እርባ ቅምር
ክፍል ፪
መምህር በትረማርያም አበባው
ሐምሌ ፲፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? የእግዚአብሔር አምላካችን ስም የተመሰገነ ይሁን! ባለፈው የትምህርታችን ክፍለ ጊዜ ‹‹እርባ ቅምር›› በሚል ርእስ የመጀመሪያውን ክፍል ይዘንላችሁ ቀርበን ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ለሰጠናችሁ መልመጃ ምላሽና ክፍል ሁለትን እናቀርብላችኋለን፤ በጥሞና ተከታተሉን!
የመልመጃ ጥያቄዎች
፩) የአግመረ አሉታ ማን ነው?
፪) ተንሥኡ ለጸሎት ከሚለው
ሀ) ሰሚው ማን ነው?
ለ) አሰሚው ማን ነው?
፫) ማኅበረ ቅዱሳን የሚለውን ተናባቢ ቃል በለ እና በዘ በዘርፍ አያያዥና በዘርፍ ደፊ ጻፍ?
፬) መስቀል ኃይልነ በሚለው ቃል ሳይጠራ ያሰረ ማን ነው?
፭) የሚከተሉትን ቃላት ሥርዓተ ንባባቸውን ለይ?
ሀ) ባእ
ለ) ለትባእ
፮) የሚከተሉትን ቃላት ገቢራቸውን አውጡ?
ሀ) መላእክትየ
ለ) ኅብስትከ
ሐ) ሀገሮሙ
፯) የ “አርኂዎ” አሉታ ማን ነዉ?
የጥያቄዎች መልሶች
፩) ኢያግመረ
፪) ሀ፡- አንትሙ
ለ፡- አንቀጹ ተንሥኡ
፫) ማኅበር ዘቅዱሳን፣ ዘቅዱሳን ማኅበር፣ ማኅበሮሙ ለቅዱሳን፣ ለቅዱሳን ማኅበሮሙ
፬) ውእቱ
፭) ሀ፡- ተጣይ
ለ፡- ሰያፍ
፮) ሀ፡-መላእክት
ለ፡-ኅብስተከ
ሐ፡-ሀገሮሙ
፯) ኢያርኂዎ
አዋጅ ፩
አዕማደ አርእስት የሚባሉ አምስት ናቸው። እነዚህም አድራጊ፣ ተደራጊ፣ አስደራጊ፣ ተደራራጊ እና አደራራጊ ናቸው። ተደራጊ በግድ ሲስብ ፩ በውድ ሲስብ ፭ ተሳቢዎችን ይስባል። በግድ አንድ ሲስብ ‹‹ተሰቅለ አምላክ፤ አምላክ ተሰቅለ›› የሚለው ዓረፍተ ነገር እንደተሳበ አስተውሉ! በውድ አምስት ሲስብ ‹‹አምላክ ተሰቅለ በመስቀል በቀራንዮ በዕለተ ዓርብ በጊዜ ቀትር›› ይላል። ትርጉሙም ‹‹ዓርብ ቀን በቀትር አምላክ በቀራንዮ በመስቀል ተሰቀለ›› ማለት ነው፡፡ አድራጊ በግድ ሁለት ሲስብ ‹‹ሰቀሉ አይሁድ አምላከ›› ይላል። ትርጉሙም ‹‹አይሁድ አምላክን ሰቀሉት›› ማለት ነው፡፡ በውድ ስድስት ሲስብ ‹‹ኢዮአብ አሜሳይሀ ቀተለ በሰይፍ በእንተ ሢመቱ እምቅንዐቱ አመ የዐርግ ኀቤሆሙ ለእስራኤል›› ይላል። ትርጉሙም ‹‹ኢዮአብ አሜሳይን ስለ ሹመቱ ቀንቶ ወደ እስራኤል በሄደ ጊዜ በሰይፍ ገደለው›› ማለት ነው፡፡ ተደራራጊ በግድ ሁለት ሲስብ ‹‹አቤሴሎም ተቃተለ ምስለ ኢዮአብ›› ይላል። ትርጉሙም ‹‹አቤሴሎም ከኢዮአብ ጋር ተዋጋ›› ማለት ነው፡፡ በውድ ስድስት ሲስብ ‹‹ተቃተለ ሳኦል ምስለ አጋግ በኵናት ህየንተ ግፍዐ እስራኤል እምቃለ ሳሙኤል እምድኅረ ዐርገ ኀቤሁ ናዖስ አሞናዊ›› ይላል። ትርጉሙም ሳኦል ከአጋግ ጋር በሰይፍ ተዋጋ፤ ስለ እስራኤል መከራ ከሳሙኤል ቃል ትእዛዝ የተነሣ አማናዊ ናዖስም ከእነርሱ በኋላ መጣ›› ማለት ነው፡፡
