‹‹እስከ በዓለ ኀምሳ በኤፌሶን እቆያለሁ›› (፩ኛቆሮ.፲፮፥፰)
መምህር ቢትወደድ ወርቁ
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የቤተክርስቲያን የልደት ቀን ብሎ የጠራው ቀን በዓለ ኃምሳ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ እንደሚከበር ይህ የቅዱስ ጳውሎስ ቃል ምስክር ነው፡፡በዓለ ኃምሳ፤ በዓለ ጰራቅሊጦስ፤ በዓለ ጰንጠቆስጤ እየተባለም ይጠራል፡፡
በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተነገረም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለመጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለቅዱሳን ሐዋርያት፤ ለሰብአ አርድእትና ለቅዱሳት አንስት ጸጋውን ያደለበት፤ ምሥጢራትን የገለጠበት፤ መንፈሳዊ ጥብዓትን (ጥንካሬን) የሰጠበት፤ ታላቅ ቀን ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ዓለምን የሞላችው ወደ ሁሉ የደረሰችው በዚህ ቀን ከመንፈስ ቅዱስ በተቀበለችው ጸጋ ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደመሠከረው መንፈስ ቅዱስ ባይወርድላት ኖሮ የቤተክርስቲያን ሕልውና ከስሞኖ ቀጭጮ ይቀር ነበርና ነው፡፡
ይህች ቀን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በነቢዩ ኢዩኤል አንደበት ‹‹ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፤ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ደግሞ በዚያም ወራት በወንዶችና በሴቶች ባርያዎች ላይ መንፈሴን አፈሳለሁ፡፡›› በማለት የተናገረው ትንቢታዊ ኃይለ ቃል ፍጻሜውን ያገኘበት ዕለት ናት፡፡ ይህች ቀን ቅድመ ሥጋዌ በነቢዩ አንደበት ይህን የተናገረ አምላክ በፍጹም ተዋሕዶ በሥጋ ማርያም ተገልጦ ለአባቶቻችን ለቅዱሳን ሐዋርያት የሰጠው የተስፋ ቃል የተፈጸመባት ዕለት ናት፡፡ (ኢዩ.፪፥፳፰፤የሐዋ.፪፥፲፯)
በዓለ ኃምሳ፤ በዓለ ጰራቅሊጦስ፤ በዓለ ጰንጠቆስጤ እየተባለ የሚጠራ እንደመሆኑ መጠን ይህ ወቅት የነገረ መንፈስ ቅዱስ ትምህርት በስፋት የሚሰበክበት ወቅት ነው፡፡ ከዚህም በመነሣት እግዚአብሔር የፈቀደልንንና የገለጠልንን ያህል ስለ መንፈስ ቅዱስ በነገረ መለኮት ትምህርት መማር እንችላለን፡፡ በዚህ ትምህርት ውስጥም ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ማንነት እርሱ በገለጠላቸው መጠን አምልተው አስፍተው ያስተምራሉ፡፡
በመንፈስ ቅዱስ ላይ የተነሡ የክሕደትና የኑፋቄ ትምህርቶችንም ይመረምራሉ፤ ለሚነሡ የክሕደት ትምህርቶችም ኦርቶዶክሳዊ ምላሽን ይሰጣሉ፤ የክሕደቱ አመንጪ መናፍቃንንም ማንነትና የክሕደት ምክንያቶቻቸውን ይገልጣሉ፡፡
መንፈስ ቅዱስ ጸጋውን የሚያድለው እርሱም የሚገኘው አንድነትና መተባበር ባለበት ሥፍራ ነው፡፡ በዕለተ ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ጸጋውን ያደላቸው በአንድነትና በእምነት ተሰብስበው በነበሩበት ሁኔታ እንደነበር መጽሐፍ ሲነግረን «በዓለ ኃምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ›› ይለናል፡፡ (የሐዋ.፪፥፩-፪) እኛም የአባቶቻችን ልጆች በመሆናችን እርሱ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መሆኑን አናምናለን፡፡