አስተርእዮተ እግዚአብሔር በፈለገ ዮርዳኖስ

bb

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲጠመቅ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጥር ቀን ፳፻፱ .

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! እንደሚታወቀው በየዓመቱ ጥር ፲፩ ቀን በዓለ ጥምቀትን እናከብራለን፡፡ በቅድሚያ ለብርሃነ ጥምቀቱ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ እያልን በዛሬው ዝግጅታችን እግዚአብሔር አምላካችን በሐዲስ ኪዳን ካደረጋቸው መገለጦች ወይም ከታየባቸው መንገዶች መካከል በዮርዳኖስ ወንዝ ያደረገው መገለጥ (አስተርእዮ) አንደኛው መኾኑን የሚያስገነዝብ ትምህርት በአጭሩ ይዘን ቀርበናል፤

‹‹አስተርእዮ›› የሚለው ቃል ‹‹አስተርአየ (አርአየ) = አሳየ፣ ገለጠ፣ ታየ፣ ተገለጠ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም ‹‹መታየት፣ መገለጥ፣ ማሳየት፣ መግለጥ›› ማለት ነው /የኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት/፡፡ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር በፈለገ ዮርዳኖስ›› የሚለው ሐረግም ‹‹የእግዚአብሔር በዮርዳኖስ ወንዝ መገለጥ፣ መታየት›› የሚል ትርጕም አለው፡፡

ከዚህ ላይ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር›› ስንል የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስ መገለጥ ማለታችን መኾኑን ለማስታዎስ እንወዳለን፡፡ ‹‹እግዚአብሔር›› የሚለው ቃል ሦስቱም አካላት (ቅድስት ሥላሴ) በጋራ የሚጠሩበት መለኮታዊ ስያሜ ነውና፡፡ ‹‹አንሰ ሶበ እቤእግዚአብሔር እብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ በአሐዱ ስም ሥሉሰ ያምልኩ፤ እኔ እግዚአብሔር በአልሁ ጊዜ ስለ አብም፣ ስለ ወልድም፣ ስለ መንፈስ ቅዱስም እናገራለሁ፤ (ምእመናን) በአንዱ ስም (በእግዚአብሔር) ሦስቱ አካላትን ያመልኩ ዘንድ፤›› እንዳለ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት /ሃይማኖተ አበው/፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን እግዚአብሔር አምላክ በብሉይም ኾነ በሐዲስ ኪዳን በአንድነቱ በሦስትነቱ በግብር (በሥራ)፣ በራእይና በገቢረ ተአምራት በልዩ ልዩ መንገድ ለቅዱሳኑ ተገልጧል፡፡

በብሉይ ኪዳን ልዩ ልዩ ምልክት በማሳየት፤ በቅዱሳን ነቢያትና በመሳፍንት፣ በነገሥታት፣ በካህናትና በነቢያት ላይ በማደር ወይም በራእይ በማነጋገር፤ በተጨማሪም በጻድቃኑ ላይ ቸርነቱን በማሳየት፣ በክፉ አድራጊዎች ላይ ደግሞ ኀይሉን በማሳየት ሲያደርጋቸው በነበሩ ተአምራቱና ሥራዎቹ ይገለጥ ነበር፡፡

በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ለአዳምና ለልጆቹ በገባው ቃል መሠረት የሰውን ሥጋ ለብሶ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በአካለ ሥጋ ተገልጦ በገቢረ ተአምራቱ፣ በትንሣኤውና በዕርገቱ አምላክነቱን አሳይቷል፡፡

የብሉይ ኪዳኑ መገለጥ በምልክት፣ በራእይ፣ በድምፅና በመሳሰሉት መንገዶች የተደረገ መገለጥ ነበር፤ የሐዲስ ኪዳኑ መገለጥ ግን ወንጌላዊው ዮሐንስ ‹‹መቼም ቢኾን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው›› /ዮሐ.፩፥፲፰/ በማለት እንደ ገለጸው አምላካችንን በዓይነ ሥጋ ያየንበት አስተርእዮ ስለ ኾነ ከመገለጦች ኹሉ የተለየ ጥልቅ ምሥጢር አለው፡፡

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር በሥጋ ያደረገውን አስተርእዮ (መገለጥ) ከምሥጢረ ሥላሴ ጋር በተያያዘ መልኩ በሦስት መንገድ ይገልጹታል፤ ይኸውም በእመቤታችን ማኅፀን፤ በዮርዳኖስ ወንዝ እና በደብረ ታቦር ተራራ ላይ እንደ ኾነ ያስረዳሉ፡፡

