‹‹ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ!›› (ማቴ.፯፥፲፭)
ዲያቆን ዐቢይ ጌታሁን
ታኅሣሥ ፳፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
ነቢይ ማለት ተነበየ፣ ተናገረ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም ወደፊት ስለሚሆነውና ስለሚመጣው አስቀድሞ መናገር፣ መተንበይ ማለት ነው፡፡ ከዚህም በተመሳሳይ ‹ናቪ› ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ስያሜ ነው፤ መምራት፣ ማብሠር፣ መምከር፣ መንገር የሚል ትርጓሜም አለው፡፡ ይህ ቃል ወደ ግሪክ ሲተረጎም ‹ፕሮፌቴስ› ወይንም ‹ፕሮ› እና ‹ፌሚ› ከሚሉት ጥምር-ቃላት የተገኘ በመሆኑ ‹ፕሮ› ቅድሚያ፣ ከአንድ ነገር በፊት ማለትን ሲያመለክት ‹ፌሚ› ደግሞ መናገር፣ ማብሠርና ማሳወቅ ማለት እንደሆነ መምህር ብዙነሽ ስለሺ ‹ትምህርተ ሃይማኖት› በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ‹ፕሮፌቴስ› የወደፊቱን ነገር አስቀድሞ መናገር፣ ማብሠር ወይም ማሳወቅ የሚል ትርጓሜ እንዳለው እንረዳለን፡፡ ምዕራባውያን በመጽሐፍ ቅዱሳቸው ውስጥ ቃሉን ‹ፕሮፌት› በሚለው ሲጠቀሙ የሴሜቲክ ቋንቋ ዘር የሆነው ግእዝ ከዕብራይስጡ ቃል ‹ናቪ› የሚቀራረብ ትርጓሜ በመውሰድ ነቢይ የሚለውን ቃል ይጠቀማል፡፡ (ትምህርተ ነቢያት ገጽ ፲፩)
ነቢይ የሚለው ስያሜ የተጸውኦ ስም ሲሆን ነቢያት ሀብተ ትንቢት ከእግዚአብሔር ተሰጥቷቸው ወደፊት የሚሆነውን ሁሉ በእግዚአብሔር መሪነት በእርግጠኝነት የተናገሩ ናቸው። ነቢያት ከእግዚአብሔር ዘንድ በራእይ፣ በሕልም እንዲሁም በመገለጥ የተቀበሉትን ቃል ለሕዝቡ በማስተላለፍና በማሳወቅ ያገለገሉ የእግዚአብሔር ሰዎች ናቸው። የሰዎችን ልመናና ጩኸት ወደ እግዚአብሔር በማቅረብ ምላሽ እንዲያገኙ የሚረዱ ሲሆኑ አሕዛብንም ወደ እግዚአብሔር መንገድ በመመለስ ንስሓ ገብተው ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁም አማላጅና ተራዳኢ በመሆን አገልግለዋል። ‹‹እነሆም ለምሥራቅ አንበጣ ይመጣል፤ አንዱንም ኵብኵባ ንጉሡ ጎግ ነበር፡፡ የምድሩንም ሣር በልቶ ይጨርሳል፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፤….አልሁ›› (አሞ.፯፥፩-፪)
ቅዱሳን ነቢያት በዘመናቸው በቃለ እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚመክሩ፣ የሚያስተምሩና የሚገሥፁም ነበሩ። በዘመናቸውም እንደ ነቢዩ ሙሴ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ እና ነቢዩ ሕዝቅኤል እንዲሁም አብዛኞቹ ነቢያት ሲያስተምሩ ሕዝቡን ወደ ንስሓ እንዲመለስ በመምከር፤ ያ ካልሆነ ግን ቅጣት እንደሚመጣባቸው ደጋግመው በመናገር ሕዝቡን ይገሥፁ ነበር፡፡ መልእክታቸውና ትምህርታቸውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ስለነበር የተናገሩት የትንቢት ቃል በሕይወት እያሉ ተፈጻሚነት ያገኝ ነበር፡፡ (ኢሳ. ፩፥፳፩-፴፩፣ ሕዝ. ፱፣፩-፲፩፣ ዮና.፩-፲)
