ከቡኢ ምድረ ከብድ የሚወስደው መንገድ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

የካቲት 13/2004 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

በጉራጌ ሀገረ ስብከት የሶዶ ወረዳ ዋና ከተማ ከሆነችው ቡኢ ከተማ ጀምሮ ምድረ ከብድ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ገዳም ድረስ የሚወስደው የ18 ኪ.ሜትር ጥርጊያ መንገድ በፌደራል መንገዶች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ሙሉ ትብብር ሥራው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የገዳሙ አበምኔት አባ አብርሃም ወ/ኢየሱስ ገለጹ፡፡

ከዚህ ቀደም ይኸው መንገድ በአካባቢው ምእመናን አማካይነት በእጅ ቁፋሮ፣ ድንጋይ በመሸከምና ከጉልበት እስከ ገንዘብ አስተዋጽዖ በማድረግ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነበር፡፡ ነገር ግን ከጊዜ ብዛት በመበላሸቱ በመኪናም ሆነ በእግር ወደ ገዳሙ ለመሔድ እጅግ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቋል፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ ገዳሙ ለክብረ በዓላትም ሆነ ለጉብኝት የሚመጡ ምእመናን በመቸገራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየቀነሰ መጥቷል፡፡

 

ሙሉ ወጪውን በመሸፈን መንገዱን በጥሩ ሁኔታ ሠርቶ ያስረከበውን የፌዴራል መንገዶች ባልሥልጣንን በእግዚአብሔር ስም ያመሰገኑት አበምኔቱ በመንገዱ መበላሸት ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የምእመናንና የገዳሙን ግንኙነት ለማጠናከር ይረዳል ብለዋል፡፡

 

ቀደም ሲል ገዳሙ ሰፊ የእርሻ መሬት ርስት የነበረው በመሆኑ በገዳሙ ውስጥ የሚገኙ መነኮሳትና መነኮሳይያት እርሻ በማረስና ሰብሎችን በመዝራት የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ይተዳደሩ እንደነበር የገዳሙ አበምኔት ተናግረው፤ በአሁኑ ወቅት ግን ገዳሙ በቂ የእርሻ መሬት የሌለው በመሆኑ መተዳደሪያ ያደረገው በዓመት ሁለት ጊዜያት ጥቅምት 5 እና መጋቢት 5 በጻድቁ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ዓመታዊ ክብረ በዓላት ከሚመጡ ምእመናን ከሚለግሱት የገንዘብና መባ አስተዋጽኦ ብቻ እንደሆነ የገዳሙ አበምኔት ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ገዳሙ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ለማጠናከርና በውስጡ የሚኖሩት መነኮሳት በችግር ምክንያት እንዳይበተኑ እንዲሁም ጥንታዊነቱንና ታሪካዊነቱን ጠብቆ ለማቆየት ከምእመናን ብዙ እንደሚጠበቅና በክብረ በዓላትም ሆነ በማንኛውም ጊዜ ገዳሙ ያለበትን ሁኔታ መጥተው በማየት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

 

ገዳሙ በንጉሥ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት  በራሳቸው በጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የተመሠረተ ሲሆን በጾምና ጸሎት የተጋደሉበት እንዲሁም ያረፉበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር