አንተ ጽኑ አለት ነህ

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ

ሚያዚያ ፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በጽናትህም ላይ እሠራለሁ መቅደስ

እያለ ሲነግረው ጌታችን  ለጴጥሮስ

በምድርም ያሠርኸው በሰማይ ይታሠር

በሰማይ ይፈታ የፈታኸው በምድር

ብሎ ሾሞት ሳለ በክብር ላይ ክብር

መሳሳት አልቀረም አይ መሆን ፍጡር!

በሃያ ስድስት ምዕራፍ ነገራቸው ትንቢት

ትክዱኛላችሁ በዛሬይቱ ሌሊት

እመታዋለሁ እረኛውን ድንገት

መንጋው ይበተናል ተጽፏል ከጥንት

ይህን ሲነግራቸው አላወቁም አርድእት

ብሎም ነገራቸው ነቅታችሁ ጠብቁኝ

በሦስተኛይቱ ቀን እንደተነሣሁኝ

እቀድማችሁኃለሁ ገሊላ ጠብቁኝ

ጴጥሮስም መለሰ ተናገረ በኃይል

ሁሉም ቢክዱህ እኔ አልክድህም ሲል

ኢየሱስም አለ እልሀለሁ እውነት

ገና ዶሮ ሳይጮህ በመንፈቀ ሌሊት

አንተ ትክዳለህ ሦስት ጊዜ በቅጽበት

ጴጥሮስም መለሰ እውነት እልሀለሁ

ሞትም ቢመጣ አብሬ እሞታለሁ

አልክድህም አምላኬን ከልቤ አምናለሁ

በአንድ ቃል ተስማምተው ደቀ መዛሙርቱም

አንክድህም ሲሉ ተማማሉ ሁሉም

ወደ ጌቴሴማኒ በፍጥነት ሄደና

ይናገር ጀመረ ቃሉን አሰማና

ተግታችሁ ጸልዩ ጊዜው ደርሷልና

ሄዶ ቢያያቸውም እንደነገራቸው

ተኝተው ተገኙ ደከመ ሥጋቸው

እንዲሁም አላቸው ከኔ ጋር ሆናችሁ

አንዲት ሰዓት እንኳ መትጋት አቃታችሁ

ደግሞም ተመልሶ ሄዶ ቢያነቃቸው

ተኝተው ተገጙ እንቅልፍ ጸናባቸው

እንግዲህም ተኙ ረፉም አላቸው

ጊዜው ደርሷልና የሰው ልጅ መያዣው

ተነሡ እንሂድ ቃሌን ስሙና

አሳልፎ የሚሰጠኝ ይኸው ቀርቧልና

ይህን ሲናገር ይሁዳ መጣና

እኔ የምስመው ኢየሱስ ነውና

እንዳያመልጣችሁ እሠሩት ሂዱና

ብሎ ሲነግራቸው አይሁድ ተሰልፈው

በዱላና በሰይፍ በአንድነት ሆነው

ይሁዳ ቀርቦ ጌታችንን ሲስመው

እርሱንም ያዙት በኅብረት ተባብረው

ከጌታቸው ጋራ አብረው ከነበሩት

የተናገረውን ሐሳቡን ለማጽናት

ሰይፉን መዘዘና ተደፋፍሮ በእውነት

የማልኮስን ጆሮ ቆርጦ ቢጥልበት

ኢየሱስም ደግሞ እንዲህ ሲል አወሳ

በሰይፍ ይወድቃል ሰይፍን የሚያነሣ

ኢየሱስም አለ እናንተ ሕዝብ ሁላችሁ

ሰይፍና ጎመድን ይዛችሁ በእጃችሁ

ወንበዴ እንደሚይዝ ልትይዙ መጣችሁ

በመቅደስ ሁል ጊዜ ቆሜ ሳስተምራችሁ

አትይዙኝም ኖሯል ከእናንተ ጋር ሳለሁ?

