አስደናቂው የድንግል ማርያም ሞት

%e1%88%9e%e1%89%b3-%e1%88%88%e1%88%9b%e1%88%ad%e1%8b%ab%e1%88%9d

በዲያቆን ታደለ ፋንታው

ጥር ፳ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

እግዚአብሔር አምላካችን ፍጥረቱንና ዓለሙን ለማዳን የመረጠው ጊዜ በደረሰ ጊዜ አስቀድሞ በመልአኩ አፍ እንዳናገረ ከድንግል ማርያም በድንግልና ተወለደ፤ ክብሩም በእርሷ ላይ ተገለጠ /ኢሳ.፷፥፪/፡፡ ማኅፀኗን ከተማ አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በእርስዋ አደረ፡፡ ይህም ያነጻቸው፣ ይቀድሳቸው ዘንድ በሥጋም በነፍስም መርቶ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ያገባቸው ዘንድ በነቢያት በሐዋርያት ላይ እንዳደረው ዓይነት ማደር አይደለም፤ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሥጋዋ ሥጋን፤ ከነፍስዋ ነፍስን ተዋሕዶ ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ ኾነ እንጂ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ይህን ዘለዓለማዊ እውነት ‹‹መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑል ኃይልም ይጸልልሻል፡፡ ስለዚህ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤›› በማለት ገልጾታል /ሉቃ.፩፥፵፭/፡፡

በእግዚአብሔር፣ በመላእክቱና በሰው ፊት የከበረ ሰው መታሰቢያው ለዘለዓለም ነው፡፡ በቤቱ፣ በቅፅሩ የማይጠፋ የዘለዓለም ስምን ይቀበላልና /ኢሳ.፶፭፥፫/፡፡ ይህንን ታላቅ በረከት እንደሚሰጣቸው የተናገረውም የማይዋሸው እግዚአብሔር አምላክ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ወልድ እናት ከድንግል ማርያም የበለጠ በሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ማንን ልንጠራ እንችላለን? ከእርሷ ሊከብር የሚችል፣ በቅድስና ሕይወት ያለፈ ማን ይኖራል? እግዚአብሔር አምላክ ዘለዓለማዊ ኃይሉንና አምላክነቱን ለዓለም ከገለጸባቸው ሥራዎቹ መካከል በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ላይ የገለጸው ተዋሕዶ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡

ይህንን ኹኔታም ‹‹ብርቱ የኾነ እርሱ ታላቅ ሥራን በእኔ አድርጓል፤ ስለዚህም ምክንያት ፍጥረት ዅሉ ያመሰግኑኛል፤›› በማለት ድንግል ማርያም ገልጻዋለች /ሉቃ.፩፥፵፱/፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ‹‹ከሴቶች መካከል ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ፤›› ብሏታል /ሉቃ.፩፥፳፰/፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥም ‹‹የጌታዬ እናት›› ብላታለች /ሉቃ.፩፥፵፫/፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ልጄ›› ይላታል /መዝ.፵፬፥፱/፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም ‹‹እኅቴ›› ይላታል /መኃ.፭፥፩/፡፡ ለወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም እናት ኾና ተሰጥታዋለች /ዮሐ.፲፱፥፳፮/፡፡

ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ እንደ ገለጸው የቅድስት ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና፤ አማኑኤልን መውለዷ እና የማይሞተው ጌታ ሞት እነዚህ ሦስቱ ከዚህ ዓለም ጥበበኞችና ገዢዎች የተሰወሩ ምሥጢራት ናቸው፡፡ ‹‹እነዚህ ድንቅ ምሥጢራት በራሳቸው ከንግግርና ከቋንቋዎች ዅሉ በላይ ኾነው የሚነገሩ በእግዚአብሔር የዝምታ መጐናጸፊያ የተጠቀለሉ ድብቅና ጣፋጭ ምሥጢሮች ናቸው፤›› ይላል ቅዱስ አግናጥዮስ፡፡

