ነገረ ማርያም በነገረ ድኅነት

ኢዮብ ዘገነተ ጽጌ

ታኅሣሥ ፲፩፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ነገረ ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ትምህርት ሲሆን አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ ከምልአትነቱ ሳይጎድል ሰው ሆኖ በተገለጠ ጊዜ እመቤታችን ቅድስት ደንግል ማርያም በሰው ልጅ መዳን ላይ ያላትን ድርሻ (ምክንያትነት) የሚዳስስ ትምህርት ነው፡፡

እመቤታችን ድንግል ማርያም በሰው ልጅ የመዳን ጉዳይ ላይ ያላት ድርሻና ምክንያትነት ሙሴ በእስራኤላውያን፣ ቅዱስ ገብርኤል በሠለስቱ ደቂቅ፣ ኤልሳዕም በንዕማን፣ ሱራፊ ኢሳይያስን ከለምጹ በመፈወስ ውስጥ ከነበራቸው ድርሻ በላይ ትልቅ ድርሻ ነበራት፡፡(ዘፀ.፴፪፥ ፴፪፣ መዝ. ፻፭፥፳፫፣ ዳን.፫፥፳፰፣ ፪ኛነገ.፭፥፲፬፣ ዘፍ.፯፥፩-፲፪፣፩ኛጴጥ.፫፥፳.ኢሳ.፮፥፭)

ቀዳማዊ ሰው አዳም በበደሉና በኃጢአቱ ምክንያት ከነፍስ ተድላና ደስታ ከገነት ወጥቶ በግብርናተ ዲያብሎስ ሲሠቃይ የመከራ ዘመናቱ ያበቃው በእመቤታችን በድንግል ማርያም ምክንያትነት በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አዳኝነት ነው፡፡ ምንም እንኳን ወልድ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ሥጋና ነፍስን ነሥቶ በተለየ አካል ቢገለጥም “በማትለይ ባሕርይ” ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ ነውና ማዳኑን ፈጽሟል፡፡ ይህም ኢየሱስ ክርስቶስን “ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ አምላክ ነው” ብሎ ማመን እመቤታችንን “ወላዲተ አምላክ” ብለን እንድናምን ይመራናል፡፡

በአምስተኛው ክፍለ ዘመን የተነሣው መናፍቁ “ንስጥሮስ” ኢየሱስ ክርስቶስን “ሁለት ባሕርይ ነው” በማለት በክርስቶስ ላይ ተገዳድሮ እመቤታችንን “ወላዲተ ሰብእ” ብሎ ምንፍቅናን ተናግሯል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም “ወላዲተ ሰብእ” ያይደለች “ወላዲተ አምላክ” ናት ብላ መናፍቁን አውግዛ ሃይማኖት አጽንታለች፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይህንን የአበው ውሳኔ “ኦርቶዶክሳዊ ዐለት” በማለት ይጠሩታል፡፡ (ወላዲተ አምላክ በነገረ ድኅነት)

እመቤታችን በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላት ሚና የሚጀምረው አምላክን ከመፅነሷ አስቀድሞ በነበራት የንጽሕናና የድንግልና ሕይወት ጀምሮ ነው፡፡ አንዳንዶች “እመቤታችን ንጹሕ ሆና የተገኘችው አምላክ አስቀድሞ ስለመረጣት እንጂ የእርሷ ድርሻ አልነበረም“ ብለው ምንም ዓይነት የእርሷ ድርሻ እንዳልነበረ ምንፍቅናን የሚናገሩ አሉ፡፡ እውነታውን ግን እግዚአብሔር በእርሷ ድርሻና ተሳትፎ ለማደሪያነት እንደመረጣት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ “እግዚአብሔር አብ ከሰማይ ወደ ምድር ተመለከተ፤ ሰሜንና ደቡብን ምሥራቅና ምዕራቡን አሻተተ፤ እንዳንቺ ያ ግን አላገኘምና የሚወደውን አንድ ልጁን ወዳንቺ ላከ” እንዳለ ከዓለም ትውልድ ሁሉ እርሷን የመረጣት ከሰው ልጅ ለአምላክ እናትነት ከእርሷ ውጪ በቅታ የተገኘች ስላልነበረች ነው፡፡ ቅዱስ ሔሬኔዎስ የተባለው ደገኛ ሊቅ ደግሞ ሲናገር “ጌታ ለማደሪያነት እመቤታችንን የመረጣት በዚያ ጊዜ ከነበሩ ሴቶች ጋር ተወዳድራ ሳይሆን ዓለም ከተፈጠረ እስከሚያልፍ እርሷን የሚተካከል አንድም ሰው ስለሌለ ነው” በማለት የመመረጧን ነገር አድንቆ ይናገራል፡፡

