ከአጤ ዋሻ ተዘርፎ የነበረው ታቦተ መድኃኔዓለም ወደ መንበረ ክብሩ ተመለሰ

 ሰኔ 27 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

a 27 2006 1 1ከሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ደብረ ብርሃን ከተማ በአሥር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የአጤ ዋሻ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተዘርፎ ጅቡቲ ውስጥ ለ17 ዓመታት ተደብቆ የነበረው ታቦተ መድኃኔዓለም ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ወደ መንበረ ክብሩ ገብቷል፡፡ /ሚያዚያ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ታቦቱ ከጅቡቲ ወደ አዲስ አበባ መግባቱን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል/፡፡ 

ታቦቱ ሐምሌ 27 ቀን 1989 ዓ.ም. ሌሊት ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች ተሰርቆ ለ17 ዓመታት ጅቡቲ ውስጥ በአንድ የሌላ እምነት ተከታይ ቤት ውስጥ ተደብቆ ከቆየ በኋላ ጅቡቲ ለሚገኘው ለምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳደሪ ለአባ ዮናስ መልከ ጼዲቅ ከቤተሰቡ መካከል በአንዱ መረጃው ይደርሳቸዋል፡፡ አባ ዮናስ በደረሳቸው መረጃ መሠረት ለጠቅላይ ቤተ ክህነት በማሳወቅ ታቦቱን ለማስመለስ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡

a 27 2006 1 2ሚያዚያ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የቅርስ ጥበቃና ቤተ መዘክር ለጊዜው እንዲቀመጥ በማድረግ፤ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ወደ አጤ ዋሻ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አሸኛኘት ተደርጎለታል፡፡

የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ መዘምራንና ምእመናን በደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ለታቦቱ ደማቅ አቀባበል በማድረግ በአጤ ዋሻ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ወደ መንበረ በክብሩ አስገብተውታል፡፡

ብፁዕነታቸው በሰጡት ቃለ ምእዳን ለታቦቱ መመለስ ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ አካላት ምሥጋናቸውን አቅርበው ምእመናን በተለይም በየአጥቢያው የሚገኙ ወጣቶች ቤተ ክርስቲያንን እንዲጠብቁ የአደራ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ወደ አጤ ዋሻ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለመድረስ በጣም አስቸጋሪና ውጣ ውረድ የተሞላበት ገደልን መውረድ ስለሚጠይቅ በርካታ የቤተ ክርስቲያን የከበሩ ንዋያተ ቅድሳት በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ተሸሽገውበት እንደነበር የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋይ አባቶች ይገልጻሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የኢጣሊያ ጦር በአድዋ ጦርነት ድል እንዲነሱ ካደረጋቸው አንዱ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት በመሆኑ ይህንን ታቦት ለመዝረፍ ከ1928 ዓ.ም. ጀምሮ የኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ነገር ግን ለሃይማኖታቸውና ለሀገራቸው ፍጹም ፍቅር የነበራቸው አባቶች ታቦቱን ከቤተ መቅደስ በማውጣት ጦርነቱ እስኪያበቃ አጤ ዋሻ ወስደው ሸሽገውታል፡፡

ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ በ1937 ዓ.ም. ካህናቱ ታቦቱን አጅበው ከአጤ ዋሻ ወደ አዲስ አበባ መልሰውታል፡፡ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ካህናቱ በታማኝነት ታቦቱን ጠብቀው በማኖርና በክብር በመመለሳቸው በወርቅ የተለበጠ የመድኃኔዓለም ታቦት ይዘው እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡

ከ1937 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ይህ ታቦት በ1989 ዓ.ም. ተሰርቆ ጅቡቲ ውስጥ በሌላ እምነት ተከታይ ቤት ውስጥ ተደብቆ ቆይቷል፡፡ በቤቱ ውስጥ ደብቆ ያስቀመጠው ግለሰብ የተሰደደ ሲሆን፤ ሚስቱ ስታብድ ልጁ ሞቶበታል፡፡ በዚህ የተደናገጠው ሌላው የሰውየው ልጅ በቤታቸው ውስጥ ታቦት እንዳለና ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲወሰድ ራሱ መጥቶ መረጃ በመሥጠቱ ታቦቱ ወደነበረበት በክብር ተመልሷል፡፡