‹‹እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን እርሱ ይድናል›› (ማቴ.፳፬፥፲፫)

መምህር ቢትወደድ ወርቁ
ግንቦት ፳፪፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ማመንንና መታመንን የሚፈታተኑ ነገሮች በዓለም ባይኖሩ ኖሮ ስለ ጽናት አይነገርም ነበር፡፡ ጽናትን የሚወልደው የመከራና የፈተና ብዛት ነው፡፡ በዚህ ዘመን ክርስቲያን ለመሆን እንዲሁም ስመ እግዚአብሔርን ለመጥራት እንፈልግ እንጂ ስለ ክርስትና መከራን ለመቀበል ግን አንፈልግም፡፡ ይህ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ግን አይዟችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ›› በማለት ለተናገረው ቃል ምንኛ ባዕድ እየሆንን ለመምጣታችን ማሳያ ነው፡፡ (ዮሐ.፲፮፥፴፫) መንግሥተ ሰማያትን መውረስ እንሻለን ዳሩ ግን ስለ መንግሥተ ሰማያት ምንም ዋጋ አልከፈልንም፡፡ በዚህም አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል›› በማለት ያስተማሩትን ትምህርት በተግባር እየተቋወምን እንደሆነ ያመለክተናል፡፡ (ሐዋ.፲፬፥፳፪)

የክርስትናውን መንገድ በሚገባ ስላልተረዳነውና በመጻሕፍት ያነበብነውን በቀደምት አበውና እማት ላይ የደረሰውንም መከራ አንብበን ከማድነቅም ባለፈ በእምነት በልቡናችን ሰሌዳ ስላልቀረጽነው እጅግ በጣም ጥቂት ፈተና ሲደርስብንም ሆነ መከራ ሲጎበኘን በትንሹ እናማርራለን፡፡ እንዲህ ዓይነት ክርስቲያኖች መሆን እንደማይገባን ግን ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ሲያስተምረን ‹‹ወንድሞች ሆይ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደረርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት›› በማለት ይናገራል፡፡ (ያዕ.፩፥፫) የክርስቶስና አካሉ ስለሆነችው ቤተ ክርስቲያን የሚቀበሉት መከራ የደስታ እንጂ የኀዘን የምስጋና እንጂ የማማረር ሊሆን እንደማይገባ ይህ ቃል ያስተምረናል፡፡

ዛሬ እንደሚስተዋለው እንደ ክርስቲያን በብዙ መንገድ እየተፈተንን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በፖለቲከኞች እየታመሰች ስንመለከት እግዚአብሔር የተወን ይመስለናል፡፡ ግፈኞች ከፍ ከፍ እያሉ ስናስተውልና የግፍ ጡጫቸው አብዝቶ ሲመታንም ረዳቴ ከወዴት አለ? በሚል ቁዘማ ውስጥ ገብተናል፡፡ በቤቱ እየተመላለስንና እንደየአቅማችን ፈቃዱን ለመፈጸም እየታገልን ጤና አጥተን ስንሠቃይ ገንዘብ አጥተን የምንበላውና የምንጠጣውን ነገር ለማግኘት እንኳን ስንገዳገድ በሥራና በተሰማራንባቸው ስፍራዎችም ጠላትና ምቀኛ ሲበዛብን በእነዚህ ምክንያቶች ምሬት ውስጥ ገብተን በእምነት መቀዝቀዛችን እየታየ ያለ ነገር ነው፡፡ ከዚህም በላይ በእምነት ምሳሌ ያደረግናቸው ምንአልባትም ወደ ቤተ እግዚአብሔር ለመቅረብ ምክንያት የሆኑን ሰዎች ከፍ ሲልም ቃለ እግዚአብሔርን ያስተማሩንና ትናንት በብዙ መልኩ ሲያጽናኑን የነበሩ ሰዎች ከሃይማኖት ወጥተውና ከመልካም ምግባር ርቀው በዚህ ዓለም የዘረኝነትና “የሁሉን ለእኔ ፖለቲካ” ተነክረው ስንመለከትም “እነርሱማ እንዲህ ከሆኑ” በማለት ከቤቱ የራቅንና ከመንፈሳዊ ነገሮች የተፋታን ሰዎችም ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ለእነዚህ ሁሉ መከራዎች ግን መፍትሔና መድኃኒቱ ጽናት እንደሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግልጽ በሆነ ቃል አስተማረን፡፡ ለመዳን (መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ) መሠረቱ ጽናት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ይህን በተመለከተ ደጋግሞ አስተምሮናል፡፡ ለምሳሌም የሚከተሉትን ኃይለ ቃላት እንመልከት፡- “በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንዳታሳዩ እንመኛለን፡፡” (ዕብ.፮፥፲፩)