እግዚአብሔር እመቤታችንን አስቀድሞ ከመርገም እና ቁራኝነት ከልሎ ጠብቋታል፤ ይህም በኋላ ላይ የሚኖራትን ጽናትና ደግነት አይቶ በአዋቂነቱ ያደረገላት እንጂ ሳትበቃና ሳትጸና ከሌላው ሰው አድልቶ ያደረገላት አልነበረም፡፡ ለምሳሌ፡- ነቢዩ ኤርምያስን “በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፤ በማሕፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃሁ፤ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃሁ” ሲል ኤርምያስን ለጽድቅና ለነቢይነት ያለሱታፌው ያለ ትጋቱ የሰጠው ሆኖ ሳይሆን የበኋላ ትጋቱን በአምላክነቱ አውቆ መምረጡን ለመናገር ነው፡፡ (ኤር.፩፥፲፭)

በሌላም መልኩ ቅዱስ ዳዊት “ኃጥኣን ከማሕፀን ጀምረው ተለዩ፤ ከሆድም ጀምረው ሳቱ፤ ሐሰትንም ተናገሩ” ሲል ኃጥኣን “ኃጢአትን” የሠሩት ቀድሞ ስለተወሰነላቸውና በማሕፀን የሚበድሉ ሆነው ሳይሆን የበኋላ በደልና ኃጢአታቸውን እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደሚያውቀው የሚያስረዳ ነው፡፡ (መዝ.፶፰፥፫) የአውግስጢን አንዱ ምንፍቅናው ስሕተቱ የነበረው “ቅድመ ውሳኔ ምርጫ ሲሆን የሰው ልጅ ኃጢአትን ከሠራ በኋላ ነጻ ፈቃዱ ተነፍጎታል፤ በዚህም እያንዳንዱ በሕይወቱ የሚገጥሙት ተግዳሮትና ፈተናዎች በቅድመ ውሳኔ ላይ የተመሠረተ ነው” ብሎ ያምን ነበር፤ ይህም ምንፍቅናው በኋላ ላይ ሉተርና ተከታዮቹ ላስፋፉት ምንፍቅና ትልቅ መሠረትና መነሻ የሆነ ነበር፡፡ (መድሎተ ጽድቅ ቁጥር ፪ ገጽ ፪፲፰-፪፳፭)

ወደ እመቤታችን ስንመጣ ጌታን ከመፅነሷ አስቀድሞ የነበራት የንጽሕና ሕይወት ምን ያህል በሰው ልጅ መዳን ውስጥ የነበራትን ፋይዳ የሚያሳይ ነበር፡፡ አዳምና ሔዋን እንኳን በገነት ሳሉ አይተው የሚያስታቸው ኃጢአትን ለመሥራት አርአያ የሚሆናቸው አልነበረም፤ እመቤታችን ግን ዓለም በተለያዩ ኃጢአቶች በተያዘችበት ጊዜ ኖራ ኃጢአት ድል አላደረጋትም፡፡

ለዮሴፍም ታጭታ ዮሴፍ ቤት ስትኖር በከተማው እንዳሉ ሴቶች አንገቷን ሳታደነድን ራሷን አጋልጣ ሳታሳይ በጸሎት ተወስና አርአያነት ያለውን ሕይወት ኖራለች፡፡ (ድርሳን ቅዱስ ኤፍሬም)