አስደራጊ በግድ ሦስት ሲስብ ‹‹ሳኦል አቅተለ ዳዊትሃ ጎልያድሃ›› ይላል። ትርጉሙም ‹‹ሳኦል ዳዊትን ጎልያድን አስገደለ›› ማለት ነው። በውድ ሰባት ሲስብ ‹‹ሳኦል አቅተለ ጎልያድሃ ዳዊትሃ በዕብነ ሞጸፍ በእንተ ግፍዐ እስራኤል እምትእዛዙ እንዘ ይንእስ እምአኃዊሁ ሰብዓቱ በቤተ ዕሤይ አቡሁ›› ይላል። ትርጉሙም ‹‹ከሰባቱ ወንድሞቹ የሚያንሰው ዳዊትን በድንጋይ (ወንጭፍ) ከእስራኤል መከራ የተነሣ ሳኦል ጎልያድን አስገደለው›› ማለት ነው፡፡ አደራራጊ በግድ ሦስት ሲስብ ‹‹ዳዊት አስተወጸ አሳሔልሀ ምስለ ፈረስ›› ይላል። ትርጉሙም ‹‹ዳዊት አሳሔልን ከፈረስ ጋር ላከ›› ማለት ነው፡፡ በውድ ሰባት ሲስብ ‹‹አስተቃተለ ሳሙኤል ሳኦልሀ ምስለ አጋግ በኲናት ህየንተ ግፍዐ እስራኤል እመንግሥቱ አመ አዘዞ አምላክ በመሴፋ›› ይላል። ትርጉሙም ‹‹ስለ እስራኤል መንግሥት ግፍ መሴፋ በተባለ ቦታ አምላክ ባዘዘው ጊዜ ሳሙኤል ሳኦልን ከአጋግ ጋር በጦር አዋጋ›› ማለት ነው፡፡
አዋጅ ፪
ነባር አምስት ናቸው። እነዚህም የአንቀጽ፣ የአገባብ፣ የስም፣ የቦታ እና የሰዋስው ናቸው። የአንቀጽ ቦ፣ አልቦ የመሳሰሉ ናቸው። የአገባብ እስመ፣ እንዘ የመሳሰሉ ናቸው። የስም ሙሴ፣ ኤልያስ የመሳሰሉት ናቸው። የቦታ ፋርስ፣ ባቢሎን የመሳሰሉት ናቸው። የሰዋስው ኮከብ፣ ዖም የመሳሰሉት ናቸው።
አዋጅ ፫
ፍርቅ አምስት ናቸው። እነዚህም የአንቀጽና የአገባብ፣ የሰምና የወርቅ፣ የዘርፍና የባለቤት፣ የቅጽልና የባለቤት፣ የሳቢና የተሳቢ ናቸው። የሰምና የወርቅ ‹‹ዝናም መጽአ ሆሣዕና፤ ዝናም ሆሣዕና መጣ›› የሚለውን ዓይነት ነው። ይህም ዓረፍተ ነገር የተሳሳተ ነው። ማሰሪያ አንቀጹን አልፎ ዝናም እና ሆሣዕና አይመስልም። የዘርፍ እና የባለቤት ‹‹ደሙ በመስቀል ለአምላክ ውሕዘ፤ የአምላካችን ደሙ በመስቀል ላይ ፈሰሰ›› የሚለው ነው። ‹ደሙ እና ለአምላክ› የሚሉት ቃል ‹በመስቀል› በሚለው ቃል ተፈራቀዋል። የቅጽልና የባለቤት ‹‹ክቡር ውእቱ ዳዊት እምነ ሰማይ በኀበ እስራኤል፤ ዳዊት በእስራኤል ዘንድ እንደ ሰማይ የከበረ ነው›› አይልም። የሳቢና የተሳቢ ሰማየ ለዕርገት አይልም።
አዋጅ ፬
