አኀዝ

መምህር በትረማርያም አበባው

ጥቅምት ፲ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ውድ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? የግእዝ ቋንቋን ለመማር ይረዳችሁ ዘንድ በየሁለት ሳምንቱ እያዘጋጀን የምናቀርብላችሁ ‹‹የግእዝ ይማሩ›› ዐምድ የዝግጅት ክፍሉ ባጋጠመው ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ለተወሰኑ ጊዜያት ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም በአዲስ መልክ ለአንባብያን በሚያመች መንገድ አዘጋጅተን አቅርበንላችኋልና በጥሞና ተከታተሉን፡፡

አኀዝ ‹‹አኀዘ፣ ጀመረ፣ ቆጠረ›› ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ዘመድ ዘር ነው። ትርጒሙም ቁጥር ማለት ነው። የግእዝ ቋንቋ የራሱ የሆነ መቊጠሪያ ቊጥር አለው። በግእዝ ቋንቋ በዋናነት ፳ መሥራች ቁጥሮች አሉ። እነዚህም፦

ቊጥሩ   ሲነበብ        በአማርኛ

፩…………አሐዱ……………..አንድ

፪…………ክልኤቱ……………ሁለት

፫…………ሠለስቱ……………ሦስት

፬…………አርባዕቱ…………..አራት

፭…………ኀምስቱ…………አምስት

፮………….ስድስቱ…………ስድስት

፯………….ሰብዓቱ…………..ሰባት

፰………….ሰምንቱ………..ስምንት

፱…………..ተስዐቱ………….ዘጠኝ

፲…………..አሠርቱ…………..አሥር

፳…………..ዕሥራ………………ሃያ

፴……………ሠላሳ…………..ሠላሳ

፵……………አርብዓ………….አርባ

፶……………ኃምሳ…………..አምሳ

፷…………ስድሳ/ስሳ………..ስልሳ

፸……………ሰብዓ……………..ሰባ

፹…………..ሰማንያ……….ሰማንያ

፺……………ተስዓ……………ዘጠና

፻……………ምእት……………መቶ

፼…………..እልፍ………….አሥር ሺህ

፲፼…….አሠርቱ እልፍ/አእላፍ……መቶ ሺህ

፻፼…….አእላፋት……..አንድ ሚልየን

፲፼፻……አሠርቱ አእላፋት/ትእልፊት……አሥር ሚልየን

፼፼………ትእልፊታት……መቶ ሚልየን

፲፼፼………ምእልፊት…….አንድ ቢልየን

፻፼፼………ምእልፊታት…….አሥር ቢልየን

ከዚህ በላይ ያሉ ቊጥሮች ዘርፍ በማያያዝ እስከፈለግነው ድረስ መቁጠር እንችላለን። ለምሳሌ 100,000,000,000,000,000,000 ይህ ቁጥር ምእልፊተ ምእልፊታት ይባላል። ምእልፊት ሲባዛ በምእልፊት እንደማለት ያለ ነው።

በእነዚህ መካከል ያሉ ቁጥሮችን ለማንበብና ለመጻፍ በ4 መንገድ እንመልከታቸው። ሁለቱን መንገዶች ዛሬ እንያቸው። ሌሎች ቀሪ ሁለቶችን በቀጣይ ክፍል እናያቸዋለን።

አንደኛ መንገድ፦ከ1 እስከ 100 ያሉ ቊጥሮች

ለምሳሌ 29ን ወደ ግእዝ ቁጥር ለውጥ ቢባል 20+9=፳+፱=፳፱ ይሆናል፤ ይህም ሲነበብ ዕሥራ ወተስዓቱ ይላል። ተጨማሪ ለምሳሌ 84ን ወደ ግእዝ ቁጥር ለመለወጥ 80+4=፹+፬=፹፬ ይሆናል፤ ይህም ሲነበብ ሰማንያ ወአርባዕቱ ይላል። ከ1 እስከ 100 ያሉ ቁጥሮች በዚህ መንገድ ይሄዳሉ ማለት ነው።

ሁለተኛ መንገድ ከ100 እስከ 10,000 ያሉ ቁጥሮች፦

፻ ይህ አንድ መቶ ከሆነ ሁለት መቶ ሦስት መቶ አራት መቶ ለማለት ፊት ለፊቱ ላይ ከአንድ እስከ 10 ያሉ ቁጥሮችን መጠቀም ነው። ይኽውም፦

