ወርኃ ጳጉሜን
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ነሐሴ፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? ጾመ ፍልሰታ እንዴት አለፈ? መቼም ደስ ብሏችሁ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ፣ በመማርና በማስቀደስ እንዳሳለፋችሁ ተስፋችን ነው፤ ልጆች! አዲስ ዓመት እየደረሰ በመሆኑ ትምህርት ለመጀመር እየተዘጋጃችሁ ነው? ባለፈው ዓመት በትምህርታችን ደከም ያለ ውጤት አስመዝግበን የነበርን ዘንድሮ በርትተን በመማር በጥሩ ውጤት ከክፍል ክፍል ለመሻገር ከአሁኑ መዘጋጀትና መበርታት አለብን፡፡ እንዲሁም ደግሞ ለአገርና ለቤተ ክርስቲያን እየጸለይን የሰላምን ዘመን ተስፋ እናድርግ! መልካም!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ባለፉት ጊዜያት ለእናንተ ያስተምራሉ በማለት በጻፍንላችሁ ጽሑፎች በርካታ ቁም ነገሮችን ስንማማር እንደነበር ታስታውሳላችሁ አይደል? አሁን ደግሞ የዚህን ዓመት የመጨረሻ የሆነውን ጽሑፍ ስለ ‘ወርኃ ጳጉሜን’ ጥቂት ልናካፍላችሁ ወደድን፤ መልካም ቆይታ!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ወርኃ ጳጉሜን በዓመቱ መጨረሻ የምትገኝ በአገራችን ኢትዮጵያ እንደ ፲፫ኛ (ዐሥራ ሦስተኛ) ወር የምትቆጠር ናት፤ ወርኃን ጳጉሜ አምስት ቀናት ያሏት ስትሆን በዐራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ሉቃስ መውጫ በዘመነ ዮሐንስ መግቢያ ያለው ስድስት ቀን ይሆናል፡፡ ጳጉሜን ማለት “ጭማሪ፣ ተውሳክ፣ አምስት ቀን፣ ሩብ፣ ከዐውደ ወር ተርፎ በዓመቱ መጨረሻ የተጨመረ ስለሆነ ትርፍ ተጨማሪ ይባላል፤ ወርኃ ጳጉሜን ዕለተ ምርያ (የመዳን ወር) ትባላለች፡፡ በዚህች ወቅት ጻድቁ ኢዮብ በባሕረ ዮርዳኖስ ተጠምቆ በሰውነቱ የነበረው ደዌ ዘለክብር (ለክብር የመጣ ሕመም) የዳነለት ወቅት በመሆኑ እንዲሁም ብዙዎችም ከሕመም የተፈወሱባት ወቅት በመሆኗ ዕለተ ምርያ (የመዳን ወር ) ትባላለች፤ ምእመናን ይህን ትውፊት መሠረት አድርገው በዚህች ወቅት ጸበል ይጠመቁበታል፡፡ በዚህች ወርኃ ጳጉሜን የሚታሰቡ በርካታ በዓላት አሉ፤ በጥቂት በጥቂቱ እንገራችሁ!