‹ን› የሚሆኑ አገባባት አምስት ናቸው። እነዚህም ‹ለ፣ በ፣ እንተ፣ ውስተ፣ ላእለ› ናቸው። ‹ለ› ‹‹በሰብሐ እና በዘመረ›› ይገባል። ‹‹ሰብሑ ለስመ እግዚአብሔር›› ማለት ‹‹የእግዚአብሔርን ስም አመስግኑ›› ማለት ነው። ‹በ› ሲገባ ‹‹ቀስተ ዮናታን ኢተቀብዐት በቅብዕ›› ይባላል። ‹‹የዮናታን ቀስት ቅቤን አልተቀባችም›› ማለት ነው። ‹እንተ› ሲገባ ‹‹ፈነዎሙ እንተ ባሕቲቶሙ፤ ብቻቸውን ላካቸው›› ይባላል። ‹ላዕለ› ሲገባ ‹‹ነጸረ እግዚአብሔር ላዕለ አቤል፤ እግዚአብሔር አቤልን ተመለከተ›› ይባላል። ‹ውስተ› ሲገባ ‹‹ነጸሩ ውስተ ግብረ ጴጥሮስ›› ይባላል። ትርጉሙ ‹‹የጴጥሮስን ሥራ ተመለከቱ›› ማለት ነው።
አዋጅ ፭
ከአንድ እስከ ዐሥር ያሉ የግእዝ ቁጥሮች ሲሳቡ ‹ካዕብ› የነበረው የመጨረሻ ፊደላቸው ወደ ግእዝ ይለወጣል። ይህም አሐዱ፣ ክልኤቱ፣ ሠለስቱ፣ አርባዕቱ፣ ኀመስቱ፣ ስድስቱ፣ ሰብዓቱ፣ ሰመንቱ፣ ተስዓቱ፣ ዐሠርቱ ያለው ሲሳብ አሐደ፣ ክልኤተ፣ ሠለስተ፣ አርባዕተ፣ ኀምስተ፣ ስድስተ፣ ሰብዓተ፣ ሰመንተ፣ ተስዓተ፣ አሠርተ ይባላል። ሥርዓተ ንባባቸውም ወዳቂ ነው። ‹ሰ› ወዳቂ ንባብ ያላቸውን ቃለት ተነሥተው እንዲነበቡ ያደርጋል። በተጨማሪም ‹ዘ› በሚለው ዐቢይ አገባብ ሲወድቅ ‹ዘሰ› ሲል ተነሥቶ ይነበባል።
አዋጅ ፮
መሣግር የሚሆኑ አምስት ናቸው። እነዚህም ሀ፣ረ፣አ፣ወ፣ዘ ናቸው። ሀ መሀረ ብሎ ይሜህር ይላል። ረ ጠፈረ ብሎ ይጠፍር ይላል። አ ርእየ ብሎ ይሬኢ ይላል። ወ ወጠነ ብሎ ይዌጥን ይላል። ዘ ተዝኅረ ብሎ ይዜኀር ይላል። መሣግር ያሰኛቸው በካልዓይ አንቀጽ ርእሳቸውን ትተው የቀተለውን በቀደሰ የቀደሰውን በቀተለ የሚያረቡ ሆነው ስለተገኙ ነው።
አዋጅ ፯
የሀገር ስም ለገቢር ለተገብሮ ይከታል። ‹‹ወረደ ባቢሎን›› ሲል ‹‹ወደ ባቢሎን ወረደ›› ማለት ነው። ፍጹም ሳድስ የሆነ የሀገር ስም ግን በገቢር ጊዜ ግእዝ ያናግራል። ግብጽ፣ ጽርዕ፣ ገቢር ሲሆኑ ግብጸ፣ ጽርዐ ይላሉ።
አዋጅ ፰
ቅጽል የሚሆኑ የሚከተሉት ናቸው። ንዑስ አገባቦች፣ ደቂቅ አገባቦች፣ አሐዝ፣ ወገን ቅጽል፣ ዘር፣ ነባር፣ ግልጠዘ እና ውስጠ ዘ ናቸው። ንዑስ፣ ደቂቅና አሐዝ በፊት በፊት ይቀጸላሉ። ‹‹አይ ልሳን/ ምን አንደበት/፣ ምንት ነገር/ ምንድነው ነገሩ/፣ ውእቱ ሚካኤል /ሚካኤል ነው/፣ ዝንቱሰ ብእሲ /ይህ ሰውስ/፣ አሐዱ አምላክ/አንድ አምላክ/›› ይላል። ወገን ቅጽል ‹ኢየሱስ ናዝራዊ፣ ከለዳዊ አብርሃም› ይላል። ‹ዘርዕ› ደግሞ ‹‹ይስሐቅ ዘርዐ አብርሃም›› ይላል። ትርጉሙም ‹‹ይስሐቅ የአብርሃም ዘር/ልጅ/›› ማለት ነው፡፡ ነባር ‹‹ቅዳሴ መላእክት›› ይላል። ትርጉሙም ‹‹የመላእክት ምስጋና›› በግልጠዘ እና በውስጠዘ ‹‹ክቡር አብርሃም ዘተለዐለ እም ኵሉ፤ ከሁሉ የሚበልጠው የተከበረው አብርሃም›› ይላል።