ቅዱስ አትናቴዎስ “እግዚአብሔር ዳኛዋ እንዲሆንላት ትጸልይ ነበር እንጂ በወንዶች መታየት አትሻም ነበር፤ ከቤት ለመውጣት አትቸኩልም ነበር፤ በሕዝባዊ ስፍራዎች የሚያውቃት ሰው አልበረም፤ ማር እንደምትሠራ ንብ በቤትዋ ውስጥ ብቻ መቆየትን ትመርጥ ነበር፤ በቤትዋ የቀረውን ሁሉ ለድሆች በቸርነት ትሰጥ ነበር፤ ቃላትዋም ጥንቃቄን የተሞላ ነበር፤ ድምጿም የተመጠነ ነበር፤ ጮሃ አትናገርም ነበር፤ ማንም ላይ ክፉ ነገርን አልተናገረችም፤ ክፉ ወሬን ለመስማትም አትፈቅድም ነበር፡፡” (ድርሳነ ቅዱስ አትናቴዎስ)

እመቤታችን ጌታችንን ከመፅነሷ አስቀድሞ መጻሕፍትን እያነበበች ትንቢተ ኢሳይያስ ላይ “ጌታ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” የሚለው ላይ ስትደርስ በልቧ “ከዚች ሴት ከዘመኗ ደርሼ፣ እንጨት ፈልጬ፣ ውኃ ቀድቼ ባገለገልኳት” እያለች በትሕትና ልብ ትናፍቅ ነበር፡፡ (ኢሳ.፯፥፲፬) ጊዜው ደርሶ ቅዱስ ገብርኤል ከፊቷ እጅ ነሥቶ ባበሠራት ጊዜ እንደ ቀደመችው ሔዋን ወዲያው አምና ሳትቀበል መልአኩን መርምራ ከብዙ ንግግር በኋላ መልአኩ “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም” ባላት ጊዜ “ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” በማለቷ ምክንያት አካላዊ ቃል ከእርሷ እንዲፀነስ ሆኗል፡፡ (ሉቃ.፩፥፴፯)

እመቤታችን በነገረ ድኅነት ላይ ያላት ድርሻ በዚህ ሳያበቃ ገና ለገና “አምላክን ፀንሻለሁና ብላ ለትዕቢትና ለውዳሴ ከንቱ ልቡናዋን አሳልፋ ሳትሰጥ ራሷን በትሕትና እያስገዛች ኖራለች፡፡ አጋር እንኳን ከአብርሃም ልጅን ባገኘች ጊዜ አገልጋይነቷን ረስታ እመቤቷ ሣራን በክፉ ዓይንና በመታጀር ንቀትን አሳይታ ነበር፡፡ (ዘፍ.፲፮፥፬) እመቤታችን ግን ማንም ሊያገኘው የማይቻለውን ጸጋ አግኝታ አንድም ቀን በማንም ላይ የመታበይን ነገር አሳይታ አታውቅም ነበር፡፡ እመቤታችን ጌታን ከወለደችም በኋላ ጌታችን ገና ሁለት ዓመቱ ሳለ ሔሮድስና ሠራዊቱ ልጇን ሊገድሉባት ባሉ ጊዜ ከሀገር ወደ ሀገር ተንከራታ ከላይ ፀሐይ ከታች የአሸዋው ግለት እያነደዳት ስለ “ክርስቶስ” መከራን ተቀብላለች፡፡ አንድም ቀን “አምላክ ከሆንክ ራስህንም እኔንም አድን” ብላ ሳትዘባበት ዘወትር “በእኔ ኃጢአት ምክንያት ተንገላታህ” እያለች ራሷን በመውቀስ ታነባ ታለቅስ ነበር፤ ታዲያ ከዚህ በላይ “ምክንያተ ድኅነት” መሆን ከወዴት አለ? (ድርሳነ ቅዱስ ኤፍሬም)

እመቤታችን ከስደቷም መልስ በናዝሬት ያለ አባት የወለደችውን ልጇን በስስትና በርኅራኄ ልብ አሳድጋ እስከ መስቀል ድረስ በመታመን ለልጇ ያላትን ፍቅር በጽኑ ጽናት ያሳየች እናታችን ናት፡፡ ጌታችን ለዓለም ቤዛ ይሆን ዘንድ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ተዋሐደ፡፡ የሥነ መለኮቱ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ “ባለ መድኃኒት በድውዮች ሴት ልጅ ዘንድ አደረ፤ ከእርሷም ምድራዊ ሥጋን ተዋሐደ፤ ለድውዮችም ፈውስ በሚሆን ገንዘብ ከመለኮቱ ጋር አንድ አደረገው፤ ባለ መድኃኒት ከሰማያት መጥቷልና የፈውስ እንጨት እንደማይገኝ ባለ መድኃኒቱ አወቀ፤ ስለዚህ ራሱን ሰው ለመሆን ሰጠ” እንዲል፡፡ (መጽሐፈ ምሥጢር ገጽ ፪፻)