ነገር ግን በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጒም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና። ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናግረዋል። (፪ ጴጥ. ፩፥፳፩)
ከሁሉም በፊት ማወቅ የሚኖርብን ነገር እውነተኞቹ ነቢያት በእግዚአብሔር የሚመረጡ መሆናቸውን ነቢያት በሚያስተምሩ ጊዜ ወይንም የትንቢት ቃል በሚናገሩ ጊዜ በእግዚአብሔር ስም ይናገራሉ በእግዚአብሔር ስም ተአምራትን ያደርጋሉ፤ ባሕርን ይከፍላሉ፤ ሙታን ያስነሳሉ፤ ሰማይን ይዘጋሉ፤ ፀሐይን ያቀማሉ፡፡ ነገር ግን ነቢያት ሕልም የመተርጐምም ሆነ ታምራትንና አስደናቂ ነገሮችን የማድረግ ኃይል ቢኖራቸውም በሚያከናውኗቸው ተግባራት ሕዝብን ወደ እግዚአብሔር የማይመሩ የተናገሩትም ትንቢት ተፈጻሜ ሆኖ ካልታየ ሐሰተኞች ነቢያት ናቸውና ከፍሬያቸውም የተነሣ እናውቃቸዋለንና እነርሱን መስማት የለብንም፡፡ ከእግዚአብሔር ያልሰጣቸውን የሐሰት ትንቢት ስለሚናገሩትም የእግዚአብሔር ቊጣ በእነርሱ ላይ እንደሚበረታ ‹‹ነገር ግን ይናገር ዘንድ ያላዘዝሁትን ቃል በስሜ የሚናገር ነቢይ እርሱ ይገደል›› ሲል በመጽሐፍ ተናግሯል፡፡ (ዘዳ. ፲፰፥፳)
እውነተኞች ነቢያት በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርተው ሕዝቡን ወደ እውነተኛው ጎዳና የሚመሩ የተነገሩት የትንቢት ቃል ያስተላለፉ መልእክት ሲፈጸም መታየት ይኖርበታል እንጂ ከንቱ ተስፋ እየሰጡ ሕዝቡን የሚሸነግሉ ከሆነ ሐሰተኞች ነቢያት ናቸው፡፡ የተናገሩትም የትንቢት ቃል እውነተኛና በእግዚአብሔር ፈቃድ መሠረት የተነገረ ከሆነ ነቢዩ በሕይወት እያለ ትንቢቱ ይፈጸማል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተመዘገበው ለነቢይነት የተጠሩ ቅዱሳን አባቶታችን በዚህ ምድር ላይ አገልግሎታቸውን ፈጽመው አልፈዋል፡፡ ነቢዩ ሙሴ፣ ነቢዩ ኢያሱ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ነቢዩ ኤርምያስ፣ ነቢዩ ሕዝቅኤል፣ ነቢዩ ዳንኤል፣ ነቢዩ ሆሴዕ፣ ነቢዩ አሞጽ፣ ነቢዩ ሚክያስ፣ ነቢዩ ኢዩኤል፣ ነቢዩ አብድዩ፣ ነቢዩ ዮናስ፣ ነቢዩ ናሆም፣ ነቢዩ ዕንባቆም፣ ነቢዩ ሶፎንያስ፣ ነቢዩ ሐጌ፣ ነቢዩ ዘካርያስ እና ነቢዩ ሚልክያስ የእግዚአብሔርን ፈቃድና ትእዛዛትን ጠብቀው እና ሕዝቡን ሲያገለግሉ ኖረው በክብር ያለፉ ነቢያት አባቶችን ናቸው፡፡
ሆኖም ስለ ራሳቸው የግል ጥቅም በማሰብ ነገሥታቱንና ሕዝቡን ለማስደሰት ከራሳቸው ፈጥረው ትንቢት የሚናገሩና ሕዝቡን የሚሸነግሉ ነቢያት ግን ከእግዚአብሔር የተላኩ ወይም እውነተኞች ነቢያት አይደሉም፡፡ ጌታም ተጠበቁ ያለን እንደነዚህ ካሉት ነቢያት ነው፡፡ እውነተኞች ነቢያት የክፋትን መንገድ የማይከተሉና በተሰጣቸው የእግዚአብሔር ኃይል አጋዥነት አገልግሎቸውን በቅድስና ይጽማሉ እንጂ ሰውን ወደ ተሳሳተ መንገድ አይመሩም፤ ምክንያቱም ለዚህ ተግባር የተመረጡበትም ሆነ የተላኩበት ምክንያት እግዚአብሔር የገለጠላቸውን እውነት ሳይሸራርፉና ሳይቀንሱ ሳይጨምሩም ለሕዝቡ መንገር ስለሆነ፤ በእግዚአብሔር የሚታመኑ ናቸው፡፡ (ኤር. ፳፫፥፲፣ ፫፥፪)