አዋጅ ፱
ገቢር ቃላት ሰባት አገባባትን ያመጣሉ። እነዚህም ለ፣ በ፣ ምስለ፣ እም፣ ከመ፣ ኀበ፣ እስከ ናቸው። ‹‹አብርሃም መሐከ ነዳየ›› ማለት ‹‹አብርሃም ለነዳይ ራራ›› ማለት ነው። ‹‹ቆመ ምድረ›› ማለት ‹‹በምድር ቆመ›› ማለት ነው። ‹‹አማኑኤል ተሰቅለ ፈያተ›› ማለት ‹‹አማኑኤል ከሽፍቶች ጋራ ተሰቀለ›› ማለት ነው። ‹‹ተንሥአ ቀራንዮ›› ማለት ‹‹ከቀራንዮ ተነሣ›› ማለት ነው። ‹‹ሰብአ ቆሙ ኪሩቤል›› ይላል፤ ትርጉሙም ‹‹ኪሩቤል እንደሰው ቆሙ›› ማለት ነው። ‹‹በጽሐ ሀገረ›› ሲል ‹‹ወደ ሀገር መጣ ወይም እስከ ሀገር መጣ›› ይላል። ከዚህ በተረፈ አማርኛ አኽሎ፣ መስሎ፣ ሆኖ፣ ብሎ፣ ተብሎ፣ አሰኝቶ፣ አድርጎ፣ ኛ፣ ነት ይሆናል። ‹‹መጽአ ሰይጣን ደብረ›› ይላል። ‹‹ሰይጣን ተራራ አህሎ/መስሎ መጣ›› ማለት ነው። ‹‹ሰይጣን ወሀበ ለነዳይ ወርቀ ዕብነ›› ይላል፡፡ ትርጉሙ ‹‹ሰይጣን ለችግረኛ ድንጋይን ወርቅ ነው ብሎ ሰጠ›› ማለት ነው። ‹‹ክርስቶስ ተሰቅለ ኀጥአ›› ሲል ‹‹ክርስቶስ ኀጥእን ብሎ ተሰቀለ›› ማለት ነው። ‹‹ንጉሥ ሤሞ ለገብሩ ሊቀ›› ሲል ‹‹ንጉሥ አገልጋዩን መሪ አድርጎ/አሰኝቶ ሾመው›› ማለት ነው። ‹‹ሐንካሳን የሐውሩ ዝእበ›› ሲል ‹‹ጅብኛ ሄዱ (እንደ ጅብ ሄዱ)›› ማለት ነው። ‹‹ተሠይመ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት›› ሲል ሊቀ ሐዋርያነት ጴጥሮስ ተሾመ›› ማለት ነው።
አዋጅ ፲
‹በ› ከጊዜ ከቦታ በተጨማሪ በስድስት ግሦች ይወጣል። ግሶቹም ዐብየ፣ ንእሰ፣ ዐረየ፣ ኀብረ፣ ሰክረ እና ቀደመ ናቸው። ‹እም› ም ከጊዜ ከቦታ በተጨማሪ በሰባት ግሶች ይወጣል። ግሶቹም ተጸነሰ፣ ነድየ፣ ርኅበ፣ ጾመ፣ ጸምአ፣ ተዐርቀ፣ ተኀረመ፣ ዐብየ፣ ንእሰ ናቸው።
አዋጅ ፲፩
ምእላድ የሚሆኑ ቀለማት ስምንት ናቸው፡፡ እነዚህም አ፣ ን፣ ት፣ ሙ፣ ይ፣ ው፣ ህ፣ ል ናቸው። ‹‹ኵሎሙ፣ አድባር፣ ጻድቃን፣ ካህናት፣ አንስትያ፣ አበው፣ ኪሩቤል፣ መጣብሕ›› ይላል።
አዋጅ ፲፪
ቸልታ የሚሆኑ አገባባት ፲፩ ናቸው። እነዚህም እንዘ፣ ኢ፣ ወ፣ እም፣ ምስለ፣ ቦዝ፣ በ፣ ግእዝ፣ ራብዕ፣ ኃምስ፣ ሳብዕ ናቸው።
የሚከተሉትን የግእዝ ዓረፍተ ነገሮች ወደ አማርኛ ተርጉሙ።
፩) ሰክረ ወይነ።
፪) ክርስቶስ መጽአ መላእክተ።
፫) አምላክ ተሰቅለ ሰብአ።
፬) ለይኩን ብርሃን።
፭) ወረደ ባቢሎን
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!