‹‹እመን እንጂ አትፍራ›› (ማር. ፭፥፴፮)

በክርስቶስ ክርስቲያን ለተባልን ለእኛ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች እምነት የድኅነታችን መሠረት ነው፤ በፈተናና መከራ ለተሞላው ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ለጠላት ከመሸነፍም ሆነ በኃጢአት ከመውደቅ የሚያድነን እንዲሁም በተስፋ ነገን እንድንጠብቅ የሚረዳን እምነታችን ነው፡፡ ዘወትር በጸሎት አምላካችን ድኅነተ ሥጋን እና ድኅነተ ነፍስን ለምንማጸን እርሱ እግዚአብሔር ቸርነቱና ምሕረቱ የበዛ ነው፡፡

የሰው ዘር በዚህ ምድር መኖሩ ካለመታዘዙ የተነሳ ነውና በተለያዩ በሽታዎች እና በደዌዎች ሲያዝና በሕመም ሲሠቃይ ኖሯል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፈውሰ ሥጋን ሲያገኝ በሌላ ጊዜ ግን ወደማይመለስበት ዓለም በሞት ይለያል፤ ሆኖም ድኅነተ ሥጋን ከአምላካችን እናገኝ ዘንድ እምነት ያስፈልጋል፡፡

በማርቆስ ወንጌል እንደተጻፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰዎች ከምኵራቡ ሹም ቤት መጥተው፥ ‹‹ልጅህ ሞታለች፤ እንግዲህ መምህርን አታድክመው›› ሲሉት ጌታችን ለምኵራብ ሹም፥ ‹‹እመን እንጂ አትፍራ፤›› አለው፡፡ ከጴጥሮስና ከያዕቆብ ወንድም ከዮሐንስም በቀር የሚከተለው ማንም እንዳይኖር ከከለከለ በኋላ ወደ ምኩራብም ሹም ቤት ገባ፤ በዚያን ጊዜም ሲታወኩና፥ ሲያለቅሱ፥ እጅጉም ሲጮኹ አገኛቸው፡፡ ገብቶም፥ ‹‹ለምን ትጮኸላችሁ? ለምንስ ታለቅሳላችሁ? ልጅቱስ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም›› አላቸው፡፡ በጣምም ሳቁበት፤ እርሱ ግን ሁሉን አስወጥቶ የብላቴናይቱን አባትና እናት፥ ከእርሱ ጋር የነበሩትንም ይዞአቸው ብላቴናይቱ ወደ አለችበት ገባ፡፡ የብላቴናይቱንም እጅ ይዞ፥ ‹‹ጣሊታ ቁሚ፤ አንቺ ብላቴና ተነሺ›› አላት፡፡ ያን ጊዜም ያቺ ብላቴና ተነሥታ ወዲያና ወዲህ አለች፤ ዕድሜዋም ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ እነርሱም እጅግ ተደነቁ፡፡ ይህን ድንቅ ተአምር ያደረገ አምላክ ከበሽታና ክፉ ደዌ ማዳን እንደሚችል ማመን የእኛ ፈንታ ነው፡፡ (ማር.፭፥፴፭-፵፪)

ፍራቻ ጥርጣሬን ይፈጥራል፤ ያም የእምነት መጉደል በሰዎች ዘንድ እንዲኖር ከማድረጉ ባሻገር የእኛን መክሊት ያሳጣል፤ ዕጣ ፈንታችን መዳን ሆኖ እኛ ግን በመጥፊያው ጎዳና እንድንጓዝ ያደርገናል፡፡ በመሆኑም ካሳለፍነው ወይንም ከምንኖረው ሕይወት ተሞክሮ ከስሕተት በመመለስ በእያንዳንዱ ምግባራችን እግዚአብሔር አምላክ መኖሩን አምነን ሀሳባችንን እና የልባችንን መሻት እንዲፈጽምልን ለእርሱ መተው ይጠበቅብናል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው ለሐዋርያት እንዳስተማራቸው እምነት ኃይልን ታደርጋለች፡፡ ይህን ጌታችን ሲገልጽ  ‹‹የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት ይታዘዝላችሁ ነበር›› ብሏል፡፡ (ሉቃ.፲፯፥፮)

ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ሁለት ሁለት አድርጎ ወንጌልን እንዲያስተምሩ በላካቸው ጊዜም ‹‹.ወጥተውም ሁሉ ንስሓ ይገቡ ዘንድ ሰበኩ፡፡ ብዙ አጋንንትንም አወጡ፤ ብዙ ድውያንንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው፡፡›› (ማር. ፮፥፲፪)

በእርግጥ የተመረጡ ቅዱሳን ፈውሰ ሥጋን የማድረግ ሥልጣን ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸው ቢሆንም በእነርሱ ለመዳን በፍጹም ልብ ማመን ያስፈልጋል፡፡ ያለበለዚያ ግን ቅጣቱ በነፍስም በሥጋም የከፋ ነው፡፡ ጌታም ለሐዋርያቱ ‹‹ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ሀገርም ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ሊሆንባቸው የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ከዚያች ከተማ ይልቅ በፍርድ ቀን ሰዶምና ገሞራ ዕረፍትን ያገኛሉ›› ብሎአቸዋል፡፡ (ማር. ፮፥፲፩)

እምነት ሲኖር ተስፋ ይሆነናል፤ ተስፋም ወደ  አምላካችን ያቀርበናል፡፡ ይህን ነገር አስተውሎ ተመስገንን ማወቅ ከእኛ ይጠበቃል፡፡ ሰው ከአምላኩ ከራቀ የሰይጣን ባሪያ ሆኖ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ኃጢአትን፣ ክፋትን፣ ተንኮልን እንጂ በጎነትን፣ ጥሩነትን፣ መልካም ምግባርን አይፈጽምም፤ ፍቅር፣ ሰላምንና ደስታንም አያገኝም፡፡

በዚህ ወቅት እኛም እነዚህን ያጣነው በምንሠራው ኃጢአት የተነሳ ነው፤ ሀገራችን ውስጥ ሰላም ከጠፋ ቆይቷል፤ እርስ በእርስ ተጠላልተናል፤ የፍቅርን ትርጉም እስክንረሳ ድረስ ጥላቻ በመካከላችን ተፈጥሯል፤ መኖራችን ለሥጋችን እንጂ ለነፍሳችን አልሆነም፡፡ አብዛኛው ሰው ሥጋዊ ድሎትን በማስበለጥ እና ዓለማዊ ሕይወትን በመምረጥ የዕለት ተግባራችን ከፈጣሪ የሚያርቅና እርሱን የሚያስከፋ ብቻ ሆኗል፡፡ በተለያዩ ስፍራዎች የምንሰማው ወሬ ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ሐሰት የሞላበት ነው፡፡

የብዙዎቻችን ኑሮ ከጥቅም ጋር የተያያዘ በመሆኑ የሥራ ኃላፊነታችንን የይድረስ እናከናውናለን፤  ትዳራችንም በጥቅም ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በቤተሰባችንም መካከልም መተሳሰብ፣ መቻቻል እንዲሁም መተጋገዝ ባለመኖሩ ማኅበራዊ ሕይወታችን ደካማ ይሆናል፤ ይህም አንድነት እንዳይኖረን ያግዳል፡፡

እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ሆኖ ሥርዓተ አምልኮትን ለመፈጸም ያለንን ፍላጎት፣ አንድነት እና ትጋት ይቀንስብናል፤ ብሎም ከተቀደሱ ስፍራዎች ያርቀናል፡፡ ሁል ጊዜ ግን ማስታወስ ያለብን ነገር ሁሉን የሚያይ አምላክ እንዳለ በማመን ዘወትር ከእርሱ ትእዛዝ መውጣት እንደሌለብን ነው፡፡ የእኛን ድኅነት እንጂ ጥፋት የማይፈልገው አምላካችን እግዚአብሔር ያድነን ዘንድ ከሁሉም አስቀድሞ እምነት ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ አሁን ከመጣብን ቸነፈርም እንደሚታደገን አምነን ያለፍርሀት በጸሎት እና በበጎ ምግባር እንትጋ፡፡