እውነተኞች ነቢያት መንፈሳዊ ሕይወታቸው እግዚአብሔርን የሚያስደስት፣ ሐሰትን የማይናገሩ፣ እግዚአብሔር የገለጠላቸውን ራእይ የሚያስተውሉና መልእክቱን በወቅቱና በጊዜው ሳይፈሩና ሳያፍሩ የሚያስተላልፉ ያጠፉትንም ነገሥታት እንኳን ቢሆኑ የሚፈሠፁ ናቸው፡፡ (ኢሳ. ፳፰፥፯-፱፣ ኤር. ፳፫፥፲፩-፲፬)
ሆኖም ግን በዚህ ዘመን የተነሡ ነቢይ ነን ባዮች በዓለማችን ተስፋፍተዋል፡፡ እኛም ለዚህ ቃል ምስክር መሆን ከጀመርን ሰንብተናል፡፡ ብዙ ሐሳውያን ነቢያት በመኖራቸው ምእመናን ከእነርሱ እንዲጠበቁ ቤተ ክርስቲያናችን ታሳስባለች፡፡
በቅዱስ መጽሐፍ ላይ እንደተጻፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ዳግም ምጽአቱና ስለዓለም ፍጻሜ ምልክቶች በጠየቁት ጊዜ እንዲህ ብሏቸዋል፤ ‹‹ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያትም ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፡፡›› (ማቴ. ፳፬፥፲፩)
ሐሰተኞች ነቢያት የተሰጠ ሀብት ትንቢት እንዳላቸው አድርገው ስለራሳቸው ይናገራሉ፡፡ ይህ የሚመስሉበት ሥልጣን ምንድን ነው? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹የበግ ለምድ አልብሰው ወደ እናንተ ከሚመጡ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ! በውስጣቸውም ነጣቂ ተኵላዎች ናቸው፤ ከፍሬያቸውም ታውቋችኋላች›› በማለት እንደተናገረው የበግ ለምድ ለብሰው የሚመጡት ሐሰተኞች ነቢያት በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ናቸው። እረኛ በኮረብታማ ሥፍራ መንጋውን ሲጠብቅ የበግ ለምድ ለብሶ ነው። እረኛም ያልሆነም ሰው የበግ ለምድ ሊለብስ እና እንደ እረኛ በጎችን ሊከተል ይችላል። ነቢያትም የተለመደ የአለባበስ ዐውድ ነበራቸው። ነቢዩ ኤልያስ መጎናፀፊያ ያደርግ፣ በዚህም ከሌሎች ይለይ ነበር። ነገር ግን ይህ መለያ ልብስ ያልተገባቸውና ነቢያት ያልሆኑ ይህን ልብስ ለብሰውት ሊገኙ ይችላሉ። ለዚህም ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹በዚያም ቀን ነቢያቱ ሁሉ ትንቢትን ሲናገሩ እያንዳንዱ ስለ ራእዩ ያፍራል ያታልሉም ዘንድ የማቅ ልብስ አይለብሱም።›› (ማቴ. ፯ ፥፲፭፣ ፩ኛ ነገ ፲፱፥፲፫፥፲፱፣ ዘካ. ፲፯፥፬)
ሐሰተኞች ነቢያት በውጫዊው አቀራረባቸው እንደታማኝ መሪዎችም በመመሰል ራሳቸውን ያቀርባሉ። ይህንንም በልዩ ልዩ አለባበስ ራሳቸውን በመለየት እንዲሁም የስም ማዕረጎችን በስማቸው ላይ በመለጠፍ በሃይማኖት ሥርዓት ውስጥም ትልቅ የመሪነትን ሥፍራ ተቆናጠው ሊገኙ ይችላሉ። በትምህርትም የሥነ መለኮት ትምህርት የተማሩ አልፎም ተርፎም በሥነ መለኮት ትምህርት አስተማሪዎችም ሊሆኑ ይችላል። በእነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች እንደ ታማኝ መሪዎች ቆጥረናቸው ከሆነ ትክክል አይደልም። በየዋህነትም በውጫዊ ማንነታቸው ድምዳሜ ላይ ልንደርስ አይገባም።
