“ዮም ፍሥሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም፤ በማርያም ልደት ምክንያት ዛሬ ደስታ ሆነ!” (ቅዱስ ያሬድ)
ዲያቆን ልሳነጽድቅ ኪዳነ
ቅድስት ሐና እና ቅዱስ ኢያቄም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በአድባረ ሊባኖስ ግንቦት አንድ ቀን ወለዷት፡፡ በዚያን ጊዜ ጠላታቸውን ለመሸሽ በስደት ላይ ስለነበሩ ምግብ አልያዙም፤ ስንቃቸውም ‹‹ንፍሮና ጥራጥሬ›› ነበር፡፡ በዚህም የእመቤታችን ማርያምን የልደት በዓል በሕዝበ ክርስቲያን ዘንድ ንፍሮ እየተበላ ይከበራል፡፡ የነቢያቱ ትንቢት የተፈፀመበት፣ የብሉይ ኪዳን ማብቂያ የሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ ናትና ልደቷ ለሰው ልጆች ሁሉ (ለሕያዋን ሁሉ) ታላቅ የደስታ ቀን ነው፡፡
በንጽህናዋ እና በቅድስናዋ ተደንቀው ሰማያውያን ቅዱሳን መላእክትም ያመሰግኗታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ድንግል ማርያምን ልደት በታላቅ ድምቀት የምታከብረው ከዚህ ታላቅ በዓል በረከት ረድኤትን እንድናገኝበት ነው፡፡ የክርስቶስ እናት ዛሬ ተወልዳለችና፤ በሥርዓት ቤተ ክርስቲያን መሰረት በቀናች በተዋሕዶ እምነት ሆነን፤ የድኅነታችን ምክንያት የሆነችውን ድንግል ማርያምንም እያመሰገንን ልናከብረው ይገባል፡፡
በመጻሕፍት አምላካውያት (አሥራው መጻሕፍት) እና በሊቃውንት አበው አስተምህሮ የተነገሩ የእመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕናዋን ቅድስናዋን የሚመሰክሩ መውድሳት ቅኔያትና ዝማሬያት እንዲሁም በሰፊው የተገለጡትን ምስክርነቶች ስንመለከት እንዲሁ እንደ እንግዳ ደራሽ የተገኙ እንዳልሆነ አስተዋይ ሰው በቅጥነተ ሕሊና ቢረዳው የሚያውቀው እውነት ነው፡፡
ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ሲነሳ፣ በተለይም እመቤታችንን ማመስገን ማለት እርሷን እንደ ፈጣሪ መመልከት፤ ከዚያም ባለፈ እንደ አምልኮ ባዕድ አድርገው የሚመለከቱት እና ያልታደሉ የዘመኑ እንክርዳዶች እና አረሞች፣ ጸላዔ ሠናያት በከንቱ ትጋት የሚያገለግሉ መናፍቃን ቁጥራቸው ከጊዜ ወደጊዜ መብዛት በተጣመመ የሐሰት ትምህርታቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የምትመሰገንበትን ምስጋና መቃወም ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ቀድሞም የነበረ ነው፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለእመቤታችን ድንግል ማርያም የምታቀርበው ምስጋና የመቃወም ነገር መሠረቱ ምንድን ነው? ስንል የመጀመሪያው በክህደት እና በኑፋቄ ትምህርት መወሰድ ሁለተኛ ደግሞ የተስተካከሉ እና እንከን የሌለውን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ባለመረዳት እና በስሜት መነዳት (መመራት) መሆኑን የምንመለከተው ነው፡፡
በኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ለተሰበሰቡ ክቡራን ምእመናን የቤተ ክርስቲያናቸውን አስተምህሮ በአግባቡ ከርቱዓን መምህራን እና በቅዱሳት መጻሕፍት አማካኝነት ማወቁ፤ በተለይ በዘመናችን ለሚዘራው የክህደት አስተምህሮ እንደ ጽድቅ ጋሻ ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡
በተለይ ስለ ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ስለሚሰጣት ክብር እና ሞገስ ማወቅ ማለፊያ ነው፡፡ በዚህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ለማመስገን የሚያስፈልግ መሠረታዊ ነገር ምንድን ነው? ለመሆኑ ሰው እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ ለእመቤታችን ምስጋና እና ክብር መስጠት ይችላልን? እመቤታችንን አለማመስገን እና አለማክበርስ ውጤቱ ምንድን ነው የሚለውን በአጭሩ እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡
ምስጋና ማለት ምን ማለት ነው?