የሰው ልጅ ከመርገሙ የተነሣ ሐዲስ ተፈጥሮ ያገኘው ፈጣሬ ፍጥረታት በሆኑት በሦስቱ አካላት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድና ስምረት ነበር፡፡ በዚህም ወልድ ሥጋና ነፍስን ከእመቤታችን ነሥቶ በመስቀል ተሰቅሎ በደሙ ማዳኑ ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላት ድርሻ ጥልቅ መሆኑን በሚገባ የሚያስረዳን ነው፡፡ ለምሳሌ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር የፈጸማቸውን የማዳን ተግባራት ብንመለከት በእያንዳንዱ ማዳን ምክንያት አድርጎ የተጠቀመው ሰው እና ተፈጠሮን ነው፡፡ ሠለስቱ ደቂቅን በቅዱስ ገብርኤል፣ ሕዝበ እስራኤልን በሙሴ የግብጽን ንጉሥ በአብርሃም የሱነማዊቷን ልጅ በኤልሳዕ አማካኝነት ማዳን ሲፈጽም የተጠቀመው ቅዱሳንና ጻድቃንን ነበር፡፡

አንዳንዴ ደግሞ ድንጋይን እንጨትን፣ አፈርን፣ ውኃን ለመፈወሻነት በረድኤት አድሮባቸው ተአምራትን ፈጽሞባቸዋል፡፡ ለምሳሌ የኖኅን መርከብ ብንመለከት ስምንት ነፍሳትን እንስሳትን ጨምሮ ከጥፋት ውኃ ለመዳናቸው ምክንያት ሆና ነበር፡፡ በሰውኛ አረዳድ ለተመለከተው ግን “እንጨት እንዴት ከንፍር ውኃ ይታደጋል” የሚል ጥያቄ ሊፈጠርበት ይችላል ምክንያቱም ንፍር ውኃ ከእንጨት ጋር ሲገናኝ እንጨቱን ይፈረፍረዋል፤ የኖኅ መርከብ ግን ምንም መርከብ ብትሆንም እግዚአብሔር በረድኤቱ ጋርዷት ነበርና ስምንቱን ነፍሳት መታደግ ተችሏት ነበር፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ “ጥቂቶች ማለትም ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑባት መርከብ” በማለት መዳኛነቷን ተናግሯል፡፡ (፩ኛጴጥ.፫፥፳) መርከቧ “የዳኑባት” ተብሎ መዳኛነቷ መገለጡ የእግዚአብሔርን የሸፈነ ሳይሆን እንዲያውም የፈጣሪ አዳኝነት እንዲታይ ያደረገ ነው፡፡ እንዲሁም እመቤታችን “መድኃኒት፣ ቤዛዊተ ዓለም” መሰኘቷ የልጇ የወዳጇ የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር ይበልጥ ይገልጠዋል እንጂ አይሸፍነውም፡፡

በአጠቃላይ ነገረ ማርያም በነገረ ድኅነት ያለው ሚና እመቤታችንን መርገሙ እንዳያገኛት መንፈስ ቅዱስ ከመጠበቅ ጀምሮ እርሷ የነበራት ትጋትና ብርታት፣ ስለ ልጇ ስትል በረኃ ለበረኀ መንከራተቷ፣ በልጇ መሰቀልና መሞት ያገኛት መራራ ኀዘንን ጨምሮ ከፍጡራን ሁሉ ትልቁን ቦታ ይዛ እናገኛታለን፡፡ ዛሬም እስከ ምጽአት ድረስ በአማላጅነቷ በእናትነቷ በበረከቷ ከምእመናን ልቡና ሳትለይ ምክንያተ ድኅነት ሆና ትኖራለች፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
አሜን!!!