ነገር ግን በኔ ላይ ይህ ሁሉ የሆነው

የነቢያት ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው

ጌታችንንም ይዘው ወሰዱት ለፍርድ

ሐናና ቀያፋ ከተከማቹበት ዘንድ

ጴጥሮስ  በልቡ አስታውሶ ቃሉን

እስከ ቀያፋ ቤት ሳይለይ ጌታን

ፍጻሜውን ያይ ዘንድ የአኳኃኑን

ከአይሁድ ጋር አብሮ ገባ ብቻውን

የካህናት አለቆች ሸንጎውም በሙሉ

ጌታችንን ለመግደል ምንም ቢማማሉ

የሐሰት ምስክር አላገኙም አሉ

የሐሰት ምስክር ሁለት ሰዎች ቀርበው

መቅደሱን አፍርሼ ደግሞም እንደቀድሞው

እችላለሁ ብሏል በሦስት ቀን ልሠራው

ቀያፋም ተነሥቶ እንዲህ ሲል ጠየቀው

የመሠከሩብህን አትስማማም? አለው

ነገር ግን ኢየሱስ ምላሽም አልሰጠው

የካህናት አለቃም እንዲህ ሲል ለመነው

የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ ንገረኝ በሕያው

ኢየሱስም አለ ቀያፋ አንተ አልህ

እኔ ግን እላለሁ ከእንግዲህ ወዲህ

የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ ለፍትሕ

በደመና ሰማይ ሲመጣ ታያለህ

የካህናት አለቃ ሲሰማ ይህንን

በጣም ተናደደ ቀደደ ሸማውን

እግዚአብሔርን ሲሰድብ እነሆ ሰማችሁ

ከእንግዲህ ወዲህ ምን ትመክራላችሁ?

ይህን ሲነግራቸው አይሁድ ተሰብስበው

ሞት ይገባዋል ምንም አንምረው

ብለው ፈረዱበት በአንድነት ተባብረው

ወዲያውኑ ጌታን እያዳፉ ያዙት

በፊቱም ተፉበት ራሱንም መቱት

በጥፊ እየመቱ ምንም ሳይሳሱለት

እንዲህ ይሉ ነበር ሲዘባበቱበት

የአምላክ ልጅ ነህና ንገረን ትንቢት

ጴጥሮስንም ከቤት ውጭ ተቀምጦ ብታየው

አንዲት ሴት ቀረበች ደግሞም ጠየቀችው

አንተም ከኢየሱስ ጋር ነበርክ እኮ አለችው

የምትይውን ሰው አላውቀውም ብሎ

በሁሉ ፊት ካደ ጴጥሮስም ቸኩሎ

ሌላይቱ ሴት ዐውቃው አፋጠጠችው

ከናዝሬቱ ጋራ አብሮ የነበረው

ይህ የምታዩት ጴጥሮስ እርሱ ነው

ዳግመኛም ይህን ሰው አላውቀውም አለ

ክርስቶስን ካደ በአይሁድ ፊትም ማለ

በዚያ የነበሩት ቀርበው ጠየቁት

ቋንቋህ ያስታውቃል ንገረን በእውነት

የእነርሱ ወገን ነህ አንተ ሰው አሉት

በዚያም ጊዜ ጴጥሮስ እየተማረረ

እኔ አላውቀውም ሲል መሐላ ጀመረ

ሲምልም ሲገዘት ኢየሱስን ክዶት

ወዲያው ዶሮ ጮኸ ተፈጸመ ትንቢት

ጴጥሮስ ትዝ አለው አምላክ የነገረው

ገና ዶሮ ሳይጮህ ትክዳለህ ያለው

ጴጥሮስ አስቦ ጌታውን መካዱን

ያለቅስ ጀመረ መራራ ለቅሶውን

ጴጥሮስ መጨነቁን አየና ማልቀሱን

ይቅር ባይ አምላኩ ላከለት ምሕረቱን

ንስሓ እንግባ እኛም ይህን አይተን

መሐሪ ነውና እንደሚምረን ዐውቀን!!!