ቦጅ ትጮሀለች!

መጋቢት 10/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ኅሩይ ባየ

ኘሮቴስታንቲዝም በምዕራቡ ዓለም ተጸንሶ ተወልዶና አድጐ የጐለበተ ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ያፈነገጠ የእምነት ተቋም ነው፡፡ ተወልዶ ባደገበት ሀገር ይዞታውን አንሰራፍቶ ለጊዜው የዘለቀው ኘሮቴስታንቲዝም በሀገሩ ባይተዋር ሲሆን “ጅብ ባለወቁት ሀገር ቁርበት አንጥፉልኝ አለ” እንደሚባለው ወደ ድሃ ሀገሮች በመዝመት ባንድ እጁ ዳቦ በአንድ እጁ እርካሽ እምነቱን ይዞ ገባ፡፡ በዚህ እኩይ ተልዕኰ የተወረሩ በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ባሕላቸውን ትተው፣ ቋንቋቸውን እረስተው ዘመን አመጣሽ የሆነውን አዲስ እምነት ለመቀበል ተገደዋል፡፡

{gallery count=1 width=350 height=300 counter=1 links=0 alignment=center animation=3000}bogi{/gallery}

ሀገራችን ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስጠብቃ በጠላት እጅ ሳትወድቅ አንድነቷ ተከብሮ የኖረች ስሟ በቅዱስ መጽሐፍ ተደጋግሞ የተነሣ ቅድስት ሀገር ናት፡፡ ግማደ መስቀሉ ያረፈባት ታቦተ ጽዮን የከተመባት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የታነጹባት ያለመታከት ስመ እግዚአብሔር የሚጠራባት ልዩ ሀገር ናት፡፡ በባእዳን እጅ አለመውደቋ በቀኝ ግዥ አለመያዟ የእግር እሳት የሆነባቸው ምዕራባውያን ድንበሯን ጥሰው መግባት ባይችሉም የአእምሮ ቅኝ ግዛታቸውን አላቋረጡም፡፡

 

በዚች ሀገር ውስጥ ይህ ዘመቻ በስፋት ከሚካሔድባቸው ቦታዎች አንዱ ሰፊ የሆነው የኦሮሚያ ክልል ነው፡፡

 

ቦጅ ቅድስት ማርያም ጠላቶቿን ስታስታውስ

የፕሮቴስታንቱን ተፅዕኖ ለመግታት ማኅበረ ቅዱሳን ባዘጋጀው የካህናት ሥልጠና የካቲት 17 ቀን 2004ዓ.ም ረፋዱ ላይ በቤተ ክርስቲያኗ ቅጽር ግቢ ስንገኝ ማንም ሰውbogi 1 አልነበረም፡፡ በቅጽሩ ጥግ ለጥግ ያረጁ የመካነ መቃብር ሐውልቶች ይታያሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ ፊት ለፊት በስተቀኝ በኩል ፈንጠር ብለው በክብር የተሠሩ አጥራቸው የተከበረ የቄስ ገብረ ኤዎስጣቴዎስ ዘመስቀል /1865-1905/፣ የአቶ ዳንኤል ዲባባ /1966-1904/ እና የአቶ ገብረ ኢየሱስ ተስፋዬ /12877-1925ዓ.ም./ መካነ መቃብር ይታያል፡፡ እነዚህ ሐውልቶች ለኘሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ባለ ውለታ ለሆኑት ሦስት ግለሰቦች ለመታሰቢያ እንዲሆን የተሠራ ሐውልት እንደሆነ ነዋሪዎች አጫውተውናል፡፡ በተለይ ከሦስቱ ሰዎች አንዱ ቄስ ገብረ ኤዎስጣቴዎስ በርካታ ካሕናትን አስኮብልሎ የእኛ ቤተ ክርቲያን እንድትዘጋ ስላደረገ ኘሮቴስታንቱ ስሙን ይዘክሩታል፡፡ በዚች ጠባብ ከተማ 130 ዓመታት ያስቆጠረች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን ትገኛለች፡፡ በከተማዋ ያደረግነው ቆይታ ከሀገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ ከመጋቤ ሀዲስ ሀዲስ ዓለማየሁ እና ከወረዳው ቤተ ክህነት ሊቀ ካህናት ምሥጢሩ ዘለቀ ጋር ነበርን፡፡