ምስጋና ሰብሐ አመሰገነ በሚል የሚተረጎም ሲሆን ለዚህም “ሰብሕዎ ለእግዚአብሔር ስብሐተ ሐዲስ፤ ለእግዚአብሔር አዲስ ምስጋናን አመስግኑ” የሚለው ምስክር ነው። (መዝ. ፺፭፥፩) ስብሐት ክብርንም ያመለክታል “አባ ሰብሐኒ በቅድመ ሊቃውንቲሆሙ ለእስራኤል፤ አሁን ግን በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊት እና በእስራኤል ፊት እባክህ አክብረኘ” (፩ኛ ሳሙ. ፲፭፥፴) በሌላም ቀደሰ ብሎ አመሰገነ፣ ለየ፣ መረጠ፣ አከበረ ይላል፡፡
ምስጋና ከፍ የሚያደርግ እና የሚያከብር ድርጊት ወይም ቃል ነው። በንግግር፣ በቃልም፣ በዜማ እና በድርጊት ሊቀርብ ይችላል። ምስጋና የባሕርይ እና የጸጋ ተብሎ በሁለት ይከፈላል ። የባሕርይ ምስጋና ለእግዚአብሔር ብቻ የሚቀርብ ፣ገንዘቡ የሆነ ማንም የማይወስድበት ነው የእግዚአብሔር ምስጋና። እግዚአብሔር በፍጥረቱ “ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ ሥራህ ታላቅ እና ድንቅ ነው አንተ ብቻ ቅዱስ ነህ” እየተባለ የሚመሰገን ነው። (ራእ. ፭፥፫)
እግዚአብሔር በባሕርይው የተመሰገነ አምላክ ቢሆንም ከፍጥረት በተለየ ክብር ጥቅም እንዲሆንላቸው ሰው እና መላእክት ያመሰግኑታል። መላእክት ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡለት ምስጋና ለየት የሚለው ምስጋናቸው ሲሳይ (ምግብ) ስለሆነላቸው ነው ።ረቂቃን የሆኑ መላእክት ረቂቅ ምስጋና ለእግዚአብሔር በማቅረብ የሚያቀርቡት ምስጋና ምግብ ሆኗቸው ይኖራሉ። “ወሲሳየሙ ለመላእክት ቅዳሴ ወስብሐት ወስቴሆሙ ፍቅረ መለኮት፤ የመላእክት ምግባቸው ምስጋና መጠጣቸው የመለኮት ፍቅር ነው፡፡ እንዲል።” (መጽሐፈ አክሲማሮስ) በመጽሐፍ “እስመ አኮቴቶሙ ዕረፍቶሙ እስመ ዕረፍቶሙ አኮቴቶሙ፤ ምስጋቸው ዕረፍታቸው ዕረፍታቸው ምስጋናቸው” እንዳለ መላእክት ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት ምስጋና የማይቋረጥ በፍጹም ትጋት የሚቀርብ ነው። (ድርሳነ ሚካኤል)
የቅዱሳን መላእክት ምስጋና ለየት የሚያደርገው ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እያመሰገኑት ነገር ግን የአንድ ሰዓት የግማሽ ግማሹን ያህል እንኳን ያመሰገኑት አይመስላቸውም። ‹‹ወኢይመስሎሙ ለመላእክት ከመ ዘቀደስዎ መጠነ መንፈቀ መንፈቃ ለአሐቲ ሰዓት እም አመ ተፈጥረ ዓለም እስከኔሁ፤ መላእክት ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ አመስግነውት የአንድን ሰዓት የእኩሌታዋን እኩሌታ ያህል ያመሰገኑት አይመስላቸውም›› እንዲል፡፡ (መጽሐፈ አክሲማሮስ)
ምስጋና ለልዑል እግዚአብሔር ለጌትነቱ፤ ለአምላክነቱ የሚቀርብ ውዳሴ ሲሆን ለቅዱሳን፣ ለእመቤታችን የሚቀርብ ደግሞ ፀጋቸውን እና ክብራቸውን የሚገልጽ እና ከፍ ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡
ምስጋና ለእግዚብሔር የሚቀርብ ውዳሴ ነው፡፡ ይኸም በአምላክነቱ በፈጣሪነቱ ያደረገልንን መግቦት፣ ቸርነቱን በማሰብ ያለንን ፍቅር የምንገልጽበት ነው፡፡ ምስጋና መገኛው ባለቤቱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ስብሐቲሁ ዘእምሀቤሁ ወውዳሴሁ እምዚአሁ፤ ምስጋና ውዳሴም ከእርሱ የእርሱ ነው እንዲል ። ለእግዚብሔር የአምልኮ ወይም የባሕርይ ምስጋና ሲቀርብለት ለወዳጆቹ ደግሞ የጸጋ (የአክብሮት) ምስጋና ይቀርባል፡፡ (ዮሐንስ አፈወርቅ)