ይህንንም ‹‹በላዕሌኪ ወበዮርዳኖስ ወበታቦር ሥልሰ ጊዜያተ፤ ዘአልቦ ተውሳከ ወአልቦ ሕጸተ፤ ለውሉደ ሰብእ ያርኢ ዘሥላሴሁ ገጻተ፤ ጽጌኪ ድንግል ተአምሪሁ ከሠተ፤ ወበፀዳሉ አብርሀ ጽልመተ፡፡›› በማለት ይገልጹታል /ማኅሌተ ጽጌ/፡፡

ትርጕሙም ‹‹እግዚአብሔር አምላክ ጭማሬም ጉድለትም የሌለበትን ሦስትነቱን ለሰው ልጆች ያሳይ ዘንድ በአንቺ (በእመቤታችን በድንግል ማርያም) በዮርዳኖስ እና በደብረ ታቦር ሦስት ጊዜ በመገለጥ አበባሽ (ልጅሽ) ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራቱን (አምላክነቱን፣ ብርሃነ መለኮቱን፣ አንድነቱን፣ ሦስትነቱን) አሳየ፡፡ በብርሃነ መለኮቱም ጨለማውን አስወገደ (ብርሃን አደረገ)›› ማለት ነው፡፡

ይህም ጌታችን በለበሰው ሥጋ በእመቤታችን ማኅፀን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን መወሰኑን በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀበት ዕለት ምሥጢረ ሥላሴን መግለጡን (እግዚአብሔር አብ ‹‹የምወደው ልጄ እርሱ ነው፤ እርሱን ስሙት›› ብሎ  ሲመሰክር፣ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ ራሱ ላይ ሲያርፍ ማለት ነው)፤ እንደዚሁም በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጥ መለኮታዊ አንድነቱና አካላዊ ሦስትነቱ መታወቁን ያመለክታል፡፡

በአጭሩ ይህ ድርሰት እግዚአብሔር በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ላይ ያደረገውን አስተርእዮ የሚገልጽ ነው፡፡ ይህ ትምህርትም ጥር ፲፩ ቀን በሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳር በተመሳሳይ መልኩ ተጠቅሷል፡፡

ክብር ይግባውና በአካለ ሥጋ የተገለጠው እግዚአብሔር ወልድ (ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ) እከብር አይል አምላከ ክቡራን፣ አክባሬ ፍጥረታት፤ እቀደስ አይል አምላከ ቅዱሳን፣ ቀዳሴ ፍጥረታት ኾኖ ሳለ ለኛ የጥምቀትን ሥርዓት ሊሠራልን ሥጋ ከለበሰ ሠላሳ ዓመት ሲሞላው በመጥምቀ መለኮት በቅዱስ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠምቆ ከወንዙ ሲወጣም እነሆ ሰማያት ተከፈቱ፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀመጠ፡፡ በዚህ ጊዜ የሚሰሙትን ዅሉ ያስደነገጠ፣ ምድራዊ ፍጥረት ሊሸከመው የማይቻል ‹‹ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘሎቱ ሠመርኩ፤ በእርሱ ደስ የሚለኝ፣ ልመለክበት የወደድሁት፣ ለተዋሕዶ የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው!›› የሚል ግሩም ቃል ከሰማይ መጣ /ማቴ.፫፥፲፯/፡፡

ይህ እግዚአብሔር አብ የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አባት መኾኑን የመሰከረበት ቃልም ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር በገለጠበት ዕለት በተመሳሳይ መንገድ ተነግሯል /ማቴ.፲፯፥፭፤ ሉቃ. ፱፥፴፮፤ ፪ኛ ጴጥ.፩፥፲፯/፡፡ ከዚህ በፊት በልዩ ልዩ ምሳሌና ኅብር ሲገለጥ የነበረ ምሥጢረ ሥላሴ በዮርዳኖስ ወንዝ በግልጥ ታየ፤ እግዚአብሔር ወልድ በለበሰው ሥጋ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ፤ እግዚአብሔር አብ ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነው›› ብሎ አባትነቱን ሲመሰከር፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ከሰማይ ወርዶ በራሱ ላይ ሲያርፍ ፍጡራን በዓይናቸው አዩ፡፡

ይህንን ድንቅ ምሥጢር የተመለከቱ ዅሉ የእግዚአብሔርን ሥራ አደነቁ፤ በአምላክነቱም አመኑ፡፡ ሰይጣን ልቡናቸውን ያሸፈተባቸው መናፍቃን ግን በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ባለማመናቸው የተነሣ ለክብሩ በማይመጥን የአማላጅነት ቦታ ያስቀምጡታል፡፡ እኛ ግን ቅዱሳን ሐዋርያት እንዳስተማሩን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም እንዳስረዱን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ መለኮት፣ አንድ ሥልጣን፣ አንድ አገዛዝ አላቸው፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር፣ በሦስትነት በአንድነት የሚመለክ፣ አምላክ ወልደ አምላክ ነው ብለን እናምናለን፤ አምነንም እንመሰክራለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