እውነተኛውን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት እናስጠብቅ!
በሕይወት ሳልለው
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን በየዘመናቱ በሚነሱ መናፍቃን ስትፈተን እንደኖረች በታሪክ የታወቀ ነው፡፡ ዛሬም የተለያዩ የጥፋት ኃይሎች ቤተ ክርስቲያንንና ክርስትናን ለማጥፋት ያቀዱትን ትልም ለማሳካት በተዘዋዋሪና በይፋ ግፍ እና በደል እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ በተለይም በዚህ ወቅት እነዚህ የጥፋት ኃይሎች አብያተ ክርስቲያናት በማቃጠልና ምእመናንን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል ክርስትናን አጥፍቶ እስልምናን የማስፋፋት እቅዳቸውን ቀጥለዋል፡፡
ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በተለያዩ ክፍለ ሀገራት ማለትም በጎንደር፣ ጅማ፣ ሲዳማ፣ ምሥራቅና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ባሌ፣ አሰላ፣ ጅግጅጋ፣ ቀርሳ፣ መቱ፣ ነቀምት፣ አርሲ፣ ወሊሶ፣ ሐረማያ፣ ኮምቦልቻ፣ ባሕር ዳር፣ ከሚሴ፣ ደብረ ታቦር፣ ፍቼ፣ አሰበ ተፈሪ-ጭሮ፣ ደሴ፣ ድሬድዋ፣ አርሲ፣ ጋራሙለታ ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ እንዲሁም ከአዲስ አበባ አቅራቢያ በሆኑ እንደ ሆለታ ባሉ ስፍራዎች ይህን ጥቃት ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡ በድሬድዋና ሐረር ባሉ አንዳንድ ከተሞች ደግሞ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮችን በመያዝ ሃይማኖታቸውን ቀይረው የእስልምና ተከታዮች እንዲሆኑ ማስገደድ በመጀመራቸው በርካታ ግለሰቦች ከቤታቸው፣ ከትውልድ ስፋራቸውና ከትምህርታቸው በመስተጓጎልና በመፈናቀል ወደ አቅራቢያ ከተሞች መሸሽ ጀምረዋል፤ በየጫካው የተደበቁ እንዳሉም መረጃዎች አስታውቀዋል፡፡ በጠላት እጅ የወደቁት ግን ሃይማኖታችንን አንቀይርም ባሉ ጊዜ እንደሚገሏቸው በማስፈራራትና ማተባቸውን በማስፈታት እስልምናን እንዲቀበሉ አስገድደዋቸዋል፡፡ ሆኖም ለሃይማኖታቸው መሥዋዕት በመክፈልም የተገደሉ እንዳሉ ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡ እስከ አሁን ባለው መረጃ ፳፭ ያህል ቤተ ክርስቲያን ተቃጥለዋል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምእመናን በግፍ ተገድለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ የግለቦች ቤትና ንብረት ወድሟል፡፡
ቤተ ክርስቲያንን በማቃጠል፣ የሀገር ሰላምን በማጥፋት፣ እርስ በርስ ግጭት በመፍጠር እና የሰዎችን ቤት እንዲሁም ንብረት በማውደም ክርስትናን ለማጥፋት ደፋ ቀና እያሉ በመሆኑ እኛም የእምነቱ ተከታዮች አስፈላጊውን መሥዋዕት ለሃይማኖታችን መክፈል አለብን፡፡
ሃይማኖት በአንድ አምላክ ማመን ነው፤የፍጥረት ሁሉ ገዥ፤ቅድመ ዓለም የነበረ፣ አሁንም ያለ፣ ወደፊትም የሚኖረው ዘለዓለማዊ አምላክ እግዚአብሔርን በማመን ማምለክ ማለት ነው፡፡ ውኃን በእፍኙ የሰፈረ፣ ሰማይና ምድርን በስንዝር የለካ፣ የምድርንም አፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፣ ተራሮችን እና ኮረብቶችን በሚዛኖች የመዘነ፣ መተኪያ የሌለው፣ በቦታ የማይወሰን፣ የማይለወጥ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊትም እንደተናገረው ‹‹ተራሮች ሳይወለዱ÷ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ÷ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ አንተ ነህ››፡፡ (መዝ. ፹፱፥፪)
ሃይማኖትም ተጠብቆ እንዲኖር ቅዱሳን አባቶቻችን ለእምነታቸው ብዙ መሥዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ይህም እግዚአብሔር ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከንጽሕተ ንጹሓን፣ ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ፍጹም ሰው ሆኖ ባስተማረን ወንጌል፣ በተቀበለልን መከራ፣ በደሙ ዋጅቶ በመሠረታት ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን፣ ጻድቃንና ሰማዕታት ለሃይማኖታቸው ብዙ መከራን ተቀብለዋል፤ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትንም ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ አድርገዋል፡፡
እኛም ይህ ኃላፊነትና አደራ አለብንና ወደ ፊትም የልጅ ልጆቻችን ቤተ ክርስቲያንን እንዲጠብቁ፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን እንዲከተሉ እንዲሁም በክርስትና ሕይወት ውስጥ ኖረው ለመንግሥተ ሰማያት የበቁ ይሆኑ ዘንድ አደራችንን እንጠብቅ፤ ጠላትን በማሸነፍ ቤተ ክርስቲያንን በማስከበርና ሃይማኖታችንን በመጠበቅ ለትውልድ እናስረክብ፡፡