የጸጋ ምስጋን (ክብር) ደግሞ ቅዱሳንን በተሰጣቸው ክብር እና ጸጋ መጠን የምናከብርበት ነው። የጸጋ ምስጋና የሚቀርብላቸው ቅዱሳን ስለ ክብራቸው በተመለከተ መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይመሰክራል ‹‹ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው››።(ሮሜ፡ ፰፥፴) በሌላም ‹‹መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ››። ተብልዋል (ሮሜ፡፲፫፥፹፯) ቅዱስ ዳዊትም እንዲህ በማለት ስለክብራቸው መስክርዋል ‹‹አቤቱ በእኔ ዘንድ ወዳጆችህ የተከበሩ ናቸው፣ ከቀደሙት ይልቅ ይጸናሉ፤ ብቆጥራቸውም ከአሸዋ ይልቅ ይጸናሉ›› (መዝ. ፻፴፰፥፲፯) ስለ ምስጋና ያነሳነው ለቅዱሳን በተለይ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የምናቀርበው ምስጋና ክብር አንድ ሰው በትክክል ለመረዳት እና ለመቀበል ከዛም ባለፈ ለማመስገን የሚያስፈልግ መሠረታዊ ነገር ለማየት መነሻ እንዲሆነን ነው። እመቤታችንን ለማመስገን የሚያስፈልግ መሠረታዊ ነገር ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልሱ በአጨሩ አንድ ሰው ለእመቤታችን የሚቀርብ ምስጋና እና ክብር ለማቀበል የሚችልበትን መንገድ ለማየት እንዲመች በቅደም ተከተል ሁለት ጉዳየችን እንመለከታል፡፡
፩. መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀት
የተነገረውን ቅዱስ አምላካዊ ቃልን በተነገረበት መንገድ ሳይጨምሩ እና ሳይቀንሱ እንዲሁም የግል (የራስ) ሐሳብ ሳያክሉ ማንብበ፣ ማጥናት እና መማር ከአንድ ትክክለኛ ክርስቲያን የሚጠበቅ ተግባር ነው። ከዛም ባለፈ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የአበው ትርጓሜ መመልከትም ለሚታወክ ልብ ፍቱን መድኃኒት ነው።
ያልተከለሰ እና ያልተበረዘ አምላካዊ ቃል ለማግኘት ደግሞ በቅድስት ቤተክርስቲያን ጥላ ሥር መጠለል የግድ ነው። ምክንያቱም ይህንን ሀብት የጠበቀችውና ያላት ቤተክርስቲያን ብቻ በመሆኗ ነው። ትክክለኛ የተቃና መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀት ያለው ሰው ለቅዱሳን የሚቀርብ ምስጋና፣ ውዳሴ፣ ስግደት ለእግዚብሔር ከሚቀርብበት መንገድ ጋር እያገናኙና እያጣረሱ ግራ መጋባትን ያቆማል። በእርግጥ ከመሠረታዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ የአበው አስተምህሮ ጋር ያልተገናኙ ሰዎች ምእመናንን ወደ ማደናገር ይገባሉ። በተላይም በእኛ ዘመን የሚያደናግሩ የነፍስ ሌቦች ሞልተዋልና መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ‹‹የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች፣ ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቅቁ›› እንዲል፡፡ (ማቴ. ፯፥፲፭)
በእርግጥ መደናገሩ የፈጠራቸው ሌሎች ነገሮች እንዳሉ ሁነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ፣ ሐዋርያዊ ትውፊትና የአበው አስተምህሮ በአግባቡ ካለማወቅ የሚመነጭ ነው፡፡ ይህንንም ያልነው በየዋህነት ለሚነሱት ነው እንጂ አውቆ አበዶችን (ተሐድሶ መናፍቅንን) አያጠቃልልም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ወደውና ፈቅደው በኑፋቄ ማበዳቸው ስለሚታወቅ ነው፡፡ ይህንን እብደት ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ የሥጋ ሥራ ይለዋል። (ገላ ፭፥፳፩) የሥጋ ሥራም ውጤቱ ምን እንደ ሆነ እንደሚከተለው ጽፎታል። ‹‹ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም። በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም። የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው፤ እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።›› (ገላ ፭፥፲፰-፳፩)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌለ መንግሥቱ ‹‹መጻሕፍት እና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ›› በማለት እንዳስተማረው ቅዱሳት መጻሕፍትን በአግባቡ አለማወቅ ለስህተት የሚዳርግ ነው። ስለ እመቤታችንና ቅዱሳን የተሰጣቸውን ክብር ለማወቅ ሁነኛ መድኃኒት ቅዱሳት መጻሕፍትን ማወቅ ነው፡፡ ለምሳሌ የተቃና መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀት የሌለው ሰው የቅዱሳን አማላጅነትና የክርስቶስ ቤዛነት፣ በማምለክ እና በማክበር መመሳሰል ያለው ተዛማችነትና ልዩነት ይምታታበታል፡፡
በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ‹‹እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ›› (ዮሐ፡፰፥፪) እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፡፡ (ማቴ. ፭፥፪) እንዲሁም ‹‹ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ›› (ማቴ፡፬፥፪) ወንድሞችህ አንተን ያመሰግኑሃልና፣ በፊትህ ይሰግዳሉ፡፡ (ዘፍ፡-፭፥፰) የሚሉትን ጥቅሶች ስናያቸው የቅዱሳን ብርሃንነት እና የክርስቶስ ብርሃንነት፣ የእግዚብሔር እረኝነት እና የቅዱሳን እረኝነት፣ ለጌታ መስገድ ብቻ እና ቅዱሳንን ማመስገን ለእነርሱም ስግደት ማቅረብ እነርሱን ማክበር እንደሆነ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለ ማምለክ እና ማክበር የተነገሩበትን መንገድ ካልተገነዘብን ለብዙ ክህደት መዳረጉ አይቀሬ ነው፡፡ ጽሑፈ መጻሕፍ ቅዱሳን በአግባቡ አለማጥናት እና አለመማር ስለ ማምለክ እና ስለ ማክበር ለመለየት ያስቸግራል፡፡
ወደ ቀድሞ ነገር እንመለስና እመቤታችንን ማመስገን፣ ምስጋና ማቅረብ እመቤታችን ማምለክ አይደለም ክብሯን መናገር እና መመስከር እመቤታችንን ፈጣሪ እና አምላክ አድርገን ቆጠርናት ማለት አይደለም፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ለአብርሃም የሚባርክህን እባርካለሁ የምድር ነገዶች ሁሉ ከአንተ የተነሳ ይባረካሉ ያለውን፤ ስናይ፤ የሚባርክህን እንጂ የሚያመልክህን አላለም፡፡ ምክንያቱም መባረክ ማመስገን ማክበር ነውና፡፡ ‹‹ወንድሞችህ አንተን ያመሰግኑሃል በፊቱም ይሰግድልሃል›› ተብሎ እንደተጻፈ አንድ ሰው በቅን ልቡና ቢመለከት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አብርሃም እና ይሁዳ ሲመሰገኑ ስለ እነርሱ ምስጋና ሲነገር በማየት እመቤታችንን እንዴት ከይሁዳ እና ከአብርሃም አሳንሶ ይመለከታል፡፡ ታዲያ እመቤታችንን ማመስገን ወንጀል ነው? ወይስ ከአብርሃም እያሳነሷት ነው? እግዚአብሔር እንዲህ ዓይነቱን ከንቱ ሐሳብ ያርቅልን፡፡
ይቆየን