‹‹አንተ አምላኬና መድኃኒቴ ነህና›› (መዝ. ፳፬፥፭)
ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ እንደተማጸነው
ድኅነትን ዐውቆ እንደተነበየው
አንተ ነህ መድኃኒት እስከመጨረሻው
ጥፋቴን አውቄ ስለምንህ “ማረኝ”
ይቅር በል ኃጢአቴን ከጥፋትም ሰውረኝ
አብዝቼ እጮሃለሁ ፈውሰኝ እያልኩኝ
በንስሓ ጸጸት ስሆን ተለመነኝ
አንተ ነህ አዳኝ ፈውስና ድኅነት
መልካሙ እረኛ ፍኖተ እውነት
ከንቱ ነው ይህ ዓለም የሚያታክት
የሐሰት መንደር ተሞልቶ በክፋት
ትውልድን አሰረ በኃጢአት ሰንሰለት
ስንሆን ደካማ ተሞልተን በትዕቢት
አሁንስ ቀጣኸን በበሽታ መቅሠፍት
ሐኪምም በሌለው ፈውስና መድኃኒት
ጸሎቴን ተቀበል ቸል አትበል እባክህ
ድክመቴን አውቄ አድነኝ ስልህ
ቸርነትህ በዝቶ ከመዓት ርቀህ
እስኪ ተመልከተኝ በምሕረት ዐይኖችህ
ለጥያቄዬ መልስ እጅግ ካንተ እሻለሁ
አምላኬ ሆይ ማረኝ እለምንሃለሁ