 

በቦጂ ድርመጂ ወረዳ ዐሥር አድባራት ይገኛሉ፡፡ ከሕዝቡ በመቶኛ ዘጠና አምስት በመቶ የኘሮቴስታንት እምነት ተከታዮች እንደሆኑ ይገመታል፡፡ በጥንታዊነቷ የምትታወቀው የቦጂ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስትያን አንድ መቶ ሠላሳኛ ዓመቷን የምታከብረው የፊታችን ግንቦት 1 ቀን 2004 ዓ.ም ነው፡፡

 

bogi 2ሊቀ ካህናት ምሥጢሩ ስለ ቦጂ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ታሪክ በአጭሩ ነግረውናል፡፡ እኛም እድሜ ጠገብነቷ አስደምሞን ልቡናችን በቤተ ክርስቲያኗ ታሪክ መዋለል ዓይኖቻችን በሕንፃዋ መንቀዋለል ጀመሩ፡፡ ከወፍ ድምጽ በቀር ምንም የማይሰማባት ቤተ ክርስቲያን ናት ማህሌቱ፣ቅዳሴው፣ጸሎተ እጣኑ ከተቋረጠ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህቺ ደብር የወላድ መካን የሆነች ካሕናቷ በኘሮቴስታንት ሰባኪያን የተወሰዱባት ቤተ ክርቲያን ናት፡፡ በልጆቿ መጥፋት ያዘነችው ቦጂ ቅድስት ማርያም ልጆቼን! እያለች ትጮኸለች፡፡

 

ተሐድሶ በዚያን ዘመንም

ከቦታው ያገኘነው ታሪክ እንደሚያስረዳው በ1890 ዓ.ም ከሲዊዲን ሀገር የመጡ የኘሮቴስታንት እምነት ሰባኪዎች ፊት ለፊት ከሚታየው ከርከር ተራራ ጸሎት ቤት ከፈቱ፡፡ እነዚህ ነጭ ሰባኪያን የመጀመሪያ ሥራቸው ያደረጉት የእኛን ቤተ ክርስቲያን ካሕናት መለወጥ ነበር፡፡ ኘሮቴስታንቶች በኢትዮጵያ ያደረጉት ተልእኮ መሠረት የተጣለው በዚህች ከተማ ነው፡፡ የመካነ ኢየሱስ ምዕራብ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የሚገኘው በዚህች ከተማ ነው፡፡

 

በቤተ ክርስቲያኗ ያኔ በርካታ ካህናትና ዲያቆናትና ነበሩ፡፡ ከካህናቱ መካከል ከኤርትራ ሀገር የመጣ ቄስ ገብረ ኤዎስጣቴዎስ የሚባል “ካህን” ነበር፡፡ መናፍቃኑ ይህን ቄስ ቀስ በቀስ ሰብከው ከለወጡት በኋላ አሠልጥነው የውስጥ ዘመቻቸውን አቀጣጠሉ፡፡

 

ቄስ ገብረ ኤዎስጣቴዎስ ለበርካታ ጊዜያት ራሱን ሰውሮ ጠዋት በእኛ ደብር እየቀደሰ ከሰዓት በኃላ በመናፍቃኑ አዳራሽ እየተገኘ የመናፍቃኑን ተልእኮ ይፈጽማል፡፡ /ምን አልባት ተሐድሶዎቹ የዚያን ጊዜም እንቅስቃሴያቸውን ጀምረው ይሆን?/ ይህ ቄስ ለ15 ዓመታት በዚህች ደብር ሲያገለግል የነበረ ሰው ነው፡፡ በኋላ ወደ አምስት የሚሆኑ ካህናትን ሰብኮ ወደ መናፍቃኑ አንድነት ቀላቀላቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኗ በካህናት እጥረት አገልግሎቷ ታጐለ፡፡ አሁን ቤተ ክርስቲያኗ  ልጆቿ የሉም፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች ምን ያህል እንደሆኑ ትክክለኛ ቁጥራቸውን መናገር ባይቻልም የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች 14 የሚሆኑት ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ አባወራዎች አብዛኛዎቹ ሚስቶቻቸው ኘሮቴስታንት የሆኑባቸው አባቶች ናቸው፡፡ በሃይማኖት ተለያይቶ በአንድ ቤት መኖር ከባድ ቢሆንም አማራጭ ስለጠፋ አብረው ለመኖር እንደተገደዱ አባወራዎቹ ይናገራሉ፡፡

