አሰግድመኝ ቅድስት ማርያም ክፍል ሁለት

 ግንቦት 19 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በካህናቱ መሪነት ከተራራው ሥር ወደምትገኘው ወደ ቀድሞ ዋሻ ቤተ ክርስቲያን ስናመራ፤ ከተራራው አናት ላይ ሆነን ቁልቁል ስንመለከት ትልቅ ወንዝና ደረቱን ለኛ የሰጠ ተራራ ተመለከትን ፡፡ ካህናቱንና ዲያቆናቱን ተከትለን ቁልቁል የሚወስደውንa washa 1 ቀጭን መንገድ ተያያዝነው፡፡ ወንዙ ምን ይባላል አልናቸው ለአንድ አዛውንት “ የማርያም ዥረት ነው የሚባለው” አሉን ፡፡ እንደመቀነት የሚጠማዘዘውን ቀጭን መንገድ እየተከተልን ወደ ዋሻው አፋፍ ደረስን፡፡ ወደ ዋሻው መግቢያ በስተቀኝ በኩል በመጠኑ የጎደጎደ ሥፍራ ይታያል፡፡ ምን እንደሆነ ጠየቅን፡፡ “ከተራራው ሥር እየፈለቀ የሚወርድ ማየገቦ የሚጠራቀምበት ጉድጓድ ነበር፤ (ማየገቦ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ በቦታው ያልነበረው አንድ ዓይና ሌንጊኖስ ከአይሁድ ጋር ለመተባበር ብሎ ኢየሱስ ክርስቶስን በጦር ቢወጋው ውኃና ደም እንደ ለ ፊደል ፈሷል ፡፡ የፈሰሰው ውኃ ማየገቦ ይባላል፡፡) ዋሻው ቤተ መቅደስ ከተደረመሰ በኋላ ደርቋል” አሉን አዛውንቱ፡፡

የተናደው የድንጋይ ክምር አልፈን ወደ ውስጥ ዘለቅን፡፡ ቀድሞ ቅድስትና መቅደስ ሆኖ ሲያገለግል የነበረውን ቤተ ክርስቲያን ለማየት ቻልን፡፡ ቀጥለን በጧፍ ብርሃን እየተመራን ሰፋፊ የዋሻውን ክፍሎች ተመለከትን፡፡ ውስጥ ለውስጥ በሚያስኬደው መንገድ ሽቅብ ወጥተን እንደገና ወደጎን በመሄድ በሌላ መንገድ ከዋሻው ወጣን፡፡

በቀጣይነትም የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ መቅደስ የነበረውን ዋሻ ለማየት ተጓዝን፡፡ ቤተ መቅደሱ መጠነኛ እድሳት ከመፈለግ ውጪ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ቅኔ ማኅሌቱ፤ ቅድስቱና መቅደሱ በር ቢገጠምላቸው ዛሬም አገልግሎት ሊሰጥ ይችላል፡፡ የጉዶ በረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ጽላት ከዚህ ዋሻ መሄዱንም ከካህናቱ ተነገረን፡፡ በገዳሙ ውስጥ 24 የሚደርሱ ጽላት ሲኖሩ፤ በተለያዩ ዘመናት የተጻፉ የብራና መጻሕፍት በብዛት እንደሚገኙም ተገለጸልን፡፡

ይህ የዋሻ ቤተ ክርስቲያን እስከ 1951 ዓ.ም. ድረስ አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበረና በወቅቱ በሥፍራው የነበሩት መምሬ ጥላዬ ስለሁኔታው እንዲህ ይገልጻሉ፡፡ “ሰኔ 21 ቀን 1951 ዓ.ም. ምሽት ወደ ቤተ መቅደስ የምንገባበት ስዓት እስኪደርስ እረፍት ለማድረግ ተኝተን ሳለ ከተራራው የተፈነቀለ ትልቅ ድንጋይ እኛ ወዳለንበት ተምዘግዝጎ በመውረድ ለጥቂት ዳንን፡፡ በሁኔታው ተደናግጥን ቦታ ቀየርን፡፡ ሐምሌ 23 ቀን 1951 ዓ.ም. ተራራው ተንዶ ቅኔ ማኅሌቱ መሉ ለሙሉ ፈርሷል፡፡