ምስጋናዋ የበዛለት ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊም ‹‹አቤቱ መሰንቆ ልቡናዬን አነቃቃ፤ የልቤንም እንዚራ፡፡ ድምፁን ከፍ አድርጎ የዳዊት ልጅ የኾነችውን የጌታውን እናት ድንግል ማርያምን ያመሰግናት ዘንድ፡፡ ለዓለም ሕይወት የሚሰጠውን የወለደች እናቱ የኾነች እርሷን ከፍ ከፍ ያደርጋት ዘንድ፤›› በማለት ለምስጋናዋ ይዘጋጃል፡፡ በሌላ አንቀጽም ‹‹ከሕሊናት ዅሉ በላይ ለኾነ ለዚህ ነገር አንክሮ ይገባል፤ ምድራዊት ሴት ፈጣሪዋን ወለደችው፡፡ እርሱም እናቱን ፈጠረ፤›› ይላል፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በመጽሐፈ አርጋኖን ድርሰቱ ‹‹ከሚያሰጥመው ባሕር ሞገድ የተነሣ የማትነቀነቅ፤ መልኅቆቿም በሦስቱ ሥላሴ ገመድ የተሸረቡ ናቸው፡፡ ይህቺ ደግሞ ከነፋሳት ኃይል የተነሣ የማትናወጥ በጭንጫ ላይ ያለች የዕንቈ ባሕርይ ምሰሶ ናት፡፡ እርሷን የተጠጋ መውደቅ፣ መሰናከል የለበትም፤›› የሚላት እመቤታችን ሞት ሥጋ ለለበሱ ዅሉ አይቀርምና እርሷም እንደ ሰው የምትሞትበት ጊዜ ደረሰ፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአባት በእናቷ ቤት ሦስት ዓመት፤ በቤተ መቅደስ ዐሥራ ሁለት ዓመት፤ ከልጇ ጋር ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር፤ ከጌታችን ስቅለት በኋላ ደግሞ ዐሥራ አምስት ዓመታት በምድር ኖራለች፡፡ ጌታን የፀነሰችበትን ወራት ስንጨምር በዚህ ዓለም በሥጋ የቆየችበት ጊዜ ስድሳ አራት ዓመት ይኾናል፡፡ ያረፈችውም ጥር ፳፩ ቀን ነው፡፡ እመቤታችን ባረፈች ጊዜ ሐዋርያት ሊቀብሯት ሲሹም ከአይሁድ ክፋት የተነሣ ልጇ ሌላ ክብርን ደረበላት፡፡ ከጌቴሴማኒ ሥጋዋ ተነጥቆ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር እስከ ነሐሴ ፲፮ ቀን ለሁለት መቶ አምስት ቀናት ቆይታለች፡፡

ልጇ ወዳጇ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሥልጣኑ እንዳሸነፈ ዅሉ እርሷንም በእርሱ መለኮታዊ ኃይል ሞትን አሸንፋ እንድትነሣ አድርጓታል፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም የኃያሉ እግዚአብሔር እናቱ፣ መቅደሱ፣ ታቦቱ፣ መንበሩ ኾና እያለ ሞትን መቅመሷ በራሱ የሚያስገርም ምሥጢር ነው፡፡ ከቤተ ክርስትያን ወገን ሞትን እንዳያዩ የተወሰዱ ቅዱሳን ሄኖክ፣ ኤልያስ፣ ሌሎችም አበው እንዳሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡

ይህ ከሕሊናት ዅሉ በላይ የኾነው የእመቤታችን ዕረፍት ርቀቱ በመጽሐፈ ዚቅ እንዲህ ተብሏል፤ ‹‹ለምንት ይዜኃር ኃያል በኃይሉ ወባዕል በብዝኃ ብዕሉ ኢያድለወ  ሞተ ክርስቶስ ለሥጋ አባሉ ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐፅብ ለኵሉ፡፡ ኃይለኛ በኃይሉ ለምን ይታጀራል? ባለ ጸጋም በሀብቱ ብዛት፡፡ ክርስቶስ ለአካሉ አላደላም፤ ሞትስ ለሟች ይገባዋል፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ማርያም ሞት ግን አስደናቂ ነው፡፡››