ሐዋርያው በመንፈስ ጀምረን በሥጋ፣ በትሕትና ጀምረን በትዕቢት፣ በእውነት መንገድ ጀምረን በሐሰት ጎዳና በትጋት ጀምረን በዳተኝነት እንዳንፈጽም በአደራ ቃል ተማጸነን፡፡ በመንፈሳዊ ጉዞው ያልተፈተነ መሰናክል ያልገጠመው መከራ ያልተፈራረቀበት ማንንም ቅዱስ አናገኝም፡፡ የመዳኑ ምሥጢርም ሐዋርያው እንዳስተማረው እስከ መጨረሻው ጸንቶ በትዕግሥት መመላለስ ነው፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት ስንጓዝ እንዲሞሉልን የምንፈልጋቸው ሁለት ዓይነት ተስፋዎች ይኖራሉ፡፡ የመጀመሪያው ሥጋዊ ተስፋ ሲሆን ይኸውም ሠርቶ ማግኘት፣ ተምሮ መመረቅ፣ አጭቶ ማግባት፣ አግብቶ መውለድ፣ ነግዶ ማትረፍ፣ ታሞ መዳንና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ ዓረፍተ ዘመን ገትቶን በሞተ ሥጋ ስንወሰድ በምድር የሚቀሩ ናቸው፡፡ ዋነኛው ከመቃብርና ከሞት በኋላ የሚሻገረው ግን ሰማያዊው ተስፋ ነው፡፡ ሰማያዊው ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን መውረስና በመንግሥቱም ከእግዚአብሔርና ድል ከነሡ ከወዳጆቹ ጋር መኖር ነው፡፡ (ዕብ.፲፪፥፳፩)

በሥጋችን ልንደርስባቸው የምንፈልጋቸው ተምኔቶቻችን ከግብ እንዲደርሱ፣ ከሞት በኋላ ተስፋ የምናደርጋት መንግሥቱንም እንድንወርስ የፈተናውን ማዕበል በእምነት መቅዘፊያነት መሻገርና መከራውንም ማለፍ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው፡፡ ‹‹የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና፡፡ ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፤ ሊመጣ ያለውም ይመጣል፤ አይዘገይምም፤ ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል፤ ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ በእርሱ ነፍሴ ደስ አይላትም፤ እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑት ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉት አይደለንም›› ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ (ዕብ.፲፥፴፮) ‹‹ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች እያሳቱና እየሳቱ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፡፡›› (፪ኛጢሞ.፫፥፲፫)

ሐዋርያው ‹‹በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር›› አለን፡፡ በሃይማኖት ጸንቶ መገኘት ይገባልና፡፡ የክሕደት ማዕበል ቢበረታ የኑፋቄ ወጀብ ቢመጣ በቤተ ክርስቲያን በተማርነው በአንድነት በሦስትነቱ በነገረ ሥጋዌው (ሰው በመሆኑ) በነገረ ጥምቀቱና በምሥጢረ ቁርባኑ እንዲሁም በተስፋ ትንሣኤ ሙታንና እግዚአብሔር ወዳጆቹን እንዳከበረ በተማርንበት የነገረ ቅዱሳን ትምህርት ጸንተን መገኘት አለብን፡፡ ‹‹ቃሉ የታመነ ነው እንዲህ የሚለው ከእርሱ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን ብንጸና ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን ብንክደው እርሱ ደግሞ ይክደናል፤ ባናምነው እርሱ የታመነ ሆኖ ይናራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና፡፡›› (፪ኛጢሞ.፪፥፲፩)

ሐዋርያው ሰው እውነተኛውን የክርስትና መንገድ እየተከተለ ማናቸውም መከራና ፈተና ቢገጥመው ወደ ፊት ሊሰጠው ካለው ክብር አንጻር መከራው ኢምንት እንደሆነ ሲያስተምር ‹‹ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ›› በማለት ተናግሯል፡፡ (ሮሜ ፰፥፲፰፡) ‹‹ከእርሱ ጋር ከሞትን›› የሚለውን ቃል እናስተውል! ክርሰቶስ ስለምን ሞተ? ብንል እውነተኛ ሆኖ ሳለ እንደ ሐሰተኛ ቆጥረውት በሐሰት ወንጅለውት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ከእርሱ ጋር መሞት ማለትም እውነተኛ ሆኖ ሳለ በሐሰት መወንጀል ቢመጣም እርሱን በማመን በመከራ ጸንቶ መገኘት ነው፡፡ ‹‹ከእርሱ ጋር ብንጸና›› ማለትም እርሱ ፈጣሪያችን ክርስቶስ ምሳሌ ሊሆነን እርሱ በዘረጋት የእውነት መንገድ ተጉዞ መከራን ሲቀበል በእውነት እንደጸና እኛም በእርሱ መንገድ ተጉዘን በእርሱ ወንጌል ጎዳና ብንጸና ማለት ነው፡፡ በዚህ ዓለም ያለውን መከራና ፈተና ከእርሱ ጋር ሆኖ ማለፍም ፍጻሜው ከእርሱ ጋር መንገሥ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን!