‹‹ትርጓሜ ያሐዩ›› በሚል ኃይለ ቃል የውይይት መርሐ ግብር ተካሔደ
ነሐሴ ፳፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በዝግጅት ክፍሉ
በማበኅረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አዘጋጅነት ‹‹ትርጓሜ ያሐዩ፤ ትርጓሜ ያድናል›› በሚል ኃይለ ቃል ነሐሴ ፳፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በግዮን ሆቴል ብሉ ሳሎን አዳራሽ የውይይት መርሐ ግብር ተካሔደ፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው ምእመናን የተገኙ ሲኾን የዋና ክፍሉ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ መሠረት ለተሳታፊዎች የእንኳን ደኅና መጣችሁ ንግግር ባደረጉበት ወቅት የመርሐ ግብሩ ዓላማ የመጻሕፍት ትርጓሜ ቤቶችን አስተዋጽዖ በማስገንዘብ ጉባኤ ቤቶችን ለማስፋፋትና ተተኪ ሊቃውንትን ለማፍራት የሚያስችል ግንዛቤ ለማስጨበጥ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡
በዕለቱ የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኀኔ ዓለም የአራቱ ጉባኤያት ምስክር መምህርና የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ በአንድምታ ትርጕም ያዘጋጇቸው ትንቢተ ኢሳይያስ፣ ሃይማኖተ አበውና ድርሳነ ቄርሎስ ወጰላድዮስ ምስለ ተረፈ ቄርሎስ ተመርቀዋል፡፡
ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ መጻሕፍቱ ለጉባኤ ቤት መምህራንና ለደቀ መዛሙርት እንደዚሁም ለምእመናን የሚኖራቸው ጠቀሜታ የጎላ መኾኑን ጠቅሰው ‹‹መጻሕፍቱ በስሜ ቢዘጋጁም የመጻሕፍቱ ባለቤት ግን ጉባኤ ቤቱ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም›› ብለዋል፡፡ ከመጻሕፍቱ ሽያጭ የሚገኘውም ገቢም ሙሉ በሙሉ ለጉባኤ ቤታቸው መኾኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤልና በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ የትርጓሜ መጻሕፍትን ትውፊትና አስተዋጽዖ የሚዳስስ ጥናታዊ ጽሑፍ፤ እንደዚሁም የትርጓሜ መጻሕፍትን ታሪካዊ አመጣጥና የጉባኤ ቤቶችን ችግር የሚያስቃኝ ዘጋቢ ፊልም ከቀረበ በኋላ ሊቃውንቱንና ተጋባዥ እንግዶችን ያሳተፈ ጠቃሚ ውይይት ተካሒዷል፡፡
ከሰዓት በኋላ በዮድ አቢሲንያ የምግብ አዳራሽ በቀጠለው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብርም ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ‹‹የታቦር ጉባኤ›› በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል የሰጡ ሲኾን በትምህርታቸውም ከደብረ ታቦር ምሳሌዎች አንደኛው የመጻሕፍት ትርጓሜ ጉባኤ ቤት መኾኑን አስረድተዋል፡፡
ሊቀ ሊቃውንት በመቀጠልም የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኀኔ ዓለም የትርጓሜ መጻሕፍት ምስክር ቤት ደቀ መዛሙርትን እያስተማረ የሚገኘው በመቃብር ቤት መኾኑ ለሥርዓተ ትምህርቱ መሰናክል እንደ ኾነባቸው ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ለጉባኤ ቤቱ አገልግሎት የሚሰጥ ኹለ ገብ ዘመናዊ ሕንጻ በጎንደር ከተማ ለመገንባት በ፳፻፰ ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ ቢቀመጥም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሕንጻው እስከ አሁን ድረስ አለመገንባቱን አስታውሰው ይህን ሕንጻ ለመገንባት መላው ሕዝበ ክርስቲያን ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም በአባቶች ጸሎት የውይይት መርሐ ግብሩ ተፈጸሟል፡፡