይገባልና ጊዜ ሳንጠጥ በንስሓ ወደ አምላካችን በመመለስ ይቅርታና ምሕረትን ልንማጸነው የሚገባው በለቅሶ ጭምር ነው፡፡ በፍልሰታ ጾምም ይህን መከራና ችግር እያሰብን ልናለቅስና ልንማጸነው ይገባል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ቸርነቱንና ምሕረቱን ያብዛልን፤ አሜን፡፡
ምንጭ፡ ‹‹ዕንባ በመንፈሳዊ ሕይወት›› በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ፣፳፻፻፰ ዓ.ም፣ በመጽሐፍ ቅዱስ- ብሉይና ሐዲስ ኪዳን