በዚህች ወር በሦስትኛው ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው በዓላት አንዱ የሊቀ መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል በዓል ነው፤ አንዲት ደግ ክርስቲያን ሴት በቅዱስ ሩፋኤል ስም በባሕር መካከል ባለች ደሴት ቤተ ክርስቲያን አሳነጸች፤ በወቅቱ የነበረው ሊቀ ጳጳሱ ቴዎፍሎስ በዚህች ዕለት ቅዳሴ ቤቱን አከበረ፤ ከደሴቲቱ ሥር የነበረ ግዙፍ ዓሣ ነባሪ ቤተ ክርስቲያኑን ያፈርስ ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው፤ ባሕሩን ባናወጠው ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗን ሊያፈርስ ደረሰ፤ በውስጧም ለበዓል ተሰብስበው የነበሩ ምእመናን በጸሎት ወደ ቅዱስ ሩፋኤል ተማጸኑ፤ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤልም ከእግዚአብሔር ተልኮ መጣ፤ ሕዝቡን ታደገ፤ ከደሴቲቱ ሥር ያለውንም ግዙፍ ዓሣ ነባሪ እንዳይንቀሳቀስ በጦር ወጋው፤ “እግዚአብሔር አዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጽ ጸጥ ብለህ ቁም!” አለው ጸጥ ብሎም ቆመ፤ ሕዝቡም ከባሕሩ ከመስጠም፣ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኒቱም ከመፍረስ ተረፈች፤ ቅዱስ ሩፋኤል ይህን ድንቅ ተአምር አድርጎ ከፈጣሪው አማልዶ ለጠሩት ፈጥኖ የደረሰበትን ይህን በዓል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓመቱ መጨረሻ ባለችው ወርኃ ጳጉሜን በሦስተኛው ቀን በድምቀት ታከብሯለች፡፡ ይህች ዕለት የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል የተሾመበት መታሰቢያ ነው፡፡
ይህች ዕለት ርኆተ ሰማይ (የሰማይ መስኮቶች የሚከፈቱባት) ሊቃውንቱ የሰማይ ደጆች ተከፍተው የምእመናን ጸሎት የሚርጉበት በዓመት ዐራት ጊዜያት እንዳሉ ይገልጻሉ፤ ታዲያ የመጀመሪያው ዕለት ጳጉሜ ሦስት ቀን በመሆኑ ይህች ዕለት ርኆተ ሰማይ ትባላለች፤ የሰማይ መስኮቶች ተከፍተው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል የምእመናንን ጸሎት ለእግዚአብሔር የሚያሳርግበት ዕለትም መታሰቢያ ነው፤ የእግዚአብሔር የምሕረት ደጆች የሚከፈቱባት ዕለት መታሰቢያ ናት፤ ርኆተ ሰማይ! አባቶች እናቶች በትውፊት በዚህች ዕለት ዝናም ሲዘንብ በእምነት የቤታቸውን ዕቃ (ሌማቱን፣የቡሀዕቃ…ከሰማይ በሚወርደው ዝናመ ምሕረት እንዲባረክላቸው ከውጭ አውጥተው ያስመቱታል፤ ምእመናን በዚህች ዕለት በሚዘንብ ዝናብ ይጠመቁበታል፤ በርኆተ ሰማይም በጳጉሜን ሦስት ቀን!!!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሌላው በዚህች ወር የዕለተ ምጽዓት መታሰቢያም ዕለት ናት፤ እግዚአብሔር ለፍርድ ወደዚህ ምድር የሚመጣበት ወቅት መታሰቢያ ነው፤ጌታችንም በደብረ ዘይት ተራራ ለደቀ መዛሙርቱ ዳግመኛ ለፍርድ እንደሚመጣ በገለጸው መሠረት ወደዚህ ምድር ለጻድቃን ሊፈርድላቸው፣ በኃጥአን ሊፈርድባቸው ይመጣል፤ ጌታችን መቼ እንደሚመጣ ዓመቱንና ዕለቲቱን በግልጽ ባይነግረንም ዳግመኛ ግን እንደሚመጣ ነግሮናል፤ ‹‹…ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና፡፡›› (ማቴ.፳፬፥፵፬) ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የዕለተ ምጽዓቱን መታሰቢያ በዐቢይ ጾም እኩለ ጾም ላይና በወርኃ ጳጉሜን ሦስተኛው ቀን የምጽዓቱን መታሰቢያ ታከብራለች፤ አምላካችን እግዚአብሔር ‹‹…ኑ እናንተ የአባቴ ቡሩካን…›› ከሚላቸው ወገን ይደምረን!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ወርኃ ጳጉሜን በጣም በአጭሩ ጻፍንላችሁ፤ ብዙ ምእመናን ይህችን ወር ጸበል በመጠመቅ በጾም በጸሎት (በሱባኤ) በፈቃደኝነት ያሳልፏታል፤ መጪው ዘመን የተቀደሰ እንዲሆን በመማጸን ለዚህ ወቅት ያደረሰንን እግዚአብሔር በማመስገን ያሳልፏታል፤ እኛም ልጆች አምላከችን ለእኛ የሠራልንን ውለታ እያሰብን ለሰዎች መልካም በማድረግ፣ አብዝተን ለአገራቸችን ሰላም ለሕዝባችን ፍቅር እየጸለይን ይህቺን ወርኃ ጳጉሜን እናሳልፍ፤ አምላካችን እግዚአብሔር በረከቱን ያድለን! ቸር ይግጠመን !
(ምንጭ ድርሳነ ቅዱስ ሩፋኤል የወርኃ ጳጉሜን፣ ስንክሳር ጳጉሜን ሦስት)
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!