a washa 2ዋሻው የተደረመሰበት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ የሚታመነውም በወቅቱ አንዲት ሴት ለአሰግድመኝ ቅድስት ማርያም ገዳም አንድ ጋሻ መሬት ለመገበሪያ ብላ በስጦታ ለግሳ ነበር፡፡ አገልግሎት ሲሰጥ የተወሰኑ ዓመታት እንደተቆጠሩም ሴትየዋ ቃሏን በማጠፍ መሬቱን ከእመቤታችን በመውሰድ ለሌላ ግለሰብ ሰጠችው፡፡ ሴትየዋም ይህንን በማድረጓ ለሰባት ዓመታት በደዌ ዳኛ ተይዛ ስትማቅቅ ቆይታ አርፋለች፡፡ አስከሬኗንም በዚሁ ገዳም አምጥተው ይቀብሩታል፡፡ እመቤታችን ለአባቶች እየተገለጠች “የዚህችን ሴት አስከሬን ከዚህ ቦታ አውጡልኝ፤ ሸተተኝ” እያለች ነግራቸዋለች፡፡ ነገር ግን ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ሐምሌ 23 ቀን 1951 ዓ.ም. ዋሻ ቤተ ክርስቲያኑ ሊፈርስ ችሏል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም የሴትየዋ ግማሽ አስከሬን ከአንድ ድንጋይ ተጣብቆ ተንጠልጥሎ የነበረ ሲሆን አሁን የት እንደሔደ አይታወቅም በማለት የዋሻውን መደርመስ ምክንያት አወጉን፡፡

ከሁለቱም ዋሻዎች ግራና ቀኝ ተራራው ተቦርቡሮ በድንጋይ የተከደኑ መቃብሮች ይታያሉ፡፡ ከሌሎቹ መቃብሮች ለየት ባለ ሁኔታ በድንጋይ ሳይዘጋ የቀረና በግልጽ የሚታይ የሬሳ ሳጥን ተመለከትን፡፡ ምንድ ነው? ማለታችን አልቀረም፡፡ ለመስዋእት a washa 3የተዘጋጀውን መገበሪያ የበላችው አቃቢት አስከሬን እንደሆነና እንደ ሎጥ ሚስት የጨው አምድ ሆና መድረቋን ነገሩን፡፡ ሳጥኑ በቀላሉ የሚከፈት ሲሆን በአቡጀዲ የተጠቀለለውን አስከሬን ለማየት ቻልን፡፡ አስከሬኑ ሙሉ ለሙሉ አልፈረሰም፡፡

በአካባቢው በርካታ ዋሻዎች እንዳሉ ለማየት ችለናል፡፡ ስንጠይቅም ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ምእመናን ሱባኤ መያዣ እንደሆኑና በርካታ ዋሻዎች እንዳሉ ተነገረን፡፡

መምሬ ጥላዬ “በግራኝ ወረራ ዘመን ብዙ ታቦታት በዚህ አካባቢ ተሰውረው ተቀምጠው ነበር ሲሉ ሰምቻለሁ” አሉን ፡፡ እውነትም የተዘጉ ዋሻዎች እንዳሉ ተረዳን፡፡ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን እያስተባበረ የሚያሰራው ወጣቱ አቶ ይስማ “ ይህ ዋሻ እስከ ጅብ ዋሻ ማርያም ይወስዳል አለን፡፡”