 

ሚስቶቻቸው በኘሮቴስታንቶች ተሰብከው ከተነጠቁባቸው አባወራዎች መካከል አቶ ተሰማ ደበበ አንዱ ናቸው፡፡ በኦሮምኛ የነገሩንን ወደ አማርኛ እነዲህ ተርጉመነዋል፡፡ “ ወደ ኘሮቴስታንት እምነት ከሔዱት ሰዎች በጣም በርካታ ቁጥር ያላቸው ከዚህች ቤተ ክርስቲያን የወጡ ምእመናን ናቸው፡፡ ይህቺ ቤተ ክርቲያን ወጣት የሚባል ተተኪ የላትም፤ ሚስቶቻችን ወደ ቀድሞ የኦርቶዶክስ እምነታቸው እንዲመለሱ ጥረት ብናደርግም እሺ ሊሉን አልቻሉም፡፡ አሁንም የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን፤ ማን ያውቃል አንድ ቀን ሊመለሱ ይችላሉ” በማለት ተስፋቸውን ነግረውናል፡፡

 

ቤተ ክርስቲያኗ ለ4 ዓመታት ያህል ተዘግታ መኖሯን የገለጠልን አንድ ዲያቆን ከ1982 ጀምሮ ዲቁና ተቀብሎ እያገለገለ ቢሆንም ካለበት bogi 4የመንግሥት ሥራ ጋር አጣጥሞ አገልግሎቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳልቻለ ገልጦልናል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎችም ሥራ ለማግኘትና በኘሮጀክት ታቅፈው የእለት ኑሮአቸውን ለመግፋት ሳይወዱ በግድ ወደ ኘሮቴስታንት እምነት ለመሔድ እንደሚገደዱ ነዋሪዎች ይገልጣሉ፡፡

 

በአሁኑ ሰዓት የቤተ ክርስትያኗን ቁልፍ ይዞ ካህንም ፣ዲያቆንም፣ ሰንበት ተመማሪም፣ አስተማሪም፤ ጠባቂም ሆኖ የሚያገለግለው ዲያቆን አበበ ኅሩይ በኘሮቴስታንቱ የደረሰባቸውን  ከፍተኛ ጉዳት እንዲህ ይናገራል፡፡ “እኔ እንደማስታውሰው በ1988 ዓ.ም የተወሰኑ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች ነበሩ፡፡ በዚያን ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚያስተምር ሰባኪ ስላልነበረን የነበሩት ምእመናን በአንድ ላይ ተሟጥጠው ወደ ኘሮቴስታንቱ የጸሎት ቤት ገቡ፡፡ ሌላው ይቅርና የቤተክርስቲያኗ ቁልፍ ያዥ የነበረው ቄስ አዳሜ ገብረ ወልድ በጠዋት መጥቶ ‘በል ይህን የቤተ ክርስቲያን ቁልፍ ተረከበኝ ወደ ኘሮቴስታን የጸሎት ቤት መሔዴ ነው’ ብሎ ጥሎልኝ ሔደ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቁልፉን ይዤዋለሁ፡፡ በአጥቢያዋ የሚኖሩ 14 የሚሆኑ ምእመናን አቅመ ደካሞች ናቸው፡፡ እነሱ ሲያልፉ ማን እንደሚተካ ሳስበው ይጨንቀኛል፡፡” ይላል፡፡

 