የቤተ ክርስቲያን ትውፊት የድንግል ማርያም ሞት በሚከተሉት ምክንያቶች እንደ ኾነ ያስረዳል፤ የመጀመሪያው ‹‹ለመለኮት ማደርያ ለመኾን የበቃችው ኃይል አርያማዊት ብትኾን ነው እንጂ እንደ ምድራዊት ሴትማ እንደምን ሰማይና ምድር የማይችለውን አምላክ ልትሸከመው ይቻላታል?›› የሚሉ ወገኖች ነበሩና እግዚአብሔር ወልድ የተዋሐደው የሰው ልጆችን ሥጋ መኾኑን ለማጠየቅ ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲያስረዳ ‹‹እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፣ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፣ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፡፡ በሕይወታቸው ዅሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሠሩ የነበሩትን ዅሉ ነጻ እንዲያወጣ፣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡ የአብርሃምን ዘር ይዟል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም፤›› አለ /ዕብ.፪፥፲፬-፲፭/፡፡ በዚህም ድንግል ማርያም የአዳም ዘር መኾኗ ታወቀ፡፡ ሁለተኛውም ቅዱስ ያሬድ እንደ ተናገረው ጌታችን በፍርዱ አድልዎ የሌለበት አምላክ መኾኑ ይታወቅ ዘንድ ነው፡፡ ሥጋ የለበሰ ዅሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ የግድ ነውና፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ወዳጄ ሆይ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ ነዪ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ፤ ዝናሙም አልፎ ሔደ፡፡ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፤ የዜማም ጊዜ ደረሰ፡፡ የቍርዬም ቃል በምድር ላይ ተሰማ፤›› /መኃ.፪፥፲-፲፬/ በማለት የተናገረው ትንቢት እመቤታችን የዚህ ዓለም ድካሟ ዅሉ መፈጸሙን ያስረዳል፡፡ ልጇን ይዛ ከአገር ወደ አገር በረሀብና ጥም የተንከራተተችበት ጊዜ አሁን አለፈ፡፡ ታናሽ ብላቴና ሳለች ልጇን አዝላ በግብጽ በረሃ የተቀበለችው መከራ ዅሉ ፍጻሜ አገኘ፡፡

ከእግረ መስቀል ሥር ወድቃ የልጇን የቈሰለ ገላ እየተመለከተች የደረሰባት ልብ የሚሰነጥቅ ኀዘን ወደ ደስታ ተለወጠ፡፡ ልጇ ሲንገላታ፣ ሲሰደድ፣ ሲገረፍ፣ ሲሰቀል፣ ሲቸነከር ያየችበት ዓለም አለፈ፡፡ ‹‹በነፍሷ ሰይፍ ያልፋል›› ተብሎ የተነገረው ልብ የሚሰነጥቅ መከራ የሚቀጥልበት ጊዜ ተፈጸመ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ለዛቲ ብእሲት ሠረቀ ላዕሌሃ ብዕለ ጸጋሁ ለአብ ወአግዓዛ እምእኩይ ውስተ ሠናይ እሞት ውስተ ሕይወት፤ በድንግል ማርያም ላይ የአብ የባለጸግነቱ ብዛት ተገለጠ፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከክፉ ዓለም ወደ በጎ ዓለም አሸጋግሯታልና፤›› ሲል የተነጋረውም ይህንኑ ምሥጢር የሚገልጽ ነው፡፡

እመቤታችን አሁን የልጇን ልዕልና ከሚያደንቁ ጋር ታደንቃለች፤ ከፍ ከፍ ከሚያደርጉት ጋር ታከብረዋለች፡፡ ይኸውም ከገቡ የማይወጡበት፤ ኀዘን፣ መከራ፣ ችግር የሌለበት ሰማያዊ አገር ነው፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት ስደት፣ መከራ፣ ኀዘን፣ ሰቆቃ፣ መገፋት፣ መግፋትም የለም፡፡ ቅዱሳን ሩጫቸውን ጨርሰው የድል አክሊልን የሚቀዳጁበት ሥፍራ ነው፡፡ በዚህም ከፍጡራን ኹሉ ከፍ ባለ በታላቅ ክብርና ጸጋ ለዘለዓለም እንደምትኖር እናምናለን፡፡ ልመናዋ፣ ክብሯ፣ ፍቅሯ፣ አማላጅነቷ፣ የልጇም ቸርነት በኹላችን ላይ አድሮ ይኑር፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