jibwasha mariyamትኩረታችንን ሳበውና ጅብ ዋሻ ማርያም የት ነው? ጅብ ዋሻ ለምን ተባለ? ጅብ ዋሻ እንዴት ይኬድ ነበር? በማለት ለጠየቅነው ጥያቅ የጅብ ዋሻ ማርያም የተባለበትንም ምክንያት የቀይት ወረዳ ቤተ ክህነት ሊቀ ካህናት ቀሲስ ብርሃኑ ለገሰ እንዲህ በማለት ያስረዱን ጀመር “ጀብ ዋሻ ማርያም /አሁን ገነት ዋሻ ቅድስት ማርያም ተብሎ ይጠራል/ ከተመሠረተ 620 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በአካባቢው አንድ ሰው ሞቶ ፍታት ለማድረግ በቤተ ክርስቲያን የነበረውን ከበሮ ወደ ውጪ ወጥቶ ፀሐይ እንዲሞቅ ይደረጋል፡፡

ከአገልግሎት በኋላ ከበሮው ተረስቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሳይገባ ይቀራል፡፡ ምሽት ላይ ጅብ መጥቶ ከበሮውን ይደበድባል፤ በአካባቢው የከበሮው ድምጽ ይሰማል፡፡ በወቅቱ የነበሩት ሰዎች ማነው ከበሮ የሚደበድበው? ብለው ቢወጡ ከበሮውን የሚደበድበው ጅቡ መሆኑን ተረዱ፡፡ በዚህ ጊዜ ኧረ ቦታው የጅብ ዋሻ ሆኗል ብለው በመናገራቸው ጅብ ዋሻ ማርያም ተብሎ ሲጠራ ኖሯል፡፡ አሁን ግን ስሙ ገነት ዋሻ እየተባለ የሚጠራና ብዙ ተአምራት እየተደረገበት የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ነው” ብለውናል፡፡

አለቃ ተሰማ ወልደ ጊዮርጊስ አሁን የ97 ዓመት አረጋዊ ናቸው፡፡ ቀድሞ በደብረ ሲና መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ስለ አስገድመኝ ማርያምና ጅብ ዋሻ ማርያም የሚያውቁትን ንገሩን አልናቸው “ከልጅነቴ ጀምሮ የማውቃት aleka tesemaታቦት ነች፡፡ ስዕለት ሰሚ፤ ተአምር አድራጊ በመሆኗ ወደዚህ ቦታ የማይመጣ ክርስቲያን አልነበረም፡፡ ልጅ ስለነበርን “እስከ ጅብ ዋሻ ማርያም ድረስ ውስጥ ለውስጥ የሚያስኬድ መንገድ አለ፡፡” ሲሉ ሰምተን ከጓደኞቼ ጋር ቅብዓ ኑግ የኑግ ጭማቂ በገል አድርገን እያበራን ውስጥ ለውስጥ ሄደናል፡፡ በጣም ያስፈራል፤ በዋሻው ውስጥ ባህር አለ፡፡ ማን እንዳዘጋጀው ለምን እንደተዘጋጀ ባናውቅም በዋሻው ውስጥ ወደ ጅብ ዋሻ ሄደናል” ሲሉ የቦታዋን ታሪክ ነገረውናል፡፡

የደብረ ብርሃን አውራጃ አስተዳዳሪ በኋላም በደርግ ዘመን የወንበሮና ጠቆ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ሊቀ መንበር የነበሩት አቶ ተሾመ በቀለ መሬት ለአስግድመኝ ማርያም ሰጥተዋል፡፡ ስለ አሰግድመኝ ማርያምና ጅብ ዋሻ ማርያም የነገሩን “ልጅ ሳለሁ ወደ ጅብ ዋሻ የሚወስድ መንገድ መኖሩን ሰምተን በጨለማ ጉዞ ጀምረን ነበር ነገር ግን በጣም ስለሚያስፈራ ተመልሰናል፡፡” በማለት የዋሻውን መኖር ነገሩን፡፡

ከአስግድመኝ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጀርባ ከተራራው አናት ጀምሮ ቁልቁል በቀጭኑ መስመር ሰርቶ የሚወርደው ጸበል መቀበያ ቀጭን ቱቦ ገብቶለት ያለማቋረጥ ይወርዳል፡፡ ሥፍራው በድንጋይ ተከልሏል፡፡ ገዳሙ ሲመሠረት ጀምሮ ጸበሉ እንደነበር አባቶች የሚገልጹ ሲሆን በፈዋሽነቱም ይታወቃል፡፡