መፍትሔ

የአከባቢው ተጽእኖ የኘሮቴስታንቱ ድባብ የዋጣቸው በርካታ ወገኖቻችን አሉ፡፡ስለ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ሳያውቁ በጭፍኑ የኮበለሉ ብዙ ነፍሳት አሉ፡፡ በቅርቡ በተደረጉ ሁለት መንፈሳዊ ጉዞዎች ባለፈው ክረምት ለ2 ወራት በተደረገው ጠንካራ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ አርባ ሁለት ሰዎች ወደ ኦርቶዶክስ እምነታቸው እንደተመለሱ የምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ያብራራሉ፡፡ የአካባቢው ፕሮቴስታንታዊ ተጽእኖ ከባድ መሆኑ ስለታመነበት የካህናት ሥልጠና እንዲሰጥ ታምኖበታል፡፡ ይህ በመሆኑ በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል አዘጋጅነት በምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት በጊምቢ ከተማ መንበረ ጵጵስና ከየካቲት 12-16 ቀን 2004 ዓ.ም. ከአሶሳ፣ ከቄለም እና ምዕራብ ወለጋ አህጉረ ስብከት ለተውጣጡ 150 ካህናት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ በብፁዕ አቡነ ሄኖክ ጸሎተ ቡራኬ የተጀመረው የካህናት ሥልጠና በነገረ ሃይማኖት መግቢያ፣ በአእማደ ምሥጢራት፣ በነገረ ድኅነት፣ በነገረ ቅዱሳን፣ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ በሕግጋተ እግዚአብሔር፣ በትምህርተ ኖሎት እና በወቅታዊ የተሐድሶ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

 

በስልጠናው ማጠናቀቂያ ዕለት ካህናቱ በሰጡት አስተያየት የተሰጠው ሥልጠና ለቀጣዩ የስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጠዋል፡፡ በተለይ በምዕራብ ወለጋ የሚታየውን የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ለመፍታት በንቃትና በትጋት እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የሰጠው ይህ ሥልጠና እጅግ ጠቃሚና ወቅታዊ በመሆኑ ለወደፊቱ ተደጋጋሚ የሆነ የካህናት ሥልጠና ቢደረግ በቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ከፍተኛ የሆነ ስኬት ሊመጣ እንደሚችል ካህናቱ አስተውቀዋል፡፡

 

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ምሥጢሩ እና በዕለቱ ያገኘናቸው ምእመናን እንዲሆንላቸው የሚመኙትን እየተማጸኑ ነግረውናል፡፡

 

  1. በዚህች ከተማ መናፍቃኑ መሠረታቸውን ጥለው የእኛን ቤተ ክርስቲያን እና ምእመናን አስከልክለውብናል፡፡ የነገሩን ምንጭ ለማድረቅ በዚህች ከተማ የተጠና ፕሮጀክት ቢጀመር በሥራ እጦት እየተጨነቁ ሃይማኖታቸውን ጥለው የሔዱት ወገኖቻችን ሊመለሱ ይችላሉ፡፡
  2. በኦሮምኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ ሰባኪያነ ወንጌል ቢመደቡልን
  3. ተተኪ ወጣቶችን የሚያስተምሩ የአብነት መምህራን ቢቀጠሩልን እና
  4. በመጪው ግንቦት 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ለምናከብረው ዓመታዊ በዓል ሰፊ ጉባኤ እንዲደረግልን ለመምህራን ትራንስፓርት፣ ለድምጽ ማጉያ፣ እና ለአንዳንድ ወጪዎች የሚሆን ገንዘብ የሚደግፉን በጎ አድራጊ ምእመናን ቢገኙ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ይመጣል፡፡ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በተከታታይ የሚሰጥ ከሆነ ባለፈው ጊዜ የተመለሱት ምእመናን በእምነታቸው ይጸናሉ ያልተመለሱትም ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ይመጣሉ ይላሉ፡፡

 

bogi 5ቦጂ ቅድስት ማርያም ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ያጣቻቸውን ልጆች መልሳ ለማግኝት በሯን ከፍታ ትጠብቃለች፤ ተከታታይ ጉባዔያት ቢካሔዱ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሚያስተምራቸው ሰባኬ ወንጌል ቢመደብላቸው የጠፉት ነፍሳት ሊመለሱ እንደሚችሉ ምእመናን በመሉ ተስፋ ይናገራሉ፡፡ እኛም ታሪክ ተቀይሮ መናፍቃኑ መሠረት ከጣሉበት ቦታ አንድ ለውጥ ይመጣ ይሆን? የሚለውን ጥያቄ በውስጣችን ይዘን ተመልሰናል ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን ከመገንባት ሕንጻ እግዚአብሔር ሰውን ማነጽ ይበልጣል፡፡ የጠፉት በጐች ወደ በረታቻው ካልተመለሱ እዳው የቤተክርስቲያን መሆኑ አያጠያይቅም ስለዚህ ባለ ድርሻ አካላት የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ ቦጂ ትጮሀለች፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር