ኢትፍርሕዎ ለሞት ፍርሕዋ ለኃጢአት፤ቅዱስ ያሬድ

           

ሞት በብዙ መንገድ ቢተረጎምም ቀጥተኛ የቃሉ ፍቺ ግን መለየት ማለት ነው፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በሚል መጽሐፋቸው “መሞት፣ መለየት፣ በነፍስ ከሥጋ፣ በሥጋ ከነፍስ መራቅ፣ እየብቻ መኾን፣ መድረቅ፣ መፍረስ፣ መበስበስ፣ መነቀል፣ መፍለስ፣ መጥፋት፣ መታጣት” በማለት ይፈቱታል፡፡ (ኪዳነ ወልድ፣ገጽ፣፭፻፹፩) እንዲሁም አለቃ “ሞት በቁሙ የሥጋዊና የደማዊ ሕይወት ፍጻሜ በአዳም ኃጢአት የመጣ ጠባይዓዊ ዕዳ ባሕርያዊ ፍዳ” በማለት ይፈቱታል፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

ከላይ በተገለጸው ገጸ ንባብ እንደምንረዳው ሞት አንድ ላይ የነበሩ አካላት መለያየት፣ ለየብቻ መሆን፣ መራራቅ፣ ወዘተ ማለት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ሞትን በአጭር አገላለጽ እንዲህ ነው ብሎ መተርጎም ከባድ ስለሚሆን በዓይነት ከፋፍለን ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

ሞት ከላይ በተመለከትነው መልኩ መለየት፣ በሥጋ ከነፍስ መራቅ፣ እየብቻ መኾን ማለት ሲሆን በዋናነት ሞተ ሥጋና ሞተ ነፍስ ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡

ሀ.ሞተ ሥጋ፡- የሥጋ ሞት የሚባለው የነፍስ ከሥጋ መለየት ማለት ነው፡፡ ይህ ሞት የማይቀር ስለሆነ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “ኢትፍርሕዎ ለሞት ፍርሕዋ ለኃጢአት እስመ ሞትሰ ኢየኀድገክሙ ዘበላዕሉ ኀልዩ ወአኮ ዘበምድር፤ ሞትን አትፍሩት ኃጢአትን ግን ፍሩ ሞት አይቀርምና ስለሰማያዊው አስቡ እንጂ ስለምድራዊው አይደለም” እያለ ያስተምራል፡፡ ስለዚህ ሞተ ሥጋ ሲባል በተዋሕዶ አንድ ሁነው የኖሩት ነፍስና ሥጋ መለያየት ለየብቻ መሆን ማለት ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ሃይማኖትና ምግባር የማይነጣጠሉ እንደሆኑ በምሳሌ ሲያስተምር የጠቀሰው የነፍስና የሥጋን ህልውና ነው። «ከመ ሥጋ ዘአልቦ መንፈስ ምውት ውእቱ ከማሁ ሃይማኖትኒ እንተ አልባቲ ምግባረ ሠናይ ምውት ይእቲ ለሊሃ፤ ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው» (ያዕ.፪፥፳፮) እንዲል፡፡ ስለዚህ ነፍስ ያለሥጋ ሥጋም ያለ ነፍስ ህልውና አይኖራቸውም። ይህ ማለት በሰውነት ህልውና እንጂ ነፍስና ሥጋ ተለያይተው ነፍስም በገነት  ወይም በሲኦል ሥጋም በመቃብር አይኖሩም ማለት አይደለም፡፡ በመሆኑም የሥጋ ሞት የሚባለው የነፍስ ከሥጋ መለየት ነው። ይህ የነፍስ ከሥጋ መለየት የጻድቅ ከሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ነው።

ለ. ሞተ ነፍስ፡- የነፍስ ሞት ማለት የነፍስ ከእግዚአብሔር መለየት ማለት ነው፡፡ የነፍስ ከእግዚአብሔር መለየት በሁለት መንገድ ወይም ወቅት ሊከሠት ይችላል፡፡ የመጀመሪያው ገና ነፍስ ከሥጋ ሳትለይ ወይም በአጸደ ሥጋ ሳለ ኃጢአት በመሥራት የሚፈጠረው ከእግዚአብሔር መለየት ነው፡፡ አባቱን ቀብሮ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሊከተል ጥያቄ ያቀረበውን ደቀ መዝሙር “ሙታኖቻቸውን ይቀብሩ ዘንድ ሙታንን ተዋቸው፡፡” (ማቴ.፰፥፳፪) በማለት ነፍሳቸው ከሥጋቸው ሳትለይ ኃጢአት ሠርተው ከእግዚአብሔር የተለዩት (ሙታን) ነፍሳቸው ከሥጋቸው የተለችባቸውን ሙታን ይቅበሯቸው ብሎ አስተማረ፡፡

ነፍስ በባሕርይዋ የምትሞት አይደለችም፤ ሞተ ነፍስ የሚባለው የማትኖርበት ጊዜ ስላለ ሳይሆን ከምትኖርበት ሁኔታ አንጻር ነው። ይህ ማለት ነፍስ በሃይማኖት ጸንታ በምግባር ቀንታ ባለመኖሯ ወደ ሲኦል በኋላም ገሃነመ እሳት ትወርዳለች። የነፍስ ሞት ማለት ገነት በመግባት ፈንታ ሲኦል፣ መንግሥተ ሰማያት በመግባት ፈንታ ገሃነመ እሳት መግባት ነው። «ድል የነሣው ሁለተኛውን ሞት አያይም» (ራእ.፪፥፲፩) ተብሎ የተጻፈው ነፍስ ከሥጋ መለየትን ሳይሆን ገሃነመ እሳት መውረድን አያይም ለማለት ነው።

ሞት ማለት መለየት ነውና ነፍስ ከፈጣሪዋ ከእግዚአብሔር ተለይታ ካልፈጠራት ከዲያብሎስ ጋር መኖር ስትጀምር የነፍስ ሞት ይባላል። ሁለተኛ ሞት የተባለውም እግዚአብሔር ያዘጋጀውን መንግሥተ ሰማያት አጥታ በኃጢአቷ ምክንያት ገሃነመ እሳት መውረድ ነውና «ድል የነሣው ሁለተኛውን ሞት አያይም» ማለት ከላይም እንደተገለጸው ገሃነመ እሳት አይገባም ማለት ነው።

ከላይ ለተመለከትናቸው የሥጋም ሆነ የነፍስ ሞት ልዩ ልዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡

ሀ.ተፈጥሮ፡- እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥር የስሙ ቀዳሽ፣ የመንግሥቱ ወራሽ ሁኖ እንዲኖር ነው፡፡ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረው የሰው ልጅ ትእዛዙን ጠብቆ ለጊዜው ይኖርባት ዘንድ ከተሰጠችው ከገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዲሸጋገር ነው፡፡ ይህ ከገነት የሚሸጋገርበትም መንገድ ዕፀ ሕይወትን በልቶ ታድሶ ነው፡፡

ይህ ሞት ዕፀ በለስን በልቶ ከእግዚአብሔር በጸጋ ያገኘውን ከተነጠቀ በኋላ ሥቃይ የበዛበት ሁኗል፡፡ በተለይም ከውድቀት በኋላ እስከ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ድረስ የከፋ ነበር፡፡ ሰው ሁሉ በጻእር፣ በጋር፣ በጭንቅ ይሞት ነበር፡፡ ሞቶም ወደ ሲኦል ይወርድ ነበር፡፡ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት “ሕያው ሁኖ የሚኖር ሞትንስ የማያይ ሰው ማን ነው? ነፍሱንስ ከሲኦል እጅ የሚያድናት ማን ነው?” (መዝ.፹፰፥፵፰) በማለት እንደገለጸው ሞትን አሸንፎ የሚቀር ከሲኦልም መዳን የሚችል አልነበረም፡፡

በሐዲስ ኪዳን ግን ለኃጥኣን ነው እንጂ ለጻድቃን ሞት የገነት መውረሻ ነው፡፡ ኢትዮጳያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ “ሞቶሙሰ ለጻድቃን ሕይወቶሙ ውእቱ እስመ ለጻድቅ ይትሌዓል ቀርኑ በክብር ጻድቃን እለ አስመርዎ ለእግዚኦሙ ምድረ ብርህተ ወጽእዱተ ይወርሱ፤ የጻድቃን ሞታቸው ሕይወታቸው ነው፡፡ የጻድቅ ክብሩ እጅግ ከፍ ከፍ ይላልና፡፡ ጌታቸውን ደስ ያሰኙት ጻድቃን ብርህት ጽእዱት የሆነች ምድርን የወርሳሉ፡፡” በማለት ድጓ በተባለ ድርሰቱ ያስረዳል፡፡ ስለዚህ ለጻድቃን ሞተ ሥጋ ማለትም የነፍስ ከሥጋ መለየት ሕይወታቸው ነው፡፡ የነፍስ ሞት የለባቸውም፡፡ የነፍስ ሞት ካለባቸው ጥንቱኑ ጻድቃን ሊባሉም አይችሉም፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም «ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር፤ የጻድቅ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው» (መዝ.፻፲፭፥፭) በማለት ስለሕዝቅያስ በተናገረው  ኃይለ ቃል ያስረዳን የነፍስ ከሥጋ መለየት ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም፣ ውጣ ውረድ፣ ድካም ካለበት ዓለም ውጣ ውረድ ድካም ወደሌለበት ዓለም መሄድ እንደሆነ ነው። ስለዚህ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ በዚህች ዕለት የቅዱሳን ዕረፍት ነው እየተባለ ይነገራል። ድካም ካለበት ድካም ወደሌለበት ስለሆነ ዐረፈ ወይም ዐረፈች እየተባለ ይነገራል።

ለ. ኃጢአት፡- በኃጢአት ምክንያት የሚመጣ ሞትን እግዚአብሔር አልፈጠረውም፡፡ መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን እንደሚነግረን እንዲህ ያለው ሞት የሰው ልጅ የፈጣሪውን ትእዛዝ በመተላለፉ ምክንያት የሰለጠነበት ነው። «በሕይወታችሁ ስሕተት ለሞት አትቅኑ፤ በእጃችሁም ሥራ ጥፋትን አታምጡ። እግዚአብሔር ሞትን አልፈጠረምና፤ የሕያዋንም ጥፋት ደስ አያሰኘውምና። ነዋሪ ይሆን ዘንድ ፍጥረቱን ፈጥሮአልና፣ የዓለም መፈጠርም ለድኅነት ነውና፣ በእነርሱም ዘንድ የጥፋት መርዝ አልነበረምና፣ ለሲኦልም በምድር ላይ ግዛት አልነበረውምና። ጽድቅ አትሞትምና። ክፉዎች ግን በእጃቸውና በቃላቸው ጠሩት ባልንጀራም አስመሰሉት። በእርሱም ጠፉ። የእርሱ ወገን መሆን ይገባቸዋልና ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረጉ» (ጥበ.፩፥፲፪-፲፯) በማለት ነግሮናል።

ሕይወት የተባለው የጻድቃን ሞት እንጂ የኃጥአን ሞት  አይደለም። ምክንያቱም ኃጥአን ምንም እንኳ ወደማያልፈው ዓለም የሚሄዱ ቢሆንም መከራ ወደ አለበት፣ ሥቃይ ወደሚበዛበት እንጂ ዕረፍት ወደአለበት መሄድ አይችሉም። መከራና ሥቃይ ወደሚበዛበት ዓለም መሄድ ደግሞ ሕይወት ሊባል አይችልም። እንዲያውም ነቢዩ ዳዊት «ሞቱ ለኃጥእ ጸዋግ፤ የኃጥእ ሰው ሞት ክፉ ነው» (መዝ.፴፫፥፳፩) በማለት አስረድቷል። ጻድቃን ግን ሞተ ሥጋን እንጂ ሞተ ነፍስን አያዩም። ኃጥኣን ደግሞ ሞተ ሥጋም ሞተ ነፍስም ያገኛቸዋል። ስለዚህ ለኃጥእ ሰው ሞተ ሥጋውም ሆነ ሞተ ነፍሱ ክፉ እንጂ መልካም የሚባል አይደለም።

ከላይም እንደገለጽነው ኢትዮጵያዊው “ሊቅ ኢትፍርሕዎ ለሞት ፍርህዋ ለኃጢአት፣ እስመ ሞትሰ  ኢየኃድገክሙ ዘበላዕሉ ኃልዩ ወአኮ ዘበምድ፤ ሞትን አትፍሩ ኃጢአትን ፍሩ ሞት ግን አይተዋችሁምና ስለ ሰማያዊው አስቡ” በማለት የነገረን ከኃጢአት መራቅ ይቻላል፡፡ ከሥጋዊ ሞት ግን መራቅ አይቻልም፡፡ በእርግጥ ከድንገተተኛ ሞት ንስሓ ሳይገቡ ከሚመጣ ሞት፣ መዳን ይቻላል፡፡ ሰብአ ትካት በንፍር ውኃ ሲጠፉ ኖኅ ከነቤተ ሰቡ ድኗል (ዘፍ.፯፥፩-ፍጻሜ)፤ የሰዶምና የገሞራ ሕዝብ ሲጠፉ ሎጥ ከሁለት ልጆቹ ጋር ድኗል (ዘፍ.፲፱፥፲፪-፳፪) ፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ሥጋዊ ሞት ጊዜው ሊረዝም ይችላል እንጂ አይቀርም፤ የነፍስ ሞት ግን ማለት ከኃጢአት መራቅ ይቻላል፡፡ በሚቻል ነገር እንጂ በማይቻል ገር መታገል ደግሞ አግባብ ስላልሆነ መፈራት ያለበትን ብቻ ፍሩት በማለት ሊቁ ያስረዳናል፡፡

በዚህ ንኡስ ርእስ መግለጽ የተፈለገው ድንገተኛና አሰቃቂ በሆነ የሞት ቅጣት የተቀጡትንና የመቀጣታቸው ምክንያት ምን ነበር የሚለውን ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈውን ሁሉ መዘርዘር አይቻልም። ለምሳሌ ያህል የተወሰኑ ማሳያዎችን ብቻ  እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

. ሰብአ ትካት፡- እግዚአብሔር አምላካችን ከሰዎች ኃጢአት የተነሣ እጅግ አዝኖ የነበረበት ዘመን ነው፡፡ ከኃጢአታቸው ክፋትና ጽናት የተነሣም እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በመፍጠሩ ተጸጸተ የተባለበት ዘመን እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ በዚህም የከፋና እጅግ የጠነከረ ኃጢአታቸው በንፍር ውኃ ጠፍተዋል፡፡ በእነርሱ ኃጢአት ያልተጨመረው ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ትእዛዝ በአዘጋጀው መርከብ ድኗል፡፡ (ዘፍ.፯፥፩-ፍጻሜ)

ለ. ግብጻውያን፡- በግብጻውያን የተቃጣው አንዱ ሞት ነበር፡፡በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ እንደምናነበው እስራኤላውያን በፈርዖናውያን ዘንድ እጅግ የከፋ በደል ደረሰባቸው፡፡ እግዚአብሔርም “መከራቸውን አየሁ ለቅሷቸውንም ሰማሁ እንግዲህ ላድናቸው ወረድሁ” (ዘጸ.፫፥፱) በማለት ምክንያተ ድኅነት ይሆናቸው ዘንድ ሙሴን አስነሣ፡፡ በሙሴ መሪነት በእርሱ አምላካዊ ቸርነት እስራኤልን ከፈርዖናውያን ሊያድን ፈቃዱ በሆነ ጊዜና ፈርዖርናውያን ደግሞ እስራኤልን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባልሆኑ ጊዜ በዘጠኝ መቅሰፍት በዐሥረኛ ሞተ በኵር በዐሥራ አንደኛ ስጥመት ቀጥቶ እስራኤልን ነጻ አድርጓቸዋል፡፡ (ዘጸ.፲፩፥፩-፲)

ሐ. እስራኤላውያን፡- ከፈርዖናውያን ዘንድ በብዙ ተአምር ያወጣቸውን አምላክ ረስተው ጣዖት ማምለክ ጀመሩ፤ ባሕር ከፍሎ ጠላት ገድሎ ያሻገራቸውን፣ ደመና ጋርዶ በበረሃ የመራቸውን፣ መና አውርዶ የመገባቸውን፣ ዓለት ሰንጥቆ ውኃ አፍልቆ ያጠጣቸውን አምላክ ረሱና አሮንን “አሮን አሮን ግበር ለነ አማልክተ እለ ይቀውሙ ቅድሜነ ወእለ ይመውዑ ጸረነ ዝስኩሰ ሙሴ ዘአውጽአነ እምድረ ግብጽ ኢነአምር ከመምንተ ኮነ፤ አሮን አሮን ከፊታችን የሚቆሙ ጠላታችንን ድል የሚያደርጉ አማልክትን ሥራልን፤ ከግብፅ ያወጣን ሙሴ ምን እንደሆነ አናውቅም” ብለው ጥያቄ አቀረቡ፡፡ በአቀረቡት ጥያቄ መሠረት ወርቃቸውን ብራቸውን ጌጣቸውን ሁሉ ሰብብስቦ ቢያቃጥለው የተድቦለቦለ ነገር ወጣ ቅርጽ ሠርቶ አምላካችሁ ይህ ነው አላቸው፡፡ በብዙ ተአምር ከጠላት ያዳናቸውን አምላክ በተቀረጸ ምስል ለውጠው ማምለክ ጀመሩ (ዘጸ.፴፪፥፩-፳፱) ፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ተቆጣ በአንድ ቀን ሦስት ሺህ እስራኤላውያን ሞቱ፡፡

መ. ዳዊት፡- ዳዊት በበደለ ጊዜ ለቅጣት ከቀረቡለት ቸነፈር፣ ጦርነት፣ ረኃብ መካከል አንዱ ምርጫው ቸነፈር ነበር፡፡  የሦስት ዓመት ረኃብ  በሀገርህ ላይ ይምጣብህን ፣ ወይስ ጠላቶችህ እያሳደዱህ ሦስት ወር ከእነርሱ ትሸሽን ወይስ የሦስት ቀን ቸነፈር በሀገርህ ላይ ይሁን በማለት ከታዘዙበት የእግዚአብሔር የቁጣው መገለጫዎች መካከል አንዱ ቸነፈርና በቸነፈሩ ምክንያት የሚመጣ ሞት ነበር፡፡ ዳዊት የእግዚአብሔር የቁጣው መገለጫ የሆኑትን ሦስት ትእዛዛት መርምሮ የመረጠው እግዚአብሔር መሐሪ ነውና ይምረናል በማለት ቸነፈርን ነበር፡፡ በእግዚአብሔር እጅ ብወድቅ ይሻለኛል ብሎ ቸነፈርን መርጦም ሰባ ሺህ ሰው ሞተበት (፪ሳሙ.፳፬፥፩-ፍጻሜ)፡፡

ከላይ የተዘረዘሩትን ምሳሌዎች መሠረት በማድረግ በአሁኑ ወቅት ዓለምን ስጋት ውስጥ የጣለው የኮቪድ-፲፱ (ኮሮና ቫይረስ) የዓለም ሕዝብ ኃጢአት እጅግ ከፍቶና እግዚአብሔርን አሳዝኖ የመጣ ሊሆን ይችላል ብሎት ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ በኃጢአታቸው ምክንያት በሞት የተቀጡ እንደነበሩ ሁሉ በደዌ የተቀጡም ነበሩ። ለምሳሌ፡-

ዖዝያን፡- ዖዝያን በንግሥናው ዘመን እግዚአብሔር እየረዳው ጠላቶቹን ድል እያደረገ በሰላም ይኖር ነበር።  ነገር ግን እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኘው አገልግሎቱ ከመኖር ይልቅ የማይገባውን ነገር አሰበ፡፡ ልብሰ ተክህኖውን ለብሶ በቤተ መቅደሱ ሊያጥን ገባ፡፡ ሕዝቡና ካህናቱ ለአንተ ክብር አይሆንህም እያሉት በድፍረት ገባ በግንባሩ ላይ ለምጽ ወጣበት፡፡ ያልተሰጠውን ክህነት ሲሻ የተሰጠውን ንግሥና አጣ፡፡ በኃጢአቱ ምክንያት በለምጽ ተመታ፡፡ ለምጽ ስለወጣበት ሲሞት እንኳን የነገሥታቱ መቃብር ባልሆነ እርሻ ውስጥ ቀበሩት፡፡ (፪ዜና መዋ.፳፮፥፲፮-፳፫) እንግዲህ በብሉይ ኪዳን ዘመን ኃጢአት የመቃብር ቦታ እስከመከልከል ድረስ ያደርስ ነበር፡፡ ዛሬም ይህ ለዓለም ሕዝብ አስጊ የሆነው በሽታ የመጣው በኃጢአታችን ምክንያት ሊሆን ይችላል ብሎ በማሰብ መቅሰፍቱን ይመልስልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ይግድ ይላል፡፡

በዚህ ወቅት ሕግ ተላልፎ ለእርሱ ያልተፈቀደውን የክህነት አገልግሎት እፈጽማለሁ ብሎ ወደ ቤተ መቅደስ የገባው ዖዝያን ብቻ ሳይሆን ይህን ስሕተት መገሠጽ ሲገባው ፈርቶ ዝም በማለቱ ነቢዩ ኢሳይያስም በለምጽ ተመትቷል፡፡ (ኢሳ. ፮፥፮-፯) ዛሬ እንኳንስ ኃጢአት እየተሠራ ነው ብለን ባለመናገራችን በሠራነው ኃጢአት ብቻ እንኳን መቅሰፍት ቢመጣብን ምን እንሆን ይሆን ብሎ ማሰብ ተበጊ ነው፡፡

ከላይም እንደተገለጸው ሥጋዊ ሞት ከሆነ አይቀርም፡፡ ይህ ማለት ሰው በሃይማኖት ጸንቶ ቢኖር በበጎ ምግባር ፈጣሪውን ቢያስደስተው ከሥጋ ሞት አያመልጥም፡፡ ነገር ግን ከላይ እንደ ዘረዘርናቸውና እንደነዚህ ካሉት ድንገተኛ ሞቶች ይድናል፤ የንስሓ እድሜ ይኖረዋል፤ በፍጹም ግን ሳይሞት የሚኖር የለም፡፡ ስለዚህ ሥጋዊ ሞት እርሱም “ሞትስ አይተዋችሁምና” ብሎ እንደነገረን  የማይቀር ስለሆነ መንፈሳዊውን ሞት ደግሞ ማምለጥ ስለሚቻል አትፍሩት ተባለ፡፡ ባጭሩ መፍትሔ ስላለው ነው፡፡

    ይቆየን