በጸበሉ በርካታ አገልጋዮችና ምእመናን የተፈወሱ ሲሆን ዓይን ከማብራት እስከ ዘመናችን በሽታ በኤድስ የተያዙ ሰዎችን ጭምር ተፈውሰዋል፡፡ ወደዚህ ቅዱስ ቦታ መጥቶ ሳይፈወስ የተመለሰ እንደሌለ በእርግጠኝነት መረጃ በመጥቀስ አገልጋዮቹ ይናገራሉ፡፡

አሰግድመኝ ቅድስት ማርያም ገዳም ለ800 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ነው፡፡ ነገር ግን የዋሻው ቤተ መቅደስ አገልግሎት ካቆመ 55 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ዋሻ ቤተ መቅደሱን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የእድሳትና ጥገና ለማከናወን፤ እንዲሁም ዋሻው ቤተ መቅደስ ከፈረሰ በኋላ የተሰራው መቃኞን ወደ ዘመናዊ ሕንፃ ለመለወጥ ኮሚቴ ተዋቅሮ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡

በንቡረ ዕድ አባ ገብረ ሕይወት መልሴ የበላይ ጠባቂነት ሁለቱንም ሥራዎች ለማከናወን የመሠረት ድንጋዩ ከተቀመጠበት መስከረም 21 ቀን 2006ዓ.ም. ጀምሮ አዲስ አበባ፤ ጉዶ በረትና፤ አጥቢያው በተዋቀሩ ኮሚቴዎች አማካይነት አዲሱን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ርብርቡ ቀጥሏል፡፡ ኮሚቴው ከሌሎች ልምድ ካላቸው መሰል የቤተ ክርስቲያን አሰሪ ኮሚቴዎች ጋር በመወያየትና ልምድ በመቅሰም የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በማዘጋጀት ሕንፃውን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

ቤተ ክርስቲያኑ እስከ 4 ሚሊዮን ብር ሊፈጅ ይችላል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ካህናቱና ምእመናን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ለመሥራት ቁርጠኛ ሆነዋል፡፡ ንቡረ ዕድ ግን ፍቅር ሳይኖር ቤተ ክርስቲያን መሥራት ተገቢ አይደለም በማለት፤ የተጣላ አስታርቀው ጉልበታቸውን ሳይቆጥቡ ሌት ተቀን በማስተባበር ሕዝቡም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ለሥራው ቀና እንዲሆን ከጉዶ በረት ጀምሮ ያለውን የስድስት ኪሎ ሜትር ጥርጊያ መንገድ ምንም አስቸጋሪ ቢሆንም በመሥራት መኪና እንዲገባ ለማድረግ ችለዋል፡፡

ንቡረ ዕድ አባ ገብረ ሕይወት መልሴ መልእክታቸውን ሲያጠቃልሉ “ሕዝቡ በጉልበቱ ከመሥራት ውጪ አሥራት በኩራት የማውጣት ልምድ የለውም፡፡ ማስተማራችንና መቀስቀሳችንን እንቀጥላለን፡፡ በብዙ ነገር ይረዱናል፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ መጀመሩን መረጃ የደረሳቸው ከካናዳ፤ ከአሜሪካና ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ ልጆቻችን ገንዘብ እየላኩልን ነው፡፡ ስለዚህ የዋሻ ቤተ መቅደሱንም ወደ ቀድሞ ይዞታው ለመመለስና የታሪክ ቅርስነቱን ጠብቆ ለማቆየት እንሰራለን፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ታንጻ አይቼ መሞት ምኟቴ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህንን ምኟቴን ይፈጽምልኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምእመናንም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ያሉ ሁሉ እንዲረዱን ጥሪዬን ነው የማስተላልፈው” ብለዋል፡፡