፻………አሐዱ ምእት….አንድ መቶ

፪፻…….ክልኤቱ ምእት…ሁለት መቶ

፫፻…..ሠለስቱ ምእት…..ሦስት መቶ

፬፻….አርባዕቱ ምእት…..አራት መቶ

፭፻….ኀመስቱ ምእት….አምስት መቶ

፮፻….ሰደስቱ ምእት….ስድስት መቶ

፯፻…..ሰብዓቱ ምእት….ሰባት መቶ

፰፻….ሰመንቱ ምእት…ስምንት መቶ

፱፻…..ተስዓቱ ምእት…..ዘጠኝ መቶ

፲፻…..አሠርቱ ምእት…..አንድ ሺህ ይላል ማለት ነው።

ከዚህ በኋላ በእነዚህ መካከል ያለውን ቁጥር ለምሳሌ 208ን በግእዝ ጻፍ ብትባል 200ን እንዳለ ትወስድና ስምንትን መጨመር ነው ይሄውም ፪፻፰ ይላል። ሲነበብ ክልኤቱ ምእት ወሰመንቱ ተብሎ ይነበባል። ሌላ በተጨማሪ 975ን በግእዝ ጻፍ ብትባል 900ን እንዳለ ትወስድና 75ን መጨመር ነው።75ን ከአንድ እስከ መቶ ባለው አካሄድ መሠረት 70+5=፸+፭=፸፭ ሰብዓ ወኀምስቱ ይሆናል። ስለዚህ 975 በግእዝ ፱፻፸፭ ይሆናል ሲነበብ ተስዓቱ ምእት ሰብዓ ወኀምስቱ ተብሎ ይነበባል ማለት ነው። በግእዝ ቋንቋ አንድ ሺህ ስንል አሥር መቶ ማለት ሲሆን ይህም አሠርቱ ምእት ይባላል። ሁለት ሺ ስንል ደግሞ ዕሥራ ምእት ይላል። ሃያ መቶ ማለት ነው። እንዲህ እያለ ዘጠኝ ሺህ ተስዓ ምእት ይላል ይህም ዘጠና መቶ ማለት ነው። አሥር ሺ ሲደርስ መቶ መቶ ከማለት ይልቅ የራሱ መሥራች እልፍ የሚል ስያሜ ያለው ቊጥር ነው።

፲፻………አሠርቱ ምእት……አንድ ሺህ

፳፻…….ዕሥራ ምእት…….ሁለት ሺህ

፴፻……..ሠላሳ ምእት……ሦስት ሺህ

፵፻……..አርብዓ ምእት….አራት ሺህ

፶፻……..ኃምሳ ምእት…..አምስት ሺህ

፷፻……..ስድሳ ምእት…..ስድስት ሺህ

፸፻……..ሰብዓ ምእት…..ሰባት ሺህ

፹፻…..ሰማንያ ምእት…..ስምንት ሺህ

፺፻……ተስዓ ምእት…….ዘጠኝ ሺህ

፼…….እልፍ………….አሥር ሺህ ይላል።

በዚህ መካከል ያሉ ቁጥሮችን ለማንበብና ለመጻፍ ለምሳሌ 2014 ዓ.ም የሚለውን ስንጽፍ 2000ን እንዳለ ወስደን 14ን መጨመር ነው። ይህም ፳፻፲፬ ይላል። ሲነበብ ዕሥራ ምእት አሠርቱ ወአርባዕቱ ይላል። ሌላ ለምሳሌ 5500ን በግእዝ ለመጻፍ 5000ን እንዳለ ወስደን 500ን መጨመር ነው። ይኽውም ፶፻፭፻ ይላል ሲነበብ ኀምሳ ምእት ወኀምስቱ ምእት ይላል። ሌላ የመጨረሻ ምሳሌ 9999ን በግእዝ ጻፍ ብትባል።9000ን እንዳለ ትወስዳለህ ከዚያ 900ን እንዳለ ትወስዳለህ ከዚያ 90ን እንዳለ ትወስዳለህ ከዚያ 9ን ትወስዳለህ ስለዚህ ፺፻፱፻፺፱ ይሆናል፤ ሲነበብም ተስዓ ምእት ወተስዓቱ ምእት ተስዓ ወተስዓቱ ተብሎ ይነበባል።

የዕለቱ ጥያቄዎች

የሚከተሉትን ጥያቄዎች ወደ ግእዝ ቊጥር ቀይሩ!

1) 456

2) 72

3) 4734

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን፤ አሜን።