ትንሣኤ

መምህር አብርሃም በዕውቀቱ

ሚያዚያ፤፳፻፲፬ ዓ.ም

ለሰው ልጆች ዘለዓለማዊ ትንሣኤ በኩር የሆነው የክርስቶስ ትንሣኤ ነው፡፡ መድኃኒዓለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአባታችን ለአዳም በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በአይሁድ እጅ መከራ መስቀልን ከተቀበለና ነፍሱን በራሱ ሥልጣን አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ዐርብ በ፲፩ ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ መስፍኑ ጲላጦስን አስፈቅደውና ከመስቀል አውርደው ዮሴፍ ራሱ ባሠራው መቃብር በንጹሕ በፍታ ገንዘው ቀበሩት፤ መቃብሩንም ገጥመው ሲሄዱ ጸሐፍት ፈሪሳውያንና መስፍኑ በመቃብሩ ላይ ማኅተማቸውንና ጠባቂዎችን አኖሩ፡፡ (ማቴ. ፳፯፥፶፯-፷፮፣ ማር.፲፭፥፵፪፣ሉቃ. ፳፫፥፶፣ ዮሐ.፲፱፥፴፰፥፵፪) በሦስተኛው ቀን እሑድ በእኩለ ሌሊት መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በታላቅ ኃይል ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሣ፤ ይጠብቁ የነበሩ ጠባቂዎችም ደንግጠው ተበታተኑ፤ በመቃብሩ ዙሪያ ቅዱሳን መላእክት ታዩ፡፡

ትንሣኤውን ቅዱሳን መላእክት ለሴቶች አበሠሩ!

ልደቱ ለእረኞች በመልአክ እንደተበሠረ ትንሣኤውም በመልአክ ለሴቶች ተበሠረ፡፡ ይህም ‹‹ተነሥቷል፤ በዚህም የለም›› የሚለው የመላእክት ብሥራት በአራቱም ወንጌላት እንደሚከተለው ሠፍሯል፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ ‹‹መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው። እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁም ሂዱ። ከሙታን ተነሣ፥ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው። እነሆም፥ ነገርኋችሁ›› በማለት ገልጾታል፡፡ (ማቴ.፳፰፥፭-፲)

ቅዱስ ማርቆስ፡ ‹‹ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ። እርሱ ግን ‹‹አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ። ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ለጴጥሮስም ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ እንደ ነገራችሁ በዚያ ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሩአቸው አላቸው›› በማለት አስፍሮታል፡፡(ማር.፲፮፥፭)

ቅዱስ ሉቃስ፡ ‹‹እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሏቸው። ‹‹ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም። የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ›› ብሎ መልአኩ እንደነገራቸው አስፍሮልናል።(ሉቃ. ፳፬፥፬-፱)

ቅዱስ ዮሐንስ መግደላዊት ማርያም ሁለቱን መላእክት እንዳየችና ከእነርሱም ጋር እንደተነጋገረች ሲገልጽ ‹‹ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች። እነርሱም። አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? አሏት›› ብሏል። (ዮሐ.፳፥፲-፲፫)

ሁለቱ ደቀ መዛሙርት የትንሣኤውን ዜና ከሴቶች ከሰሙ በኋላ ወደ መቃብሩ በመግባት የጌታችንን መነሣት አረጋግጠዋል፡፡ ይህንን ወንጌላዊው ዮሐንስ ‹‹ስለዚህ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና አስቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ፤ ዝቅም ብሎ ቢመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ነገር ግን አልገባም። ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ፤ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ። ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ። በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም ሌላው ደቀ መዝሙር ደግሞ ገባ፥ አየም፥ አመነም›› ሲል ገልጾታል፡፡ (ዮሐ.፳፥፫-፰) ቅዱስ ሉቃስም ይህንን የጴጥሮስን ወደ መቃብር ገብቶ የጌታን ትንሣኤ ማረጋገጡን ሲገልጽ ‹‹ጴጥሮስ ግን ተነሥቶ ወደ መቃብር ሮጠ፤ በዚያም ዝቅ ብሎ ሲመለከት የተልባ እግር ልብስን ብቻ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተደነቀ ወደ ቤቱ ሄደ›› ብሏል። (ሉቃ.፳፬፥፲፪)

ጌታችን ራሱ ተገልጦ ትንሣኤውን አረጋግጦልናል

ከትንሣኤ በኋላ ጌታችን በተለያየ ጊዜ ተገልጧል፡፡ አስቀድሞ ለማርያም መግደላዊት በመቃብሩ ስፍራ ተልጦላታል፡፡ እርሷም ያየችውን ለደቀ መዛሙርቱ ተናግራለች፡፡ (ዮሐ.፳፥፲፬-፲፯) ወደ ኤማሁስ ይሄዱ ለነበሩት ሁለቱ ደቀመዛሙርትም መንገደኛ መስሎ ተገጦላቸዋል፡፡ (ሉቃ. ፳፬፥፲፫-፴፩)፡፡ ዐሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም በተሰበሰቡበት ተገልጦ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› ካላቸው በኋላ ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ፥ ከማር ወለላም ሰጥተውት ተቀብሎም በፊታቸው በልቷል፤ አስትምሯቸዋልም፡፡ (ሉቃ.፳፬፥፵፪-፵፫) በማዕድ ተቀምጠው ሳለም ለዐሥራ አንዱ ተገለጧል፤ተነሥቶም ያዩትን የተነገራቸውን ስላላመኑአቸው አለማመናቸውንና የልባቸውን ጥንካሬ እንደነቀፈ ተጽፏል። (ማር.፲፬፥፲፬) ዮሐንስ ወንጌላዊ እንደጻፈው ጌታችን ለደቀመዛሙርቱ ሁለት ጊዜ (የመጀመሪያው ጊዜ ቶማስ በሌለበት) በተዘጋ ቤት ተገልጦላቸዋል (ዮሐ.፳፥፲፱-፴፩)፡፡ ከዚያም በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ተገልጦላቸዋል፡፡ (ዮሐ.፳፩፥፩-፳፭) እነዚህ ለማሳያነት ቢገለጹም ጌታችን ከትንሣኤ በኋላ እስከ ዕርገቱ ድረስ ከደቀመዛሙርቱ ጋር የተገለጠባቸው ጊዜያቶች ግን እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡

እነዚህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታዎች መሠረት በማድረግ ከዐበይት በዓላት አንዱ የሆነው የትንሣኤ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ ይህም ከጥንት አበው የነበረውን የአከባበር ሥርዓት የተከተለ ነው፡፡ የትንሣኤ በዓል መከበር የተጀመረው በቅዱሳን ሐዋርያትና በሰብዐ አርድእት ነበር። በኋላም በየጊዜው የተነሡ ምእመናን ማክበር ቀጠሉ፡፡ ድምቀቱና የአከባበር ሥርዓቱ ይበዛ ይቀንስ እንደሆን እንጂ መከበሩ ግን ተቋርጦ አያውቅም፡፡ የትንሣኤ በዓል የሚከበረው ‹‹ዘመነ ትንሣኤ›› የሚባሉትን ከትንሣኤ እሑድ ቀጥለው ያሉትን ሰባቱን ቀናት ጭምር ይዞ ነው፡፡