ሐሰተኞች ነቢያት በፍሬያቸው ይታወቃሉና በውጫዊ ማንነታቸው ላይ ተመሥርቶ መደምደም ትክክል አይደለም፤ ለዚህም ነው በፍሬያቸው መለየት እጅግ ጠቃሚ እና አስፈላጊ የሚሆነው። የዛፍ የሥሩ ምንነት መታወቂያው በፍሬው ነው። ‹‹መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬን ያፈራል። ክፉ ዛፍም ክፉ ፍሬን ያፈራል›› እንዲል፤ ስለዚህም ታማኝ የሆኑ መሪዎችን የመመዘኛ መንገዱ በፍሬዎቻቸው መሆን አለበት። (ማቴ.፯፥፲፯)
እነዚህ ፍሬዎች ታድያ ምንድን ናቸው? እዚህ ላይ ልብ ማለት ይገባል፤ ሐሰተኞች ነቢያት ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን የሚፈጽሙ አይደሉም። ይልቁንም በሐሰተኞች ምልክቶች እና በሚመስሉ ታዓምራቶች የተሞሉ ናቸው። ይህንንም በማቴዎስ ወንጌል ላይ ‹‹በዚያ ቀን ብዙዎች አቤቱ! አቤቱ! በስምህስ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፤ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል፡፡ ያንጊዜ ከቶ አላውቃችሁም፤ ዐመጽን የምታደርጉ ሁላችሁ ከእኔ ራቁ እላቸዋለሁ›› ብሎ የተናገረላቸው ናቸው። (ማቴ.፯፥፳፪)
ሌላው ሐሰተኞች ነቢያት ልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ተግባራትን ሊፈጽሙ ይችላሉ። ተአምራትን የማድረግ ኃይልም አላቸው ለማስባል ልዩ ልዩ መሰል ምግባራትን ይፈጽማሉ። የሚያደርጉትን ተአምራትም በእግዚአብሔር ስም ሊያደርጉት ይችላሉ። ‹‹የሚተነኰሉ፥ ራሳቸውን የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሐዋርያት የሚያስመስሉ፥ ነገር ግን ዐመፅን የሚያደርጉ ሐሰተኞች ሐዋርያትና አሉና። ይህም አያስደንቅም፤ ሰይጣን ራሱ ተለውጦ እንደ ብርሃን መልአክ ይመስላልና። መልእክተኞች የጽድቅ መላእክትን ቢመስሉ፥ ይህ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜያቸው ግን እንደ ሥራቸው ነው›› እንዲል፡፡ (፪ኛ ቆሮ. ፲፩፥ ፲፫-፲፭)
ሐሰተኞች ነቢያት አልፎ አልፎ ለየት ባሉ እና አግራሞት ባላቸው የሃይማኖት ሥርዓቶች ሲታጀቡ ሊታዩ ይችላሉ። ሰይጣንም ብዙዎችን እንዳሳተ እና ሰዎችን ለእርሱ ፈቃድ እስከአስገዛ ድረስ ክብርን ለእግዚአብሔር መስጠት ችግሩ አይደለም።
በዓለማችን ሐሰተኞች ነቢያት በመኖራቸው እኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ሁልጊዜም እውነተኛውን የእግዚብሔርን ቃል በማዳመጥ፣ በማንበብና በቃሉም በመገዛት እንዲህ ካለው ፈተና ልንርቅ ይገባል፡፡ በተለይም የቤተ ክርስቲያን ትምህርትን ያልተማርን እና በቂ የትምህርተ ሃይማኖት ዕውቀት የሌለን ሰዎች ጊዜ ሳናጠፋ እንደ ክርስቲያን ማወቅ የሚጠበቅብንን ትምህርት እና ሥርዓት በመማር ሐሰተኞች ነቢያትን ልንከላከላቸው እና ልንነቅፋቸው ይገባል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!